ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ ለፕሮፌሰር መስፍን መልስ የሰጠው ትችት አላረካኝም።
ጌታቸው ረዳ
ethiopiansemay.blogspot.com
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ለወያኔው ስብሐት ነጋ ባንድ ጉዳይ ላይ ተመርኩዘው ፍትሕ በተባለው ጋዜጣ ላይ “ንግግራችን ትርፋማ እንዲሆን ከአሉባልታ እንውጣ” በሚል ርዕስ -ነሐሴ 2003 ዓ. ም. በፍትሕ ጋዜጣ የሰጡትን መልስ ያሰፈሩትን ጽሑፍ መጀመሪያ እንመልከት።
“አቶ ስብሓት ነጋ ህወሓት የሚማር ድርጅት ነው ሲል ህወሓት እንኳን መማርና የተማረ ሰው አጠገቡ እንደማያስደርስ ሃያ ዓመታት ሙሉ ያወቅነውን ሊያስክደን ነው? መማር የሚለው በተላላኪና በዶላር የሚገኘውን ዲግሪ ይሆን? ስብሓት ነጋ እየደጋገመ ስለታሪክ ይናገራል፤ የዛሬ መቶ ዓመትና ሁለት መቶ ዓመት የሆነውን ከማውራት የዛሬውን ምስክርነት ማስተካከሉ አይበልጥም ወይ? የህሊና ፍርድም ለመስጠት ከደረቁ እውነት መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የአድዋን ጦርነት እናንሳ አፄ ምኒልክ ከደቡብ፣ ከምዕራብና ከምስራቅ ጦራቸውን ሰብስበው ለጦርነት ሲዘጋጁ ምን ያህል ጊዜ ፈጀባቸው? መንገዱ ምን ያህል ጊዜ ወሰደባቸው? የምኒልክ ጦር ከኢጣልያ ጦር ጋር ሲወዳደር ምን ያህል የሰለጠነ ነበር? የምኒልክ መሳሪያ ከኢጣልያ ጋር ሲወዳደር እንዴት ነበር? ስብሓት ሊመልሰው የሚገባ ሌላም በጣም በጣም ዋና ጥያቄ አለ፤
…አፄ ምኒልክ ጦራቸውን ሰብስበው በእግርና በበቅሎ ከደቡብ ተነስተው ትግራይ እስቲደርሱ ኤርትራና ትግራይ ምን አድርገው ጠበቁዋቸው? የኢጣልያ ጦር ትግራይን ሰንጥቆ አምባ አላጌ እስቲደርስ ማን ሊያቆመው ሞከረ? የኢጣሊያ ጦር መቀሌ ገብቶ ሲመሽግ ማን ተከላከለው? ስብሓት እስከዛሬ ሳይገለጥለት ቀርቶ ከሆነ የኢጣልያንን ጦር ከአምባ አላጌ ያስወጣው የምኒልክ ጦር ነው፡፡ ከመቀሌም ምሽግ ያስወጣው የጣይቱ ዘዴና የምኒልክ ጦር ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ተሸፋፍኖ የቆየውን እናፍረጥርጠው ከተባለ ለማን አሳፋሪ እንደሚሆን ግልጽ ነው።”(ፕሮፈፌሰር መስፍን ወ/ማርያም)
እንዲህ ሊሉ የተገደዱበት ምክንያት ያላባራው የወያኔዎች የውሸት ዝናብ ስለ ሰለቻቸው ይመስለኛል።እኔ እንደገባኝ ከሆነ ወያኔዎች ሸዋን ምኒሊክን አምሓራን በመውቀስ ለኤርትራ መገንጠል ተጠያቂ በማድረግ ዛሬም ሁሌም ስለሚከሱ ነው። ወያኔዎች እንደሚሉት ሳይሆን እውነታው ካሁን በፊት በመጽሐፍ መልክ ስለሄድኩበት አሁን አልመለሰውም።አሰዛኙ ሁኔታ ግን የትግራይ ይሁኑ የጎጃም የጅማ የከፋ የሃረር ኤሚሪቶች እና ንጉሶች የራሳቸውም የሌላው አካባቢም በድለውታል፤ አድነውታልም፤ተከላክለውለታልም ። ወያኔዎች የሚያኝኩት የታሪክ ማስቲካ ግን በመጥፎ
ጊዜን ለደረሰልን ንጕሥ እንደጠላት ማየቱ እና መዘባበቻ ማድረጉ ትልቁ በሽታቸው እንዴት ነውር እንደሆነ እና እንደሚያስጠላባቸው አላወቁትም። ሁሉም የየራሱ ጥፋት እየሸሸገ ወደ ሌላው ማትኰሩ በየትኛው ሐኪም መፈወስ እንደሚቻል ግራ የገባ ጉዳይ ነው።በወያኔ-ትግሬዎች “የተፈጸመው ያሁኑን ጥፋት ብናተኩር ይበልጥ አከራካሪ ነው።” ማለታቸው ፕሮፌሰር መስፍን የተሳሳቱት የት ላይ ነው?
ፕሮፌሰር መስፍን ጽሑፋቸው በመቀጠል
“ስለአድዋው ጦርነት ምስክርነት የሚሰጠን ገለልተኛ ታዛቢ እስክናገኝ ስለማይጨው ጦርነት የነበረ የዓይን ምስክር አንድ በቅርቡ ያነበብሁት መጽሐፍ ትዝ አለኝ፤ አንድ የቼኮዝላቫኪያ ጎበዝ የጻፈውን የሃበሻ ጀብዱ የሚል መጽሐፍ ተጫነ ጆብሬ መኮንን የተባለ ሰው የተረጎመውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሳትሞታል፤ አቶ ስብሓት ብቻ ሳይሆን ማንበብ የሚችል ሁሉ ሊያነብበው የሚገባ መጽሐፍ ነው፤ እኔ ፈረንጅ ስለኢትዮጵያ የፃፈውን ማንበብ ከተውሁ ብዙ ዓመታት ሆኖኛል፡፡ ይህንን ግን በአንድ ቀን ተኩል ጨረስሁት፤ የኢትዮጵያን ዘማቾች ከኋላ እያጠቁት ስለነበሩት ..የትግራይ ሽፍቶች.. ‘ማን ይናገር የነበረ’፤ ነውና እንዲህ ይላል፡-….የትግራይሽፍቶች) ለምን ወንድሞቻቸውን ይገድላሉ?… ከመሀል አገር ስድስትና ሰባት ወር ሙሉ ፍዳውን እያየ ሲጓዝ ከርሞ እዚህ የደረሰው ወንድማቸው፣ የነዚህን ምስኪኖች ህይወትና ንብረት ከጠላት ለመከላከል የገዛ ህይወቱን አልጋ ላይ ጥሎ፣ ቤት ንብረቱን በትኖ መከራውን ባየ ለምን ይገድሉታል? እነዚህ ሽፍቶች ወንድሙን የገደሉበት አብቹ የሚባል የአስራ ስድስት ዓመት የሰላሌ ዘማች በጣም ተናዶ የራሱን የግል ቡድን አቋቁሞ ያሳድዳቸው ነበር፡፡
ከዚያም በላይ እህል ውሃ ለዘማቹ እንዳይሸጡ ኢጣልያኖች በመከልከላቸው ዘማቾቹ ችግር ነበረባቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ ለመናገር አልፈልግም፤ ነገር ግን ይህንን እውነት ለመሸፈን በመሞከር የመሀል አገሩን ሰው መወንጀል ትክክል አይደለም፤ እውነት ተደብቆ አይቀርም፡፡
እንነጋገር ማለት አንድም ሆነ ሁለት የጋራ ችግር አለን ማለት ነው፡፡ እንነጋገር ማለት የጋረ አገር፣ የጋራ ወገን፣ የጋራ ሀብት፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ራዕይ አለን ብለን ማመን ነው፡፡ እንነጋገር ማለት እውነትን በማስረጃ አስደግፎ ነው፤ እንነጋገር ማለት እንግባባ ማለት ነው፤ እንግባባ ማለት ባንስማማም እንፋቀር፣ አንሸዋወድ፣ አናስሸብር ማለት አይደለም”። {ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም- ንግግራችን ትርፋማ እንዲሆን ከአሉባልታ እንውጣ - ነሐሴ 2003 ዓ. ም. ፍትሕ ጋዜጣ }
“የውጫሌን ውል ለምን አስፈለገ?” ብሎ የትግራይ ሪፑብሊክ አቀንቃኙ “ስብሓት ነጋ” ሲጠይቅ ፦
ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ ደግሞ እሱን ደግፎ
“አዎ ለምን አስፈለገ? ይህ እንቆቁልሽ እስካልተፈታ ድረስ በዚህ አገር ሰላምና መረጋጋት አይመጣም”
ብሎ በጣም በሚያሳፍር ካንድ ምሁር የማይጠበቅ ምላሽ ለፕሮፌሰር መስፍን ሲሰጥ ምን ይባላል? ምኒሊክ የተፈራረሙት የውጫሌው ውል ለጦሩነቱ መንስኤ ይሁን አይሁን “የሆኖ ሆኗል”።ያኔ የሆነው ሁኔታ በጊዜው በነበሩ የመሪዎቹ ችሎታ እና ወቅት፤ትምህርት፤ ቁሳቁስ እና ነባራዊ ሕሊና ፈትተውታል። እነ ፕሮፌሰር ገበሩ እና ስብሓት ነጋ “በዛሬው ዓይን ለዛው ጊዜ መፍትሄ ለማድረግ መሞከራቸው እና ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸው “እብደት ነው”።
ለዚህም ነው ፕሮፌሰር መስፍን፦
“ስብሓት ነጋ እየደጋገመ ስለታሪክ ይናገራል፤ የዛሬ መቶ ዓመትና ሁለት መቶ ዓመት የሆነውን ከማውራት የዛሬውን ምስክርነት ማስተካከሉ አይበልጥም ወይ? የህሊና ፍርድም ለመስጠት ከደረቁ እውነት መነሳት ያስፈልጋል፡፡” በማለት የበገኑት። እነ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ ግን ታሪክ አሳዳፊው የስብሃት ነጋን አጉል ኢትዮጵያዊ ተቆርቋሪነት ወይንም “ጸረ-ሸዋ ትግራዊ ብሄረተኛነት” ለመደገፍ ሲል የሚከተለውን አስገራሚ ውሸት ለፕሮፌሰር መስፍን መለስ ሰጥቷል፦
“አፄ ምኒልክ የእነዚያ 4ዐዐ የሚያህሉ ኤርትራውያን እጅና እግር አስቆርጠው የሕይወት ሽባዎች ያደረጉዋቸው፤ከኢትዮጵያ ታሪክም የማይፋቅ አሻራ ተውልን፤ ከታሪካችን ጋር ለመታረቅ፣ ከድላችን ትረካ ጋር ገመናችንም አብሮ መጠናት የለበትም ይላሉ።” ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ በዛው ጋዜጣ የሰጠው አስተያየት/ምላሽ።
ፕሮፌሰር ገበሩ የታሪክ ምሁር እንደሆነ እኔም ሁሉም ያወቀዋል። ገብሩ የላቀ የቀለም (አካዳሚሺያን)ነው። ይህ ታሪክ ጠፍቶት ሳይሆን ለሻዕቢያ (ኤርትራውያን) የነበረው ፍቅር አሁንም እንዳለ ለመግለጽ ካልሆነ በስተቀር እውነት ይህ ታሪክ ስላላወቀው አይደለም።ለባንዳዎቹ የመቆረጥ ምክንያት የወተወቱት ራስ መንገሻ ዮሃንስ እንደሆኑ እና በዚህም ምክንያት ኤርትራውያኖቹ ለራስ መንገሻ ዮሃንስ ምን ብለው እንደገጠሙላቸው ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ አያውቀውም ወይንም ሰምቶት አያውቅም የሚል እምነት የለኝም።
ባህ አይበልካ
ራዕሲ መንገሻ ወዲ ኹሪ
አያ ጥልያን ተኺሉለይ እግሪ”
ደስ አይበልህ ተቆጥተሃል/አዝነሃል እንዴ ራስ መን ገሻ?ሳለ ጣሊያን (አያዋ ጣሊያ) እግር ተክሎልኛል/ተክቶልኛል። (ሰው ሰራሽ እግር/አርቲፊሲያል እግር አምጥቶ በሁለት እግሬ እንድራመድ አደርጎኛል “እርር በል’ደስ አይበልህ ማለት ነው (በግረድፉ ስተረጉመው
እና የመሳሰሉ ብዙ ግጥሞች ለራስ የተገጠመላቸው መሆኑን ያውቀዋል።ካስፈለገም ሌላው ግጥም መጨመር ያስፈልጋል፤ለዛሬው ይህ በቂ ነው። ግልጽ ለማድረግ፦ የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ ስለ ለኤርትራውያኖቹ ማላዘን እና ጉዳዩ ወደ ምኒሊክ ጫንቃ ብቻ መወርወር አዲስ ነገር አይደለም። ለዚህ ማስረጃ ጥለቅ ትንተና ውስጥ መግባት አላስፈለገኝም።ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ለሻዕቢያ ድጋፍ ሌት ተቀን ይንቀሳቀስ እንደነበረ ሎስ አንጀለስ እያለ ብዙ ታዛቢዎች ይናገራሉ።ያ እንዳይበቃ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ ለሻዕቢያው መሪ እና ለወያነ ትግራይ መሪ ለኢሳያስ አፈወርቂ እና ለመለስ ዜናዊ ታላቅ አክብሮት እንዳለው የባድሜን ጦርነት አስመልክቶ ካፍቃሬው ወያኔ ከፕሮፌሰር ይስሐቅ ኤፍሬም ጋር ከአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ክፍል ውይይት ሲያደርጉ እንደገለጸ ይታወቃል። ፕሮፌሰሩ የታሪክ ምሁር እና ሊቅ ከሚባሉት ኢትዮጵያውያን አንዱ ሲሆን ለተጠቀሱት ሁለቱ አከብራቸዋለሁ ያላቸው በሰው ልጆች ህይወት ላይ ብዙ ወንጀል እና ግፍ የፈጸሙ ከተራ ሽፍቶች ተግባር የባሱ የሽምቅ ተዋጊ ፋሺስቶች አክብሮቱን ሲገልፅላቸው፤ በዶላር ያልተሸመተው የፕሮፌሰር ገብሩ ምሁራዊነት ስመዝነው ምን ዓይነት ሰብአዊ እና አገራዊ ወንጀሎች እንደፈጸሙ ማወቅ አቅቶት ከሆነ ዶክተርነታቸው በዶላር ከሸመቱት ዶክተሮች በምኑ ተሻለው? ወይስ ቀደም ብየ እንደገለጽኩት ለሻዕቢያ እና ለወያኔ ያለውን አክብሮትነት ሉጓሙ እየጐተተ ስላስቸገረው?
ይቀጥል እና ገብሩ ታረቀኝ እንዲህ ይላል።
“አንደኛ፣ አቶ ስብሐት ነጋ “የውጫሌ ስምምነት ለምን አስፈለገ;” ብሎ ሲጠይቅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አይመስለኝም፡፡ ሌሎችም ጠይቀውታል፡፡ እውነትም የውጫሌ ውል ለምን አስፈለገ? ለዓድዋው ጦርነት ዋናው መንስዔ ውሉ ያስከተለው ንትርክና ሙግት ነበርን? እነዚህና የመሳሰሉት ጉዳዮች በግልጽነት በጥልቀትና በሚዛናዊነት እስካልተፈተሹ ድረስ በዚች ሀገር ዕርቅና አስተማማኝ ሰላም ይገኛል ብለው ያምናሉ ?” ለፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም መልስ ገብሩ ታረቀኝ ፍትህ ጋዜጣ 8/26/11 (በጎርጎራውያን አቆጣጠር)
ፕሮፌሰር ግበሩ ታረቀኝ እውን “እነዚህና የመሳሰሉት ጉዳዮች በግልጽነት በጥልቀትና በሚዛናዊነት እስካልተፈተሹ ድረስ በዚች ሀገር ዕርቅና አስተማማኝ ሰላም ይገኛል ብለው ያምናሉ ?” ብሎ ፕሮፌሰር ገብሩ ለፕሮፌሰር መስፍን እና ለተቀረነው ሲጠይቅ “የውጫሌ ውል ለምን አስፈለገ?” የሚለው የስብሓት እና የገብሩ ታረቀኝ መጨነቅ መልስ ካላገኘ “ዕርቅና ሰላም” በኢትዮጵያ ምድር አይገኝም ሲል እውን ይሄ ነጥብ ነው ዋናው ኢትዮጵያ ሰላምና ዕርቅ ለመደፍረሱ ምክንያት የሆነው? በጣም አስገራሚ ትምህርት ነው! እነኚህ ምሁራን ምንድነው የቀመሱት?
ዶ/ር ገብሩ ታረቀኝ እንደ ወያኔዎቹ በዶላር የገዛው ዲግሪ አይደለም እሱ እንዳለው አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች ነው የተማረው። እኔ የሄ ጎበዝ ተማሪነቱን አሜሪካ አገር ከታደሰ ገ/እግዚአብሄር ጋር ሲሄድ ሁለታችንም ያንድ ከተማ ሰዎች ስለሆንን ትንሽ ወጣት ሆኜ እሱ በዕድሜ ትልቅ ስለነበር አሜሪካ ለትምህርት ሲመላለስ ኤለመንታሪ ት/ቤት ሆኜ በአድናቆት እንመለከተው እንደነበር ትዝ ይለኛል። ስለ ትምህርቱ ብቃት አያጠያይቅም። ግን በዚህ ትንተና ሲገባ “ብሐረተኛነት” ወይስ ጠባብነት ወይስ ታሪክን በቅጡ ባለመመለክት”? መልሱ ለወንድሜ ለፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ልተው።
ማይጨው ላይ ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት “የትገሬ ሽፍቶች” ወይንም ፕሮፌሰር ግብሩ ታረቀኝ እና ሌሎች ጸሃፊዎች እንዳሉት የራያና ዓዘቦ “ኦሮሞዎች” ለኢትዮጵያ አርበኞች ጉዳት አድርሰዋል። ከ10 ሺህ የትግራይ ተዋጊዎች በላይ አንዳንዱ ከዛ በታች ወይንም በላይ ይገምቱታል የንጉሡ አማች ሃይለስላሴ ጉግሳ ወራሪ ጣሊያን ጋር ሆነው ጉዳት አድርሰዋል። የህዝቡ ልቦና ገምሰውታል። ኦሮሞ ይሁኑ አገው ወይንም ኩናማ ሁሉም በትግራይ ክፍለ ሃገር የሚገኙ የተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪ ትግሬዎች ናቸው። ስለዚህ ለተደረገው ክህደት ወይንም ከጣሊያን ጋር ባደረጉት ሽርክና የታሪክ ወቀሳ ሲነሳ በትግሬነታቸው ነው የሚነሱት ማለት ነው። ስለዚህ ያ ታሪክ ለማን ልንጥለው ነው የውጫሌ ውል ምኒሊክ ለምን እንደፈረሙ ካልነገሩን “በዚህ አገር ዕርቅና አስተማማኝ ሰላም አይገኝም” ብሎ ገብሩ ታረቀኝ በተማረው አንደበቱ እንዲህ ዓይነት የወያኔዎች ማማሰያ ይዞ የወያኔ ወጥ እንዳያር ማማሰሉ ምን ይባላል?
አዎን ልክ ነው። በዚህ ሁናቴ የበኩሌን አነድ ነገር ልጥቀስ። በቅርቡ ታትሞ የሚወጣው አዲስ መ-ጽሐፌ ውስጥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ስለ ዓድዋው ጦርነት እና ምኒሊክ ዮሐንስ አንስተው የጠቀሱትን ልጥቀስ:-
“ጽሑፌን ከመደምደሜ በፊት የኤርትራና የትግራይ ጎሰኞች፥ "ኤርትራን ለኢጣሊያ የሰጡ አጼ ምኒልክ ናቸው" ስለሚሉት ሐሜት አንተ በማስረጃ ባስተባበልከው ላይ ጥቂት የድጋፍ አንቀጾች ልጨምር። ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለችው ታሪክ በመዘገባቸው አንድ፥ ሁለት፥ ሦስት ተብለው በሚቆጠሩ ታሪካዊ እርምጃዎች ነው። አጼ ምኒልክን የሚያስወቅሳቸው በየትኛው እርምጃ የተጫወቱት ሚና እንደሆነ ለኔ ግልጽ አይደለም። ሐሜቶቹን እጄ ያረፈባቸውን ያህል አንብቤያቸዋለሁ። ሁሉም ንጉሠ ነገሥቱ አድዋ ላይ የተቀዳጁት ድል ያጎናጸፋቸውን ዓለም አቀፍ ዝና ለመግፈፍ የተዘረጉ እጆች የጻፏቸው ናቸው።
ከመጨረሻው ልጀምርና፥ የመጨረሻው እርምጃ የተወሰደው አጼ ዮሐንስ መተማ የዘመቱ ጊዜ ነው፤ አንተም አንሥተኸዋል። አጼ ዮሐንስ መተማ የዘመቱት የጊዜውን ሁኔታ በደረሷቸው መረጃዎች አጥንተው አውጥተው አውርደው ለኢትዮጵያ ምን ማድረግ እንደሚሻል የመሰላቸውን ገምተው ነው። ከጎንደር አብያተ ክርስቲያን የመጣላቸውን የዋይታ ደብዳቤ እናስብ፤ የደርቡሾቹ መሪ "ስለምና እንታረቅ" ብሎ የጻፈላቸውን ደብዳቤ እናስታውስ። ከዚያ ቀጥለን አጼ ዮሐንስ ማን እንደነበሩና እነዚህ ደብዳቤዎች ሲደርሷቸው ምን እንደተሰማቸው እንመርምር። ንጉሡ ሃይማኖታዊነታቸው ከ"አጼ ዮሐንስ" ይልቅ "አቡነ ዮሐንስ" የሚያስብላቸው ነበር። ለግርማዊነታቸው የታየው እነዚህ (ጣሊያኖቹና የግብጽ እንግሊዞች) ክርስቲያኖች ናቸው፤ በክርስቲያኒቱ ኢትዮጵያ ላይ ጨክነው አይጨክኑም። እነዚያ (ደርቡሾቹ) ግን ክርስቲያኒቷን ኢትዮጵያ ሊያጠፉ ቊርጥ ሐሳብ ያላቸው፥ ብዙ አብያተ ክርስቲያን በማቃጠል ሐሳባቸውን በግብር ያሳዩ፥ እስላሞች ናቸው፤ "የግራኝ ርዝራዦች።" ግራኝ እንኳን ለአጼ ልብነ ድንግል የላከበት "ልጅህን ዳርልኝና እንታረቅ" ብሎ ነው እንጂ፥ ስለም አላለውም።
ከክርስቲያኖቹ ጋር የጀመሩትን ድርድር ሲመለሱ ከተመኙት ግብ ለማድረስና ያባቶቻቸውን ምድር ለማስመለስ የሰሜን ምሥራቁን ችግር በይደር አቆይተው መተማ ዘመቱ። እንዳሰቡት ሳይሆን ቀረ። ግርማዊነታቸውም ያባቶቻቸውም ምድር ሳይመለሱ ቀሩ። የኋላ ቀር አገሮች ጦርነት በአሸናፊነትና በተሸናፊነት የሚያልቀው እንደ ቸዝ ጨዋታ ንጉሡ ሲሞት መሆኑን ዘንግተው ራሳቸውን ለጥይት በማጋለጣችው ኢትዮጵያ ንጉሧን አጣች፤ ድልም አመለጣት። ያ ብቻ ሳይሆን በረሐ ውስጥ ሰፍሮ የነበረ የኢጣሊያ የጦር ሠራዊት ባዶ ቤት ስላገኘ ማንንም ሳይፈራ፥ ወደ ደጋው አገር ወጥቶ ራስ አሉላ ከተማ (አስመራ) ላይ ለመስፈር ሰላምና በቂ ጊዜ አገኘ። ይኸስ እንዲህ ሆነ፤ አጼ ምኒልክስ? የኢጣሊያንን ሠራዊት ከኤርትራ ማስወጣት ይችሉ ነበር? ይኸ ጥያቄ የመጨረሻው እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ወደ ተወሰዱት ቀደምት እርምጃዎች ይወስደናል። አጼ ዮሐንስ ምጽዋን በወዳጃቸው በእንግሊዝ እርዳታ በሰላም መንገድ የሚያገኙ መስሏቸው በመጻጻፍ ላይ ነበሩ። ስለዚህ ራስ አሉላ ከወደቡ ወጥተው በሰፈሩት የጣሊያን ሠራዊት ላይ እንዳይዘምቱባቸው ከለከሏቸው። በኋላ ግን ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የሚያደርጉት መጻጻፍ ተስፋ ቢስ መሆኑን ሲያዩ፥ ከእሳቸው ዘመን በፊት የተወሰደችውን ምጽዋን ማስመለስ እንኳ ቢያቅት ከምጽዋ ውጪ በእሳቸው ዘመን የተወሰደውን መሬት ለማስመለስ የዘመቻ ክተት ዐወጁ። ሁለት መቶ ሺ የደጋ ሠራዊት ይዘው መሽጎ ወደሚጠብቃቸው ጠላት ቆላ ወረዱ። የሞተው ሞቶ ግምቡን እንደመናድ በሩቁ ሰፍረው የአጥሩን ድንጋይ በጥይት ይጠዘጥዙት ጀመር። ጥይት ድንጋይ በስቶ የመሸገውን እንደማይጎዳው ሲያዩ ድርድር ጀመሩ። በማህል ቤት የደጋው ሠራዊት ተቅማጥ ገባው፤ ስንቁም ማለቅ ጀመረ። ስንት ሰው በተቅማጥ አልቆ አንድ የጠላት ሰው ሳይሞት ከተቅማጥ የተረፈው ዘማች ተመለሰ። ብዙ ሳይቆዩ ወደ መተማ አዘመቱት።
ከዚህ በኋላ መቸና እንዴት ነው ራሱን ያላጠናከረ የንጉሥ ምኒልክ መንግሥት የተደላደለውን የኢጣሊያ ሠራዊት ከሸዋ ገሥግሦ ከኤርትራ የሚያሶጣው? ሁለተኛም፥ አጼ ዮሐንስ ሀገሪቱ የሚነግሥባት ጡንቻ ያለው መሆኗን እያወቁ፥ በዚያች ሰዓት ጡንቸኛው ማን እንደሆነ ዘንግተው፥ ሲያርፉ አልጋቸውን ላላዘጋጁትና ድንገት ብቅ ላደረጉት ልጃቸው ለልዑል መንገሻ ስላወረሱ ብጥብጥ ይነሣል ተብሎም ይጠበቅ ነበር። ንጉሥ ምኒልክ ውርሳቸውንም ገና ማረጋገጥ ነበረባቸው።
ከአድዋ ድል በኋላስ? ወደ አስመራ ሊገሠግሡ አይችሉም ነበርን? ታሪኩን እንዳነበብኩትና ታሪኩን ከጻፉት ብዙዎች ጋር ተወያይቼ እንደደረስኩበት ከሆነ፥ እንኳን ወደ አስመራ ሊገሠግሡ፥ ከዚያም ቆላ ወርደው ምጽዋን ሊያስለቅቁ ቀርቶ፥ አድዋ ላይ ድል ማግኘታቸው እንኳን እንደ ተአምር የሚቈጠር ነው። የአጼ ምኒልክ ችሎታ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የጦር ስልት ዐዋቂም ነበሩ፤ አንደኛ፥ የኢጣሊያን የጦር ሠራዊት ከምሽጉ ውስጥ እንዳለ ሊገጥሙት አልፈለጉም፤ እስኪወጣ ጠበቁት። በዚህ ጊዜ በሁለቱም በኩል ስንቅ ማለቅ ጀመረ። እነሱ ከዋሻቸው መውጣት፥የኢትዮጵያ ሠራዊት ስንቅ ፍለጋ መሄድ ነበረባቸው። ስለዚህ፥ብዙዎች በውጊያው ላይ አልተገኙም። ሁለተኛ፥ንጉሡ ጦርነት እንደ ቸዝ ጨዋታ መሆኑን ስላወቁ አደጋ በቀላሉ ከማይደርስባቸው ቦታ ሆነው ነበር ያዋጉት። ቅዱስ ጊዮርጊስ ረዳን የሚሉት ሊታመን የሚቻል ነው። ምክንያቱም በዓሉ በዋለበት ዕለት ጦርነቱን ያወጁት አራቱ ጀኔራሎች የሚመሩት የኢጣሊያ ሠራዊት የተቃጠረበት ቦታ ስለጠፋው እኩል አልደረሱም። መጀመሪያ የደረሰው ብቻውን ተገኝቶ ተመታ። ሆኖም፥ ከኢትዮጵያ ብዙ ሰው ገድሎብናል። ከሞቱት ውስጥ አንዱ ንጉሡ ቢሆኑ ኖሮ፥ የተሸነፈው ጠላት መሸሹን ትቶ ተመልሶ መጥቶ ድላችንን ይነጥቀን ነበር፤ አድዋም ሌላዋ መተማ ትሆን ነበር። ግን በንጉሡ የጦር ስልት ዐዋቂነት ተሸንፎና ተደናግጦ ሸሸ።
ጠላት መሸሽ ሲጀምር፥ የኢትዮጵያው ሠራዊት ጦርነቱ ያለቀ መስሎት ወደ እርሻው ለመመለስ ቸኮለ፤ የመልስ ጒዞውን ጀመረ። ሌላው ያነበብኩት ነገር ይህ የጥቁር ሕዝብ ድል በቅኝ ግዛት ስር ላሉ ሕዝቦች መጥፎ አርአያ እንዳይሆን እንግሊዝ ኢጣሊያን ለመርዳት በቅርብ የሚገኘውን ሠራዊቷን አንቀሳቅሳ እንደነበር ነው። እንኳንስ ወደ አስመራና ምጽዋ ሲዘምቱ ዝም ሊሏቸው የአድዋ ድል እንኳን ከንክኗቸው "አበሾች ጥቁሮች አይደሉም" ወደሚል ድምዳሜ ሄደው ነበር።
እነዚህ ጎሰኞች ኢጣሊያ ኤርትራን እንዴት እንደወሰደቻት የሚያወሻክታቸው ያው የተጠናወታቸው የጎሰኝነት በሽታ መሆኑ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። ንጉሣችንን አጼ ዮሐንስን የግላቸው ሲያደርጓቸው፥ ንጉሡ ከነስሕተታቸው የግላቸው ስለሆኑባቸው፥ ስለስሕተቱ ምን እንደሚያደርጉ ተቸገሩ። ሁለት ወሳኝ እርምጃዎች ወሰዱ፤
(1) የአጼ ዮሐንስ ስሕተት ንጹሕ የአስተሳሰብ ስሕተት መሆኑን በማስረዳት ፈንታ ባለማንሣት ሊደብቁላቸው ፈለጉ፤
(2) የአጼ ዮሐንስን ንጹሕ ስሕተት በሌላ ላይ ለማላከክ ኤርትራ ስትወሰድ በቦታው ያልነበሩት የአጼ ምኒልክ ወንጀል አደረጉት። የመሰላቸው ተጨማሪ ጥቅም የአጼ ምኒልክን ክብር ማናናቅ ነበር። አይሠራም፤ ታሪክ በምንም ኬሚካል ቢፍቁት አይፋቅም።
የአጼ ምኒልክ ስም ከተነሣ አድዋ ላይ ያገኙት ድል ተወዳዳሪ ስለሌለው ስለዚያ ብቻ ይወራል እንጂ እንግሊዞችንም በጽሞና አምበርክከዋቸዋል። ከአድዋ ድል በኋላ አምባሳደራቸው አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ ሊያነጋግራቸው የቻለው ከአንድ ሳምንት ደጅ ጥናት በኋላ ነበር። አምባሳደሩ የመጣው ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን ጠብ እንዳታበርድ ለመደለል ነበር።" ለሱ አትስጋ፤ በናንተ በክርስቲያኖች ላይ ከእስላሞች ጋር ስምምነት አናደርግም" ብለው መልስ ሲሰጡት፥ ለስምምነት የጋበዟቸው ሱዳኖች ከጓዳ ሆነው ይሰሙ ነበር። የኢትዮጵያን የጥንት ድምበር ለዓለም በማሳወቅ፥ በኬንያ በኩል የሚመጡትን የእንግሊዝ ወታደሮች ፋኖው እንዲመታቸው በመፍቀድ የቅኝ ግዛት መስፋፋቷን ገትተውታል። ብዙው የኢትዮጵያ መሬት ወደ ሱዳንና ወደ ኬንያ ከመግባት የዳነው በአጼ ምኒልክ ብርታት ነው።
ኢትዮጵያ የዓባይን ውሐ ያለሱዳን መንግሥት ፈቃድ እንዳትገድብ አጼ ምኒልክ ውል ገብተዋል እያሉ የእንግሊዝኛውን ሰነድ እየጠቀሱ ያናፍሳሉ። አጼ ምኒልክ የተስማሙበት የአማርኛው ሰነድ የሚመሰክረው ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር መዋዋላቸውን ነው። ከፋም ለማም ውሉ እንግሊዞች ከሱዳን የወጡ ዕለት ውድቅ ሆኗል።
የሱዳን ስም ከተነሣ፥ ንጉሡ ለእሷም ጠቃሚ ምክር ሰጥተዋታል። በእንግሊዝና በፈረንሳይ መካከል ያለውን መጠላለፍና መከባበር ስለሚያውቁ፥ ሱዳንን እንግሊዞች ከሰሜን ፈረንሳዮች ከደቡብ ሲመጡባቸው አጼ ምኒልክ ለሱዳኖች የሰጧቸው ምክር እንግሊዞች ሲመጡባችሁ የፈረንሳይ ባንዲራ፥ ፈረንሳዮች ሲመጡባችሁ የእንግሊዞች ባንዲራ ይዛችሁ መልሷቸው ብለው ነበር።
ለማጠቃለል ያህል፥ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን ሁሉ ነገሥታቷ አጠፉም አለሙም፥ የሁላችንም መሆናቸውን ያምናል። አጼ ቴዎድሮስ የተመኙትን የኢትዮጵያ አንድነት አጼ ዮሐንስ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት፥ አጼ ምኒልክ እውን እንዳደረጉት፥ ከታሪክ ይማራል።
አቶ መለስ ዜናዊ ካድሬዎቹና ኤርትራ
አቶ መለስ ዜናዊና ካድሬዎቹስ? ኢጣሊያ ኤርትራን ስለወሰደቻት አቶ መለስ ዜናዊና ካድሬዎቹ ከተቆጩ መቆጨታቸውና መጻፋቸው የሚገባ ነው። ኢጣሊያ ኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠሏ ቢቆጫቸውና ቢያሳዝናቸው ነው። አለዚያማ ሌሎች ሀገሮች በቅኝ አገዛዝ ስር ስለመውደቃቸውም ያንኑ ያህል ይጽፉ ነበር። ታዲያ እንዲህ ከሆነ፥ በኤርትራውያንና በኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ትግል እንደገና የተቀላቀለችው ኤርትራ በማን ክሕደት ተመልሳ እንደተገነጠለች ውሸት መፍጠራቸውን ትተው ለምን እውነቱን አይጽፉልንም?ሌላው ቢቀር በቅርጫው ጊዜ ለኤርትራ ምንም የማይጠቅማት ለኢትዮጵያ ግን እንደ አንድ የደም ስር የሚቈጠረውን የአሰብ ወደብ ኢትዮጵያ እንድትወስድ ለምን አልተቃረጡላትም? ለኢትዮጵያ በጎ ነገር ባይፈልጉላት ነው እንጂ፥ አቅም ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም። አሰብን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ቢፈልጉ ኖሮ፥ በባድመ ጦርነትም ጊዜ ሌላ ዕድል ገጥሟቸው ነበር። ለነገሩ ነው እንጂ፥ ይኸን ሁሉ ብሐራዊ ወንጀል እነሱ እንደማይጽፉት የታወቀ ነው። ግን እነሱ ባይጽፉት ሳይጻፍ ይቀራል፤ የሚጽፈው አይኖርም የሚል ተስፋ ካላቸው ተስፋቸውን ይቊረጡ። "…የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግምባር አባላት ያወጁት ዘመቻ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ አይደለም፤ በትናንቷ ኢትዮጵያ ላይ ጭምር ነው። ዓላማቸው" ትናንት ያልነበረች ኢትዮጵያ ነገ መኖር የለባትም" ነው።" አጼ ዮሐንስ ትግሬ ነበሩ፤ አጼ ምኒልክ አማራ ነበሩ" የሚሉት "እኝህኛው የኛ ናቸው፤ እኛኛው የናንተ ናቸው" ለማለት ነው፤ እኛን መኲሪያ የታሪክ ሰዎች ሲያሳጡን እነሱም አጼ ምኒልክን ያህል ታላቅ መኲሪያ እንዳጡ ተሰማቸው። ለዚህ ችግር የፈጠሩት መፍትሔ፥ እኛንም እንደነሱ መኲሪያ አልባ ማድረግ ነው። ለዚህ ዓላማ የአጼ ምኒልክን ገናናነት ሊንዱ ይሞክራሉ። የማይቻል ሙከራ ነው። አጼ ዮሐንስ ከመንገሣቸው በፊት ስማቸው "ካሳ"ነበረ። ከመከፋፈል ተንኮላቸው ብዛት የተነሣ፥ ምንም ማስረጃ ሳይኖራቸው ካሣን ወደ "ካሕሳይ" መለወጥ ይዘዋል። የተንኮሉ ዓላማ የኛ የሚሏቸውን ለማመስገን፥ የኛ አይደሉም የሚሏቸውን ለመኰነን ብቻ ሳይሆን፥ ሁላችንም "የኛ የምንላቸው ነገሥታት አልነበሩንም፤ ኢትዮጵያ በአንድ ንጉሥ ስር የምትተዳደር፥ አንድ መንግሥት የነበራት አንድ ሀገር ሆና አታውቅም"ለማለት ጭምር ነው። አጼ ዮሐንስን ስማቸውን ሲያጠፉና የሁሉ ንጉሥ አልነበሩም እያሉ ድርብ ወንጀል ሲፈጽሙባቸው ንጉሡ እንኳን አልሰሙ። በአማርኛ በሚያስችሉት ችሎት ላይ አቅርበው ባደባባይ መላሳቸውንና ጣታቸውን ያስቈርጡላቸው፥ እንዳባታቸው እንደ አጼ ዘርአ ያዕቆብ አፍንጫቸውን ያስፎንንኑላቸው ነበር። እኛም አንለቃቸውም። በእናት ሀገራችን ላይ የዘመቱባት ዘመቻቸው በኋላና በፊት፥ በሁለት ግምባር፥ መሆኑን በግልጽ ተረድተናል። በከፈቱት የዘመቻ ግምባር ሁሉ ግምባር ግምባራቸውን እንላቸዋለን። እነሱ ከአንድ አካባቢ ተገዶ ዘማች ሠራዊት ሲኖራቸው፥ እኛ ከመላ ኢትዮጵያ ወዶ ዘማች የኢትዮጵያ ሕዝብ አለን። እነሱ ውሸት ሲፈጥሩ እኛ ታሪክ የፈጠራት እውነት ከእኛ ጋር ናት። እንደኛ፥ እውነትንና ብዛትን ይዞ በዘመቻ የተሸነፈ ራሱን እንጂ፥ ጠላቱን እንደማይወቅስ ተረድተንና አምነን ገጥመናቸዋል፤ እናሸንፋለን። "“ጌታቸው ኃይሌ (ምንጭ -የወያኔ ገበና ማህደር”ደራሲ ጌታቸው ረዳ -በህትምት ላይ ከሚገኘው አዲስ መጽሐፍ የተገኘ)።
ለመሆኑ ፕሮፌሰር ግበሩ ታረቀኝ ስለ ወያኔ ጦርነት እና ስለ ደርግ/ኢትዮጵያ ያን ያህል-ትልቅ ወታደራዊ መጽሐፍ ሲጽፍ ምስጢራዊ የምረምር ሰነዶችና ምስጢራዊ ምሽጐች ጉብኝት በወያኔ መሪዎች ተፈቅዶለት መጽሐፉን ሲጽፍ “ወያኔዎች በትግራይ እና በሌላው ዜጋ በእሳት የጠበሱት፤ታጋይ እና ሌሎች ወንጀሎች ከመዘርዘር ለምን ታቀበ?ሐገረ ሰላም ውስጥ የሚገኘው የወያኔ ከፍተኛ ወታደራዊ-አመራር-ጉድጓድ /አንደር ግራውንድ/የዘመቻ ጠቅላይ ማዕከል ጽ/ቤቱ ግድግዳዎች እና ወንበሮች ፎቶ ግራፍ አንስቶ መጽሐፉ ውስጥ ከሚያሳየን ይልቅ “ግህነም”የተባለው ፀገዴ ውስጥ ያለው 150 ክፍል የያዘ አንደር ግራውንድ የጉድጓድ እስር ቤት እና ማንስ አንደሰራው ምንስ ወንጀል እንደተፈጸመበት ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ እና ፎቶግራፍ ማቅረቡ ምነዋ ተቆጠበ? ጉድጓዶቹ እስካሁን ምን ይዘዋል? ነፃ ናቸው? ሕዝብ ጎብኝተዋቸዋል? ገብሩ ታረቀ በምርምሩ ይህ ጉድ እስካልገለጽልን ድረስ በዚህ አገር አስተማማኝ ዕርቅና ሰላም አይገኝም ብለን ፕሮፌሰር ገብሩን የተቸው የለም። ታዲያ-የወያኔ-ወጥንጨት ይዞ ወጥ-ማማሰሉ ላልተማሩት ቢተውላቸው ምን አለበት? ምሁራን አደከማችሁን እኮ! አስተማሪ እያለ እንዴት ተማሪ አስተማሪን ያንቃው? ወይ አንቺ ማርያም! ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ ሰማይ አዘጋጅ ሳን ሆዜ ካሊፎርኒያ።www.ethiopiansemay.blogspot.com
No comments:
Post a Comment