ክፍል 2 ትግርኛ ተናጋሪ ኤርትራውያን እና ትግሬዎች
መልስ
ለቬሮኒካ መላኩ
ጌታቸው ረዳ
(ኢትዮ ሰማይ አዘጋጅ)
ባለፈው ሰሞን በክፍል 1 ጽሑፌ ኤርትራኖች እና ትግሬዎች በቋንቋ
ብቻ ሳይሆን በደም አጥንትና በሃይማኖት የተዛመዱ መሆናቸውን በማስረጃ አቅርቤአለሁ። ቬሮኒካ መላኩ <<“ትግራዮች እና የኤርትራ ብሄረ ትግርኛ ሁለቱ የተለያዩ ነገዶች /ብሔሮች ናቸው !” በማለት ስለ ጻፈቺው>> የሰጠሁት መልስ የትግራይ
ተወላጆች የቅርብ ጓደኞቼ የቬሮኒካን የታሪክ ደንቆሮነት አስገርሞአቸዋል። በርካታ ኢመይሎችም ደርሰውኛል። አንዳንዶቹ ኤርትራውያን ናቸው። በቀረበው ሰንድ ጭራሽ
ያልገመቱት የሕዝብ ትስስር እና ስብጥር ሆኖ ስላገኙት በጣም በመገረማቸው፤ ከነሱ መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፤-
<< “አገር ለመመስረት ትግሉን በመምራት እውን ያደረጉት
የትግራይ ተወላጆች ወልደአብ ወልደማርያም እና ኢሳያስ አፈወርቅ ብቻ የመሰለን ብዙ ነን።የእነሱ ትግሬነትም በድፍን ድፈን
ብዙ አይወራም ነበር። እንደብቅ ካላልንና እራሳችንን ለማሞኘት ካልፈለግን አንተ እንዳልከው እያንዳንዱ ኤርትራዊ ውስጣዊ ሐረጉ ምን
እንደሆነ ስለሚጠራጠር ስለነሱ ትግሬነት ቀልብ አልሰጠውም ነበር ። በሚገርም ዘዴ በልዩ ሕዝብነት የሰበኩን ደግሞ እራሳቸው በአባትም
እናትም ከትግራይ የተወለዱ እነ ወልደ አብ እና ኢሳያስ አፈወርቂ መሆናቸውን ስንመለከት ልዩ ጥናት ያስፈልገዋል። በጣም እናመሰግንሃለን፤
አስገራሚ ሰነድ!”>> ሲሉ በትግርኛ ጽፎልኛል። እኔም አመሰግናለሁ።
ቬሮኒካ በጥርጣሬ ሻዕቢያው ተስፋየ ገብረአብ ሊሆን ይችላል
በሚል አንድ መላምት ጠቅሼ ነበር። አሁን ግን እሱ አይደለም። ችግሩ ጸሐፊዎች በራስ መተማመን እና ያላወቅንላቸው ፍራቻ ስላላቸው
በድብቅ ስም እየጻፉ ሕዝብን ሲያወናብዱ ማየት ከሚያሳዝነው ነገር አንዱ ይህ ችግር ነው። ባለፈው ክፍል መላው የትግራይ ክ/ሃገር
አውራጃዎች ያካተተ በርካታ የትውልድ ሓረግ፤ እዛው መረብ ምላሽ ከነበረው ቀደምት ትውልድ ጋር በመደባለቅ የዛሬውን ትውልድ የፈጠረ
መሆኑን እና በርካታ የኤርትራ ትውልዶች እና የቦታ ስሞች በነዚህ የትግራይ ሰዎች እንደተሰየሙ በማስረጃ አቅርቤአለሁ። ሳልጠቅስ
የማላልፈው ግን፤ ያልተጠቀሱ የዛሬዎቹ የደምበዛን (ሓማሴን) ኗሪዎች ከደምብያ ጎንደር አካባቢ እንደመጡ በጣም በርካታ ማስረጃዎች
በመጽሐፉ ውስጥ ይገኛሉ። እነሱም አስፈላጊ ስላልነበረ ዘልየዋለሁ።ከሞላ ጎደል ከያንዳንዱ የትግራይ አውራጃ/ወረዳ ወደ መረብ ምላሽ ሄደው ከዘመነ አክሱም ጀምረው እስከ
ቅርብ ጊዜ እንዴት እንደተዋለዱ አሳይቻለሁ። ያንን እውነታ የማፍረስ ሃይል ያለው “ፈጣሪ” እንጂ በቅዠት ዓለም እየባነኑ ያሉት እነ “ቬሮኒካ መላኩ” ወይንም የቬሮኒካን ጽሑፍ
ወደ ትግርኛ የተረጎመው ያልተከረከመው የሻዕቢያው “ድንጋይ” ኢብራሂም መሐመድ አይቻላቸውም።
ዛሬ የማቀርብላችሁ፤ በቬሮኒካ መላኩ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ “ብሔረ ትግርኛ” በሚል ሻዕቢያ የሰጣቸውን
አዲስ የመጠሪያ ስም ተቀብለው ራሳቸውን የሚጠሩ የኤርትራ ትግርኛ ተናጋሪ ‘ትግሬዎች” ከመረብ ምላሽ ‘ወዲህ’ ላሉት ትግርኛ ተናጋሪ ትግሬዎች እንዴት እንደሚመለከትዋቸው በዓድዋው
እና በተምቤኑ ተወላጁ በኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩ የሻዕቢያ “ካልቶች” በሚከተለው ሁኔታ ያይዋቸዋል ብላ ስላለቺው መልስ እሰጣለሁ።
የቬሮኒካ ውሸት እጠቅሳለሁ፦
<< ብዙ ወገኖች ትግራዮች እና የኤርትራ ብሄረ ትግርኛ አንድ አይነት ብሔር ይመስሉዋቸዋል። በመሰረቱ ግን ሁለቱ ፍፁም የተለያዩ ነገዶች ናቸው።ትግራዮች የኤርትራ ብሄረ ትግርኛን ትግራዮች ናቸው፤ አንድ ብሔር ነን ብለው ያስባሉ። ብዙ ትግራዮችም ኤርትራዊ የመሆን ፍላጎት አላቸው። የባድመ ጦርነት ከመነሳቱ በፊት ብዙዎቹ ትግራዮች ራሳቸውን ኤርትራዊ እያሉ ይጠሩ ነበር። ከባድመ ጦርነት በሁዋላ እነዚህ ትግራዮች ከፍተኛ የሆነ የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል። በተቃራኒው ብሄረ ትግርኛዎች ስለ ትግራዮች ያላቸው ስሜት ምን እንደሆነ ሲጠየቁ ትግራዮች ወይም አጋሜዎች እያሉ ይጠሩዋቸዋል። (Hassan Adem, M.T., Tekle B, 2010) እነዚህ ኤርትራውያን ብሄረ ትግርኛዎች ትግራዮችን የማይታመኑ እና ልባቸው የማይገኝ አድርገው በአሉታዊ መንገድ ይስሉዋቸዋል። ”Eritreans sometimes contemptuously refer to them-
cannot be trusted and never could.” (Smith,et al. 2003, Africa, volume 73,
p.377) ። በኤርትራውያን ብሄረ ትግርኛዎች ላይ በተደረገው በዚህ አንትሮፖሎጅካል ማህበራዊ ጥናት ላይ አንድ የ eplf ታጋይ የነበረ ለፕሮፌሰር ሪድ ”አባቶቻችን እና ቅድመ አያቶቻችን እነዚህ ትግራዮች አደገኛ ናቸው በደንብ እናውቃቸዋለን ብለው አስጠንቅቀውናል” ብሎ ኤርትራውያን ነፃነታቸውን ባወጁበት ዓመተምህረት በአውሮፓ አቆጣጠር በ1991 ወይም በ1983 ኢ.አ ምስክርነት ሰጦ ነበር። “Be careful, these people are dangerous, we know them
well!” (Smith,et al. 2003, Africa, volume 73, p.377 )>> (ቬሮኒካ መላኩ)
ስትል ሻዕቢያና የሻዕቢያ ፈረንጆች በማስረጃ አጣቅሳ የተናገሩትን የሻዕቢያ ስነልቦና አላዋቂነትዋን ነግራናለች። እንዲህ ያሉ ሕሊናዎች ትንንሽ ሰዎች ከመሆን አልፈው ያስተማራቸው ግብር ከፋይ ሕዝብ ቤተሰብንትና አንደነቱን ለመበተን ሲጥሩ ማየት ያሳዝናል። በሁለቱም በኩል ያሉት የተማሩት ክፍሎች በአሳፋሪ የሕሊና ውድቀት ሲታዩ ፈረንጆች “ቦቶም ራክ ረገጠ” የሚሉት የዝቅተት ወለል መርገጣቸውን ብዙ አመት ተናግሬአለሁ።፡ለዚህም ነው የተማሩ ክፍሎች አሁን ላለንበት ውድቀት ዳርገውናል ስል የነበረው።
ትግሬዎች
የማይታመኑ ናቸው ስለተባለው መልስ እነሆ።
የኤርትራ
አገርነት ምስረታና ህልውና ያለ ትግሬዎቹ ለምሳሌ ያለ ኢሳያስ አፈወርቂና ወልደአብ ወልደማርያም የማይታሰብ ነው። ኤርትራኖች በተለይ በትግሬው ኢትዮጵያዊው ኢሳያስ አፈወርቂ የተመራው የኤርትራን አገርነት የመመስረት ሰልት የሌላ አገር ሕዝብ መስሎ ለመታየት ምን ያህል ርቀት
ተጉዞ በራስ ላይና በወላጆቻቸው ታሪክ ጭምር ክሕደት እንደተኬደ የማቀርብላችሁ ሚከተለው ማስረጃ ስትመለከቱ ሻዕቢያዎች ትግሬነታቸውን ብቻ ሳይሆን አፍሪቃዊ ማንነታቸውንም ጭምር በመፋቅ ለቅኝ ገዢዎች አጎብዳጆች ብቻ ሳይሆኑ የነጭ ቆዳ ልእልና በጥቀሮች ትግል ቅስም መሰበሩን አሳዝኖአቸው
እንደነበር አሳያለሁ። ማስረጃየም እነሆ፡
የጥቁር ሕዝቦች አካል የሆነው በትግሬዎች የተመራው በቅኝ ገዢዎቹ በጣሊያኖች ላይ የተቀዳጀው የዶጋሊ ጦርነት ታስታውሳላችሁ። የጀግንነት ታሪክና አይበገሬነት ከወራሪዎች ጋር ሲተናነቁ ለወደቁት በርካታ “የባሕረ ምድር እና የትግራይ ተወላጆች” ለከፈሉት ክቡር መስዋዕት የደርግ መንግሥት ያቆመው የመታሰቢያ ሃወልት ማን አፈረሰው? ለምንስ እንዲፈርስ ተደረገ? የሚለው በዚህ ጥያቄ እንድንጀምር እንድታሰምሩበት እፈልጋለሁ።
<<“ሻዕቢያ ኤርትራን ነፃ ካወጣ በኋላና በኤርትራ ‘መንግሥት’ ካቋቋመ በኋላ ተቀዳሚ ተግባሩ ያደረገው ዶጋሊ ላይ የራስ አሉላን ሐውልት ማፍረስ ነበር። በ1879 ዓ.ም ዶጋሊው ጦርነት ላይ 500 ጣሊያኖች በሞሞታቸው ኤርትራውያን ለምን እንዳዘኑ ብዙ ታዛቢዎች በውል ሊገባቸው አልቻለም።”>>
(መድሃኒየ ታደሰ -አዲስ አበባ በኮተቤ የትምህርት ተቋም አስተማሪና የምስራቅ አፍሪቃ ግጭቶችና የፖለቲካ ተንታኝ ልዩ ባለሞያ)
Eritrean and Ethiopian war -Retrospect and Prospect (የኤርትራና የኢትዮጵያ ጦርነት የግጭቱ መነሸና መድረሻ ገጽ 34)
“በ1879 ዓ.ም ዶጋሊው ጦርነት ላይ 500 ጣሊያኖች በሞሞታቸው ኤርትራውያን ለምን እንዳዘኑ” ከአንትሮፖሎጂስቶቹ ቬሮኒካ መላኩና ኢበራሂም መሐመድ መልስ እንጠብቃለን።
ትግሬዎች እነማን ናቸው ብላ
ቬሮኒካ ለምትጠራጠረው ሕዝብ መልስ ልስጥ ። ለእርስዋ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ለምናያቸው መሰል ጸሐፍትም ጭምር። ትግራይ የሚለው
ስም በአገር ስም፤ በክፍለሃገር ስም መጠሪያ ሆኖ ‘በአክሱም ዘመነ መንግሥትም ሆነ በዛጉዌ ዘመነ መንግሥት’ ትግርኛ ቋንቋ
ተናጋሪዎች ማንነት ወይንም መጠሪያቸው ምን እንደነበር የሚታወቅ እንደሌለ ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች ይከራከራሉ። እኔ ደግሞ ለዚህ
የሰጠሁት መልስ ነበር። እሱም በዘመነ አብርሃ አጽብሃ ትግሬዎች እንደነበሩና በስማቸው አንደተጠሩ ባለፈው ሰሞን በአቡነ ሰላማ
የተጠቀሰ መሆኑን የግዕዙን ጥቅስ ገልጫለሁ። የኔን ክርክር ካልተቀበላችሁ፤ አንድ ነገር መስማማት እንችላለን። ይኼውም እንዲህ
ነው።
“የታሪክ ምሁራን የሚስማሙበት አንድ ሃቅ አለ።ይሄውም ክልሉ የትግርኛ ተናጋሪዎች ማዕከል
መሆኑ ነው” (ታደሰ ታምራት1964-53) (መድሃኔ ታደሰ) ዘኒ ከማሁ}። ይህንኑ አጠቃላይ ግንዛቤ የሚጻረር እስካልቀረበ ድረስ
የዛሬዎቹ የትግርኛ ናጋሪዎች በአክሱምና በጥንቶቿ ቅርሶች አካባቢ መኖራቸው ከላይ በተጠቀሰው ድምዳሜ ይሆናል።
የትግርኛ ተናጋሪዎች
አካባቢ ማለትም የዛሬው የኤርትራ ትግርኛ ተናጋሪ እና የትግራይ ትግርኛ ተናጋሪ አካባቢ ማሕበረሰብ ሲመሰረት ቋንቋን መሰረት ያደረገ
የግዛት አስተዳደር ነበር ብሎ ማለት ይቻላል። አሁን በቅርቡ በ17ኛ ምዕተ ዓመት ሁለተኛው አጋማሽ ላይ እንኳን የትግራይ ክልል
ካርታ እንደሚያመለክተው የክልሉ ድንበር ሐማሴን ሰሜን ምስራቅ ጫፍ ወይም ቀይ ባሕር ዳርቻ ሲጠጋ ደቡብ ደግሞ እንደርታ ይደርሳል።>>
(ባራዳስ) Tractatus
Tres Historico-geographici 1634: A Seventeenth Century Historical and
Geographical Account of Tigray, Ethiopia (Aethiopistische Forschungen) Dec 31, 1996 by
Manoel Barradas and Elizabet Filleul) የውስጥ አስተዳደርን በተመለከተ ደግሞ የተለያዩ ገዢዎች በተለየ
የማዕርግ መጠሪያ እስከ ዘመነ መሳፍንት መጀመሪያ ድረስ ገዝተዋል።ለምሳሌ የትግሬ መኮንን፤ባሕረ ነጋሽ፤,,,ወዘተ። ነገር ግን ሹም
ሽሩን በተመለከተ ወሳኝ ሥልጣን የነበረው የጐንደር ቤተመንግሥት ወይም ንጉሥ ነበር። ይህንን አባባል በማስረጃ ለማስደግፍ ከተፈለገ
ከ1512-1519 ዓ.ም ብቻ አራት ባሕረነጋሾች በንጉሡ ትዕዛዝ ሥልጣን እንዲለቁ ተደርገዋል ወይንም ቦታ ቀይረዋል (አልቫሬዝ፤
1953፡93) ከላይ ከተጠቀሰው ዘመን በኋላም ቢሆን በትግራይ አካባቢ ያሉት የአካባቢ ገዢዎች (የባሕረ ነጋሹም
ጭምር) ዕጣ ፈንታቸው የሚወሰነው በጐንደር ነገሥታት ነበር። ቢሆንም ግን የትግርኛ ተናጋሪዎች አከባቢ ትግራይን የፖለቲካ ማዕከል
በማድረግ የተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ማዕከል በማድረግ አንድ ዓይነት የሆነ (ከጥንት ጀምሮ የተገነባ) የቋንቋና የባህል መለያ
ፈጥሯል። {መድሃኔ ታደሰ (ዘኒ ከማሁ)}። የሕዝቡን አንድነት እንኳን ከተመሳሳይ ባሕል፤ሃይማኖትና ቋንቋ ካለው አንድ ሕዝብ ቀርቶ
አማርኛ ከሚናገረው የጎንደር አማራ ጭምር የተዛመደ መሆኑንም ጭምር ያሳያል።
ትግሬዎችና ኤርትራኖች በተለያዩ ወቅቶች ጦርነት ውስጥ ገብተው ግጭት መፍጠራቸው የተለያዩ
ሕዝቦች አድርገው ለመሰሪ ዓላማቸው መጠቀሚያ እንዲሆን እነ ቬሮኒካ መላኩ እና ሻዕቢያዎች የሚስሉት ጠማማና ከፋፋይ ስዕል
በሚመለከትም መልሴ የሚከተለው ነው።በተለያዩ ከምድሪ ባሕሪ ወዲያ ና ወዲህ የሉት አውራጃ ወይንም አካባቢ ገዢዎች በየጊዜው
ይታዩ የነበሩት አለመግባባቶች ምክንያቶች “አንድ ሕዝብ አይደለንም” ከሚል ሳይሆን የነዚህ አካባቢ ተወላጅ መኳንንቶች ራሳቸውን
የትግርኛ አካባቢ የበላይ ገዢዎች ለማድረግ ከነበራቸው የሥልጣን መያዝ ፍላጎት እንጂ የተለዩ ሕዝቦች ሆነው ለማሳየት አልነበረም። የተለየን ሕዝቦች ነን ብለው ብቅ ያሉት
አስገራሚ የሚያደርገው እራሳቸው
ባባታቸውም በናታቸውም ከአክሱም፤ከዓድዋ፤ዓዲግራትና ከተምቤን የተወለዱ የኤርትራን ልዩ አገርነት እውን ለማድረግ የመሰረቱና
የመሩት ሟቹ ወልደ አብ ወልደማርያም እና እስካሁንም በሠልጣን ላይ የሚገኙት እነ ኢሳያስ አፈወርቂ እና በሥሩ ያሉ የካቢኔው
ባለሥልጣኖች ብዙዎቹ ትግሬዎች እንጂ ከዚያ በፊት በልዩ ሕዝብነት የተመሠረተ የጎላ እንቅስቃሴ አልነበረም።
ከዚያ ባሻገር በጥንቱ ዘመን ሥልጣን ለማግኘት ራሳቸውን ያካባቢው ተወካዮች አድርገው በጎንደር ነገሥታት ፊት ለመታየት
ሲያደርጉት የነበረው ግጭት እንዲሰመርበት እፈልጋለሁ።
ለዚህም ማስረጃ ላቅርብ፡
አንድ ሕዝብና አካባቢ መሆናቸውን የሚያሳየው፤ የሕዝቡን መደበላለቅና መዋለድ ትልቁ ማስረጃ
ያሳየሁት በቂ ሆኖ፤ አስተዳደራዊ ቁርኝቱም ቢሆን በፈረቃ አንድ ጌዜ የትግራይ ገዢዎች ከመረብ ምላሽ ሰሜንና ደቡብ ያለው ግዛት
ሲገዙ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሃማሴኑ ተወላጅ አምደሃይማኖት መቀመጫቸው ዓድዋ አድርገው ይገዙ እንደነበር ይታወቃል። <<
የትግራይ ትግርኛ ተነጋሪ ገዢዎች ከመረብ ምላሽ ትግርኛ ተናጋሪ ገዢዎች በብዙ መልኩ ተሰሚነት ስለነበራቸው፤ከመረብ ምላሽ ሰሜን
ያሉት ትግርኛ ተናጋሪዎች ከመረብ ደቡብ የሚገኙ የትግራይ ገዢዎችን እንደታላላቅ ወንድሞቻቸው ስለሚያዩዋቸው “ጥቃት”
ሲደርስባቸው እንዲያግዣቸው ይጠይቋቸው ነበር።>> መድሃኔ ታደሰ (ዘኒ ከማሁ)። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ሁለቱም በመረብ
ወንዝ የተጋረዱ ትግርኛ ተናጋሪዎችም ሆኑ ሌሎች ነገዶች ምንም ልዩነት እንደሌላቸው ነው። አፋር፤ ኩናማ፤ ትግርኛ፤ አገው፤ ሳሆ፤
እስልምና፤ ክርስትያን በሁለቱም ወገኖች ያሉት አንድ እንጂ የተለዩ አይደሉም።በሁለቱም ወገኖች የሚደመጡ የቃላት አወጣጥ
አደማመጥ ዘይቤ ለልዩነት መነሻ አድርገው የሚወስዱ ወገኖች ካሉ እውቀት ያተራቸው ወገኖች ብቻ ናቸው። እነዚህ ጥቃቅን ድምጾች
ለልዩነት የሚፈይዱት ፋይዳ አልነበርም፤ የለምም፤ አይኖርምም። ከመረብ ምላሽ ሰሜንም ሆኑ ደቡብ ያሉት የትግርኛ እና ሌሎች
ነገዶች የሚደመጡት የቃላትም ሆነ የድምጽ አወጣጥ ካውራጃ አውራጃ የሚለያዩ መሆናቸውንም ልብ አላሉትም። ይህ በሌሎችም የሚታይ
ሃቅ ነው።
ቬሮኒካ መላኩ <<ብዙ ትግራዮችም ኤርትራዊ የመሆን ፍላጎት አላቸው።>> ስለምትለው ቅዠት ማስረጃ የላትም። ይህ ቅዠት ኤርትራኖች እራሳቸው የፈጠሩት
ከጣሊያን የተማሩት ከንቱ ራንስ የማሳበጥ ዕብደት እንጂ መሠረትም
መረጃም የለውም።
ቬሮኒካ አሁንም <<የባድመ ጦርነት ከመነሳቱ በፊት ብዙዎቹ ትግራዮች ራሳቸውን ኤርትራዊ እያሉ ይጠሩ ነበር።>> ብላለች ይህም ከላይ እንዳሰመርኩበት መሰረተ ቢስ የኤርትራኖቹ ቅዠት ካልሆነ ምንም መረጃ የለም። ኤርትራኖቹ እንደ ትግሬው እና
መላው ኢትዮጵያ 85% በግብርና ድህነት የሚኖር ገበሬ ነው። ስለሆነም በምን ስለተሻሉ ነው ትግሬዎች ኤርትራኖች ሊሆኑ ፍላጎት
የሚያድርባቸው? ይህ ቅዠት ኤርትራዊው ዮሴፍ ገብረህይወት እንዳለው “አስማሪኖቹ” 85% የሆነውን ከኢትዮጵያ ገበሬዎች እኩል
የሚኖሮው አርሶ አደር እና ዘላን ሕዝብ ጣሊያኖች በገነቡዋት በኮምቢሽታቶ ጎዳና የሚኩራሩ “የአስማሪኖ” ልጆች “ኤርትራን ሕዝብ” ባህልና
አኗኗረት አያውቁትም።” ሲልኤርትራዊው ዮሴፍ ገብረህይወት ያረጋገጠልን
ቬሮኒካ የሰማች አትመስልም።
በመቀጠልም ቬሮኒካ መላኩ እንዲህ ትላለች፦
<<ከባድመ ጦርነት በሁዋላ እነዚህ ትግራዮች ከፍተኛ የሆነ የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል። >> ስላለችው አውነታው የተቃራኒ ነው።
ትግሬዎች ከጥንት ጀምረው ሃይለኛ ተዋጊዎች መሆናቸውን የሚጠራጠር ሰው ካለ ታሪክን
አላነበበም ወይንም ሆን ብሎ በግል ጥላቸው ተነሳስቶ የሻዕቢያን ፈለግ የተከተለ ብቻ ነው። የትግራይ ታጋዮች የፖለቲካ
መስመራቸውን ወደ ጎን ትተን፤ በተዋጊነት ብርታታቸው፤በርሃብ እና ውሃ ጥም ቻይነት ብርታታቸው እንደ ተንታኞች ለመነጋገር ከሆነ
ሃቁ ኤርትራኖች ያለ ሃይለኛዎቹ የትግራይ ተዋጊ ሠራዊቶች (ወታደራዊም ፤ፖለቲካም) ድጋፍ “በምንም መልኩ” የኤርትራ ነፃነት
ቅዠት ሆኖ ይቀር እንደነበር በእርግጠኛነት መናገር እችላለሁ (በዚህ የማይስማማ ተንታኝ ካለ በፈለገው መድርክ ክርክር ሊገጥመኝ
እጋብዘዋለሁ)። ትግሬዎች በኤርትራኖች ላይ የበላይነት ያሳዩበት መድረክ የጀመረው ጀብሃ በተባለው ኤርትራ ተዋጊ
ቡድን ላይ ነው። ይህ ቡድን ትግሬዎችን ብቻ ሳይሆን ሻዕቢያንም ጭምር ያስቸገረ የኤርትራን ትግል ጀማሪ የነበረው አንጋፋውና
ሃይለኛው የጀብሃን ተዋጊ ሠራዊት ‘ኤርትራ ድረስ’ በመዝለቅ ‘እንክትክቱን’ አውጥቶ እስከወዲያኛው ድረስ ድምጥማጡ እንደማይሰማ
አድርጎ ለበርካታ አመታት መሽጎበት ከነበረው ከኤርትራ መሬት ያስወጡት የትግራይ ተዋጊ ሠራዊቶች (ወያኔዎች) ናቸው።በዚህ የጀመረው
የትግሬዎቹ ታጋዮች ቆፍጣና ተዋጊነትና የበላይነት ስሜት በኤርትራኖች መንፈስ ላይ የንቀትና የልዕልና ስሜት ያልጠበቁት ድንገተኛ
ጫና በማሳረፍ ቀደም ብሎ በሻዕቢያም ሆነ በበርካታ ኤርትራኖች
በትግራይ ሕዝብም ሆነ በትግራይ ተዋጊ ሃይሎች ላይ የነበራቸው የተሳሳተ የንቀት ግምታቸው ባልጠበቁት ሁኔታ ስለተኮላሸባቸው ቆም
ብለው እንዲአስቡ አድርጎአቸዋል።
በዚህም ምክንያት፤ ሳሕል ተራራ ላይ እንደ አይዮች እራሳቸውን ሸሽገው ለበርካታ አመታት
ታራራ ላይ ተጣብቀው በጋለው የሳሕል ሓሩር እየተቃጠሉ ሲኖር የነበሩት ሻዕቢያዎች፤ “የወያኔ ትግሬ ተዋጊ ሃይሎች” ነፃ
ባወጡላቸው የጀብሃ ሰፊ የኤርትራ መሬቶችን እንዲይዙ እና ከሳሕል ወጥተው ወደ ደጋማው ኤርትራ እንዲወርዱ ረዳቸው። ይህ ብርታት
በጀብሃ ብቻ ሳየወሰን በተራ ሽፍቶችና ልምድ በነበራቸው ተዋጊ ሃይሎች በሱዳን እና በአሜሪካኖች ሲደገፍ በነበረው በኢድዩና
በኢሕአፓ ላይ ሃያል ተዋጊነቱን አስመስክሮ ሁሉንም ከጥቅም ውጭ አድርጎአቸዋል። የዚህ ሽንፈት ቀማሾች ራስን ለመሸንገል ካልሆነ
የሚክዱት አይሆንም። ታሪካዊ ትንተና ስለሆነ ከራስ ጋር ሲጋጭ ቢኮመጥጥም ‘ሃቁን’ መቀበል የግድ ይላል።
ጦርነቱ እየገፋ በሄደ መጠን የሻዕቢያ ተዋጊ ሃይሎች በኢትዮጵያ ተዋጊ ሠራዊቶች እየተነተረ፤
አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ የኢትዮጵያን ተዋጊ ሃይሎች ብርቱ ክንድ መቋቋም ስላቃተው እንደገና ወደ መሸሺያው የሳሕል ታራራዎች ሸሽቶ
ለሁተኛ ጊዜ ወገቡን አጎንብሶ “በሳሕል” ተራሮች ላይ እንዲወሰን ሆነ። አሁንም በከንቱ ጉራ ሲወጣጠር የነበረው ሻዕቢያ
ለሁለተኛ ጊዜ በትግሬዎቹ ተዋጊ ሃይሎች የመዋጋት ብቃት የመዳኑን ውሳኔ ዕጣ ፍንታው በትግሬዎች እጅ ወደቀ። በዚህም የተነሳ
የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር የተላከው ኢትዮጵያዊው ሠራዊት ሃያል ክንዱን በሻዕቢያ አከርካሪ ወገብ ላይ እያሳረፈ የሳሕልን ተራራ ወገብ መክበብ ሲጀምር ፤ “ሻዕቢያ” ኤርትራ ውስጥ በሚኖሩ
ኢትዮጵያውያን ዜጎች በተለይም ትግሬዎችን ከደርግ ጋር አብረዋል እያለ “በሰላይነት” እየከሰሰ ኤርትራኖች በመቀስቀስ ጥላቻ
እንዲያድርባቸው ለሽንፈቱ መሸፈኛ
የሚያገለግለው አዲስ ሴራ ጎነጎነ።
ሻዕቢያ ለሽንፈቱ መሸፈኛ እንዲረዳውም በኪነት (ድራማ/ቲያትር) መልክ አዘጋጅቶ እንደ አይጥ
በየመንደሩ ሾልኮ በመግባት ሕዝብ በመሰብሰብ ‘ኤርትራኖች’ በትግሬዎች ላይ ጥላቻ እንዲቋጥሩ ቀሰቀሰ። የድራማው ቅንብርም
እውነት ለማስመሰል ከፌደሬሽኑ ጀምሮ እንደጀመረ ያላሰለሰ ጥርት በማድረግ ኤርትራዉያን የሆኑት የሐገር ፍቅር አባሎችም ሳይቀሩ
በትግሬነትና በሰላይነት ኤርትራኖችም ጭምር በአባሪነት መክሰስ ጀመረ። በድራማው ውስጥም ትግሬዎች ሕዝብ በሚጠቀምባቸው ወንዞችና
የጉድጓድ ውሃዎች ላይ “መርዝ እየጨመሩ ነው” በማለት በመዋሸት ሲያስፈልግም ውንጀላው አውነታ እንዲኖሮው እራሱ በኩሬዎች ላይ መርዝ
እየጨመረ ሕዝብን ለማሳመን ሲል ያደረገውን ድራማ ወደ እውነታ እንደቀየረው ጦርነቱ ካበቃ በሗላ አንዳንድ ኤርትራኖች የተደበቀው
የሻዕቢያ ወንጀል ሲዘረዝሩ ባደረጉት የፓልቶክ ቃለ መጥይቅና ውይየት በጆሮየ አድምጫለሁ። በዚህም ኤርትራ ውስጥ ለዘመናት የኖሩ
ምስኪን የትግራይ ተወላጅ እረኞችማ ገበሬዎች እንዲሁም በንግድም ሆነ በሌላ ጉዳይ በየገጠሩ ሲዞሩ የተገኙትን ሁሉ እየለቀመ ሲሰልሉ
ወይንም መርዝ በሚጠጣ የውሃ ምንጭ ላይ ሲጨምሩ የተያዙ “አጋሜዎች” እያለ ሕዝብ ፊት እያዞረ ከፍተኛ የጥላቻና የመለያየት ሴራ
በመስራት ለሽንፈቱ መሸፈኛ ዘዴ እንዲሆነው ማጠንጠን ጀመረ።
ሕዝብን መዝለፍ ነውር ባልሆነባቸው በነዚህ የጫካ ትውልዶች ልሳን በድራማው ውስጥ የተካተቱ
የጥላቻና የንቀት መቀስቀሻዎች “አጋሜ” የሚል ጣሊያኖች ያስተማርዋቸው የትግራይ አውራጃ አንዱ ክፍል በሆነው ጥንታዊው
የአጋሜ አውራጃ ስም በማንኳሰስ መልክ መጥራት ነበር። ለዚህም ነው ምስኪንዋ “ቬሮኒካ መላኩ” << ብሄረ ትግርኛዎች ስለ ትግራዮች ያላቸው ስሜት ምን እንደሆነ ሲጠየቁ ትግራዮች ወይም አጋሜዎች እያሉ ይጠሩዋቸዋል። (Hassan Adem, M.T., Tekle B, 2010)
>> ስትል እንደ ማስረጃ
ታሳየናለች። በግልባጩ ትግሬዎች (ኢትዮጵያውያኖች) ኤርትራኖችን ምን ብለው እንደሚዘልፏቸው ቬሮኒካ ላንባቢዎቿ ልትነግር
አልፈለገችም። አስቀድሜ እንደገለጽኩት በመሰዳደብ ምንም የምታስረዳው ነገር ስለሌለ ይህንን እንለፈውና እንቀጥል።
ከላይ እንደጠቀስኩት አጉል ጉራ ምክንያት አከርካሪው ላይ እስኪጎብጥ የተቀጠቀጠው ሻዕቢያ፤ ጦርነቱ
እየገፋ በሄደ መጠን የሻዕቢያ ተዋጊ ሃይሎች በኢትዮጵያ ተዋጊ ሠራዊቶች እየተነተረ፤ አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ እንደገና ወደ
ለመደበት የመሸሺያው የሳሕል ታራራው ሸሽቶ ለሁተኛ ጊዜ “በሳሕል” ተራሮች እንደ አይጥ ሲወሸቅ፤ ሻዕቢያ ከደርግ ጋር ተደጋጋሚ
ሚስጥራዊ ስምምነት በማድረግ “የዓሰብ ወደብን” ለኢትዮጵያ ለማስረከብ ምጽዋን ለኤርትራ ሰጥቶ በፌደሬሽን እንዲተሳሰሩ ጦርነቱ
እንዲቆም መለመኑን እና መንግሥቱም እምቢ ብሎ ጦርነቱን እንደቀጠለ ይታወቃል። ሆኖም የትግሬ ተዋጊዎች ድረድሩ እንዲደናቀፍ
ስለፈለጉ፤ የሻዕቢያ ዋነኛ ወታደራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቅላይ እዝ (ቤዝ) የሆነውን የደቡብ ሳሕልን ክንፍ ከኢትዮጵያ ተዋጊ
ሠራዊቶች ጥቃት ለመከላከል ተወዳዳሪ በሌለው ጽናት ተዋግቶ ሻዕቢያን ከመጨረሻ ግብአተ መሬቱ ጎትቶ አዳነው። ሻዕቢያ ማመን
ቀርቶ መጠነኛ ምስጋና እንኳ ሊለግስ አልፈቀደም (መድሃኔ - ዘኒ ከማሁ)። ለሐፍረቱ መሸፈኛ ሲል ሊገልጸው ባይፈልግም
በገለልተኛ ታዛቢዎች ሊካድ ከቶ አይቻልም።
መድሃኔ ታደሰ እንዲህ ይላል፡ “በ974 ዓ.ም በቀይ ኮከብ ዘመቻ የተከፈተው በማክሸፍ ረገድ
ህወሓት ወሳኝ ሚና መጫወቱን የሚያሳይ ፊልም ሆን ብለው እንዳጠፉት ይነገራል። እንዴት “ሃየለኞቹ”
<<ኤርትራዉያን>> ትግራይ ሊያድናቸው ይቀበሉ?>> ካለ በኋላ <<ይኼውም የህወሓት ድጋፍ አንድ ቁም ነገር ያስታውሰናል።ይኼውም የጥንቶቹ
ትግሬዎች ለመረብ ምላሽ ትግርኛ ተናጋሪ ወገኖቻቸው ያደርጉት የነበረው ድጋፍ መደገሙን ነው።>> መድሃኔ ታደሰ (ዘኒ
ከማሁ)።
ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል የሆነው የትግሬ ሕዝብ መሬት በመድፈሩ የተነፈሰው ይህ
የነ ቬሮኒካ መላኩ <<የኤርትራኖች የበላይነት ስሜት>> እንቆቅልሽ ለሦስተኛ ጊዜ እራሱ ሻዕቢያ በተነኮሰው
ጦርነት በትግሬዎችና በኢትዮጵያውያን የተባባረ ክንድ ቁስሉን ላሰ። ለዚህም “ድፊትድ ኤርትራ/Defeated Eritrea” በሚል “ቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ” የተባለው ዓለም አቀፍ የእንግሊዞች የቢቢሲው የዜና አውታር ይህንን ማቅረቡ ይታወሳል።
ባድሜም እስካሁን ድረስ መንጠቅ አልቻለም። ለመንጠቅ ቢሞክር ያችን መራረ ብትር ጀርባው ላይ እንደምታርፍ ስለሚያውቅ ከጭኸትና
አማልዱኝ በቀር በጉልበት ሊወስዳት አይቻለውም (አሁን ጦርነት ቢነሳም ሻዕቢያ ባድሜን መንጠየቅ እንደማይችል በእርግጠኛነት
ስናገር በድፍረት ነው። ብዙ ተንታኞች በዚህ ከኔ ሊለዩ ይችላሉ። ካለው ሁኔታ፤ ሃቁ ግን ምንም ቢሆን ኢትዮጵያውያን በኢሳያስ
ላይ ያላቸው ቂም ስላልበረደ ወያኔ ጥሪ ቢያደርግ የሚዋጋለት እንደማያጣ እሙን ነው፡ ከሚል ብቻ ሳይሆን፤ የኤርትራ ወጣቶች
ባይል የተያዙ ስለሆኑ የመዋጋት አቅማቸውና ፍላጎታቸው የሟሸሸ ስለሆነ በጥቂት ሰአታት ውግያ እጃቸውን ይሰጣሉ። ሞላ አስገዶምን
ያህል ተራ የሽምቅ ተዋጊ ቡድን ኤርትራን ድምበር ጥሶ ተዋግቶ ማለፍ ያቸለው የሚነግረን ነገር በወታደራዊ ዓይን እናንተው
እንደትገምቱት እተወዋለሁ። ለዚህ ነው ኢሳያስ የባድመን ነገር በይደር ለማስቀመጥ እየመረጠ ያለው። የበሬው ቆለጥ ሲወዛወዝ
ይወድቅልኝ ይሆን በሚል የቀበሮ ምኞት! ቢወድቅም ባይወድቅም ቢሞቱ ትግሬዎች ባድሜን ለሻዕቢያ አሳልፈው አይሰጡም። ለዚህ
ነው፤በወያኔ ውስጥ የተሰገሰጉ “ለኤርትራ የሚያዳሉ ወያኔዎችም” መለስ ከሞተ በኋላ “ድፍረታቸውን” ውጠው ዝም እንዲሉ የተገደዱት)። ምክንያቱም ወያኔዎች ባድመን ለኤርትራኖች በተግባር አሳልፈው
ከሰጡ በትግራይ ሕዝብ የቁጣ ማዕበል
የወያኔ መሪዎች ህልውና በማግስቱ
እንደሚያከትም ያውቃሉ
(Defeated Eritrea Licks Its Wounds–BBC Focus
On Africa -Ethiopian Semay 2000)
የኤርትራኖቹ የማንነት ቀውስ ዓለም ሙሉ ቢመጣ እናሸንፈዋለን ከሚለው ጀምሮ ማንነታቸውንም
ጭምር ለአረቡ እና ለእስላም አገሮች ሸጠዋል። ቬሮኒካ ያላነበበቺው ማስረጃ ሊሆን ስለሚችል፤ ኣእምሮዋ ቢከፍትላት ይህ የሻዕቢያ
ጋዜጣ እንዲህ ያለውን ልጥቀስ።
<ኤርትራ የዓረቡና
የእስላሙ ዓለምም እምብርት ናት>> (ሓዳስ ኤርትራ፤- 1988 ታሕሳስ 18)
የራስ ፍለጋ ቀውሱ በዛው ብቻ አልተቋጨም።የራስ ማንነት አግዝፎ በመሳልም ዓንደብርሃን (ዶ/ር) የተባለ የድሮ ኢሳያስ አገልጋይ የነበረ ዛሬ
በተቃዋሚነት ወዲያ ወዲህ የሚል ይህ ግለሰብም እንዲህ በሚል የግዝፍነት ቅዠት ሲቃዥ እንመለክት። እንዲህ ይላል፦
<< የኤርትራ ፖሊሲ ከኤርትራ ድምበሮች ዘልቆ ወደ ኢትዮጵያ ድምበሮች ይመለከታል።
ከኤርትራና ከኢትዮጵያ ድምበሮች ዘልቆም ወደ አፍሪቃ ቀንደም፤ ከአፍሪቃ ቀንድም ባሻገር አሁጉሪቱና ዓለማችንን ባጠቃላይ
ይቃኛል።>> ሲል እራስን አግዝፎ በማሳየት ያስሰማው ትዕቢት ዛሬ ሕዝቦችዋ ነብር እንዳየች ፍየል ድምበሮችን እየጣሱ
ከኤርትራ በመሸሽ የሲኦል ምድር ብለው አውግዘዋታል። እንዲህ ያለ ራስን ያለማወቅ ቁማር ገብተው የዓለም መሰቅያ
ሆነዋል።
ኢትዮጵያን ቀርቶ ዓለምን እናሸንፋለን ሲሉ በአጉል ጉራ ሲበጠረቁ የነበሩት
ኤርትራኖች “ቁስላቸውን ወደ መላስ ገብተው፤ ድሮ ጀምሮ የተካኑበትን ወደ ጥቁር ገበያ ገብተው ከሩስያ እስከ ኮንጎ ድረስ
በተዘረጋ የመሳርያና የሉል/አልማዝ/ ሕገወጥ ግብይት በመሰማራት አውሮጳ ፤ዓረብ አገር እና አሜሪካ ድረስ አባሎቹን
በማሰማራት በሕገ ወጥ ግብየት መሰማሩ አልፎ ሕገ ወጥ በሆነው የሰዎች ሽግግር ገበያ በመሰማራት የሚላስ የሚቀመስ የሌለው
ኤርትራን ሕዝብ በሚያሰቅቅ ስቃይ ውስጥ ከተቱት (ውጭ ጋር ልጆቻቸው ባይኖሩዋቸውና ገንዘብ ባይላክላቸው ሕዝቡ ባሰቃቂ ርሃብ
ያልቅ ነበር)።
ቬሮኒካ መላኩ እንደምትቃዠው ሳይሆን ‘ትግሬዎች’ ከጦርነቱ በፊትም ሆነ በኋላ ትግሬዎች ኤርትራኖች የመሆን ፍላጎት ጭራሽ አድሮባቸውም አያወቅም፤ድሮም ዛሬም። አብሮነት
አድሮባቸው ከሆነም አንድኖታቸውን ለማሳየት የሄዱበት ብቻ ነው። ለዚህም በትግሬዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ለኤርትራኖች ምዝበራ
ያጋለጥዋት መሆናቸው እራሳቸው የትግሬዎቹ መሪዎች ለሁለት አንዲሰነጠቁ ከሆነው ምክንያት አንደኛው እና ቀንደኛው ምክንያት ይህ
ነበር። ሆኖም የኤርትራ ማንነት መስራቾች የሆኑት ሻዕቢያ መሪዎችና ተከታዮቻቸው የማይታመኑ ስለሆኑ፤ የመክዳት ባሕሪን
እንደ አደገኛ አመል ስለተጠናወታቸው የፖለቲካ ዕውር ካልሆነ በቀር “ሻዕቢያን” አምኖ የሚራመድ ቡድን ካለ “ራሱን
ችግር” ውስጥ ለመክተት ፈቃደኛ የሆነ ጅል ብቻ ነው።
ካስፈለገም በክፍል 3 እስክመለሰበት ድረስ “በመድሃኔ ታደሰ” ትንተና በዚህ ላጠቃልል።
< አንዳንድ ኤርትራውያን ምሁራንን ጨምሮ ስልጣኔን እንዴት እንደሚተረጉሙት ማየት ብቻ
ይበቃል። ለነዚህ ክፍሎች የስልጣኔ ትርጉም ጣሊያኖች የተውትን ፊያት መኪና ከማሽከርከርና በጣሊያኖች ቪላ ከመኖር አያልፍም።
“ከሌሎቹ የተሻለ ስልጡን ነን” የሚለው አባባል አልፋና ኦሜጋው
የጣሊያንን አገዛዝ ከማድነቅ አይዘልም። አፍሪካውያንና መላው የዓለም
ሕዝብ የሚኮንነውን በባርነት የመገዛት ተግባር ኤርትራውያን ታዋቂ ሰዎች እርካታን ያገኙበታል። በእርግጥም በርካታ
ኤርትራውያን የአውሮፓ አገዛዝ ለሦስተኛው ዓለም ተስማሚ ነው ብለው በማስተዋወቅ ረገድ ዝነኞች ሁነዋል።
የዛሬይቱም ኤርትራ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለቅኝ አገዛዝ ትልቅ ፍቅርን ሲያሳዩ ማየት
ግራ የሚያጋባ ሁኗል። በአጠቃላይ ለመናገር ካስፈለገ የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ አወዳሽ የሆኑት የኤርትራ ምሁራን ስለዛሬይቱ ኤርትራ
ተጨባጭ ሁኔታ ከማውራት ይልቅ ስለቅኝ አገዛዝ ዘመን መጥቀሱ ይቀናቸዋል። ግራ የሚያጋባ ማሕበራዊ ስነልቦና ነው? ገጽ 55
(ዝኒ ከማሁ)
ለዚህ ነው ብዙ ታዛቢዎች ኤርትራውያን ጣሊያኖች ይፈፅሙባቸው የነበረውን የጥላቻና የትምክሕት
ድርጊት እንደማካካሻነት በትግሬዎች (ኢትዮጵያውያን) ላይ
አማራውን ‘አድጊ’ ትግሬውን ‘አጋሜ’ እያሉ ያንጸባርቁታል
የሚሉት። “መድሀኔ ታደሰ” ለዚህ ማጠቃለያየ እንዲህ ሲል በጥሩ ደምድሞታል << ተገዢዎች የገዢዎችን የኩራትና የጥላቻ ስሜት ተቀፅላ ናቸው፡ ብለው ብዙ ተንታኞች
ያምናሉ>>።
አመሰግናለሁ ጌታቸው ረዳ
No comments:
Post a Comment