Tuesday, March 20, 2018

የስብሰባን ምንነት በተመለከተ በተለይ ለሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ብሥራት ደረሰ

የስብሰባን ምንነት በተመለከተ በተለይ ለሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ

ብሥራት ደረሰ

 ስብሰባ ምን እንደሆነ ከሕጻን እስከ ዐዋቂ የማያውቅ የለም፡፡  ከቤተሰብ ጀምሮ ዕድሮችንና አካባቢያዊ ማኅበራዊ ስብስቦችን አልፎ እስከ ግላዊና መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና ከፍተኛ ሀገራዊ መዋቅሮች ድረስ ልዩ ልዩ መደበኛና ድንገተኛ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፡፡ በስብሰባዎች ወቅት አጀንዳዎች ይያዛሉ፤ ሊቃነ መናብርት ስብሰባዎችን ይመራሉ፤ ቃለ ጉባኤ የሚይዝ ሰው ይኖራል፤ ምልዓተ ጉባኤ መሟላቱ ይረጋገጣል፤… ቀድመው የተያዙ አጀንዳዎች በቅደም ተከተላቸው በሰብሳቢው እየቀረቡ ውይይት ይካሄዳል  - (እንደየስብሰባው ዓይነት ተጨማሪ አጀንዳዎች ካሉ ከተሰብሳቢዎች ሊጠየቅም ይችላል)፤ አጨቃጫቂና አወዛጋቢ ጉዳዮች ሲኖሩ በድምጽ ብልጫ እያለፉ ወይ እየወደቁ የስብሰባው መቋጫ ይደርስና ወደምሣ ወይም ወደ ቤት ይኬዳል፡፡ እኔ የማውቀው ስብሰባ እንዲህ ያለውን ነው፡፡ ከዚህ ያለፈ ካለ ትርጉሙ ሌላ ነው፡፡ ወረድ ብለን እናየዋለን፡፡

ሕወሓት የሚያካሂደው ስብሰባ ሲቃኝ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ እጅግ የተለዬ ነው፡፡ ወደዚያ ከመግባቴ በፊት ግን ቀጣይዋን ቤተ ክህነታዊ ታሪክ ላስታውሳችሁ፡፡

“ውስጠ ወይራ
 ሲባል ሳንሰማ አንቀርም፡፡ እንደሰማሁት መነሻ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ አንድ የቆሎ ተማሪ የቅኔ ትምህርት ላይ ነው፡፡ መምህሩ መስተዋድዳን (prepositions) በቅኔ ቤት ያላቸውን አገባብና አጠቃቀም እያስተማሩ ናቸው፡፡ በግዕዝ ትምህርት እያንዳንዱ መስተዋድድ አብሮት የሚሄድ ቃል አለው፡፡ ማንኛውም ቃል ማንኛውንም መስተዋድድ በዘፈቀደ አይወስድም፡፡ ለምሣሌ “እም…” የሚለው “እስመ…” ከሚለው ይልቅ የሚስማሙት ሌሎች ቃላት ይኖራሉ፡፡ ያ ተማሪ በአገኝ-አጣ ዓይነት (trial and error) አንዱን መስተዋድድ ከአንዱ ቃል እየሰደረ ሲያመጣላቸው መምህሩ በአሉታ ራሳቸውን ይነቀንቁና እንደማይሆን ደጋግመው ይነግሩታል፡፡ ተማሪው ሰለቸው፡፡ ዕውቀት ስትርቀው፣ ጥበብ ስትከዳው፣ … አንድ ዘዴ ተከሰተለት፡፡ ያም ዘዴ የወይራ ቁድራ(አጭር ዱላ) በሥውር ይዞ በመግባት ሦስት መስተዋድዳንን በአንድ ላይ በመደርደር ልክ መሆን አለመሆኑን መምህሩን መጠየቅና አይሆንም ካሉት (እንደሚሉትም እንኳን እርሱ እኛም እናውቃለን!) በዚያች ደብቆ በያዛት ቁድራ መምህሩን መፈንከት - ከዚያም ማሳመን፤ ከዚያም የቅኔ ቤት ትምህርቱን በ”ስኬት አጠናቅቆ” መመረቅ፡፡ ተሜ ወደ መምህሩ መጣ፡፡ “እስመ፣እንዘ፣እንተ አኮኑ…” አለና እንዳይሆን እንዳይሆን አድርጎ ሦስት መስተዋድዳንን በአንድነት ደራርቦ አነበበላቸው፡፡ መምህሩም ተሜ ጉያው ውስጥ ወሽቆ በድብቅ የያዛትን ቁድራ አጮልቀው አይተዋት ኖሮ “አዎ፣ እንዲያ ነው፤ ይበል ነው! አሁን በውስጠ ወይራ ትክክል ነህ!” አሉት ይባላል፡፡ የቅኔ መምህሩ በብልጠታቸው ከተሜ ዱላ ተረፉ፡፡ እነለማና አቢይስ? … ነገና ከነገ ወዲያ የምናየው ይሆናል፡፡ ገበሬው ሲዘራ የዋለው እህል ምን እንደሆነ ስትጠይቀው አተር እንዳልዘራ ሁሉ የማትበላውን መርጦ “ተልባ ነው” ሲላት “ወርደን እናየዋለን” ብላለች አሉ ጦጢት፡፡

ሕወሓት ትክክለኛ ስብሰባ አካሂዶ ስለማወቁ በውስጡ ያለፉ ሰዎች ቢያወሩት ይበልጥ ተዓማኒነት ይኖረዋል፡፡ እንደውጪ ታዛቢ ግን ሕወሓት ተፈጥሮው ስለማይፈቅድለት በትምህርትም ሆነ በልምድ የምናውቀውን ፓርላሜንታዊ የስብሰባ አካሄድ ሥርዓት  ያውቃል ተብሎ በፍጹም አይገመትም፡፡ ጠባብ ቡድን እንደመሆኑ እንደዚያ ከይሲ ተማሪ በውስጠ ወይራ ምሥኪን ተሰብሳቢዎችን በቁድራ እያራወጠ የሚፈልገውን አጀንዳ ይይዛል፤ የሚፈልገውን ውሳኔ ያስተላልፋል፤ የሚፈልገውን ዐዋጅ ያጸድቃል እንጂ በብዙኃን አሸናፊነት የሚያምን ቡድን አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም - ወያኔ ጉልበትና ዐይን ያወጣ ብልጣብልጥነት እንጂ አመክንዮና ተጠየቃዊ አካሄድ ኖሮት አያውቅም፤ ሊኖረውም አይችልም - የድምጽ ብልጫን እንደጦር ይፈራላ! ወያኔ ፍትሃዊና ምክንያታዊ ሊሆን የማያስችሉትን ምክንያቶች ጠንቅቀን እያወቅን ከወያኔ መልካም ነገር የምንጠብቅ እኛ ነን እንጂ ስህተተኞቹ ወያኔ በሚከተለው የትግልና የኅልውና ማስጠበቅ ሥልት ተሳስቶ አያውቅም - ወደፊትም አይሳሳትም፡፡ ስለዚህ ወያኔ “እንዲህ አደረገ፤ እንዲህ ያለ ወንጀል ሠራ” የምንለው ጉንጭ-አልፋ ነው - ሕወሓታውያን ጊዜ ካገኙ ከእስካሁኑም በበለጠ ምድርንና ሰማይን የሚያንቀጠቅጡ ብዙ ነውሮችንና ወንጀሎችን ይፈጽማሉ - ለምን ቢባል የሚፈሩት ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ፣ አካላዊም ይሁን መንፈሳዊ ነገር የላቸውም፤ ልባቸው የደነደነ ፍጹም ጭራቆች ናቸው፡፡  ጭራቅነት ላይ ማይምነትና ሆዳምነት ሲደረቡ እንግዲህ ምን ዓይነት የለየላቸው ዐውሬዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታያችሁ፡፡ በነዚህ ነው የምንገዛው፡፡ አቤት ቅጣት!
ዓለም አቀፋዊ ጠቅላላ ድምራቸው 16.5 ሚሊዮን አካባቢ እንደሚሆኑ የሚነገርላቸው እሥራኤላውያን የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ መቆጣጠር የቻሉት “ብዙ ነን” እንደሚሉትና ብዛታቸው መከራ እንዳስከተለባቸው ለማወቅ እንደተቸገሩት አማሮችና ኦሮሞዎች ሌት ከቀን ተኝተው ጥልቅ እንቅልፍ በመድቃት አይደለም፡፡ ጥቂትነት የብልጠትንና ለከት የለሽ ራስ-ወዳድነትን፣ ብዝኃነት ደግሞ የሞኝነትንና ጉዳት ላይ የሚጥል “overconfidence” ባሕርይን የሚያላብሱ ይመስላል፡፡ ክፉ ህልም ሲገጥም ቶሎ መንቃት ነው ቁልፍ መፍትሔው፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ወያኔዎች ከአሁን ቀደም ገጥሟቸው የማያውቅ ዓይነት ለየት ያለ ችግር ውስጥ ሳይገቡ አልቀሩም፡፡ በስብሰባ ርዝማኔ ሕወሓት ዱሮውንም የታወቀ ቢሆንም ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ግን የሚጠሯቸው ስብሰባዎች እኛ ከምናውቀው የስብሰባ ምንነትና አስፈላጊነት የተለዩ ናቸው፡፡  አንድ ስብሰባ በአማካይ ግማሽ ቀን ቢፈጅ ነው፡፡ እርግጥ ነው የአጀንዳዎችና የተሰብሳቢዎች ብዛት እንደዚሁም የጉዳዮች ጡዘትና ክረት እንደዬሁኔታው የስብሰባውን የጊዜ ርዝማኔ ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ ይሁንና አንድ ስብሰባ ሁለትና ሦስት ወር ከፈጀ ይህ ስብሰባ፣ ስብሰባ ሳይሆን ምናልባት ጋሪ ካስፓሮቫዊ የቼዝ ጨዋታ ቢባል ይመረጣል፡፡ ስብሰባ በመሠረቱ አሰልቺ ነው፡፡ እንኳንስ ለወራት ለአንድ ቀንም ቢሆን ስብሰባ ያደክማል፤ ያንገፈግፍማል፤ በበኩሌ የ30 ደቂቃ ስብሰባም ከትግስቴ በላይ ነው - አልወድ…ም!! ለ17 ቀን፣ ለ30 ቀን፣ ለሦስት ወራት … የሚደረግ ስብሰባ ግን የአጋች ታጋች ድራማ ለመሥራት የታቀደ ይመስላል፡፡ “ተሰብሳቢዎች ከአዳራሽ ቢወጡ ነገር ያመጣሉ” ከሚል ፍርሀትና ሥጋት በመነጨ ወያኔዎች ተጠርጣሪ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ያዋሏቸው ይመስለኛል - እንደብዙዎች ግምት፡፡ ማታ ማታ ግን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀላቅሏቸው ይሆን? ወይንስ እንዳሠሯቸው ያድሩ ይሆን? ምንም የሚታወቅ ነገር እኮ የለም፡፡ ሁሉም ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ መጨረሻችን ይናፍቃል - መጨረሻ ካለን፡፡

በአሁኑ ሰዓት እነለማና ዶ/ር አቢይ የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡ በስብሰባ ሰበብ እንደታሰሩ ነው የምንገምተው፡፡ ይህን ወቅታዊ አንገብጋቢ ጉዳይ በሚመለከት መሳይ መኮንን ጥሩ ጽሑፍ ጽፏል - “የለማ ኦህዲድ ፈተና” በሚል ርዕስ፡፡ ይህን ጽሑፍ ሁሉም ሰው እንዲያነበው በትህትና እጠቁማለሁ፡፡ መሳይ እንዳመላከተው ሕወሓት በዚህ ስብሰባ አማካይነት ለማክሸፍ የፈለገው ነገር አለ፡፡ እሱም የሕዝብን ለለውጥ መነሳሳት ማጨናጎልና የሕዝብን ተስፋዎች ማጨለም ነው፡፡ ስለሆነም “ስብሰባ ላይ ናቸው” የሚባለው ነገር ማደናገሪያ እንጂ ስብሰባ የለም - ወራትን የሚፈጅ ጦርነት እንጂ ስብሰባ ሊኖር አይችልም፡፡ የሕዝብን ቀልብ የገዙ ሰዎችን በስብሰባ ስም በወታደር አስከብቦ ሀገርን በራሱ ቅልብ የአጋዚ ጦር እያስጨፈጨፈ የሚገኘው  ሕወሓት አደብ እንዲገዛ ሕዝቡና የተቃውሞው ጎራ አንድ ነገር ካላደረጉ መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከእስካሁኑ ይልቅ እጅግ የጨለመ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

አሁንና እዚህ አንድ “ስብሰባ” ላካሂድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አልፈጅም፡፡ ይህን “ስብሰባ” የማካሂድበትን ጊዜ ከወያኔ የፌዝ ስብሰባ ጋር አነጻጽሩትና ራሳችሁ ፍርዳችሁን ስጡ፡፡ ስብሰባን እኮ ከአሥር ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥም ማከናወንና ፍሬያማ ውጤት ላይ መድረስ ይቻላለ፡፡ በግድ ከልደት እስከሞት መንዘባዘብና መንዘላዘል የለበትም፡፡ በአንድ ጥናት የተረጋገጠ የሰው ልጅ አንድን ንግግር በትኩረት የማዳመጥ ፍላጎት ደግሞ በአማካይ 8 ደቂቃ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ትኩረቱ ወደኩሽናውና ወደቀን ህልሙ የሚያዘነብል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ጎምቱዎቹ ወያኔዎች ከግድግዳና ከጣርያ ጋር ካልሆነ ከሰው ጋር ሊሰበሰቡ አይችሉም፡፡ ይህንንም እናስታውስ - “አንድን ፈረስ አንድ ሰው ወደ ወንዝ ሊወስደው ይችላል፤ ሃያ ሰዎች ግን እንዲጠጣ ሊያስገድዱት አይችሉም፡፡” - ወደ “ስብሰባየ” አመራሁ፡-

አጀንዳ

“በጋራ እንደግ” የተባለው ድርጅት በጠራው የንግድ ትርዒት መሥሪያ ቤታችን እንዲካፈል ቢደረግ የሚኖረው ፋይዳ

ውይይት

ሰብሳቢው - የተከበራችሁ የመሥሪያ ቤታችን የሥራ አመራር ቦርድ አባላት እንኳን በሰላም መጣችሁ፡፡ ቀድመን እንደገለጽነው የዛሬ አጀንዳችን አንድ ነው፡፡  “በጋራ እንደግ” የተባለው ድርጅት ያዘጋጀው የንግድ ትርኢት በኢግዚብሽን ማዕከል በመጪው ሚያዝያ ወር ውስጥ ይካሄዳል፡፡ በደብዳቤም ተጋብዘናል፡፡ ምን ይመስላችኋል? እስኪ እንወያይትበና በትርዒቱ መካፈል አለመካፈላችን ያለውን ፋይዳ ወይም ጠቀሜታና ጉዳት በቅጡ ተረድተን የሚጠቅመንን በዚህ ስብሰባችን እንወስን፡፡

ከተሰብሳዎች አንዱ - ይሄማ ምን ያጠያይቃል? መካፈላችን በጣም ይጠቅመናል፡፡ አንድም ድርጅታችንን እናስተዋውቅበታለን፡፡ አንድም የተወሰነ ሽያጭ እናካሂድበትና ትርፍ እናገኝበታለን፡፡ ዋናው ግን ድርጅታንን ለማስተዋወቅ የምናገኘው ዕድል ነው፡፡ ይህ ዕድል በውነቱ በስንት ጊዜ አንዴ የሚገኝ ወርቃማ ዕድል በመሆኑ ባያመልጠን ጥሩ ነው….
ሰብሳቢ - ተጨማሪ ሃሳብ አለ? ከተጨማሪ በፊት እንዲያውም አቶ አይተንፍሱ ያሉትን የሚቃወም ካለ…ሰብሳቢ - ምነው ዝም አላችሁ ፤ የሚቃወም ከሌለ ትደግፉታላችሁ ማለት ነው -  እንደዚያ ከሆነ በጭብጨባ ግለጹልኛ! አለዚያ የሚቃወም ካለ እንስማውና ወደ ድምጽ አሰጣጥ ሄደን በድምጽ ብልጫ እንጥለዋን ወይም እናሳልፈዋለን፡፡ተሰብሳቢዎች - (የመጀመሪያውን ሰውዬ በመደገፍ የቀለጠ ጭብጨባ)

ሰብሳቢ - አመሰግናለሁ፡፡ ድርጅታችን በዚህ በተጠራው የንግድ ትርዒት መሣተፍ ወይ አለመሣተፍ እንዳለበት ከነጥቅምና ጉዳቱ በስፋት ተወያይተን መሣተፋችን እንደሚጠቅመን በመተማመን በአብላጫ ድምጽ ያመንበትን ውሳኔ አሳልፈናል፡፡ ይህም ውሳኔ በቃለ ጉባኤው ይሠፍርና ተፈራርመንበት ተግባራዊ ይሆናል፤ አሁንም ቢሆን ይህን የአብላጫ ድምጽ ውሳኔ የሚቃወም ካለ ሃሳቡን ሊሰነዝር ይችላል፡፡ የስብሰባውን ጥሪ አክብራችሁ በሰዓቱ በመገኘታችሁ ምሥጋናየ የላቀ ነው፤ የዛሬውን ስብሰባ በዚህ እንቋጫለን፤ መልካም ቀን፡፡ (ይቅርታ - በምልክት “ የሻይ ፕሮግራም አለ” እየተባልኩ ነውና ወደዚያች ኮሪደር ሄደን ሻይ ቡና እያልን ጥቂት እንጫወት፡፡) 

….. ስብሰባው ተፈጸመ ….. 

የወያኔዎች ጭንቀትና ዜጎችን በመያዣነት በስብሰባ መሰል ማገቻዎች ማጎር መንስኤ ግን ሌላ ነው፤ ወያኔዎች ሕዝብ ተስፋ የጣለባቸውንና እነሱው ጉያ ውስጥ ያሉ ወጣት ፖለቲከኞችን እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ ቀይዶ በቅርብ ርቀት መቆጣጠር ነው ዋናው የወቅቱ ተግባራቸው፡፡ እንደእውነቱ ወያኔዎች የፈጠሩት ችግር በስብሰባም ሆነ በኮንፈረንስ አይፈታም፡፡ ወንድ ቢኖር(እንዲሁም ሴት) በጠበንጃና በጦር መፍትሔውን የሚያገኝ የዘመናት ክምር ዕድፍ ነው ወያኔዎች ግቢ ውስጥ ተቆልሎ እያመሰን ያለው፡፡ ስለዚህ በሌለ ስብሰባና ባልተካደ ውይይት አንዳች ነገር መጠበቅ በትንሹ ጅልነት ነው፡፡ ስብሰባ የሚካሄደው ደግሞ እኩል መብት ባላቸው ተሰብሳቢ ወገኖች መካከል እንጂ በአንበሣና በሚዳቋ፣ በነብርና በፍየል የጉባኤ አባላት ተወስኖ ይፋ የሚደረግ የስብሰባ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ የታወቀ ነው፤ ስለዚህ በማያጠግብ የተስፋ ዳቦ ሆዳችንን አንቀብትት፡፡ ይህን የምለው ልክ እደዚያች የበሬው ምናምን ይወድቅልኛል ብላ ስትከተል እንደዋለችው ሞኝ ቀበሮ ከወያኔ “ስብሰባ” አንድ መልካም ነገር ይገኛል ብለው ለሚያንጋጥጡ ወያኔን ለማያውቁ ምሥኪን ወገኖች ነው፡፡ “በሺዎች ተጋሩ ደም የተገኘ ወርቃማ ዕድል በምንም መንገድ ቢሆን ከእጃችን ሊወጣ አይገባም!” ብለው የሚያምኑ ከጽንሰታቸው ጀምሮ ፀረ-ኢትዮጵያና ሕዝቧ የሆኑ የባንዳ ልጆች ለወራት ይቅርና ለክፍለ ዘመናት ቢሰበሰቡ አንድም አወንታዊ ነገር ጠብ አይልምና ይልቁንስ የነብርን ጅራት የጨበጣችሁ ወገኖች አትዘናጉ፡፡ በትንሽ ድል ደግሞ አትስከሩ፡፡ የዛሬ ድል ለነገ ሽንፈት መሠረት ሊሆን እንደሚችል መርሳት ግብዝነት ነው፡፡ በሌላም በኩል አንድ ድል ዘለቄታ ሊኖረው የሚችለው በብዙኃን ሲደገፍና ሲታቀፍ ነውና የግል ድል ሊኖር ቢችል እንኳን ያንን ድል ከብዙኃን ተመሳሳይ ግፍና በደል ከሚደርስባቸው ወገኖች ጋር ማስተሳሰር ጊዜው የሚጠይቀው አብይ ተግባር ነው፡፡ የተናጠል ጉዞ፣ በስሜት አምባላይ ፈረስ የሚያስጋልብ መለስተኛ ስኬት … ሁል-አቀፍ እስካልሆነ ድረስ ተመልሶ ጭቃ የማይሆንበት ምክንያት የለምና በተለይ ኦሮሞውና አማራው በየፊናው የሚያደርገውን ትግል ነገ ሳይሆን አሁንና ዛሬውኑ ማስተባበር ይኖርበታል፡፡ 

በስሜት ወለድ የፈጠራ ታሪኮች ተተብትቦ አሁን የሚገኙ ጠባብ ዕድሎችን ማባከን ከብልህ የነፃነት ታጋይ አይጠበቅምና በተለይ ልሂቃን የምትባሉት የሁለቱም ዘውጎች የማኅበረሰብ አባላት ከልብ ልታስቡበትና ልትሠሩበት ይገባል፤ አስተሳሰባችሁ ቅርብ ሳይሆን ሩቅ ይሁን፡፡ የጠፋነው ሩቅ በሚያስቡና ስለሩቁ በሚያቅዱ መሠሪ ጠላቶቻችን ነውና የእናንተም ዕይታ ነገና ነገ ወዲያን ካላካተተ መቼም ቢሆን ሕዝባችሁ ከባርነት አይወጣም፡፡ መገፈታተር ለወያኔ እንጂ ለእናንተ ጠቃሚ አይሆንም፡፡ ጠላት እናንተን ለማጋጨት የማይሸርበው ሤራ የለም፡፡ ስለዚህ “እዚህና እዚያ ቦታ አማራ ኦሮሞን እንዲህ አደረገ!” ወይም “እዚያና እዚህ ቦታ ኦሮሞ አማራን እንዲህ አደረገ!” ሲባል በግንፍልተኝነት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ጉዳዩን በተለያዬ አቅጣጫ ማጥናትና እውነቱን መረዳት ተገቢ ነው፤ በዛሬ ጊዜ የሀሰት ወሬ አገር ምድሩን ሞልቶት ዘመኑ የሽብር ሆኗልና ሳናጣራና እውነቱ ላይ ሳንደርስ በትንሹም በትልቁም እምቡር ከማለት እንቆጠብ፡፡ የጠላትን መሠሪነት ሳይገነዘቡ የሁለትዮሽም ሆነ የሦስትዮሽ ወዳጅነትን ማዳበር እንደሚከብድ የታወቀ ነውና በተለይ ከአሁን በኋላ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊመልሳቸው በሚችሉ ጥያቄዎች አሁን መነታረክና መጨቃጨቅ አስፈላጊ አለመሆኑንም እንገንዘብ፡፡ “ወጡ ሳይወጠወጥ…” እንደሚባለው ሀገር ሳትፈጠር፣ መንግሥት ሳይኖር፣ ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት መኖር ሳይጀምር፣ ሀገርና የሀገር ሀብት በአንበጣና በግሪሣ እየተረመረመ ባለበት ሁኔታ … የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ክርክር ኃይልንና ገንዘብን በከንቱ ከማባከን ውጪ አንዳችም ፋይዳ የለውም፡፡ የእግረ መንገድ ሃሳብ ነው፡፡

1 comment:

Unknown said...

Agree, 100%. Keep the good work.
Many thanks.