Monday, March 19, 2018

ኮማንድ ፖስት” ምን ማለት ነው? ነፃነት ዘለቀ Ethiopian semay


ኮማንድ ፖስት” ምን ማለት ነው?
ነፃነት ዘለቀ Ethiopian semay

ስያሜና የስም አወጣጥ እጅግ አነጋጋሪ ከሆኑ የዕለት ከዕለት ገጠመኞቻችን ውስጥ የሚካተቱ ይመስሉኛል፡፡ ስያሜን በተመለከተ በርካታ አባባሎች ቢኖሩም “ስም አይገዛም” የሚለው አሁን ለማነሳው የነገር ብልት በጣም የቀረበ ነው፡፡ “ስም አይገዛም” የምንለው ስያሜና ተሰያሚ ማለትም ወካይና ተወካይ እየተለያዩብን ስንቸገር ነው፡፡ ለምሣሌ በመንደራችን ውስጥ በስስታምነቱ የምናውቀው ሰው ስሙ “ቸርነት” ቢሆን፣ ቁርሱን እንደምንም አንድ ነገር ቀምሶ ለምሣው የሚጨነቅ ድሃ ጎረቤታችን  “ሀብታሙ” ተብሎ ቢጠራ፣ ሠፈር ዳር እስከዳር በነጭናጫነቷ የሚያውቃት ሴት “ዐመለወርቅ” ብትባል፣ በጎረቤት የምናውቀው ቀዳዳ ውሸታም “እውነቱ” ሲባል ብንሰማ፣ … በርግጥም በስም አይገዜነት መደነቃችን አይቀርም፡፡

በመሠረቱ ቋንቋ ባሕርያዊ አይደለም (ይባላል በሥነ-ልሣን ትምህርት)፡፡ ምን ማለት ነው - ስያሜና ተሰያሚ ስምምነታዊ እንጂ ተፈጥሯዊ ወይም ባሕርያዊ ግንኙነት የላቸውም ለማለት ነው፡፡ ለአብነት አንድ ግዑዝ ነገር “ድንጋይ” ተብሎ ተሰየመ፡፡ “ድንጋይ”ን በእማሬያዊም ሆነ በፍካሬያዊ ትርጉሙ ሁሉም አማርኛ ተናጋሪ ኅብረተሰብ  ይረዳዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ስለዚህ “ድንጋይ” የሚል ቃር ሲጠራ ወደ አእምሯችን የሚመጣ ምስል አለ፡፡ ያ ምስልና “ድንጋይ” የሚለው ቃል ግንኙነታቸው ስምምነታዊ እንጂ ባሕርያዊ አይደለም፡፡ ማኅበረሰቡ ከተስማማ “ድንጋይ”ን - ለምሣሌ - በ“ይጋንድ” ወይም በሌላ ቃል ሊተካና የቀደመውን “ድንጋይ” የሚል ቃል ከነአካቴው ሊተወው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ግን እንደሥነ ልሣናዊ ልማድ ቃላት በተናጠልም ይሁን በኅብረት እየተነገሩ አንዳች ጽንሰ ሃሳብ መስጠታቸው አይቀርምና እነዚያ ጽንሰ ሃሳቦች ደግሞ ትርጉማቸው በሰፊው ይታወቃልና ከትርጉማቸው የተዛነፈ ፍቺ እንዲሰጡ በምንፈልግ ጊዜ ወይም ከእውነታው የተለዬ ፍቹ እንዲያስተላልፉ በማወቅ ወይም ባለማወቅ በምንጠቀምባቸው ጊዜ ግርታንና ከፍ ሲል ደግሞ አለመግባባትን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡እንደመግቢያ ይህን ካልን ዘንድ ስለወያኔዎች ድንበር የለቀቀና አስቂኝ የቋንቋ አጠቃቀም ትንሽ እናውራ፡፡

ወያኔዎች የሰው ግኝት የሆነውን ቋንቋን መግደልና አላግባብ መጠቀም አይደለም የእግዜር ፍጡር የሆነውን ሰውን ሲያሰቃዩና ሲገድሉ ርህራሄ የሚባል የላቸውም፡፡ በተለይ በጠላትነት የፈረጁትንማ አያድርስ ነው!

በነዚህ ጉዶች ያልተሰቃዬ የመዝገበ ቃላት(dictionary) አንድም ቃል የለም፡፡ እጅግ በጣም ከሚያሳዝኑኝ ውስጥ “ነፃነት፣ ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ፍትህ፣ ሕገ መንግሥት፣ እኩልነት፣ ፌዴራል፣ ፓርላማ፣ ፀጥታና ልማት” የሚሉት ናቸው፡፡ ከወያኔዎች መነሻ አካባቢ ጀምሮ እነሱን እከታተል ስለነበር የሚሉትንና የሚሆኑትን ወይም የሚያደርጉትን በሚገባ አውቃለሁና ለነዚያ በወያኔ በየቀኑ ለሚሰቃዩ ቃላት እጅግ አዝንላቸው ነበር፡፡ ገና በረሃ ሳሉ ጀምሮ እነዚህንና ሌሎችንም ቃላት ሲጠቀሙ እንሰማ ነበር፡፡ አድራጎታቸው ሁሉ ግን እነዚህ ቃላት ከሚያስተላልፉት ሁለንተናዊ ፍቺ ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ ወያኔዎች በግብር የማያውቁትን ነገር በምኞትና በቃል አጠቃቀም  የሚያገኙት እየመሰላቸው ሳይሆን አይቀርም በቋንቋ አጠቃቀማቸው ለሚሰማቸው ሰው ብቻ እንከን የማይወጣላቸው ሰላማውያን ፍጡራን ይመስላሉ፡፡ በተግባር ግን ሣር ቅጠሉ እንደሚያውቅላቸው ነፃነትን በባርነት፣ ዴሞክራሲን በአምባገነንነት፣ ሰላምን በጦርነት፣ ፍትህን በአድልዖ፣ ሕገ መንግሥትን በድርጅታዊ ማኒፌስቶ፣ እኩልነትን በዘረኝነት፣ ፌዴራልን በሕወሓታዊ የአንድ ጎሣ የበላይነት፣ ፀጥታን በዘላለማዊ ሁከት፣ ልማትን በማወናበጃነት … ለውጠው ወረደ መቃብራቸው ሊፈጸም በታሪክ የጊዜ አቆጣጠር ደቂቃና ሴከንዶች ቀርተው እንኳን ከዚህ ተፈጥሯዊ የሚመስል ጠባያቸው ሊታቀቡ አልቻሉም - “መጥፎ ጠባይ ሳያስቀብር አይተውም” የምንለው ወደን አይደለም፡፡ ምናልባት እነሱም ያሳዝናሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ተፈጥሮን በውዴታ የሚቀበል ፍጡር ስለማይገኝ በጠማማ ተፈጥሯቸው ብናዝንላቸው በእግረ መንገድም  በነሱ ሌጌሲ ምክንያት ለሚጎዳው በሚሊዮን የሚቆጠር ትውልድ እንደማዘንም ነው፡፡ ማንኛውም ጠንቅ የሚጎትተው ሌላ የከፋ ጠንቅ አለ፡፡

ከሁሉም ይገርሙኝ ከነበሩ የቃላት አጠቃቀማቸው አብዮትንና ዴሞክረሲን ያዛነቁበት ሁኔታ ነው፡፡ ሁለቱ ቃላት ዐይንና ናጫ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ከአንድ በሕዝብ ብዛቱ አነስተኛ ከሆነ ነገድ ወይም ዘውግ የወጣ ቡድን አብዮት ቢል ያምርበት እንደሆነ እንጂ ዴሞክረሲን መደረብ የለበትም - ነጭ ጨርቅ ላይ ጥቁር እራፊ ጨርቅ አይጣፍም፤ ባልጠፋ ጨርቅ አስጠሊታነቱ ከሩቅ የሚጣራ ነውረኝነት ውስጥ አይገባም፡፡ ወያኔዎች ያን ማድረጋቸው ማይምነታቸውን ወይም ማንአለብኝነታቸውን በግልጽ አሳይቷል፡፡ ከፍ ሲል እንደገለጽኩት የወያኔው ቡድን ለቋንቋ  ይቅርና ለብሔራዊም ይሁን ለዓለም አቀፋዊ፣ ለባህላዊም ይሁን ለሃይማኖታዊ፣ ለኅሊናዊም ይሁን ለሰብኣዊና ተፈጥሯዊ ህግጋት የማይገዛ በመሆኑ እንደፈለገው ቢዘላብድ ደንታው አይደለም፡፡ በዚያም ላይ  የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጠላቶች ቡራኬ ስላለበት በንግግሩም አይደለም በዕኩይ ድርጊቱም ሃይ የሚለው አካል ከየትኛውም አቅጣጫ ኖሮ አያውቅም፤ አሁንና ወደፊትም ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ይህን መለኮታዊ እውነት አጥርተን እናውቃለን፡፡ የእምዬ ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ አምላኳ እንጂ ሰው ወይም ወዳጅ ሀገር እንዳልሆነም ከታሪክ ተምረናል፡፡ ሊያጠፏት ሲነሱ የሚታደጋት እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ አሁንም እንደሰው የማይሆነው አንድዬ በቅርቡ ትንሣኤዋን ያሳየናል፡፡ 

ሕወሓት የሚሠራትን ብቻ ሣይሆን የሚያደርጋትን እያንዳንዷን እንቅስቃሴና የድርጊት መርሐ-ግብር ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተብዬው ይከታተላል፤ ያውቃልም፡፡ ስለዚህም እየሣቁባቸው ይሁን ብለው ትተዋቸው እንጂ ለምሣሌ አብዮትንና ዴሞክረሲን ሲያጫፍሩ “ተው፤ እንደሱ አያስኬዳችሁም” ብለው ሊመክሯቸው በተገባ ነበር፡፡ አብዮት ዐመፅ ነው፤ አፍራሽ ነው፤ “በለው!” ነው፤ “ግደለው! እሰረው” ነው፤ ስለዚህ በድምጽና በድምጽ ብቻ ከሚከናወን፣ በአብላጫ ስሜትና ፍላጎት ከሚፈጸም የዴሞክራሲ ተፈጥሮ ጋር አንድም ኅብረት የለውም፡፡ ከሰማይ በታች ምንም የሚያቅተው የሌለው ወያኔ ግን ነጭና ጥቁርን ዴሞክረሲንና አብዮትን አንድ ላይ አስቀምጦ በተለመደው አገላለጽ “ተጨፈኑልኝና ላሞኛችሁ” ሲለን ባጀ - ሊያውም የአንድን ኢትዮያዊ አማካይ ዕድሜ ለሚጠጋ ረጂም ዘመን፡፡ የነሱ ብልጥነትና የኛ ፍርሀት ወይም ‹ትግስት› ተመሳስሎኣዊ ምጣኔ በጣም ይደንቀኛል፡፡ የልብ ልብ የሰጠናቸውና ለድንቁርናቸው  ትልቁን አስተዋፅዖ ያደረግነው እንግዲያውስ እኛው ነን - በ “ወርቃማው” ዝምታችንና ወደር በማይኝለት “ትግስታችን”፡፡ ከአሁን በኋላስ? ጊዜ ራሱ ይነግረናል፡፡

የወያኔን ንግግር መገንዘብ የሚፈልግ ሰው ወያኔው የሚለፍፈውን ሁሉ ገልብጦ መረዳት ነው፡፡ የዋህ የወያኔ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆነ ሰው እየቆዬ እውነቱን ሲረዳ በመሳሳቱ ምክንያት ለከፍተኛ ጸጸት መጋለጡ አይቀርም - መሳሳቱ ሆን ተብሎ በዓላማ አንድነት ወይም በዘር መሳሳብ ሳይሆን ከአንጀት ከሆነ ነው ታዲያ፡፡

ልጨርስ ነው፡፡ ጥቂት ወያኔዊ ኮዶችን እንመልከት፡፡

“ህገ መንግሥቱን ለመናድ” ሲሉ ሕወሓትንና የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች የሆኑ ትግሬዎችን ለማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግሥት ብሎ ነገር የለም፡፡ ሆነም ቀረም ህገ መንግሥት ዱሮ ቀረ፡፡ የአሁኑ ህገ መንግሥት ወያኔ ማለት ነው፡፡
“መከላከያ ሠራዊታችን” ሲሉ ሕወሓትንና የሥርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ ትግሬዎችን ከማንኛውም አደጋ የሚከላከል ጦር ማለታቸው ነው - ልክ እንደ አጋዚው ቅልብ ጦራቸው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሠራዊት የላትም፡፡ በቋንቋ፣ በባህልና በሥነ ልቦና ከሕዝቡ ጋር አንዳችም ትስስርት የሌለው፣ ከየት እንደተመለመለና በምን መልክ እንደሰለጠነ የማይታወቅ፣ ከፍተኛ ዘመናዊ  ትምህርት ቀርቶ የመሠረተ ትምህርትን እንኳን ያልተሰጠው ማይም፣ …. ለመግደል ብቻ የተሠማራ ሮቦታዊ ጦር ሠራዊት አለ እንጂ ከሕዝብ አብራክ የወጣና የሚገድለው እህቱንና አባት እናቱን እንደሆነ የሚገነዘብ የሀገር መከላከያ ጦር ኢትዮጵያ የላትም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ኢ-ሰብኣዊ ጦራቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ተከፍሎ የማያልቅ ዕዳ እያስቀመጡ መሆናቸውን እነሱ ማወቅ ባይፈልጉ ወዳጆቻቸው ሊረዱትና ወያኔዎች አሟሟታቸውን እንዲያሳምሩ ሊመክሯቸው ይገባል፡፡

“የኢትዮጵያ መንግሥት” ሲባል በቀጥታ ሕወሓት ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ብሎ ነገር አሁን የለም፡፡ እንዲህ ሲባል ያናድዳል፡፡ ለወያኔ ግፍና በደል  ዕውቅና እንደመስጠትም ነው፡፡ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ተጠይፎና ክዶ ሀገርና ሕዝብ እያወደመ የሚገኝን የውስጥ ቅኝ ገዢ ኃይል “የኢትዮጵያ መንግሥት” እያሉ በሚዲያ ማንቆላስ የቆሙለትን ዓላማ ገደል እንደመክተት ይቆራል፡፡  ከዚህ መሠረታዊ ጭብጥ አኳ ኢሳትን ጨምሮ በርካታ የተቃውሞ ሚዲያ አውታሮች ይህን አባባላቸውን ቢመረምሩት መልካም ነው፡፡ ወያኔ እንዴት “የኢትዮጵያ መንግሥት” ይባላል? “የሕወሓት መንግሥት” ወይም “ሕወሓት መራሹ መንግሥት” ቢባል ምን አለ? ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ለምን ይቃረናሉ?

“ኢሕአዴግ” ሲባል የሕወሓት የመሀል አገር ቀሚስ ነው - አዲስ አይደለም - የተለመደ አባባል ነው፡፡ ሰዎች “ሕወሓት/ኢሕአዴግ” ሲሉ ይገርሙኛል - ከዱሮ ጀምሮ፡፡ ኢሕአዴግ ብሎ ነገር የለም - ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ፡፡ “አብዮት” ዴሞክረሲ” በሚሉት ቃላት ምክንያት ስያሜው ትርጉም አልባ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ስብስብ ውስጥ ከሕወሓት በስተቀር ሕይወት ያለው ድርጅት ስለሌለ የሦስት ዞምቤዎችና የአንድ ፈላጭ ቆራጭ ውድብ ኅብረት ከመነሻው የቁጩ ነው - የሌለ፡፡ ባርያና ጌታ አንድ የፅዋ ማኅበር ሊጠጡ አይችሉም፡፡ ፈጣሪና ፍጡር በአንድ ጉዳይ ላይ እኩል አንደበት የላቸውም፡፡ ሰውን ስታታልል ትንሽ ሊታመን የሚችል “ፊንታ” መሥራት ይጠበቅብሃል እንጂ እንደወያኔ ዐይን ያወጣ የውሸት ድራማ ያሳፍራል - እርግጥ ነው እነሱ “ማሳመኛቸው” ጉልበት በመሆኑ ጠያቂ የለም፡፡ (“በረረም አልበረረም ‹በግ ነው› ብየሃለሁ፤ ‹በግ ነው›” የሚለውን የአንድ ጉልበተኛና የአንድ አቅመቢስ ሁለት ጓደኛሞች ታሪክ አስታውሱልኝ - በአንድ ነገር አሞራነትና በግነት ሲከራከሩ ቆይተው ሲጠጉት በረረ፤ ደካማው “አሞራ ነው” ነበር ያለው - ወያኔው አባ ጉልቤ  ግን “በግ ነው” ብሎ ነበር….፡፡)

“ፌዴራል ሥርዓታችን” ሲሉ ሕወሓት የሚምነሸነሽበትና በቅምጥ ሎሌዎቹና በነሱ ራስጌና ግርጌ ባስቀመጣቸው አባሎቹ የሀገርን ሀብት የሚዘርፍበትን ክልላዊ አደረጃጀት ማለቱ ነው (ቤንሻንጉል ጉሙዝ ሂዱ - የፖሊስ ኮሚሽነሩ የዚያው ክልል ተወላጅ ሆኖ የምታሾረው ግን ትግሬዋ ሚስቱ ናት - በሁሉም ክልሎች ይህን ዓይነት አሠራር የተለመደ ብቻ ሣይሆን በህግ የጸደቀ ያህል ነው፤ አለን እንላለን እንጂ በቁም ሞተናል እኮ! የብዝኃዊነታችንን ኃይል በልዩ ዘዴያቸው በረዶ አደረጉትና እኛ ስንልፈሰፈስ በጣት የሚቆጠሩት እነሱ በላያችን ላይ ይጨፍራሉ፤ አበጁ! “ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ” ነው ተረቱም የሚለው)፡፡ መነሻው ግን “ሲወልዱ አይታ ምንትስ አደረገች” እንዲሉ “ፌዴራል” ሲሉ ሰሙና ይህን ዓይነት ማኅበረሰብኣዊ ሥርዓት ባልጠየቀና በማያውቅም አንድ ሕዝብ ውስጥ የውሸት ፌዴራል ዐውጀው መሪር ሣቅ እያሳቁ ያደናቁሩናል፡፡ ፈረንጆቹንማ እንዴት በሣቅ እንደሚገድሏቸው በምናቤ እያየሁ እገረማለሁ፡፡ በለዛ ቢስ ትያትር ቅመራ ወያኔን የሚስተካከል በዓለም ላይ የለም፡፡ ዐይናቸውን በጨው ያጠቡ ቁጭበሉዎች ናቸው - ለነገሩ የጠነዛና የገለማ ትያትር በማየት የሚዝናና ሕዝብ እስካለ ድረስ ደራሲውም ሆነ ተዋንያኑ ምን ጨነቃቸው? ዕድሜ ለጌቶቻው፣ ዕድሜ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እስካሁን “አልፎረሹም” ማለትም አፍዝ አደንግዛቸውን የሚያረክስ አብነት ተገኝቶ ሀገርና ሕዝብ ከዚህ አሣዛኝ የታሪክ ስብራት ሊፈወሱ አልቻሉም፡፡ ወያኔዎች በቀን 48 ሰዓት በተንኮልና በሸር ፈጠራ ሥራቸው ሲጠመዱ የነሱ ተቃራኒ የሆነው ጎራ እርስ በርስ በመወራረፍና አንዱ ሌላውን በመብላት ተወጥሯል፡፡ አንዱና ምናልባትም ዋናው የወያኔ የእስትንፋስ መቀጠያ ገመድም ይሄው ነው፡፡ አንድ ፈረንጅ በቀደም ለት - “The main ARV of TPLF is the discord among the opposition.” አለኝ፡፡

“ፓርላማ” ሲሉ የሕወሓት ሥሪት የሆኑ እንዲናገሩ የማይጠበቅባቸው ጋኖችና ምንቸቶች ማለት ነው፡፡ እንደወያኔ የቃላት አጠቃቀም ከሆነ ይህ “ፓርላማ” የሚባል ቃል እስከወዲያኛው አስጠልቶኝ በቀረ ነበር፡፡ ግን ነገም ሌላ ቀን ነውና በሌሎች ሀገራትም በአግባቡ ሥራ ላይ ሲውል ይስተዋላልና ልወደው የምችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል ተስፋ አልቆርጥም ፡፡

“ኮማንድ ፖስት” ሲሉ የሕወሓትን ነፍስ አድን ዓለም አቀፍ ዘመቻ ማለታቸው ነው፡፡ ሕወሓት ሞተች ማለት ኢትዮጵያ ተነሣች ማለት ነው፡፡ ሕወሓት ጠፋች ማለት ይህችን ታሪካዊ ሀገር ከነታሪኳ ለማጥፋት ሲባል ከ300 ዓመታት በላይ የተለፋበት ዓለም አቀፍ ታላቅ ሤራ በአጭሩ ከሸፈ ማለት ነው፡፡ ይህችን ሀገር ለማውደም ከዚህ የበለጠ ምቹ ጊዜ ደግሞ የለም፡፡ ስለሆነም በባሌም ሆነ በቦሌ ወያኔ አፈር ልሶ መነሳት አለበት - እንደነሱ አስተሳሰብ፡፡ ከዚህ አኳያ ከተቻለ ወያኔን እንደምንም ማቆየት፤ ያ ካልተቻለ ወያኔን የሚመስል ሌላ ኃይል አሰልጥኖ የፈረደበት አራት ኪሎ ማስገባትና በምዕራፍ ሁለት ቀጣይ ዘመቻ ይህችን ሀገር መቀመቅ ማውረድ፡፡ ዕቅዱ ብታምኑም ባታምኑም ይሄው ነው፡፡ ግን ከፍ ሲል እንደጠቆምኩት የአንድዬን ፍርድ መጠበቅ ነው፡፡ 
የሆኖ ሆኖ ኮማንድ ፖስትም ይባል አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅም ይባል - ምንም ይባል ምን - ይህ ሁሉ የቃላት ጋጋታ በአንድ ቃል ሲተካ “ሕወሓት” ነው የሚሆነው፡፡ አስፈጻሚዎቹም ፈርጋሳም ይባል ደቻሳ፣ ስንሻውም በሉት አለምነው፣ ዘበርጋም ይባል ኡጁሉ …. ዋናው ኣዛዥና የእሽክርክሪቱ ተቆጣጣሪ “ሐጎስ” ነው - የሕወሓት ልጅ- የዐውሬውም የቀኝ እጅ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከገቡበት ማጥ በአፋጣኝ ያውጣልን፤ አሜን፡፡

No comments: