Monday, February 19, 2018


የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ቅኝት የተጠናወታቸው የፓለቲካ እንቅስቃሴዎች ባህርያት
በዶክተር አሰፋ ነጋሽ - 
(በሆላንድ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ)
Email address: Debesso@gmail.com

ክፍል አንድ፡

በዓለም ታሪክ ውስጥ ጽንፈኛነትንና አክራሪነትን የሚያራምዱ እንቅስቃሴዎች በፓለቲካ ድርጅት፤ በብሄረተኛ ድርጅትና በሃይማኖታዊ ድርጅት ሥም ሲካሄዱ ታይተዋል። እነዚህን ጽንፈኛነትንና አክራሪነትን መመሪያቸው አድርገው የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች፤

ሀ) በፓለቲካ ስም (አብዮታዊ ሌኒኒዝም/እስታሊንዚም/ማኦይዝም ወዘተ) ሥም፤
ለ) በአንድ ህዝብ ማንነት ላይ በቆመ ብሄረተኛ እንቅስቃሴ ሥም (የናዚ/ፋሽስት ሥርዓቶች ለዚህ ምሳሌ ናቸው)፤

ሐ) ወይም በአክራሪ ኃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ሥም (አክራሪ የእስልምናም ሆነ የክርስትና ድርጅቶች) ይመሩ እንጂ ሁሉም አንድ በጋራ የሚጋሩት ባህርይ አለ)። በዘመናችን ሳውድ አረቢያን በመሳሰሉት መንግስታት የሚረዳው የወሃቢ እንቅስቃሴ ለዚህ ኃይማኖታዊ አክራሪነት በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል።

በ ሀ እና ለ ሥር የጠቀስኳቸው እንቅስቃሴዎች ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው የጋራ ባህርይ የሁለቱም እንቅስቃሴዎች ተከታዮች የግለሰብ ነጻነታቸውንና ማንነታቸውን ለመሪ ድርጅታቸው መሪዎች አሳልፈው የሰጡና በደመነፍስ መሪያቸው አድርጉ የሚላቸውን የሚፈጽሙ መሆናቸው ነው። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦች እንደ ሰው የሚገልጻቸውን በራሳቸው አይምሮ የመመራት ነጻነት ለመሪ ድርጅታቸው አሳልፈው በመስጠት የድርጅት መሪዎቻቸውን በጭፍንነት የመከተል ዝንባሌ ጠንክሮ ይታይባቸዋል። እነዚህ በቁጥር አንድና ሁለት ሥር የጠቀስኳቸው እንቅስቃሴዎች ኃይማኖታዊ ባህርያትን የተላበሱ ናቸው። ኃይማኖታዊ ናቸው ያልኩበት ምክንያት ሳትጠይቅና ሳትመረምር ድርጅትህንና መሪህን በጭፍን እንደ ፈጣሪ አምላክ እመን፤ መሪዎችህን በሙሉ እምነት ተከተል የሚል ጭፍን እምነትን የሚያራምዱ ስለሆኑ ነው። የሰው ልጆች በመንፈሳዊ ህይወታቸው የሚፈልጉትን ኃይማኖት ማምለካቸውን አልቃወምም፤ ይህንንም ለማድረግ ያላቸውን መብት አከብራለሁኝ። ነገር ግን ጭፍንነትን የተላበሰ የፓለቲካ እምነት የሰውን ልጆች ህሊና በማሳወር እንደ መንጋ አምባገነን ምድራዊ መሪዎችን እንዲከተሉ ሲያደርግ እያንዳንዱ የሰው ልጅ በተፈጥሮው የታደለውን በራሱ ሃሳብና ፈቃድ የመመራት ጸጋ የሚገፍ አክራሪ ምድራዊ የፓለቲካ ሃይማኖት (secular political religion) ይሆናል። ይህ አክራሪ የፓለቲካ ኃይማኖት የእያንዳንዱን ግለሰብ ነጻነት ስለሚገፍ የተገዢነት፤ የጭቆና መሰረት ይሆናል። በዚህም ምክንያት ነው ከላይ የገለጽኳቸው የፓለቲካ፤ የብሄርተኛ እንቅስቃሴዎች የተከታዮቻቸውን በራስ የማሰብና በግል ፈቃዳቸው የመመራት ነጻነት ይገፋሉ የምለው። እነዚህ በቁጥር አንድና ሁለት የጠቀስኳቸው እንቅስቃሴዎች ዓላማቸውን እጅግ ጣሪያ በነካ የጭፍንነትና የአክራሪነት ስሜት ይተገብራሉ።

በፓለቲካም ሆነ በብሄረተኛነት ስም የሚካሄዱ አክራሪና ጽንፈኛ እንቅስቃሴዎች እንደ አክራሪ ሃይማኖት ከሚያራምዱት የፓለቲካ ዓላማ ዝንፍ የማይሉ (ግትርነት የሚገንባቸው)፤ የሃሳብ ልዩነትን የማያስተናግዱ በሃሳብ የሚቃወማቸውን በጠላትነት በመፈረጅ ለማጥፋት የሚነሱ ናቸው። በእነዚህ በቁጥር አንድና ሁለት ሥር የጠቀስኳቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከግለሰብ ይልቅ አንድ-ወጥ (homogeneous) የሆነ የቡድን ወይም የመንጋ አስተሳሰብ (group thinking) በተከታዮቹ ላይ የሚሰለጥንበት ሁኔታ ይታያል። በዚህ ሰዎች እንደ እንስሳ መንጋ በቡድን ስሜት አንድን የፓለቲካዊም ሆነ ብሄረተኛ እንቅስቃሴ በሚከተሉበት ሁኔታ ውስጥ የግለሰብ ማንነት ይደበዝዛል፤ የግለሰብ ድምጽ ይዋጣል። የእያንዳንዱ የእነዚህ የአክራሪ ፓለቲካም ሆኑ አክራሪ ብሄረተኛ እንቅስቃሴዎች ተከታይ የሆነ ግለሰብ የማመዛዘን ችሎታው በእጅጉ ይዳከማል ወይም ጨርሶ ይከስማል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በዚህ ዓይነት የመንጋ ወይም የቡድን አስተሳሰብ የሚመሩ፤ ኃይማኖታዊ መሰል ጭፍን እምነትን የሚያራምዱ አክራሪና ጽንፈኛ የሆኑ የፓለቲካ፤ የብሄር እንቅስቃሴዎች ተከታዮች በአይምሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ይሆናሉ። የመንጋ ቡድን ተከታዮች የሆኑ ሰዎች የግል ነጻነታቸውን አረጋግጠው እንደ ነጻ ሰው ማሰብና ማመዛዘን የማይችሉ ስለሆነ የሚከተሉት አክራሪ የፓለቲካም ሆነ የብሄረተኛ ድርጅት ዓላማ ቆይቶ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር አስቀድመውና አሻግረው ማየትና መገንዘብ አይችሉም። የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ባለፉት አርባ አራት ዓመታት እነዚህን መሰል የመንጋ አስተሳሰብን የሚያራምዱ የፓለቲካ እንቅስቃሴዎችን በሁለት ዓይነት መልክ ሲያስተናግድ ቆይቷል። አንደኛው ቡድናዊ አስተሳስብን ያራምዱ በነበሩ የግራ ኃይሎች (ደርግና ተቃዋሚዎቹ በሆኑ የግራ ፓለቲካ ድርጅትች) አማካይነት ሲሆን ሌላው ደግሞ ማንነትን መሰረት አድርገው ቡድናዊ አስተሳሰብን ይዘው በተነሱ ብሄረተኛ እንቅስቃሴዎች (የኤርትራ፤ የትግራይ፤ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅቶች ወዘተ) አማካይነት ነው። በተለይ የነገድ ማንነትን ይዘው የሚነሱ የመንጋ እንቅስቃሴዎች (crowd movements) እጅግ ጥልቅ የሆኑና የሰዎችን ስሜት ሊኮረኩሩ የሚችሉ ስለሆኑ ተከታዮቻቸውን በስሜት
የማሳበድና ህሊናቸውንም የማሳወር አቅምና ክህሎት አላቸው። (Ethno-nationalism has the propensity and quality of fanning effectively or emotionally-charged sentiments among its blind followers).

የወያኔ ትግሬዎች መንግስት ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የከፋፍለህ ግዛው አስተዳደሩን ያጠናክርልኛል ብሎ ሰፊ የመፈንጫ ሜዳ የሰጠውና ከከበርቴ የነዳጅ ሀብት ባለቤቶች በሆኑ የአረብ ሀገሮች ይጎርፍለት በነበረ ገንዘብ በሺህ የሚቆጠሩ መስጊዶችን ሲገነባ የቆየ፤ ታሪካችንን የሚያፋልሱ፤ ህዝብን የሚከፋፍሉ የፕሮፓጋንዳ መጽሃፍቶችንና መጽሄቶችን በገፍ የሚያሰራጭ አክራሪ የሆነ ፓለቲካዊ ቃና ያለው የእስልምና እንቅስቃሴ (political islam) ወደ ኢትዮጵያ የፓለቲካ መድረክ ብቅ ብሏል። እስከ 2000 ዓ. ም ድረስ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ 180 መስጊዶች 130ዎቹ የተሰሩት ከ1986 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ባሉት ወያኔ ሥልጣን ላይ በመጣባቸው 14 ዓመታት ውስጥ ነው። በዚሁ ጊዜ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ቁጥር ደግሞ130 ነበር። (ምንጭ፡ “በኢትዮጵያ የኃይማኖት መቻቻል አለን? የሚለውን በሚያዝያ 2000 ዓ.ም. በአባ ሳሙኤል የተዘጋጀ መጽሃፍ ገጽ 40 ላይ ሄደው ይመልከቱ)።

ዛሬ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን 16.2% የሚሆኑት የእስላምና ተከታዮች ሲሆኑ (Central Statistical Authority 2007) የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች የሆኑት ደግሞ 74.7% (source EPRDF's Revolutionary Democracy and Religious Plurality: Islam and Christianity in post-Derg Ethiopia Jörg Haustein and Terje Østebø) የሚሆነውን ድርሻ ይወስዳሉ። እነዚህ ሁሉ መስጊዶች ከሀገር ውስጥ በተዋጣ ገንዘብ ብቻ የተገነቡ እንዳይደሉ ማንም ህሊናው በአክራሪ የእስልምና እምነት ያልታወረ ሰው ይረዳል። ይህ አክራሪ እስላማዊ ፓለቲካን የሚያራምድ ኃይል አድብቶ ጊዜ የሚጠብቅና ለሀገራችን ህዝብ ሰላም ከፍተኛ አደጋን የሚጋብዝ ክህሎት ያለው ነው። ይህንን ገደምም ጠመምም ሳላደርግ ለመናገር እፈልጋለሁኝ። ኃይማኖትን የመሰለ ከሰዎች ስሜት ጋር በጥልቅ የተያያዘ ጉዳይ ሊያተኩርበት ከሚገባው መንፈሳዊ ህይወት ወጥቶ ምድራዊ የሆነ ሀገራዊ ፓለቲካ ውስጥ እጁን ሲያስገባ ለአንድ ሀገር ሰላምና ነጻነት ታላቅ አደጋን ይጋብዛል። እኔ ፋሽስት የምለው የወያኔ መንግስትም ሆነ የተግባር ወላጁ የሆነው የጣሊያን ፋሽዝም ኃይማኖትን ተገን በማድረግ ህዝባችን በመከፋፈል ያደረሰውን ጉዳት አንርሳ (ይህን ጽሁፍ የምታነቡ የጣሊያን ፋሽስቶች እንዴት አድርገው የእስልምናን ኃይማኖት መሳሪያ በማድረግ፤ አንዱን ኃይማኖት ወግነው ሌላውን በማዳከም የኢትዮጵያን ህዝብ እንደከፋፈሉ የኢጣሊያዊውን የታሪክ ጸሃፊ የAlberto Sbacchiን Ethiopia Under Mussolini: Fascism & the Colonial Experience እና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሰባት መጽሃፍቶችን የጻፈው እስራኤላዊው የታሪክ ጸሃፊ Haggai Erlichን Saudi Arabia & Ethiopia: Islam, Christianity & Politics Entwined የሚሉ መጽሃፍቶች እንድታነቡ አሳስባለሁኝ)።

ወያኔም ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ቅንጅት ምርጫ ድረስ ይህንን የጣሊያን ፋሽስቶችን ስልት በመጠቀም ራሱን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ወገን አድርጎ በተለይ የኦርቶዶክስ ክርስትና ኃይማኖት ተቋሞችን ለማዳከም ሞክሯል። ዛሬ ሳውዲዎች የመን ውስጥ እያደረጉ ያሉትን ቀጥተኛ ጣልቃ-ገብነት በማየት በሀገራችን ላይ የተደቀነውን አደጋ መረዳት ይችላል። ሳውዲ አረቢያ የግመል መፈንጫ ሆኖ ሥራ የፈታውን የአሰብ ወደብ ለሃምሳ ዓመታት ተኮናትራ አፍንጫችን ሥር ጦሯን ያሰፈረችበት ሁኔታ አለ። እድሜ ለወያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ የወሃቢዎች አክራሪ እስላማዊ እምነት ስር ሰዷል። ኢትዮጵያ ውስጥ በልማት ሥም ሳውዲ አረቢያም ሆነ ሌሎች በአካባቢው ያሉና በረጅሙ ታሪካችን ለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት የሌላቸው እስላማዊ መንግስታት እያበረታቱ ያለውን አክራሪ እስላማዊ ፓለቲካን (radical political islam) መመልከቱ ሊመጣ ያለውን አደጋ መጠን መገንዘብ ያስችላል። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ በኢትዮያ ውስጥ በእነ ሳውዲ አረቢያ ገንዘብ በሚጎርፍለት የወሃቢዎች እንቅስቃሴ ምክንያት ከአለባበስ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የፈጠሩዋቸውን ተፅእኖዎች፤ በኢትዮጵያ ክርስቲያኖችና እስላሞች መካከል የፈጠሩዋቸውን በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ መራራቅና መጠራጠር ልብ ማለቱም ይበጃል። ይህንን እየሻከረ የመጣውን የኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች ግኑኝነት በተመለከተ መሀመድ ሰልማን የተባለ ጋዜጠኛ “ፒያሳ መሀሙድ ጋ ጠብቂኝ” በሚለው መጽሃፍ ውስጥ ሼ-መንደፈር በመርካቶ በሚል ርዕስ ሥር ያሰፈረውንና መጪውን ጊዜ በተመለከተ የሚያስፈራውን ሁኔታ በሚከተለው መልክ ገልጿል።

“የክሩሴድ (የመስቀል) ጦርነት ክተት የታወጀ እስከሚመስል ሁለቱም እምነቶች ዛቻን ያዘሉ ጽሁፎችን በአልባሳት እያተሙ ለአደባባይ አብቅተዋል። ይህች ደሴት እኔ ከምከተለው ኃይማኖት ሌላ ለማስተናገድ ቦታ የላትም ሲሉም ያወጁ ነበሩ። ይህን መሰሉን ነገር ስመለከት አብሮነታችን በቋፍ ያለ መስሎ ይሰማኛል። በድሮ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ እስላምና ክርስቲያን በአንድ ላይ ተዋደው ይኖሩ ነበር ሊባል የሚችልበት ጊዜ ቅርብ ሆኖ ይሰማኛል። እንዲህም አስባለሁ። የሼ-መንደፈር ታሪካችን ዘፈን ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችላል፤ አላህና እግዚአብሄር ካልታደጉት በቀር።” ምንጭ “ፒያሳ መሀሙድ ጋ ጠብቂኝ” ገጽ 151 በአቶ መሀመድ ሰልማን 2004 ዓ. ም. የተጻፈ መጽሃፍ። ምንም እንኳን መሀመድ ሰልማን ይህን ከላይ እሱ ከጻፈው መጽሃፍት የጠቀስኩትን ሁኔታ ከአክራሪው የወሃቢ ወይም ሳላፊዝም እምነት መስፋፋት ጋር ባያያይዘውም በእኔ እምነትና አረዳድ ይህ አዲስ ክህስተት በከፊል ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች የመጣ መሆኑ አያጠራጥርም። ይህን እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ያለ አሳዛኝ የኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ግኑኝነት ሁኔታ የሚያሳይ ትዝብቱን ለእኔ ከሀገሬ ከረጅም ዓመታት በፊት ወጥቼ ላልተመለስኩት ኢትዮጵያዊ ስለአስነበበኝ መሀመድ ሰልማን ምስጋና ይግባው።

የወያኔ ሥርዓት በፈጠራቸው እጅግ አሳዛኝ የሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የስነ ልቦና ችግሮች ሰለባ ሆነዋል። ይህን የስነ ልቦና ሰለባ የሆነና መድረሻ ያጣ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግርህ እርኩስ መንፈስ ነው እያሉት የሚያስጮኹትና የሚያደነዝዙት አክራሪ የፕሮቴስታንት እምነት አራማጆች ከምዕራቡ ዓለም ካሉ ኃይማኖታዊ ተቋማት ድጎማ የሚጎርፍላቸው ሲሆኑ ኢትዮጵያን በእጅጉ እየጎዱና ጠንካራ ዘመን ተሻጋሪ የነበሩ እሴቶቿንም እየሸረሸሩ ነው። እነዚህ በወያኔ መንግስት ይሁንታን ያገኙት የፕሮቴስታንት አክራሪዎች በበርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሥርጭቶቻቸው አማካይነት የኢትዮጵያን ህዝብ እያደነዘዙ ይገኛሉ። እነ መምህር ግርማን የመሳሰሉትም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ነን ባዮች እንደ አክራሪዎቹ ፕሮቴስታንቶች የወያኔ ሥርዓት በፈጠረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድቀት የጭንቀት ህይወት ውስጥ የገባውንና መድረሻ ያጣ ህዝባችንን ሰይጣን ነው፤ እርኩስ መንፈስ ነው ወዘተ የሰፈረብህ እያሉ ያደነዝዙታል። የወያኔም ሥርዓት በኃይማኖት ሥም እነዚህን መሰል ማደንዘዣዎችን እየሰጡ ህዝቡን የሚያታልሉትን አክራሪ የኃይማኖት ተቋማት እንዲስፋፉ በማድረጉ ህዝቡ ለእነዚህ ሁሉ አይምሮ-አዋኪና ጭንቀት-ፈጣሪ የሆኑ ወያኔ-ወለድ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ዋነኛ መንስዔ በሆነው የወያኔ የአፓርታይድ ሥርዓት ላይ እንዳያተኩር አድርገውታል።

የኤርትራ ብሄረተኞችና ጭፍን እምነታቸው፤ ለታላቁ መሪያቸው የነበራቸው አክብሮት የመንጋ እንቅስቃሴ ላይ መሰረቱን የሚያደርገው ብሄረተኝነት እንዴት በህዝብ ውስጥ ጭፍንነትንና ድንቁርናን እንደሚያስፋፋ ለማሳየት አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። ከዛሬ ሰላሳ አራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ማህበር በሆላንድ ያዘጋጃቸው በነበሩ ስብሰባዎች ላይ በሻቢያና ባጠቃላይ በኤርትራውያን ብሄረተኞች ላይ ያለኝን የተቃውሞ አስተያየት በአደባባይ በነጻነት እገልጽ ነበር። በዚያን ጊዜ በኤርትራዎች እንደ አምላክ የሚታየው የሻቢያ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ከደርግ መሪዎች የባሰ ሰው እንደሚሆንና ኤርትራውያንን ሲዖል ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል በግልጽና በእርግጠኛነት እናገር ነበር። ኤርትራውያን ብሄረተኞች ይህ አስተያየቴ እጅግ ያስቆጣቸውና ለድብድብና ለጠብ እንዲጋበዙ ያደርጋቸው እንደነበር ትዝ ይለኛል። አቶ አማኑኤል ነጋሲ የሚባል በሆላንድ የሻቢያ ወኪልና Eritrean Relief Association (ERA) የሚባል የእርዳታ አሰባሳቢ ድርጅት ተጠሪ የነበረ በዚያ ጊዜ እድሜው በአርባዎቹ ውስጥ የሚገመት ሰው ነበር። ታዲያ በአምስተርዳም ከተማ ውስጥ በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ የሻቢያን ድርጅት አምባገነንነት፤ የመሪውን የኢሳያስ አፈወርቂን አረመኔነት ስናገር አቶ አማኑኤል ወደ እኔ እያመለከተ ይህ ሰውዬ የመሪያችንንና የድርጅታችንን ሥም በሀሰት ያጠፋል እያለ ተናገረኝ። እኔ በዚያን ጊዜ ስለ ሻቢያም ሆነ ስለ አምባገነኑ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ አረመኔነት እናገር የነበረው ዝም ብዬ በጥላቻ ስሜት ተነሳስቼ ሳይሆን መረጃ ይዤ ነበር። ያኔ ኢሳያስ አፈወርቂ አረመኔ ሰው ነው ብዬ በስብሰባ ላይ የተናገርኩት ይህ ሰው መንካዕ (የሌሊት ወፍ) የሚል ስም ተሰጥቷቸው የነበሩትና ሻቢያን ተቀላቅለው ለኤርትራ ነጻነት ይታገሉ የነበሩ የኤርትራ ምሁራን እንዴት በአሰቃቂ ዓይነት በእሱ ትዕዛዝ እንደተገደሉ ከታሪክ መዛግብት አንብቤ በመረዳቴ ነበር። 

መንካዕ በሚባል ስም ከሚታወቁትና የኢሳያስ አፈወርቂን አምባገነን አሰራር ከተቃወሙ የኤርትራ ብሄረተኞች መካከል ዮሃንስ ስብሃቱን፤ ሙሴ ተስፋሜካኤል፤ አፈወርቂ ተክሉን የመሳሰሉ ግለሰቦች ይጠቀሳሉ። በወቅቱ ስለነዚህ ሰዎች መገደል ማንም ጥያቄ ሊያነሳ አልቻለም። የአገዳደላቸው ሁኔታ እንኳን በውጭ ሀገር ያሉ ኤርትራውያን ያወቁት እነዚህ ሰዎች ከተገደሉ ከአርባ ዓመታት በኋላ ነበር (ለዝርዝሩ የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ ይመልከቱ። http://mereja.com/forum/viewtopic.php?f=2&t=88221

እነዚህ በኢሳያስ የተፈጁ የኤርትራ ብሄረተኞች ቀደም ሲል በዐጼ ኃይለስላሴ ዩኑቨርሲቲ ውስጥ ተራማጅ የተሰኘና ዓለማቀፋዊነትን የሚሰብክ የግራ ፓለቲካ አቀንቃኞች ሆነው ይታዩ ነበር። ኋላ ላይ ግን እነዚህ ግለሰቦች ከሚያቀነቅኑት የግራ ፓለቲካ ጀርባ የኤርትራን የመገንጠልና ራሷን የቻለች ነጻ ሀገር የመሆን ድብቅ የፓለቲካ ዓላማ የሚያራምዱ ብሄረተኞች እንደ ነበሩ በተግባር አሳዩን። እነ ዮሃንስ ስብሃቱ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ አማራ ጠላታችን ነው ብሎ ድርጅታቸው ሻቢያ የሚያምንበትን እምነት የሚጋሩ ግለሰቦችም ነበሩ። እነዚህ በኋላ መንካዕ ተብለው በሻቢያ የተፈጁ የኤርትራ ተራማጆች ዐጼ ኃይለሥላሴ ዩኑቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች በነበሩ ጊዜ የኤርትራን ችግር ዲሞክራሲያዊ በሆነ የኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የመፍታት ዓላማ እንደነበራቸው የመሃል ሀገር ተወላጆች ለነበሩ የዋህ የኢትዮጵያ ተራማጆች ይገልጹላቸው ነበር። በተለይ ኢትዮጵያ በሚል ማር እስከ ተጠቀለለ ድረስ መርዝም ቢሆን ለመጠጣት ይሽቀዳደሙ የነበሩት የዋህ የመሃል ሀገር ተወላጆች በእነዚህ የኤርትራ ተራማጆች መታለላቸውን ያወቁት በጣም ዘግይተው ነበር። ይህ የዛሬው ትውልድ ከዚህ በትግርኛ ተናጋሪዎች (ይሄ የኤርትራን ብቻ ሳይሆን የትግራይን ተወላጆችንም ይመለከታል) በተደጋጋሚ ሲታለል ከነበረው የእኔ ትውልድ ልምድ ትምህርት ሊወስድ ይገባል። ይህ ትውልድ ዛሬ የግንቦት ሰባት መሪ ካድሬዎችና የኢሳት ቴሌቪዥን የኤርትራ መንግስት ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ስላለው “በጎ አመለካከት” የሚግቱትን ውሸት ለቅጽበትም ሊያምን አይገባም። የግንቦት ሰባትንና የኢሳትን አደንዛዥ ፕሮፓጋንዳ አምነው ኢትዮጵያን ከወያኔ ነጻ ሊያወጡ ወደ ኤርትራ የሚሄዱ የዋሆች ከእባብ እንቁላል እርግብ የሚጠብቁ መሆናቸውን ልብ ይበሉ።

በብርሃነ መስቀል ረዳ የሚመራውና ኋላ ኢህአፓ የሆነው ቡድን አባሎች ወደ ትግራይ ገብተው አሲምባ የሚባለው ቦታ ላይ የትጥቅ ትግል ለመጀመር ከማሰባቸው በፊት ወደ ኤርትራ ሄደው ሻቢያ የሚቆጣጠረው አካባቢ ለአንድ ዓመት ያህል እንዲቆዩ ተደርገው ነበር። ታዲያ እነዚህ የኢህአፓ ቡድን ሰዎች ሻቢያ ጦር ሰፈር ሲደርሱ ቀደም ሲል በዐጼ ኃይለስላሴ ዩኑቨርሲቲ ሳሉ ተራማጆች ነን፤ ኢንተርናሽናሊስት ነን እያሉ የመሃል ሀገሩን ኢትዮጵያዊ ሲያታልሉ የነበሩትን የኤርትራ ተወላጆች የሻቢያ ተዋጊዎች ሆነው እዚያ እንዳገኟቸው በሚከተለው የግርምት መንፈስ ነበር የገለጹት፡

“ወደ ኤርትራ ሜዳ እንደገባን የገረመን ዮሃንስ ስብሃቱንና አፈወርቂ ተክሉን እዛው በማግኘታችን ነበር። እነዚህ ወጣት ምሁራን በአዲስ አበባ ዩኑቨርሲቲ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ብሩህ ተስታፊዎችና መሪዎችም ስለነበሩ ነው አልዋጥልን ያለው”። ምንጭ አስማማው ኃይሉ ከጻፈው “የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት (ኢሕአሰ) ከ1964-1970 ዓ. ም.” ቅጽ አንድ ገጽ 40 ላይ ይመልከቱ። የኤርትራ ብሄረተኞች ቅዠትና በድል ማግስት የተከሰተው መራር እውነታ
እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የኤርትራ ብሄረተኛነት ስሜት በፈጠረው ሆያ ሆዬና እብደት ህሊናቸውን ስተው የነበሩ በርካታ ኤርትራውያን እንደ አምላክ ያመልኩት የነበረው ድርጅታቸው ሻቢያና አምባገነኑ መሪያቸው ኢሳያስ አፈወርቂ ይሳሳታሉ ብለው አያምኑም ነበር። በዚህ በስደቱ ዓለም በደርግ ዘመን ኤርትራዊ ሆኖ ሻቢያንም ሆነ የእሱን ተቀናቃኝ ጀብሃን የማይደግፍ ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ኤርትራውያን ዛሬ እንዲህ አንገታቸውን ሊደፉ በደርግ ዘመን በዚህ በስደት ዓለም ስንኖር የኤርትራ ብሄረተኝነት በፈጠረባቸው ስሜት ምክንያት በጠላትነት የሚያዩዋቸውን ኢትዮጵያውያንን ማናገርና መቅረብ እንኳን ይጠየፉ ነበር። እነሆ የኤርትራ ብሄረተኝነት የደስታና የሰላም ምንጭ መሆኑ ቀርቶ እንደ አሜኬላና እሾክ ኤርትራውያንን እየወጋ ከሀገር አስወጥቶ ቀጣይ የኤርትራ ትውልዶችን ለሌላ ዙር ስደት፤ ለዐረብ ሀገሮች ባርነት ወዘተ ሥቃይና ሞት የሚዳርግበት ዘመን ላይ ደረስን።

የደርግ መንግስት ወድቆ ሻቢያና ወያኔ ሥልጣን ላይ እንደወጡ በሆላንድ የነበርን የእነዚህን ሁለት ቡድኖች እኩይ ዓላማ የምንቃወም ኢትዮጵያውያን በሰኔና በሃምሌ 1983 ዓ.ም. ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፎችን ዘሄግ (the Hague) በሚባለው የሆላንድ መንግስትና የውጭ ኤምባሲዎች መቀመጫ የሆነች ከተማ ውስጥ አደረግን። በዚያን ወቅት ኤርትራውያንና ወንድሞቻቸው የሆኑት የትግራይ ተወላጆች ደግሞ ደስታቸውን በአደባባይ በጭፈራ ሲገልጹ በቴሌቪዥን ይታዩ ነበር። በወቅቱ የእኛን ሰልፍና ተቃውሞ ማንም የሆላንድ ቴሊቪዥን ዜና አድርጎ ሊዘግብልን አልፈለገም። ታዲያ በዚህ ሀገር De Volkskrant የተባለ አንድ ትልቅ እለታዊ ጋዜጣ አንዱን የደች ጋዜጠኛ ልኮ የኤርትራውያንን፤ የትግራውያንንና እንደዚሁም የወያኔ ተቃዋሚ የሆነውን ኢትዮጵያውያን አስተያየት አካትቶ ለመዘገብ ተነሳ። በወቅቱ በሆላንድ የኢትዮጵያ ማህበር ሊቀመንበር ስለነበርኩ በኢትዮጵያውያኑ በኩል ያለውን አቋም እንዳስረዳ ተጠየቅሁኝ። ጋዜጠኛው “ኤርትራውያን ሀገራቸው ነጻ ወጥታ እጅግ ተደስተዋል፤ እንዲያውም አሁን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በጦርነት የተጎዳ ሀገራቸውን ሊገነቡ እንደሚያስቡ ያነጋገርኳቸው ኤርትራውያን ሁሉ ነግረውኛል። የእናንተ ኢትዮጵያውያን ማህበር አባሎች ደግሞ ለውጡን በመቃወም ሰልፍ ትወጣላችሁ። ይህ ለምን ሆነ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም “እኛ ኢትዮጵያውያን አሁን አዲሱን መንግስት የምንቃወመው በጠመንጃ ኃይል የመጣና አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያገለለ ጠባብ ማህበረሰባዊ መሰረት ያለው አናሳ ቡድን በመሆኑ፤ ጎሳንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ የህዝብንና የሀገርን አንድነት የሚያፈርስ ፓሊሲ አራማጅ በመሆኑ፤ ጸረ-ዲሞክራሲያዊ የሆነ አቋም ያለው መንግስት በመሆኑ ነው” ብዬ አስረዳሁት። “ይህ የወያኔ መንግስት ፓለሲ ደግሞ በዘላቂነት ኢትዮጵያን የሚበታትን ነው” አልኩት። “ኤርትራውያን ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ነው ላልከኝ ምን አለ በለኝ እንኳን እዚህ ያሉት ኤርትራውያን ወደ ኤርትራ ሊመለሱ ቀርቶ ገና ብዙ ኤርትራውያን ከኤርትራ ወደ ምእራቡ ዓለም በገፍ እንደሚመጡ በእርግጠኛነት ልነግርህ እፈልጋለሁ” አልኩት። (Mark my words far from witnessing a return of Eritreans to independent Eritrea, you should expect even more Eritreans flocking out of Eritrea towards Western Europe)” ይህ ቃለመጠይቅ De Volkskrant ከሚባለው ጋዜጣ ጋር በJuly 1991 የተደረገ ነበር። 

ዛሬ ያቺ የአፍሪካ ቀንድ ሲንጋፓር ትሆናለች የተባለችው ኤርትራ የምድር ሲዖል መሆኗን የሚናገሩት ትላንት የኤርትራ ህዝብ በደርግ ደረሰበት ስለሚሉት ግፍ እጅግ የተጋነነና በቀዝቃዛው ጦርነት (የምዕራቡና የሶቪዬት ህብረት ፍጥጫ) ስሜት የተቃኘ ወገናዊ ዘገባ ያቀርቡ የነበሩት እነ አምነሲቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋችን የመሳሰሉ ተቋሞች ጭምር ናቸው። ይህንን አምነስቲ ኢነተርናሽናል From Hell to Hell: Eritreans at Home and Abroad በሚል ርዕስ ሥር ኤርትራን በሲዖልነት የፈረጀበትን ዘገባ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ ይመልከቱ። https://www.neweurope.eu/article/hell-hell-eritreans-home-and-abroad/ published on May 4, 2013.

እነሆ ከላይ እንዳመለከትኩት ይኸው ያልኩት ነገር አልቀረም፤ ኤርትራ ውጭ ያሉ ስደተኞቿ ወደ እሷ የሚጎርፉባት ሳትሆነ እንዲያውም ዋነኛ የስደተኞች ምንጭ ሆነች።ዛሬ ኤርትራውያን ጥይት እየተተኮሰባቸውም እንኳን ቢሆን ትላንት በብሄረተኛነት ስሜት ሰክረው እጅግ ያመልኩት ከነበረው ሻቢያ በመሸሽ ድንበር እያቋረጡ ወደ አውሮፓ እየጎረፉ ነው። እነሆ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2015 ዓ.ም ከመላው ዓለም ወደ ሆላንድ ከገቡት ስደተኞች ውስጥ በብዛት ረገድ የአንደኛነቱን ደረጃ ሶርያዎች(36%) ሲይዙ እነሱን በመከተል የሁለተኛውን ደረጃ የያዙት ኤርትራውያን (21%) ስደተኞች ነበሩ። (የዚህ አሃዛዊ መረጃ ምንጭ ---› VLUCHTELINGEN IN GETALLEN 2015 የሚለው የሆላንድ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ያወጣው ዘገባ)። ለስድሳ ዓመታት ያህል አማራን ጠላት አድርጎ፤ በአማራ የመሰላትን ኢትዮጵያን የጥላቻው ዒላማ አድርጎ የተነሳው የጣሊያን ቅኝ ገዢዎች ስሪትና ውላጅ የሆነው የኤርትራ ብሄረተኛነትና የሚያጠነጥንበት ኤርትራዊ ማንነት፤ ከዚሁ ብሄርተኝነት የተጸነሰውና ኤርትራውያን በኩራት “ገድሊ” እያሉ የሚጠሩት ትግላቸው ጥፋትን እንጂ ልማትን አላመጣላቸውም። የኤርትራን ብሄርተኞች የስድሳ ዓመት ከንቱ ትግል በተመለከተ ራሱን ከኤርትራ ብሄርተኞች መንጋ ተርታ በማውጣት በነጻነት ለማሰብ በመቻሉ ሚዛናዊ አመለካከት ያዳበረውን የኤርትራዊውን ምሁር የአቶ ዮሴፍ ገብረህይወትን በሳል ትንተና በሚከተለው ማስፈንጠሪያ አማካይነት ያንብቡ።
(https://dissidentdiaries.files.wordpress.com/2013/06/romanticizing_ghedli.pdf

ይህ በአፍሪካ ረጅሙ ለነጻነት የተደረገ የትጥቅ ትግል እየተባለ ይነገርለት የነበረው “ገድሊ” የተባለ የነጻነት ትግል አርቀው ማሰብ በማይችሉና በኤርትራ ብሄረተኛነት ስሜት በሰከሩ የኤርትራ ምሁራን ሲቀነቀን ኖሮ ያተረፈው ነገር ሞትን፤ ስደትን፤ የትውልድን ምክነትን፤ ምሬትን፤ ነባር ባህሉንና እሴቶቹን ያጣ የኤርትራ ትውልድና ማህበረሰብን ነው። የብሄረተኛነት ፍሬ ሲያዩት ጣፋጭና አስጎምጂ ቢመስልም በመጨረሻ ላይ ግን እጅግ ጎምዛዛ ነው። አንድ ነገድም ሆነ ህዝብ ራሱን የመንጋ እንቅስቃሴ አካል ሲያደርግ የኋልዮሽ ጉዞ ያደርጋል (societal regression ይሉታል ሳይኮአናሊስቶች)። በስተመጨረሻ ይህ ራሱን የብሄረተኛ ድርጅት ተቀጥያ አድርጎ በመንጋነት የሚነዳ ህዝብ በህይወቱና በንብረቱ ከፍተኛ ዋጋን ይከፍላል። የጀርመን ናዚዎችን አጅበው ሆ ሲሉ የነበሩ በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የጀርመን ተወላጆችና እንደዚሁም የጣሊያን ፋሽስቶችን አጅበው በሮም አደባባይ የወርቅና የአልማዝ የጋብቻ ቀለበታቸውን ጭምር ሙሶልኒ በኢትዮጵያን ላይ ለከፈተው ፋሽስታዊ ጦርነት ማካሄጃ እንዲሆን የሰጡት የጣሊያን ተወላጆች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። እንደዚሁም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኤርትራ ብሄረተኛነት ስሜት አብደው ለሻቢያ ሲያረግዱ የነበሩ ኤርትራውያንና የድል አድራጊው የሻቢያ ጦር አስመራ ሲገባ አበባና ቆሎ ሲረጩ የነበሩ የኤርትራ ተወላጆች ከባድ የህይወትና የንብረት ዋጋ ከፍለዋል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ የወያኔ ትግሬዎችም እጣ ከዚህ የሚለይ አይሆንም!!!!

እስካሁን ድረስ የሰዎችን መንጋ በማንቀሳቀስ የሚካሄዱ የፓለቲካ እንቅስቃሴዎችን ባህርይ ከገለጽኩኝ በኋላ ከዚህ ቀጥሎ በተከታታይ ትኩረቴን የማሳርፈው የነገድ ማንነትን መሰረት አድርጎ በተነሳው አክራሪ የትግራይ ብሄረተኛ እንቅስቃሴና ይህ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ በፈጠረው ፋሽስታዊ ሥርዓት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ተከታታይ ጽሁፎቼን “ፋሽዝም በአንድ ህዝብ ማንነት ላይ የተመሠረተ ጽንፈኛና አክራሪ ብሄረተኛነት መገለጫ ነው” በሚል ርዕስ ሥር አቀርባለሁኝ። አንባቢ ይህንን ስለ አክራሪ የትግራይ ብሄረተኛነት መገለጫ የሆነ የፋሽዝም ሥርዓት ምንነት ስገልጽ እያንዳንዱ የአንድን ነገድ ወይም ህዝብ ማንነት መሰረት ያደረገ አክራሪ ብሄረተኛ እንቅስቃሴ (የኦሮሞም ይሁን የሶማሌ፤ የአማራም ይሁን የጉራጌ፤ ወዘተ) በስተመጨረሻ አስከፊ ወደ ሆነ ፋሽዝምን የመሰለ ጭፍን የአምባገነነት ሥርዓት እንደሚያመራ ግንዛቤ እንዲወስድ እጠይቃለሁኝ። ማንኛውም ነጻ የሆኑ ግለሰቦች ሃሳብ የማይሰማበት፤ የመንጋ ቡድኖች ድምጽ የጎላበት የፓለቲካ እንቅስቃሴ ለአንድ ሀገር ወይም በውስጧ ለሚኖረው ህዝብ ታላቅ አደጋን ይጋብዛል። ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበት ሁኔታ በእጅጉ አውሮፓ በአስራ ዘጠኝ መቶ ሰላሳዎቹ ውስጥ የገባችበትን አክራሪ ብሄረተኛነትና የፋሽስት እንቅስቃሴዎች የተስፋፉባቸውን ወቅቶች ያስታውሰኛል። የእስላማዊ አክራሪነት አደጋም በዚች ሀገር ላይ እያንዣበበ ነው። ለሃያ ሰባት በፋሽስት አገዛዝ ምክንያት በደቀቀችና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በተንሰራፋበት ሀገር ውስጥ ለአክራሪ ፓለቲካ፤ ለአክራሪ ብሄረተኛነትና ለአክራሪ ኃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች መስፋፋት አመቺ የሆኑ እድሎች ይፈጠራሉ። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1994 ዓ.ም 55.4 million የነበረው የኢትዮያ ህዝብ ቁጥር ዛሬ ወደ 106. 6 ሚሊዮን ከፍ ብሏል። እንግዲህ ይህ ቁጥር በሃያ አምስት ዓመት ውስጥ በእጥፍ አደገ ማለት ነው። ይህ ሁሉ አሳሳቢና ችግራችንን የሚያወሳስብ ነው። ላለፉት አርባ አራት ዓመታት ከኢትዮጵያ አብዮት ፍንዳታ ጀምሮ ያስተናገድናቸው የፓለቲካ እንቅስቃሴዎች ባመዛኙ ሀገራዊ ጥፋትና ውድመትን፤ የእርስ በርስ ጦርነቶችን፤ የጅምላ መፈናቀሎችን ወዘተ አስከትለዋል። በእነዚህ ረጅም የጥፋት ዓመታት ውስጥ በአስተሳሰባቸው የሰከኑ አዋቂ ሰዎች ነጻ ሃሳቦቻቸውን እንዳያሰሙ የታፈኑበት፤ የመንጋ ቡድኖች በስሜታዊነት የሚነዷቸው ጭፍን ወገኖች ድምጾች የገነኑበት ዓመታት ነበሩ። ከሃያ ሰባት ዓመት የወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝም በኋላ ኢትዮጵያን ወያኔ ባጸደቀው የጎሳ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ሥር እንድትቀጥል የተማማሉት የአክራሪ ብሄረተኛ ኃይሎች ድምጾች ዛሬ እጅግ እየጎሉ በመምጣት ላይ ይገኛሉ። ከዛሬው ሆያ ሆዬ ባሻገር የዚህን የመንጋ ቡድኖች እንቅስቃሴዎች የገነኑበትን ፓለቲካ አሉታዊ ክትያዎች (consequences) ውጤቶች ማየት የቻሉ ድምጾች ጎልተው ዛሬም ድረስ አይሰሙም። እነዚህ የአክራሪ ብሄረተኛነት ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ድምጾች መጉላት መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ በጎ ነገርን ያመጣል የሚል ተስፋን እንድሰንቅ አያደርጉኝም።

-----------------------------------ክፍል ሁለት ይቀጥላል።  Posted at Ethiopian Semay

No comments: