ይጀመራል ከቤት፣ ይከተላል ጎረቤት!
አገሬ አዲስ
(Ethiopian Semay)
ታህሳስ 17ቀን 2013 ዓም(26-12-2020)
የአንድ ቤተሰብ ሰላምና ክብር በሌሎቹ ዘንድ ሊጠበቅ የሚችለው የቤተሰቡ አባላት ፍቅራቸው የጠነከረ፣ ለክብራቸውና ለሰላማዊ
ኑሮዋቸው ቀናዊ ሲሆኑ ነው።ሰላም፣ፍቅርና መተሳሰብ በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ሽኩቻ፣የእርስ በርስ ጠብና ግጭት መከሰቱ አይቀሬ ነው።ጠብና
ግጭቱ በከረረ ቁጥር ቤት ይፈርሳል፣ቤተሰብም ይበተናል። በውጭ ይጠባበቅ የነበረው ደበኛ ወይም ዘራፊ ሰርጎ ለመግባትና ያሻውን ለማድረግ
ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል። አድብቶ ለማጥቃት የሚጠባበቅ ጠላት በቤተሰቡ
ውስጥ ይህ ሁኔታ እንዲከሰት ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።ከቻለ ሁሉንም አጥፍቶ የቤተሰቡን ቤትና ንብረት ለመውረስ አለያም ለእርሱ
የሚመቸውን በመርዳት ጥቅሙን ለማስከበር የሚነሳበት ወቅት የቤተሰቡ
ሁኔታ ከሚፈጥረው ግርግርና ጭቅጭቅ ጋር የተያያዘ ይሆናል።
በተመሳሳይም በአገራችን ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት
ለማናጋት ብሎም ለመበታተን በውጭ ሃይሎች ድጋፍ የሚንቀሳቀሱት በጎሳ የተደራጁት የፖለቲካ ድርጅቶች በዘረጉት ስርዓትና በሕገመንግሥት
ስም በነደፉት የጥፋት ሰነድ እውቅና የተቻረው የጥፋት ዘመቻ ሳቢያ የተከሰተው ሁኔታ ይህንኑ ይመስላል።በውስጥ የነዚህ የጥፋት ሃይሎች
መብቀል ለአሁኑ የውጭ ሃይሎች ሰርጎ ገብነትና ወረራ በር የከፈተ ነው።ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው።
የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ
ሃይለሥላሴ በየካቲቱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት ከሁሉም የመከላከያ
ጦር ክፍሎች የተውጣጡትን ወታደሮች በቤተመንግሥታቸው ቅጥር
ግቢ ውስጥ ሰብስበው ባደረጉት ንግግር ወታደሩ አገሩንና መንግሥቱን ከአደጋ እንዲከላከል ማሳሰቢያና ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።በዛም
እለት “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባበታል” የሚለውን የተለመደ አባባል ተጠቅመው የውጭ ጠላቶች መጠቀሚያ መንገድ እንዳያገኙ ነቅቶ መጠበቅ
እንደሚገባ አሳስበው ነበር። ያሉት አልቀረም ከጥቂት ዓመታት በዃላ
አገራችን የውጭ ሃይሎች በተለይም አረቦች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ጣልቃ
ገብተው እስከአሁንም ድረስ የሚያተራምሷት አገር ሆነች። አዎ! ለውጭ
ጅቦች መግቢያና መሳሪያ የሆነው አገር በቀሉ ውሻ ነው።
አሁን በሱዳኖች ለተጀመረው ድፍረት፣የድንበር መጣስና ወረራ ግብጾች ከዃላ ተሰልፈው የሚመሩት ለመሆኑ አጠያያቂ ባይሆንም ለነሱ የጥቃት እርምጃ የበለጠ ሞራልና ጉልበት ብሎም አጋር የሆናቸው በዬጎሳው ስም ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱት አገር በቀል እራስ ጠል የሆኑት ቡድኖች ናቸው።ለጎሳ ትውልዳቸው ሕዝብና ቦታ መሻሻል ፣መብትና ነጻነት በሚል ሽፋን ለዘረፋ የሚያበቃቸውን ሥልጣን ለመጨበጥ ላላቸው ስግብግብ ዓላማ ተገንና መከታ የሚያደርጉት ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑትን የውጭ ሃይሎች ነው።ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዜጎቿ የተመቸች ዴሞክራሲያዊት አገር ሆና ከማዬት ይልቅ ፈራርሳ የውጭ ሃይሎች እንደዬ አቅማቸው የሚቀራመቷት የቄራ ከብት ሆና ማዬትን ይመርጣሉ።እነሱም የአንድ ልዑላዊት አገር ዜጋና ባለቤት ከመሆን ይልቅ በቅኝ ገዥዎች ሰንሰለት ታስረው ባርያና አገልጋይ መሆንን ይሻሉ።ቀደም ሲል የኤርትራ ተገንጣይ ሃይሎች ፣ጀበሃና ሻእብያ፣በነሱም ጥላ ስር የተፈጠሩት ህወሃትና ኦነግ የኢትዮጵያን መጥፋት እንጂ እንዳገር መኖር አይፈልጉም።ከመፈራረስዋ በፊት ግን በሃብቷ እንፈጥረዋለን ላሉት አገር የአቅም ግንባታ አንዳንድ የልማት መስኮችን በተለይም የመከላከያ አቅም ሲገነቡ ኖረዋል።ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ የሰፈነው የጎሰኞች የፖለቲካ ስርዓት ይህንኑ የሚያስፈጽም ተልእኮ የተሸከመ ነው።በመካከላቸው በተነሳ የጥቅምና የሥልጣን ሽኩቻ አንዳንዶቹ ቢከስሙም የቀሩት አሁንም በቦታው ላይ አሉ።ለእኩይ ዓላማቸው ሕዝብን ከሕዝብ ማናከስ አንዱ ስልታቸው ነው።ወያኔዎች አማራውንና ኦሮሞውን እሳትና ጭድ ብለው እንዳይተማመን ሲያደርጉት ቆይተዋል።የአሁኖቹም ባለተረኞች የኦነግ ውልዶች አማራውንና ትግሬውን ደም አቃብተውታል።
እነዚህን በታሪክ፣በባሕል፣በሃይማኖትና
በማህበራዊ ትስስር ለአያሌ ዘመናት አብረው የኖሩ፣በደም ና እትብት የተሳሰሩ፣ለኢትዮጵያ አገራዊ ምሥረታ ግንባር ቀደም የሆኑ ማህበረሰቦች
“አቢሲኒያ” በሚል ስያሜ እዬጠሩ ባገሪቱ ውስጥ ለተከሰተው ችግር ሁሉ ፣ለአዬር ለውጡና መዘዙ ጭምር ሳይቀር ተጠያቂ አድርገው በጠላትነት
ፈርጀዋቸዋል።በስልጣን ላይ ያለው ባለተረኛው ኦነግ/ኦህዴድ -ብልጽግና መንግሥት በህወሃት የሚመራውን ቡድን በጦር ሲያንበረክክ የአማራውን
ጎሳ ተጠቅሞ ነው።ካለው ቅርበትና የውጊያ ችሎታ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ታላቁን ሚና ተጫውቷል።ለሰራው ጀብዱ ግን በመንግሥት
በኩል ምስጋና ቀርቶ እውቅና አልተሰጠውም። የኦሮሞ መራሹ ቡድን እግሩ
ትግራይ መሬት እንደረገጠ በወያኔ መዳፍ ስር የነበረው ያገሪቱ ሃብት፣የጦርና የልማት መሳሪያዎች ቀን በቀን ተጭነው ወደ ኦሮሞ ክልል
ተዘርፈው መወሰዳቸውን የሚያወሱ ዜናዎች አጋልጠዋል።ይህም አድራጎት የቀጣዩን ሂደት አመላካች ነው።ከዚያም ቀጥሎ ጦርነቱ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ
ፊታቸውን ያዞሩት ህይወቱን ዳርጎ፣የፈንጂ ማብረጃ ሆኖ ባዳናቸው፣ በግላጭ ብቻውን በቀረው፣ለኢትዮጵያ ህልውና በጽናት በቆመው የአማራ
ጎሳ ላይ ነው።ይህ ትልቅ ሕዝብ በሚኖርበት ቦታ ሁሉ ኦነጎችና በሥልጣን ላይ ያሉት ተከታዮቹ ግልገል ቡችላ የሆኑትን ጥቃቅን ጎሰኛ
ቡድኖች በማስታጠቅና በመምራት ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲሰነዘርበት አድርገዋል። ይህንን ሲያደርጉ ግን ለከባቢው ደሃ ኑዋሪ አስበው አይደለም፤የመተከልን
ለምና የብዙ ማዕደን ጓዳ የሆነ ሰፊ መሬት ወሮ ለመያዝ፣በተለይም ለወደፊቱ የሃይል ማመንጫነት በሁሉም ኢትዮጵያዊ እርብርቦሽ በመገንባት
ላይ ያለውን ትልቁን የህዳሴ ግድብ በክልላቸው ውስጥ ለማስገባት ነው።
ለዚያም እንደ አዲስ አበባ ከተማ የሕዝቡን ስብጥር ለመለወጥ ካላቸው እቅድ የነዋሪውን ስነልቦና በመስለብ በግድ የኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ
እንዲሆን በኦሮሞ አስተሳሰብ በማጥመቅና ቁጥሩ በኦሮሞ ተወላጆች እንዲዋጥ የኦሮሞ ተወላጆችን ከሌላ ቦታ በማምጣት በማስፈር ነው።
ቢቻላቸው በዚሁ መልክ መላ አትዮጵያን ኦሮሚያ ለማድረግ ባይቻላቸው
ኢትዮጵያን አመንምኖ ኦሮሚያ የተባለ አዲስና ትልቅ አገር ለመፍጠር ነው።
አሁን በአማራ ጎሳ ላይ የሚደረገው
ጭፍጨፋ ነገ በሌሎቹ ጎሳዎች ላይ ላለመደረጉ ዋስትና የለም።ዛሬ በሰሜኑና በምዕራቡ ክፍል የሚካሄደው የመሬት ቅርምት ነገ በሌሎቹ
ቦታዎች ላይ ላለመደረጉ ማረጋገጫ የለም።ሁሉም በዬተራ የሚጋተው መራራ እጣ ፈንታ ነው።ያንን ተገንዝቦ በማንዣበብ ላይ ያለውን የመዋጥ
አደጋ በህብረት ሊያሶግዱት ይገባል።በኢትዮጵያዊነት ተሰልፎ በጋራ ከመቆም የተሻለ አማራጭ የለም።
አገራችን መሪ አልባ በሆነችበት
በአሁኑ ጊዜ ፣በውስጥ ሽብርና ቀውስ በምትናጥበት ጊዜ፣በጎሳ ማንነቱና በሃይማኖቱ ሕዝብ እዬተለዬ በሚጨፈጨፍበት ጊዜ፣በአጠቃላይ
የእርስ በርስ ውጊያ (ሲቪል ዋር) ከዳር እስከዳር ለመከሰት ጠርዝ ላይ በሚገኝበት ጊዜ፣ የውጭ ሃይሎች በጋራ መቆማቸው የሚያስገርም
አይሆንም።የሚያስገርመው ነገር ቢኖር በሥልጣን ላይ ያለው ጠ/ሚኒስቴር አብይ አህመድ ይህንን የውስጡን ችግር የሚያቀጣጥለው የጎሳ
ፖለቲካና በተለይም እሱን ያሳደገው የኦነግ መሪዎች የሚዘውሩት መንግሥት መሆኑን ክዶ ሁሉንም ችግር በውጭ ጠላቶች የተጠነሰሰ ሴራ
ነው ማለቱ ነው።ፍዬል ወዲህ ቁዝምዝም ወዲያ!
በቅርቡ በመተከል የተከናወነውን
የንጹሃን ዜጎች ጭፍጨፋ ምክንያት በማድረግ አካባቢውን በጎበኘበት ስብሰባ ላይ “ የውጭ ሃይሎች በጎሳ፣በብሔርና በሃይማኖት ከፋፍለው
ሊያጋድሉን ሙከራ አድርገዋል፤እያደረጉም ነው፤ግን አይሳካላቸውም ” ሲል ተደምጧል። ጅንጀሮ የራሱን መላጣ ሳያይ በሌላው ጅንጀሮ
መላጣ ይሳለቃል እንደሚሉት ነገር ነው።ለመሆኑ አገራችንን ለመበታተን ፣ሕዝቡን ለእርስ በርስ ግጭት፣ግድያና መፈናቀል የዳረጋት እራሱ
የሚመራው የዘር ፖለቲካ የሚያራምደው መንግሥት ተብዬው ስብስብ መሆኑን ዘንግቶት ይሆን?የጥላቻ ጡጦ አጥብቶ ያሳደገው ኦነግና ህወሃት
የተባሉ አገር አጥፊ ቡድኖች መሆናቸውንና የዘረጉት የጥፋት መረብ መሆኑን እረስቶት ይሆን? እርሱ የሚመራው መንግሥት የሚመራበት ሕገመንግሥት ተብዬው አገር የሚበታትንና ለዚህ አደጋ ያጋለጠንን
ሰነድ መኖሩን ሳያውቅ ቀርቶ ይሆን?አይደለም። ዓይናችሁን ጨፍኑ ላታላችሁ ከሚለው ብልጣብልጥነት ወይም ሕዝብን ከመናቅ
ልማዱ የመነጨ ትርክት ነው።ሕዝብን ከአንድ ጊዜ በላይ
ማታለል እንደማይቻል ቢያውቀው ጥሩ ነው።ያልተናገረ ሕዝብ አያውቅም ማለት አይደለም።
አጎንብሶ ቢሄድ ሞኝ ነው ወይ በጉ፣
ነገርን ካልተውት ናቅ እያደረጉ።
የሚለውን የትዝብት ስንኝ ማስታወሱ መልካም ይሆናል።
በውስጥም ሆነ በውጭ ላለመደፈር፣ብሔራዊ ዳር-ድንበርን ለማስከበር በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብና ዓላማ ላይ ያረፈ አደረጃጀትና
አሰላለፍ ያስፈልጋል።ለዚያ ደግሞ አሁን በአገራችን ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱትን የጎሳና የሃይማኖት የፖለቲካ ድርጅቶችና ስብስቦችን
በሕግ ማገድ ተገቢ ነው። ያም ብቻ በቂ አይሆንም፤ለነሱ ሕጋዊ እውቅና የሚሰጠውንም ሕገመንግሥት ተብዬ የጥፋት ሰነድ ቀዶ መጣል አስፈላጊ ነው።ይህንን ወሳኝና ታሪካዊ እርምጃ የአብይ
መንግሥት በራሱ ላይ ዘምቶ ይወስደዋል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው።ስለሆነም አገራችን የተደቀነባትን የውስጥና የውጭ አደጋ ለመቋቋም
የሚችል ጠንካራ ወታደራዊ፣ፖለቲካዊና ሕዝባዊ ተቋም ያለው አካል መፍጠር የግድ ይላል።ከአገር ወዳድ ሃይሎች የተውጣጣ የቀውስ ጊዜ
መንግሥት ወይም አስተዳደር (War time Administration or Government)ማቋቋም ለነገ የማይሉት ብቸኛ ምርጫ ነው።
አብይ አህመድ ደፍሮ በጡት አባቶቹ በኦነግ/ኦህዴድ፣በሕወሃትና በዘረጉት መረብ ላይ መቀስ
ያነሳል ተብሎ አይጠበቅም፤እሱ እራሱ የወንጀሉ ተካፋይ፣ለሥልጣንም ያበቃው የጎሳ ፖለቲካ ስለሆነ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ አንዱ ተጠያቂ
ነው።ለዚያም ነው ወንጀለኞቹን ህወሃትን፣ኦነግንና ሌሎቹንም በጭፍጨፋ (ጀኖሳይድ)ወንጀል ለመፈረጅ ያልደፈረው።መስተዋት ቤት የሚኖር
ሰው በድንጋይ አይጫወትም ይባል የለ!የአብይ መንግሥትም እንደዚያው ነው።የሚወረወረው ድንጋይ እራሱንም ስለማይምረው ደፍሮ እጁን
አያነሳም፤ቢያነሳም በደቃቃዎቹ ላይ እንጂ በግዙፎቹ ላይ አይሆንም።ለግላጋ
ወጣት ተማሪዎችን አግቶ ቤተሰብ የሚያስለቅሰውን የኦነግ ታጣቂ ወንጀለኛ ቡድን በሃይል አስገድዶ ወጣት ተማሪዎችን ከማስለቀቅ ይልቅ
ወንጀሉን በመሸፋፈንና ያጋለጡትን በማስፈራራት ፍትሕ እንዳያገኝ አድርጓል።
ሌላው የአብይ ጉልበቱ በእውነተኛ
የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ተቃዋሚዎቹ ላይ ነው። በነሱ ላይ ፍትሕን እረግጦ ያሻውን ያደርጋል። በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ
ፓርቲ መሪዎችና አባላት ላይ የተጣለው ክስ፣ እስራትና መቋጫ የሌለው ቀጠሮ፣በአቶ ልደቱ አያሌውና በኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ላይ
የደረሰው ሕገ ወጥ እርምጃ ፣በትንታግ ጋዜጠኞች፣በተመስገን ደሳለኝ፣በአልማዝ ሙሃመድ፣በመስከረም አበራ፣በአስቴር በዳኔና በሌሎቹም
ላይ የሚደረገው ወከባና ዛቻ የዚሁ የዘረኞቹ ማን አለብኝነት የወለደው
የግፍ ውጤት ነው።የምርጫ ቦርዱን ብትር አድርጎ በመጠቀምም ሰሞኑን በምርጫ ውድድር ያሰጉኛል የሚላቸውን ድርጅቶች ከማይረቡት ጋር
በማቀላቀል ሰርዟቸዋል።እነ እስክንድርንም በምርጫው እንዳይሳተፉ ለማድረግ የመጀመሪያውን የምስክር ቃል መቀበያ ፍርድ ቤቱን ቀጠሮ
አሽቀንጥሮ ወደ አራት ወር ወርውሮታል።የሌሎቹን ምስክሮች ቃል ለመስማት ከዓመት በላይ እንደሚፈጅ ይህ አማላካች ነው። መታወቅ ያለበት
ነገር ቢኖር የአንድን ድርጅት መሪዎች በማሰር የሕዝብን ድጋፍ ማቆም እንደማይቻል ነው።የደቡብ አፍሪካው መሪ ማንዴላ የአገሩን ሕዝብ
ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሕዝብ ድጋፍ ያገኘው በሮቢን ደሴት እስርቤት ውስጥ በሚማቅቅበት ጊዜ ነው።የባልደራስንም ሆነ የሌሎቹን ድርጅቶች የሕዝብ ድጋፍ መሪዎቹን በማሰርና በማሶገድ ለጊዜው ቢመስልም ዘለቄታ
አይኖረውም።
ከሁሉም በፊት ግን ለሃቀኛ ምርጫ
ሃቀኛና አስተማማኝ ሁኔታ በአገሪቱ ሲሰፍን፣ድርጅቶች በነጻነት ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሰው ሕዝቡን ለመቀስቀስ የሚችሉበት ሁኔታ
ሲፈጠር ነው።በአሁኑ ሁኔታ ምርጫ ለማድረግ የሚደረገው እሩጫ ግን ባለተረኞቹን ሕጋዊ እውቅና እንዲኖራቸው የሚያደርግ ከዝግ ችሎት
ያልተናነሰ ሂደት ይሆናል።
አብይ አህመድ ከፊት ለፊት ሆኖ
ሕዝብ እያጃጃለ፣ኦነግና የኦነግ ውልድ የሆነው ኦህዴድ የወደፊቷን
ኦሮሚያ የተባለች አገር ለመመሥረት ደፋ ቀና እያለ ነው።አዲስ አበባን ከኢትዮጵያውያን እጅ ፈልቅቆ በመውሰድ ፊንፊኔ በሚል ስም ሰይሞ ዋና ከተማው ለማድረግ የቤት ሥራውን ከጀመረ
ውሎ አድሯል።የነዋሪውን ሕዝብ ስብጥርነት (ዴሞግራፊ) ለመቀዬር በግላጭ
የተነገረው በተግባርም እዬተገለጸ ነው።የኦሮሞ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣የኦሮሞ ባህል ማእከል፣የኦሮሞ ርዕሰመንግሥት ቢሮ።የኦሮሞ ወጣቶች
ማእከል…ወዘተ የሚሉት ተቋማት ባጀት ተመድቦላቸው በመገንባት ላይ ናቸው።ባንኮችማ በኦሮሞ መዳፍ ስር ከወደቁ ቆይቷል።የማዕድን ዘርፎችም
እንዲሁ።ወንጀል የፈጸሙት የኦህዴድ ባለሥልጣኖች ከቦታ ቦታ እዬተቀያዬሩ ከመሾምና ከመሸለም በተረፈ ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ አልሆኑም።ሁሉም
ነገር የጎሳ ታፔላ ተለጥፎበት ህጋዊ እውቅና ተሰጥቶታል።የኦሮሞ ታፔላ ግን ከሁሉም ይበልጣል።በባለተረኝነት ስሜት፣ሁሉም የእኔ በሚል
መረን አልባ ስግብግብነት ወይም ቅዤት ከጫፍ እስከጫፍ በእብደት ፈረስ እዬጋለበ ነው።በአጠቃላይ ጎሰኝነትን በቃህ የሚለው፣ የሚያስቆመው
ኢትዮጵያዊ ልጓም፣ አገር ወዳድ ሃይል ሊነሳ ግድ ይላል።
ኢትዮጵያ በውስጥ ችግር በምትገባበት
ወቅት የውጭ ጠላቶች መነሳታቸው የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም።በታሪክ ተደጋግሞ ታይቷል። በዘመነ መሳፍንት ጊዜ የሥልጣን ሽኩቻ ሲነሳ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በተለይም ጣልያንና እንግሊዝ ግጭቱን በማባባስ፣ለአንዱ
እርዳታ በማቀበል የቅኝ ግዛት ፍላጎታቸውን ለማረጋገጥ ሞክረው በኢትዮጵያኑ ብልህነትና ቆራጥነት በአንድ ላይ በመቆም በወሰዱት እርምጃ
ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከዚያም ማእከላዊ መንግሥት እንዳይጠናከር ተደጋጋሚ
ሙከራዎች አድርገው አልተሳኩላቸውም። ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህም በተለይም በደርግ ጊዜ የነበረውን ውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት
ተከትሎ ተገንጣይ ሃይሎችን ከመርዳት ባለፈ፣የሶማሊያ መንግሥት ሲሻና ሲመኝ የነበረውን የኢትዮጵያን ግዛት ቆርሶ ለመውሰድ አጋጣሚውን
ለመጠቀም በተነሳበት ጊዜ ሱዳን፣ግብጽ፣የአረብ አገራትና የምዕራብ አገሮች በአሜሪካ መሪነት የተቀናጀ ጦርነት አውጀውባት ነበር።በዚህም
ጊዜ በኢትዮጵያውያኑ ቆራጥ እርምጃና አሁን የግራ ፖለቲካ ተብሎ በስህተት በሚፈረጀው በሶሻሊስት ስርዓት ይመሩ በነበሩት አገሮች
በተለይም የሶቪዬት ህብረት፣ምስራቅ ጀርመን፣ኩባና የመን ድጋፍና የጦር ሜዳ ውሎ ጠላት ድባቅ ሆኖ ጉዳይ አስፈጻሚ የነበረው የሶማሊያ
ጦር ተሸንፎ የዃላዃላም የራሱንም አገር እስከማጣት ደረሰ።
የውጭ ጠላት ሴራ በዚህ ብቻ አልቆመም
ለወያኔ መራሹ ስርዓት መስፈንና ለኤርትራም መገንጠል ምክንያት ሆኗል።የአሁኑም ከዚያ አይለይም።መፍትሔውም ከዚያ የተለዬ አይሆንም።አሁን
የምዕራቡ አገሮች በአሜሪካ መሪነት የሰብአዊ መብት ማስከበር በሚል ሰበብ ለሕዝቡ ያሰቡ መስለው በሚጠቀሙበት በተባበሩት የዓለም
ድርጅትና በስሩ ባሉት ተቋማት በኩል ለጣልያን ወረራ ያደረጉትን ድጋፍ በሚመስል መልክና ደረጃ ለግብጽ ጥብቅና በመቆም ጸረ ኢትዮጵያ
የሆነ ዘመቻቸውን ክፍተዋል። አገር ወዳዱ ሃይል ተሰባስቦ የውስጥና
የውጭ ሃይሎችን ድባቅ ለመምታት የሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት አለበት።ያ ካልሆነ ግን የግብጽና ሱዳን ብቻ ሳይሆን የደቃቃዎቹ ጎረቤት አገሮችም፣ የደቡብ ሱዳን፣ኬንያ፣ጅቡቲና
ሶማሊያ መቀለጃ መሆናችን ሳይታለም የተፈታ ነው።ባዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል ይባል ዬለ!
የውጩን ጠላት ከመቋቋሙ ጎን ለጎን የውስጡን ባንዳ
መምታቱ ተነጥሎ መታዬት አይኖርበትም። አዎ! ባዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል!ቁንጫውን ለማሶገድ ቤቱ በየቀኑ መጠረግ አለበት።ብጉር
ከታገሱት ኪንታሮት ይሆናል!ክንታሮት ከመሆኑ በፊት ግን ማፍረጡ ከጉዳት ያድናል።
የሕዝብን እንባና ስቃይ፣ያአገርን
ውድቀት ሃይል እንጂ ልመና አያቆመውም።
ለአገር አድን ተጋድሎ የአገር ወዳዶች
ፖለቲካዊና ወታደራዊ ግንባር ይመስረት!
አገሬ አዲስ
No comments:
Post a Comment