To see the page/font with a wider range, please press the key Ctrl and + sign. To view the page/font with a narrow range, please press the key CTRL and _ sign
የሚታየው የወያኔ ገበና ማህደር አዲሱ መጽሐፍ ለመግዛት $30.00 ዶላር ሲሆን ይድረስ ለጎጠኛው መምህር መጽሐፍ ደግሞ $25.00 ወይንም ሓይካማ የሚለው የትግርኛ መጽሐፌ ደግሞ $15.00 ዶላር ብትልኩ መጽሐፎቹን ማግኘት ትችላላችሁ።Getachew Reda P. O.Box 2219 San Jose, CA 95109 getachre@aol.com Phone (408) 561 4836
እኛና ንጉሥ የሌላቸው አንበጦች
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ ዘጋጅ) www.ethiopiansemay.blogspot.com
የሚመለከተው ግጥም የተገጠመው ከዳዊት ግርማ አዲስ አበባ በሐመር መጽሔት ላይ ታትሞ ነበር። ርዕሱ ጥቃቅን ፍጡሮች የሚል ነው።
ጥቃቅን ፍጡሮች
አንበጦች ንጉሥ የሌላቸው
በመልካም ሥርዐት ሲሔዱ አየናቸው
ጠቢቡ በመጣፍ አደናነቃቸው
የነገሥታት ንጉሥ
ሳለ ንጉሣችን ሕግና ሥርዐት ሰጥቶ አወጥቶልን
ካንበጦቹ መንጋ እንዲህ ያሳነሰን
መራመድ በስርዐት እንዴት አልሆንልን አለን?
አዎን ይህ ግጥም ለፖለቲከኞችም ሆነ ሃይማኖትን እናከብራለን ብለው በየቤተጸሎቱ (መስጊድ፤ቤተክርስትያን) እሁድ እሁድ በየሳምንቱም ሆነ በየቀኑ ጸሎታቸውን ለፈጣሪያቸው የሚያደርሱትን ሰዎች/ማሕበረሰቦችን ሁሉ ይመለከታል።
ወላጆቻችን ኢትዮጵያ የምትባል አገር መሥርተው አብሮነትን በማስተማር ሲያቆዩልን፤ ይህ ትውልድ ከገጠመው ፈተና በላይ ገጥሟቸዋል። አሁን የምናያቸው የርስ በርስ መጠላለፍ፤ጥላቻ፤ትምክሕት፤አዋቂ ነኝ ባይነት፤ምቀኝነት፤ጦርነት፤መካሰስ፤መወቃቀስ፤የነገድ ጥላቻ፤ሀሰት፤መረን ያለፈ ቁጣ፤መገዳደል፤በውሸት ራስን መካብ ክሕደት ወዘተ…የመሳሰሉ የማሕበረሰባዊ ጠንቆች አሁን የተከሰቱ ሳይሆኑ የሰው ልጅ ሲፈጠር ጀምሮ የተከሰቱ የሕሊና በሽታዎች ናቸው።
እነኚህ የሕሊና በሽታዎች እኛን እንደጠመዱን ሁሉ ፤ወላጆቻችን እና ቅድመ ወላጆቻችን የነበሩ ወላጆቻቸውም ጭምር የገጠሟቸው ማሕበራዊ ጠንቆች ናቸው። ነገር ግን በእንኚህ ጠንቆች ሲጠለፉ በፈሪሃ እግዚአብሐር/አላህ ነገሮችን በውይይት እና በትዕግሥት ሲፈቷቸው ብዙ ጊዜ ታሪክ አንብበናል። ነገሥታቱም፤ነገዶችም የተከተሉት የመፍቻ ዘዴ ሽማግሌዎች እና ወጣቶች በዕርቅ ሂደት እና በጋብቻ ነበር። ለዚህ መሳርያ የሆነው “ትዕግስት” የተባለ አቅል የሚፈትን ፈተና በመሸከም እና በመቻል ነው።
ትዕግስት የመረጡበት የመፍቻው ዘዴአቸው ተጠቅመው ለማምጣት የፈለጉት ግብ “የአብሮነትን መኖር” ለማጎልበት እና ለማቆየት የዛው ዘመን ሰዎች መለኪያቸው “ፈሪሃ እግዚአብሔር እና ወዳጆቻቸዉን ላለማስቀየም” በጣም የሚጠነቀቁ ሕብረተሰቦች ነበሩ።
የጥንት አይሁድ፤ክርስትና እና እስላም የመሰረተች አገር ኢትዮጵያ እና አሁን ያለው ትውልድ ስናወደድረው መስጊድ ወይንም ቤተክርስትያን እሁድ እሁድ/አርብ አርብ ስለሄደ ወይንም በየሬዲዮኑ እና በዘመኑ ኢንተርነት ፓል ቶክ ስለ ሃይማኖት ስለ ፖለቲካ ሰበካ ስለተወያዩ “እውነት የጨበጡ” እየመሰላቸው አብሮዋቸው በየመስጊዱ/ቤተክርስትያን ያልሄዱትን ወይንም የማይሳተፉትን ክፍሎች በየምክንያቱ ከነሱ ጋር ሳይስማሙ በቀሩ ቁጥር “ሃይማኖተ ቢሶች/ኤቲስት” “ሃጥአን” እያሉ ሲመጻደቁ ይደመጣሉ። ስለዚህም “ካለ እኔ በስተቀር አትፍረድ” ያለውን መመሪያ በመጣስ በሃሰት እና መጠን ባለፈ ትምክሕት ራሳቸውን “ክፍ፤ከፍ” በማድረግ “አንድን ነገር በራሳቸው ትርጉም እየተረጎሙ” ከፈጣሪያቸው ጋር ይጣላሉ።
ፖለቲካውና ሃይማኖቱ አሁን ባለው ሁኔታ እየደፈረሰ ያለበት ዋናው ምክንያት “ፈሪሃ እግዚአብሔር አለን” በሚሉ እና “ሃይመኖተ ቢሶች” በሚሏቸው የሃይማኖት አማንያን እና “አድሃሪ እና ተራማጅ” “ብሔረተኛ እና አገር ወዳድ” “ባንዳ እና አገር አስከባሪ” በሚባባሉት የፖለቲካ ተከታዮች እየታየ ያለው የደፈረሰው አየር ስንመለከት አብሮ ለመኖር የሚያስፈልገውን የመቀባበልን ሕግ ስላልተከተለ ነው።
ቡድንተኛነት፤ወገንተኛነት፤በጎሳ መሰባሰብ አልፍ ብሎም ሰዎች በጎሳቸው ወይንም በተወለዱበት አካባቢ በማያስፈልግ ጊዜ እና ቦታ ሰውየውን ለማስቀየም በመጥራት የሚፈልጉትን ትምክሕት ለመጫን በመሞከራቸው ነው። ብዙ ጊዜ ስለተናገርንበት መድገሙ ኣላስፈለገኝም።
ባለፉት ጽሑፎቼ እንደገለጽኩት “አገር ውስጥም ሆኑ ውጭ አገር ያሉት ተቃዋሚ ድርጅቶች እና ግለሰዎች የወያኔን ጎሰኛ እና ፀረ ኢትዮጵያ ስርዓት ለማስወገድ ከፈለጉ “በመልካም ስርዓት ተሰልፈው እንደሚጓዙ ንጉሥ እንደሌላቸው አንበጦቹ” ባንድነት እና በሥርዓት ካልተጓዙ አሁን ባለው የተዘበራረቀ፤ ጥላቻ፤ጎሰኛነት፤ውሸት፤ ትምክሕት እና ቡድንተኛነት የሚመራው ባሕሪ ከተከተለ ደግሜ ደጋግሜ እንደተናገርኩት “ወያኔን” በስሜት ካልሆነ በቀር በተግባር ወያኔን ማስወገድ አይቻልም።አራት ነጥብ።
ይህ ዕውነታ አልዋጥ ያላቸው ሰዎች እኔኑን በመሰላቸው መንገድ እየተረጐሙ ረዥሙን የጥላቻ፤የትምከሕት እና የድንቁርና እንዲሁም የጎሰኛነት ጅራፋቸው ሲያስጮሁብኝ አደምጣቸዋለሁ።
ትግሉ ከመቸውም በበለጠ “መሪ” ያጣበት ወቅት ሆኖ እያለ በስሜት እየተነዱ “ማለቂያ የሌለው “ጋዜጣዊ”መግለጫ እና አዳዲስ የመሪዎች ፊት እና ቃለ መሓላ ማሰማት” የወያኔን ብርክ እያንቀጠቀጠው እንደሆነ፤ እና ወያኔ “አንድ ዓርብ” እንደቀረው አስመስለው የሚደሰኩሩ በስሜት የተጠመዱ የትግል አቀበት እና የጠላት ጥንካሬ የማያውቁ፤ዓቀበቱ ፈታኝ ሲሆን ሸብረክ በሚሉ ሰዎች/ክፍሎች የሚነዛው ትግልን የሚያሳስት አጭበርባሪ ፕሮፓጋንዳ ማስተጋባቱ የትግሉ ፈታኝነት አቅሙ ምን ያህል እንደሆነ እንዳይታይ የሚያደርጉ የዜና አውታሮች እና ተቺ ጸሃፊዎች ከዚህ ስንፍና መራቅ አለባቸው።
ያለውን የተቃዋሚው ደካማ ጉልበት እና ቆራጥ መሪ ማጣት መጠቆም ያለበት ድክምት እንዳለፈው ሌላ አሳፋሪ ውጤት እንዳይከሰት ከመደገሙ በፊት በጊዜው ስንጠቁም የውሸት እና የስሜት ፕሮፓጋንዳ እና የፓል ቶክ ጎሰኞች ወሬ ሱስ የየዛቸው ዙረተኞች ተግሳፅ ስናዳምጥ ‘ተቃዋሚን መውቀስ’ ታቦትን እንደ መንካት አስመስለው የሚተረጉሙ ሰዎች አሉ። በአንጻሩ አንድ የተቃዋሚ መሪ ከአገር ውስጥ እንዳስተላለፉልኝ መልዕክት ግን “ያንተ ወቀሳ ለክፋት ሳይሆን ለኛ ብርታት ፍለጋ በመሆኑ በርታ፤እንፈልገዋለን እንጂ አንጠላውም” ሲሉኝ ከልብ አመሰገንኳቸው። ለዚህም አንዲት የበረሐ ወፍ የተናገረችው ተግሳፅ ምሳሌን ያስታውሰናል።
“አንድ ገበሬ የአንዲት ወፍ አንድ ዐይን በወንጭፍ ድንጋይ ያጠፋል። ወፊቱ ደሟን እያንጠፋጠፈች ስታለቅስ አንድ ሥራ ጠል ዘዋሪ ባሕታዊ አይቶ ርኅሩሕ በመመሰል “የዚችን ወፍ አንድ ዐይን እንዳጠፋህ የአንተ ሁለት ዐይኖች ድርግም ይበሉ፡ እስኪ ምን በድላህ ነው አንድ ዐይኗን ያጠፋህ?” እያለ ረገመው፡
የእግዚአብሐር መንፈስ ሰብአዊ አንደበትን የሰጣት ያች ወፍ ሰምታ “እረ የአንተ ዐይኖች ድርግም ይበሉ! ገበሬው ዐይኔን ቢያጠፋ እየመገበ ያድነኛል። እንዳንተ ካለው ሥራ ፈት ግን ምን ይገኛል? ስለዚህ በእኔ እና በገበሬው መካከል ምንም አያገባህም ዝም ብለህ ዙረትህን ቀጥል” አለችው ይባላል። (መጋቤ አእላፍ መክብብ አጥናፉ)።
የፖለቲካ መሪዎቹ ደካሞች እንኳ ቢሆኑም ትግሉ እና ትግሉን የሚመሩ መሪዎች እንዳይጠነክሩና ጠላትን በበቂ እንዳይመክቱ የሚያደርጉት “አትውቀሷቸው፤አትንኳቸው፤አታርሟቸው፤…” የሚሉን ደጋፊዎቻቸው እና የፓል ቶክ መሸተኞች እንጂ መሪዎቹ ለድክመታቸው ብዙም ተጠያቂዎች አይመስለኝም።
እንዲህ ከሆነ፤ እኛ በስርዐት ከሚሄዱ ንጉሥ ከሌላቸው አምበጦች እና ጥቃቅን ፍጡሮች የበለጠ ሕሊና ይዘን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ማቅናት ካልቻልን፤ዳዊት ግርማ ተዋናይ በሚለው ግጥሙ እንዳለው፤
“ሞትን ሰባት ሳይሆን ሺሕ ዓመት በቆምከው
ፊት ዘመን ያለፉ ደጋግ አባቶቼን አሁን እንዳያቸው” ያሰኛል።
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ ዘጋጅ) www.ethiopiansemay.blogspot.com
No comments:
Post a Comment