Wednesday, July 7, 2021

“የገባን ላልገባችሁ የማስረዳት ግዴታ አለብን” - የሀገራችንን ከፍታ ጠቋሚ ዋና ዋና ምልክቶች አምባቸው ዓለሙ (ከወልዲያ) 7/7/2021

 

“የገባን ላልገባችሁ የማስረዳት ግዴታ አለብን” - የሀገራችንን ከፍታ ጠቋሚ ዋና ዋና ምልክቶች

አምባቸው ዓለሙ (ከወልዲያ)

7/7/2021

1.     በአዲስ አበባ መስተዳድር ጥናት መሠረት በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ምግብ ማግኘት የማይችሉ ዜጎች በአዲስ አበባ ከተማ አሉ፡፡ በሌሎች ከተሞችም ጭምር፡፡

2.    በዚህችው መናገሻ ከተማችን ውስጥ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ በረንዳና ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ዕብዶችና የትም አዳሪ ሰካራሞች፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤት አልባዎች፣ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ሴተኛና ወንደኛ አዳሪዎች፣ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ሌቦችና አጭበርባሪዎች፣ ሹዋሹዋዎችና መታቾች … እየተርመሰመሱ ይገኛሉ፡፡ ይመዝገብልን፡፡

3.    አንድ ሰው በየትኛውም ዲግሪ ተቀጥሮ በሚያገኘው የወር ደመወዝ ብቻ እየተዳደረ ቀዳሚውን ከተከታዩ ወር መግጠም የማይችልባት ብቸኛዋ ሀገር ናት - ኢትዮጵያ፡፡ በስርቆትና በሙስና ወይም በዘመድ አዝማድ ድጎማ ካልተደገፈ በስተቀር በተለይ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በሚከፈለው ደመወዝ ወሩን ይቅርና ሣምንቱንም መኖር አይችልም፡፡ የጂቡቲና የሃርጌሳዋ ሶማሊያ ሠራተኞች የኢትዮጵያን የዱሮ ንዑስ ከበርቴ የአሁኑን ነጫጭባ ድሃ ሠራተኛ ሊደጉሙት ይችላሉ፡፡ አብዛኛው ዜጋ በሁለት ሽህ ብር ደመወዝ የ50 ሽህ ብር ኑሮ እንዲኖር ይገደዳል፡፡ ለቤት ኪራይ ብቻ እንኳን በማይበቃ ደመወዝ እንዴት ኑር ይባላል? ይህ የወያኔና የልጁ የዶክተር አቢይ አንጻባራቂ ክፍለ ዘመናዊ ድል በጉልኅ ቀለም ይመዝገብልን፡፡

4.   ከቀበሌ እስከ ከፍተኛ፣ ከከፍተኛ እስከሚኒስቴር መሥሪያ ቤት፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እስከባንኮችና አየር መንገድ፣ ከዚያም እስከ መከላከያ፣ ፖሊስና ደኅንነት ከያለበት እየተጠራራ ሥልጣኑንና የጥቅም ቦታዎችን የሚይዘው አክራሪ ኦሮሞና የነሱ ተላላኪ ብቻ ነው፡፡ ቀደም ሲል የቀን ጅቡ የትግሬ መንግሥት እንደዚሁ ከዐድዋና ከሽሬ እየተጠራራ የሀገሪቱን የጥቅምና የሥልጣን ቦታ መቆጣጠሩ የሚታወቅ ነው፡፡ አሁንም ቅኝቱ ስላልተለወጠ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይህም ድል በወርቅ ቀለም ይመዝገብልን፡፡ አንዱ የከፍታችን ጠቋሚ ነውና፡፡

5.    በእንስት የዛር መንፈስ የሚነዳው ወጣቱ የአውሊያ ፈረስ በውሸታምቱ በዓለም አንደኛ ከመሆን አልፎ ወደፊትም ሆነ ወደኋላ በውሸታምት እርሱን ሊስተካከል የሚችል አንድም የዓለም ዜጋ ሊኖር አለመቻሉ ከከፍታችን ድሎች አንዱ ነው፡፡ ሲዋሽ ደግሞ ሀፍረት የሚባል ነገር ቅንጣት አይሰማውም፡፡ ከመቀሌ ለጥሞና ወጣን ሲል ጦሩን አካፑልኮ ቤይ ለሽርሽር ወስዶ ለማዝናናት አስመሰለው፡፡ አንዳቸው ለገበሬው ስንል፣ ሌላኛቸው ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ጫና ስንል፣ አንዳቸው አንድ ነገር ሌላኛቸው ሌላ ነገር እየዘባረቁ ውሸታቸው ለከት ያጣ መሆኑን ለዓለም ገለጹ፡፡ ካለበት የተጋባበት ነው፤ መምህራቸውና ፈጣሪያቸው ወያኔም ቆርጦ በመቀጠል የሚስተካከለው አልነበረም - የአሁኑን አያድርገውና፤ አሁንማ አቢይ አስከንድቷቸዋል፡፡

6.   መቶ ሽህ ብር የሚፈጅ አነስተኛ ፕሮጀክት በአምስትና አሥር ሚሊዮን ብር ይሠራና የአንበሣ ድርሻው የፕሮጀክቱ ገንዘብ ለባለሥልጣናት ይከፋፈላል፡፡ የተሠራው ሥራ እንደነገሩ ከመሆኑ የተነሣ ገና ከመመረቁ ወይም በተመረቀ ማግሥት ድራሹ ይጠፋል፡፡ እንዲያውም በአካል የሌለና ፍጹም የማይታይ ፕሮጀክት እንደተሠራ ተቆጥሮ ገንዘቡ እንደሚመዘበር ይሰማል፡፡ የትም ቢሮ ሄደህ ካለገንዘብ ጉዳይ ማስፈጸም ህልምና ቅዠት ነው፡፡ ገንዘብ እየተመለከ ነው፡፡ የግል ህክምናው ሌብነትና የለዬለት ዝርፊያ ነው - ለአልጋ የሚያስፍሉት ከሸራተን ዕጥፍ ነው፡፡ የትም ሂድ ገንዘብ ካልዘራህ ምንም ነገር አይሳካልህም፡፡ ቢሮክራሲው ሁሉ የሚከፈትልህ በብዙ ብር ነው፡፡ ዘረኝቱና ሙስናው ተባብረው ሊያጠፉን የቀራቸው አንድ ሐሙስ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በሙስናና ንቅዘት በዓለም አንደኛ መሆናችን የከፍታችን ስኬት አንዱ ማሳያ ነውና ይመዝገብልን፡፡

7.    ትምህርት፡፡ ትምህርቱ “ወደቀ”” የሚለው ቃል አይገልጸውም፡፡ የአብዛኛው ዜጋ ጥረት ወረቀት ለመያዝ እንጂ ዕውቀት ለመገብየት አይደለም፡፡ ውድድሩና ሩጫው ሁሉ ያበላል በሚባል አንድ ወይም ከአንድ በላይ የትምህርት መስክ እቤት ተቀምጦ በግዢና በለብ ለብ ልክ እንደመንጃ ፍቃድ ዲግሪን  ማግበስበስ የተለመደ ሆኗል፡፡ ዶክተር ሆኖ ስሙን በየትኛውም ቋንቋ አስተካክሎ የማይጽፍ የተማረ ደንቆሮ የሚገኝባት ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናትና ይህም በከፍታችን ጠቋሚነት ይመዝገብልን፡፡ ለዚህም ነው እኮ “the ruling party” ወይም “the incumbent government” ለማለት “the buying government” የሚል ዶክተር የዩኒቨርስቲ መምህር፣ “unequivocally” ለማለት “equivocally” እና “by implication” ለማለት “by implies” የሚሉ ጠ/ሚኒስትሮች ልናይ የተገደድነው፡፡ ያልዘራነውን ከየት እናገኛለን ዱሮውንስ? ጉዳችን ፈልቶ! ብቻ ይህም ይመዝገብልንና ለታሪክ ይቆይልን፡፡ ማን ያውቃል - ነገ ሌላ ቀን ሊሆን ይችላል፡፡

8.   ትምህርቱ እስካጥንታችን ዘልቆ ብዙ ዐዋቂና አስተዋይ እንድንሆን ከማድረጉ የተነሣ እነዶክተር አቢይና ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ያዘጋጇቸው ኦነግ ሸኔዎች የነፍሰ ጡርን ሆድ በመዘርገፍ የሚያወጡትን የአማራ ሕጻን በሟች እናት ፊት መብላት የደረሱት፣ አማራን በተገኘበት ለማረድ የማይመለሱት፣ የአማራን ሀብትና ንብረት እየወረሱ የሚወስዱት ወይም የሚያቃጥሉት ሁሉ ለደረስንበት የከፍታ ማማ ጠቋሚ ነውና ይመዝብልን፡፡ ሰው ወደዐውሬነት መለወጡ ከፍታ ነዋ፡፡

9.   በየትም ሀገር የሌለ በኛ ሀገር ብቻ የሚገኝ የዘር ፖለቲካ አንዱን ጎሣ የበላይ አንዱን የበታች እያደረገ የበታቹን ለግድያ የበላዩን ለሥልጣንና ለጥቅም የሚያበቃ በመሆኑ ከፍታችን ከዓለም ወደር አይገኝለትም፡፡ በጎሣና በሃይማኖት የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመሠረት የሚፈቅድ ህገ መንግሥት ያለን ብቸኛዎቹ የኅዋ ውስጥ ፍጡራን በመሆናችን አጋንንተ ዓለም ጥልሚያኮስ ምሥጋና ይድረሰውና ይህም ይመዝገብልን፡፡

10.  ክልሎች ሁሉ ሌላ የልማትና የዕድገት ሥራቸውን እርግፍ አድርገው ትተው ልዩ ኃይልና ሚሊሽያ በማሰልጠንና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ወደማያባራ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ርሀብንና በሽታን፣ ኋላ ቀርነትንና ዕርዝታን በቅጽበት የሚያጠፋ ታላቅ ትልም በመሆኑ በዚህም የከፍታችን ታላቅነት ሊታወቅልን ይገባልና ይመዝገብልን፡፡ አፋር ልዩ ኃይል፤ ትግራይ ልዩ ኃይል፤ ኦሮሞ ልዩ ኃይል፣ አማራ ልዩ ኃይል፤ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ልዩ ኃይል፤ ሶማሌ ልዩ ኃይል፣ ሲዳማ ልዩ ኃይል፣ ደቡብ ልዩ ኃይል፤ ቅምብቢት ሚሊሻ፣ ዶሮ ግብርና ጎብዬ ሚሊሻ፣ ቱሉቦሎ ሚሊሻ፣ ደምቢዶሎ ሚሊሻ ….. ደስ ሲል! ከዚህ በላይ ከፍታ የት ይገኛል ታዳ?

11.    አሁን ዕድሜ ለጫጩ የዚህና የዚያ ወገን አእምሮዎች ‹ትግራይ›ና ኢትዮጵያ የሚባሉ ሀገራት ተፈጥረዋል፡፡ ዕድሜ ለኢሱ፡፡ የኢሱ ጦር በአቢይ ይሁንታ ትግራይን የዶግ ዐመድ አደረገ፡፡ ትግራይ ከሞላ ጎደል ጠፋች፡፡ አሁን ግን በእልህና በፖለቲካ ሤራ ምክንያት አንሰራራች፤ እውነትም እልህ ጩቤ ያስውጣል፡፡ ቢሆንም ግን የትም አትደርስም፤ ቋቷ ሞልቷልና፡፡ ጊዜያዊ ጉዳት ማስከተሏ ግና ገና ከጧቱ እየታዬ ነው፡፡ አማራ ካላወቀበት ለተወሰነ ጊዜ ይጎዳል፡፡ የአቢይ አካሄድም ለዚያ ይመስላል፡፡ ዝግጅት ያልተደረገበት ሽሽት መንስኤው ለአማራ እሾህ አሜከላ ለመፍጠር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አማራው ራሱን ይጠብቅ፡፡ ተስፋ የቆረጠ ዐውሬ የንጋት ጅብ እንደማለት ነው፡፡ ለማንኛውም ይህም የከፍታችን ምልክት ነውና ይመዝገብ፡፡

12.   ኦሮሚያ በትራክተር ልትታስና በስንዴ ልትጥለቀለቅ፣ አማራና ትግራይ በቦምብ ሊታረሱና በሰው ደም አላባ ሊጥለቀለቁ ዐውድማው ተሰናድቶ አልቋል፡፡ ጅሎች ይገዳደላሉ፤ ብልጦች ዳር ቆመው በማን አባት ገደል ገባ ሞኞችን ያጨራርሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ አቻ የማይገኝለት የቅርብ ጊዜ የከፍታችን ምልክት ነው፡፡ ብዙ ማለት በተቻለ፡፡ ግን የሚሆንን ነገር ከመሆን ማስቀረት ላይቻል የሆድን ሁሉ ዘርግፎ መናገሩ ከንቱ ድካም ነው፡፡ አዳኛችን ግን አንድዬ ብቻ መሆኑን እንረዳ፡፡

No comments: