መጠመዘዣ ላይ ቆመዉ መጠምዘዝ ያቃታቸዉ የዑዘይር አህዬች
ጌታቸዉ ረዳ http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/
ሀማ ቱማ “በዝብርቅርቅ ፖለቲካ”-መጣጥፉ የሚለዉ ወይንም በ “Democratic Cannibalism”መጽሃፉ ላይ “Of Boring Politicos and Change of Times” ያነበብኩትን ትዝ ሲለኝ አንዳንድ የፖለቲካ ተቃዋሚ ቡድን መሪዎች እና ደጋፊዎቻቸዉ ድርጅታቸዉን በማይገባ ለማሸብረቅም ሆነ ከእነርሱ ጋር በተለያዩ አቁዋሞቻቸዉ የማይግባቡ የተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ የሚሰነዝሩት ከሃቅ የራቀ በሬ ወለደ ዉግዘታቸዉም ሆነ ለኢትዮጵያ ላላቸዉ ራዕይና የመታገያ ስልታቸዉ በስሜት ከመነዳታቸዉ ብዛት፤ እነሱ አሜሪካ እና አዉሮጳ ሀገር ሆነዉ “መለስ ዜናዊን በማንቁርቱ ይዘዉ ለማመረክ አዲስ አበባ ከተማ ከብቦ የነበረዉ የሽምቅ ተዋጊ ሠራዊታቸዉ ከመቅጽበት ከተማዉን ሰንጥቆ በመግባት ከቤተመንግሥቱ ደጃፍ ላይ ርቀት እንደቀራቸዉ”-አስመስለዉ የሚያሰራጩት የፓል ቶክም ሆነ የጽሁፍ እና በሚጠሩት ሕዝባዊ መደረካቸዉን የሚያስተላልፉት ትኩሳት ሳዳምጥ ዕዉነትም “ዝብርቅ” ያለብን ነን። እላለሁ። ፔንሰልቪኒያ የተባለው ግንቦት 7- ቤተመንግሥት ተገኘ? በማለት ተመልሶ አንባቢዎቹን በአግራሞት የጠየቀ አንድ ከወደ ዋሽንገተን ዲሲ የሚታተምጋዜጣም ሳነብብ “ፈጣን ጉሬላ ይሉሃል ይሄ ነዉ!” አልኩኝ”
ከ10 ዓመታት በፊት ተቃዋሚዉ እርስ በእርሱ ያለመስማመት ችግር የኖረዉ ቢሆንም፤ እንደዛሬው እንደዚህ ዓይነት በነፋስ የሚጋልብ ስነ ፖለቲካዊ ልቦና የጎደለዉ መድረሻዉና መታገያ ሜዳዉ የማያዉቀዉ ስሜተኛ የፖለቲካ መሪም ሆነ ደጋፊ ተሰምቶም ታይቶም አይታወቅም ብየ በእርግጠኛነት መናገር እችላለሁ። ከጋላቢዎቹ ይልቅ ከእነርሱ ብሰዉ የነሱን የስሜት ግልቢያ የሚያጎሉ፤የጋዜጠኛነት ሙያ አለን የሚሉ ባለ መድረኮች ስታስቡ ደግሞ እዉነት የኢትዬጵያ ጋዘጠኞች እነዚህ ነበሩ? ያሰኛል።
ከግንቦት 1983 ዓ.ም አስከ ግንቦት 7 1997 ዓ.ም ማለትም ለአስራ አራት ዓመት ሙሉ ቅጥረኛዉ የወያኔዉ መንግስት ታዋቂ ምሁራን፤ (ታየ፤ አስራት፤ አበራ፤ አሰፋ ማሩ፤ ፊታዉራሪ መኮንን፤ የኢሕአፓዋ አበራሽ፤ጸጋየ፤ገለብ ተስፋየ እና ብዙዎቹ ጋዜጠኞች … በሺዎቹ የሚቆጠሩ የጦር ሜዳ ጀግኖች የማረካቸዉ ወታደሮችና መኮንኖች…) ዜጎቻችን በወያኔ የሰቆቃ (ቶርች) ቻምበር ሲያሰቃዩበት/ሲገደሉበት በነበረበት ከባዶቹ የጨለማ ዓመታት፤ ተራዉ ያልተማረዉ ዜጋ የወያኔ ምንነት እንኳ እያወቀዉ “ጉደኞች” የምንላቸዉ የግንቦት7 መሪዎች እነ ብርሃኑ ነጋ ቃሊቲ እስከታሰረበት ጊዜ ድረስ (ማለትም ለ14-ዓመታት ሙሉ ምንም ሳያወቅ-ከሰቆቃ አዛዦች ጋር ዊስኪ ሲያንቃርር) ወያኔ “በእስረኛ ላይ ሰቆቃ አይፈጽምም” የሚል እምነት እንደነበራቸዉ ሳያፍሩ የፖለቲካ ግብዝናቸዉን በመጽሃፍ ያሰፈሩትን (ጎህ ሲቀድ -በብርሃኑ ነጋ ገጽ 199 ይመልከቱ) ጉደኞችን ይዞ የሚጓዘዉ የፖለቲካዉ ዓየር እና የሃገሪቱ ሁኔታ ሳስበዉ ጭንቀቴ ከልቤ ጋር ሲተናነቅ ደረቴን ሰንጥቆ ለመዉጣት የሚያደርገዉ ትግል እስከ ናላየ ድረስ እንደምላጭ ስለት ሲተለትለኝ ይሰማኛል።
አሁን ያለዉ አሳዛኝ የፖለቲካ ዝብርቅርቅ እላይ በተጠቀሱት መሪዎች (ግንቦት 7) ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ የፖለቲካ ዋስትና እና መጠለያ ለማግኘት በቁሳቁስም ሆነ በሞራል እና በዜናዉ ማስራጫ አዉዳቸዉ ላይ ሌት ተቀን ስለ እነሱ አገር ወዳድነት ሕዝብ አፍቃሪነት እና ስባዊ መብት ተቆርቋሪነት በሰፊዉ በመሟገት በተቃዋሚነት ታዉቀዉ መድረኩን እንዲቆጣጠሩት “ወያኔ -ክፍል ለ”-ወይንም “ዓረና”በመባል የሚታወቁት ሌሎቹ ጉዶች በመደገፍ የ ፖለቲካዉ ዓየር በባሰበት መልኩ እንዲምታታ አስተዋጽኦ እያደረጉት ስላሉት “የዑዘይር አህዬችን” አንድ ለማለት ነዉ።
የዑዘይር አህያ ታሪክ ላናነበባችሁ-ዑዘይር ምንድነዉ እንዳትሉ-፦ ረዢሙን ታሪክ አላቀርበዉም። አደም የተባሉ ጸሃፊ በሐጅራ ዕትም ያቀረቡትን ዜጋ መጽሄት በ1995 ዓ.ም ዕትሙ አቅርቦት ነበር። ዑዘይር የሰዉ ስም ነዉ።ፍልስጢማዊ ነዉ። ዑዘይር የትልልቆቹ የጫካ አህዬች/የባዝራዎቹ ሳይሆን የትንንሾቹ ለማዳ አህዮች ባለቤት ነዉ። በዑዘይር ታሪኩ የሚጠቀሰዉ አህያ እንደ ሰዎች መናገር ይችላል። በየመንገዱ በየአፈሩ ላይ የቀሩት ኮቴዎችን ማንበብ እና አለቆቹ የማያያዩትን የማየት ችሎታ አለኝ ይላል።በዑዘይር ከመገዛቱ በፊት፤በዱላ ሲነርቱት ከነበሩት አይምሬ ጨካጮች ጌቶቹ ሲነጻጸር ዑዘይር የዋህ እና ደግ ነበር፤ ይላል አህያዉ። ዑዘይር ለማገልገል ሞቶ ቢነሳም ምንም ጌዜ ቢሆን ወገቤ ለእርሱ ዝግጁ ነዉ ይላል።
ከእለታት አንድ ቀን ዑዘይር እህያዉን እንደ በቅሎ መጭ ብሎት ወደ እሩቅ ጉዞ ሲጓዙ ወደ መድረሻቸዉ ሲቃረቡ አንዱን ከተማ አልፈዉ ለማረፍ ዕቅድ ስለነበራቸዉ በአንድ የከተማ ሰፊ መካነ መቃብሮች አካባቢ ሲደርሱ ጌታዉ ዑዘይር ፤-አህያዉ በተቻለዉ ፍጥነት እተጣደፈ በድንገት ፍጥነት መጨመሩን ሲረዳ “ዑዘይር”-በአህያዉ ላይ “ሳቀ”-አህያዉ እንደፈራ ያዉቃል። ከቦታዉ እስከሚርቁ ድረስ አህያዉን በእጁ መታ መታ እያደረገ ያረጋጋዉ ጀመር።
የከተማዉ ሰፊ መካነ መቃብሩን ካለፉት በሗላ ባንድ
የአትክልት ሥፍራ እንዳረፉ ይተርካል። ጌታዉ ዑዘይር ጋደም ብሎ በሀሳብ እና በማስተዋል እንደተዋጠ አህያዉ ተመለከተዉ። ዑዘይር በዓይኑ ትኩር ብሎ ስለፈራረሱት እና የተሰባበሩት አጥንቶች ፀጥ ወዳሉ ሙታኖች የሚመለከት መሆኑን ከፊቱ ይነበባል። የአላህን ችሎታ ለራሱ እንደሚያረጋግጥ ሰዉ የህችን ከተማ ከሞተች በሗላ እንዴት ሕያዉ ያደርጋታል?” ሲል ሰማሁ (አልበቂራ፡259) ይላል
የዑዘይር አህያ።
ዑዘይር ይህንን ቃል ተናግሮ ከማብቃቱ በፊት ከባዱና ድንገተኛ እንቅል ይዞት ጭልጥ አለ። የዑዘይር አህያም ስለጌታዉ መተከዝ ተጨንቀቆ ሲያስብ እሱም እንቅልፍ ወርሮት ከጌታዉ ጋር አብሮት አንቀላፋ።ይላል።
የዑዘይር አህያ እንቅልፉን ጨርሶ ሲነሳ ዑዘይር እንዳንቀላፋ በዛዉ ሳይነሳ ተሸንፎ ቀረ። ይህች ከተማ አላህ እንዴት ሕያዉ ያደርጋታል? እያለ ነበር በዛዉ ያንቀላፋዉ። አላህም ገደለዉ። መቶ ዓመት አቆየዉና ከእዚያ አስነሳዉ። ምን ያህል ቆየህ? አለዉ። “አንድ ቀን ወይንም የቀንን ከፊል ቆየሁ” አለ። “አይደለም መቶ ዓመት ቆየህ” አለዉ። “ወደ ምግብ እና ወደ መጠጥም ሂድ እና ያልተለወጠ መሆኑን ተመልከት”።አለዉ።ወደ ጉዞዉ ሲሄድ ከድኖት የቆየዉ የወይን ጠጅ መጠጡንም እንዳለ ሳይለወጥ ቆየዉ። ዑዘይርም ወደ አህያዉ ተመለከተ። የዑይዙር አህያም ጌታዉን ዑዘይር ሲመለከት በደስታ ተዉጦ ከሞት መነሳቱን ደስ ብሎት ወዳሰበዉ መንደር ለመጓዝ ከመቶ ዓመት በፊት ተቋርጦባቸዉ ወደ ነበረዉ ጉዞ እንዲመራዉ ጠጋ ብሎ ወገቡን አለጥልጦ ፈቃደኛነቱን እና ዝግጁነቱን ለጌታዉን ለዑዘይር እንደገለጸለት ይተርካል።
ዛሬም በጉደኛዉ ዓለማችን ከ 8 ዓመት የጌቶቻቸዉ ሞት ማየት በሗላም ቢሆን ጊዜዉ እንደተለወጠ ቢሰብኩንም ጊዜዉ መብረሩን እንጂ ገዳዬችን፤ረጋጮችን፤ዘረኞችን፤ አገር አፍራሾችን በታኞችን፤ ዉሸታም አፈጮሌዎችንና….ሲያዩ እንደ ዑዘይር አህያ ወገባቸዉን አለጥልጠዉ ጌቶቻቸዉን ለማገልገል ዛሬም ቃል ኪዳን ያደሱ መጠመዘዣዉ ላይ ቆመዉ መጠምዘዝ ያቃታቸዉ አህዬችን ስንመለከት በሺዎቹ የገደልዋቸዉን ጸጥ ብሎ በመታዘብ ያለዉ የሙታኖች አጥንት ዛሬም ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ ጉደኛዉ ጊዜ ሳያስገርማቸዉ እንዳልቀረ እርግጠኛ ነኝ።
ከታች በቅንፍ የምታነብቡት ጥቅስ አንብቡት እና የ18 ዓመት የኢትዬጵያን እዉነታ የማያዉቁ ፖለቲከኞች መድረኩ ላይ ዘልለዉ በመዉጣት ጭልጥ ያለ ዉሸት ከሚዋሹት ጋር ተጣምረዉ አገሪቱን እንደገና ወዴት ሊመርዋት እንደሚችሉ የሚጠቁማችሁ እጅግ አስገራሚዉ የብርሃኑ ነጋ እና የስየ አብርሃ ሹክታን ላስነብባችሁ እና ልሰናበት።
“እዚህ ላይ አንድ ገጠመኝ ልናገር። እስርቤት እንደገባን ሌሊት ላይ የተደበደበ ሰዉ ጩኸት እንሰማ ነበር። በመጀመርያ ማመን ነበር ያቃተን። ሰቆቃ (torture) በኢትዬጵያ የለም ብለን እናምን ነበር። ስነሰማዉ ግራ ተጋባን። እነ ስየ አብራሃ ከመጡ በሗላ እንደዚሁ አንድ ሌሊት ይህን የሰዉ የስቃይ ጩኸት ስንሰማ አድረን ጥዋት ስየን “ሰማኸዉ ወይ የማታዉን” ስለዉ እሱም መስማቱንና ማመን እንዳቃተዉ፤ “እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳለ እንደማያዉቅ” ነገረኝ።” ብርሃኑ ነጋ ፤- የነፃነት ጎህ ሲቀድ- ገጽ 199)።
አምላክ ከዉሸት ዓለም ከጉደኛዉ ጊዜ ያወጣችሁ!-ጌታቸዉ ረዳ http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/
Monday, August 31, 2009
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment