Friday, November 27, 2020

ጦርነቱና ከጦርነቱ ማግስት አገሬ አዲስ ህዳር 11ቀን 2013ዓም(20-11-2020) (Ethiopian Semay)

 

ጦርነቱና  ከጦርነቱ ማግስት

አገሬ አዲስ

ህዳር 11ቀን 2013ዓም(20-11-2020)

(Ethiopian Semay)

ጦርነት ጎጂና  አውዳሚነቱ ቢታወቅም ከገቡበት በዃላ ይዞት የሚወጣው ውጤት የሚፈለግ ወይም የማይፈለግ ሊሆን ይችላል። ለጦርነት ምክንያት ብዙ ቢሆንም በሁለት መልክ ይመደባል። አንደኛው ለአገር ልዑላዊነትና ነጻነት፣ ለሕዝብ ክብርና መብት የሚደረግ  ፍትሃዊ ወይም ጀስት ዋር(Just War) የሚሉት ሲሆን ሌላው በውጭ ወራሪዎች የሚካሄድ ጦርነትና  በአገር ውስጥ ለአምባገነኖች ጥቅም ሲባል ሕዝብን በመከፋፈል አጋርና ጠላት አድርጎ ለማጫረስ የሚቀሰቀስ ኢፍትሃዊ ጦርነት ወይም አንጀስት ዋር(Unjust war) ነው።

አሁን ባገራችን ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት የሁለተኛውን የጦርነት ምክንያት የተከተለ መሆኑን የሚክድና የማያውቅ የለም።የታሪክ አምድን ወደዃላ መለስ ብለን ብናገላብጠው ከሃያ ዓመት በፊት በሻቢያና በወያኔ መካከል የተቀሰቀሰውና ለብዙ ዜጎች ህይወት መጥፋትና ለአገር ንብረት መውደም ምክንያት ለሆነው ጦርነት መንስኤው የሁለት ጸረ ኢትዮጵያ ተገንጣይና አስገንጣይ ሃይሎች የጥቅም ሽኩቻ የቀሰቀሰው ነበር።የአሁኑንም ጦርነት ከዚያ የሚለዬው ምክንያት የለም።የሁለት ጸረ ኢትዮጵያ የጎሰኛ ቡድኖች ፣የህወሃትና የኦህዴድ የጥቅምና የስልጣን ሽኩቻ የፈጠረው ጦርነት ነው።

ከሻብያም ጋር በተደረገውም  ጦርነት ስልጣን ላይ የተቀመጠው የወያኔ  ቡድን ለአገር ህልውናና ልዑላዊነት የሚያደርገው ትግል እንደሆነ በማስመሰል የኢትዮጵያን ስም ከፍ በማድረግ ስሜት በመቀስቀስ አገር ወዳዱን ሕዝብ ከዃላው ለማሰለፍ ችሎ ነበር፤በዚያም ብዙዎቹ አገር ወዳዶች ዘምተው ደማቸውን አፍሰዋል፣ ሞተዋል፣ቆስለዋል። ለተደረገው ጦርነት ምክንያቱ የታወቀው ከጦርነቱ በዃላ ነበር፤የአሁኑም ጦርነት ውጤትና ምክንያቱ የሚታዬው ጦርነቱ ከቆመ በዃላ ይሆናል። ከወዲሁ የማይካደው ግን የአንዱን የጎሳ የበላይነት አሶግዶ የሌላውን ጎሳ የበላይነት የሚያረጋግጥ ለመሆኑ አያጠራጥርም።በግልጽ አባባል የትግራይ ጎሳን የበላይነት በጋላ ጎሳ የበላይነት የመተካት ግብግብ ነው።ድርጅታዊ ስያሜም ከተሰጠው ህወሃትን በኦህዴድ የመተካት የስልጣን ትንቅንቅ ነው።

  ለዓመታት በአገራችን ላይ ለደረሰው ውድቀት፣የመበታተን አደጋ፣የሕዝብ ጭፍጨፋና መፈናቀል፣ለመጠነ ብዙ ዘረፋ እጅ ለእጅ ተያይዘው የዘለቁ ወንጀለኞች እነዚህ አሁን በጦርነት ላይ የተሰለፉ መሆናቸው እዬታወቀ የሁሉም ወንጀል ተጠያቂ ህወሃት ብቻ አድርጎ  ማቅረብ ለሌላው ወንጀለኛ ቡድን የማምለጫ መንገድ መፍጠርና በሕግ እንዳይጠዬቅ ያደርጋል።ህወሃትና መሪዎቹ ተወገዱ ማለት ህወሃት የዘረጋው አገር አጥፊ የጎሰኞች ስርዓትና  በሱ ዙሪያ የተፈለፈሉት ዬዬጎሳው የክልል  አምባገነኖች አብረው ተደመሰሱ ማለት አይደለም። ሾፌር ተቀይሮለት የሚሽከረከር መኪና ማለት ነው።ተሳፋሪዎቹም ብሔር ብሔረሰብ ክልልና ሕዝቦች እያሉ የሚጮሁ ጎሰኞች ናቸው።ይህንን  መሪ ቃል በሕገመንግሥት ስም አስከብሮ የማስቀጠሉ አቋም በገሃድ እዬተነገረ ነው።በዚህ መመሪያ የሚካሄደው ጦርነት ውጤቱ ያው በገሌ መሆኑን ለማወቅ ነብይ መሆን አያሻም።የኦህዴድ መራሹ ብልጽግና በህወሃት መራሹ ኢሕአዴግ ላይ ድል ቢቀዳጅ የብልጽግና ምስለኔ  እንደሌሎቹ ክልሎች በትግራይ ክልል በተባለው ቦታ የማስቀመጥ እንጂ ስርዓት የመለወጥ ሂደት የሚከተል እንዳልሆነ በግልጽ ሰምተናል፤ምስለኔውንም አውቀናል።

 መቼም በጦር ሜዳ ላይ የአንዱ ማሸነፍና የሌላው መሸነፍ ፣የሚጠበቅ  ነውና ያ እስኪሆን ድረስ ግን ሁሉም በዬፊናው መፈራገጡ፣አልሞት ባይ ተጋዳይ መሆኑ  አይቀሬ ነው። ከዚያ ጋር በማያያዝ የማምለጫ መንገድ መፈለጉ የተለመደ ዘዴ ነው።ከዚያም ውስጥ የሽማግሌ ያለህ ማለቱና ለሰላማዊ ድርድር መጮህ አንዱ ነው።ተሸናፊው ብቻ ሳይሆን የተሸናፊው ተባባሪዎችና ተጠቃሚ የሆኑ ሁሉ ከሚከሰተው ውድቀት ለማምለጥ ይህንኑ  የድርድር መንገድ አጥብቀው ይጠይቃሉ።እዚህ ላይ የማይካደው ነገር ቢኖር ከጦርነት በዃላ የስምምነት ድርድር ማለትም ተሸናፊ መሸነፉን አውቆ የሚቀበልበት የጠረጴዛ ላይ ስምምነት  ሊካሄድ እንደሚችል በተደጋጋሚ በታሪክ ታይቷል።ለምሳሌም የጀርመን የናዚ መንግሥት በጦርነት ተሸንፎ በተወገደበት ጊዜ ሽንፈቱን አውቆ የመቀበል ውሳኔ በናዚ መሪዎች ፊርማ ተረጋግጧል።ያ በአገራት መካከል የተደረገ ጦርነትና ውል እንጂ በወንበዴዎች ቡድን የተካሄደ ግጭትና ስምምነት  አልነበረም።ይህ በአገራችን የሚካሄደው ጦርነት ግን ህወሃትንና ዓላማውን ለማሶገድ፣የተዘረጋውን የጎሰኞች ስርዓት ለማክሰም፣በአንድነትና በጸረ አንድነት ሃይሎች መካከል የተደረገ ትግል ሳይሆን ሰላምን ባደፈረሱና  ሕግን በጣሱ ጥቂት የህወሃት “ጁንታዎች” ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሎ ስለተሰዬመ ፣የሁለት አገራትም ግጭት ስላልሆነ የእርቅና ድርድር ሂደት ሊከተል አይገባውም።ሌባና ሽፍታ ወንጀለኛ በሕግ ፊት ቀርቦ ቅጣቱን ያገኛል እንጂ በእኩልነት ደረጃ ፊትለፊት ተቀምጦ አንድ መንግሥት ነኝ ከሚል ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ የመደራደር መብት አይኖረውም። ሊኖረውም አይገባም።

የውጭ ሃይሎችም በሽምግልና ስም ጣልቃ በመግባት ህወኅትን  ለማዳን የሚያደርጉትን እሩጫ ሕዝቡ ሊቃወም ይገባዋል።ለ30 ዓመታት በተለይም ላለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት ሕዝብ በማንነቱና በእምነቱ ሲጨፈጨፍ፣ሲፈናቀል ድምጻቸውን ያላሰሙ ሃይሎች በአሁኑ ወቅት የሰላም መልእክተኞች በመሆን ለህወሃት ደህንነት ሲጮሁ ጆሮ ሊሰጣቸው አይገባም።ለእውነት የቆሙ ከሆነ የችግሩን ምንጭ የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ አውግዘው ለኢትዮጵያ አገራዊ  አንድነትና ለሕዝቡ ሰላም መቆም በተገባቸው ነበር። 

    የማይካደው ነገር ይህ አሁን በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት በአገርና በሕዝብ ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል አይሆንም። ከሚያደርሰው የህይወትና የንብረት ውድመት ባሻገር በሁለቱም በኩል የተሰለፈው ወይም በስሙ የሚነገድበት ሕዝብ ለወደፊቱ ሆድና ጀርባ ሆኖ በጥላቻና በጥርጣሬ፣በቂምና ቅርሾ ስሜት  እንዲኖር ከማድረጉ ባለፈ ለሕዝቡ የተሻለ ኑሮ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።ያንን ስሜት ለማሶገድና ቁስሉ እንዲሽር ለማድረግ የሚወስደው ጊዜና ጥረት ቀላል አይሆንም።ይህንን የወደፊት ችግር ለማሶገድ የትግራይ ተወላጆች ለጎሳ ማንነታቸው አድልተው ህወሃትን ከመደገፍ ይልቅ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር ተባብሮ በስሙ ሲነግድበት ከኖረው ቡድን እራሱን እንዲነጥል፣በኢትዮጵያዊነቱ ለሃገሩ አንድነት በጋራ እንዲቆም የማድረግ ዘመቻ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።በሌላውም በኩል ያለው አስተዋይ ዜጋ በጭፍንና በጥላቻ ስሜት የሚነጉደውን ወገን  የትግራይን  ሕዝብና ወያኔን ለይቶ እንዲያይና የሕዝቡን  አብሮነት በሚያጠናክረው መንገድ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል።ለአደጋ የተጋለጡትንም ወገኖቹን ከለላና ድጋፍ ሊያበረክትላቸው ይገባል።

 

     ለዚህ ግጭት የዳረገውን፣ለወደፊቱም ተመሳሳይ አደጋ መክንያት ሊሆን የሚችለውን የጎሰኝነት ፖለቲካና አደረጃጀት ማሶገድ  ትልቁን ድርሻ ይይዛል።ክልል የተባለ የልዮነት ግምብ ፈራርሶ የኢትዮጵያ  ሕዝብ ለዘመናት በሰላምና በአንድነት የኖረበት የክፍላተ ሃገር አገራዊ አወቃቀር እንዲሰፍን ማድረግ አንዱ መፍትሔ ነው።የክፍላተ ሃገር መዋቀሩ ለአስተዳደር አመቺ ከመሆኑም በላይ በጎሳ ማንነት ያልተመሰረተ ስለሆነ  ዜጎችን ባይተዋርና እንግዳ፣ባለቤትና ጥገኛ አያደርግም።ሁሉም ዜጋ በፈለገበት ያገሪቱ መሬት ተዘዋውሮ በእኩልነት ለመኖር፣ለመሥራትና ሃብት ለማፍራት ያለውን መብቱን ያረጋግጣል።

    የኢትዮጵያ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት የሁሉም ዜጋ የጋራ ንብረቱ ስለሆነ አንዱ ብቻውን የሚያዝበትና የሚቆጣጠረው ሊሆን አይገባም።ክልል የሚለው የጎሳዎች የመሬት ቅርምት ሽኩቻ ላለንበት ቀውስ የዳረገን ስለሆነ የከባቢ መሬቶችንና የተፈጥሮ ሃብቶችን  በጎሳ ንብረትነት ከመመደብ ይልቅ ጥንት በነበረው የክፍላተ ሃገር ያስተዳደር መረብ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ  አይነተኛ መፍትሔ ነው።ወልቃይት እና እራያ የአማራ ናቸው ከማለት ይልቅ የጎንደርና የወሎ ክፍላተ ሃገር አስተዳደር ይዞታ ናቸው ብሎ ማለቱ፣የሌሎቹም ቦታዎች የክልል ማንነትና ይዞታነት ተወግዶ ወደ ጥንቱ አስተዳደራዊ አወቃቀር ቢመለሱ ከውድቀትና ከግጭት ያድናል።ለሁሉም ቦታ ጎሳን የሚያንጸባርቅ ስያሜ ከመስጠት በነባር ስሞች ቢጠሩ የቀውስና የግጭቱ አንዱ አካል ተወገደ ማለት ነው። 

    ይህ  ጦርነት የጥቅም ሽሚያ የቀሰቀሰው ሲሆን አንዱ ሌላውን አሸንፎ ቢወጣ ለሕዝቡና ለአገራችን የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብሎ መጠበቅ ጅልነት ነው።ውጤቱ ሲሰላ አንዱን ጎሰኛ አምባገነን በሌላ ጎሰኛ አምባገነን መለወጥ ነው።በአገራችን የወታደራዊና የሲቪል የአስተዳደር መዋቅሮች  የስልጣን  ሰንሰለት ውስጥ የተሰገሰጉትን ማዬቱ ለዚያ ማስረጃ ነው።በስልጣን እርከን ላይ መሰግሰጉ ብቻ ሳይሆን ገና ከጅምሩ  በስልጣኑ ወንበር ላይ ሳይረጋጉ የሚካሄደው የገንዘብ  ዘረፋ፣ የመሬት ቅርምቱ ብሎም የተረኝነት ስሜትና ማን አለብኝነት ለዚያ ማስረጃ ነው።ይህንን እውነታ ነው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለአገርና ሕዝብ ጥቅም የሚደረግ ተጋድሎ ወይም ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ተብሎ  በጥቅምና በጎሳ አመለካከት የተለከፉ የሚነዙት የወሬ ጋጋታ።ለአንዳንዶቹም የውሸት ወሬ መቸርቸር ትልቁ የገቢ ምንጫቸው ሸቀጥ ሆኗል።እውነትና ጀንበር እያደር ይወጣል እንዲሉ፣የጦርነቱ ምክንያትና  ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከጦርነቱ ማግስት የምናዬው ይሆናል።

       የወያኔ ቡድን በአገሪቱ ለተፈጸመው ሁለንተናዊ ወንጀል ተጠያቂነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም፤ እንዲደመሰስም  ከጥቅም አጋር ከሆኑት ከጥቂቶቹ  በስተቀር በስሙ የሚነገድበትም ብዙሃኑ  የትግራይ ሕዝብ  ሳይቀር ፍላጎቱ ነው።በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ፣የጎሰኝነት ትርክት ቀፍድዶ ስለያዘውና በሌላው ጎሳ ላይ እምነት በማጣቱና የእልህና ቅርሾ ሰለባ እሆናለሁ በሚል ስጋት የተነሳ የህወሃትና መሪዎቹ ዋሻ ለመሆን የተገደደ ይመስላል።ሥራ አጡ ወጣትም በመወናበድና ከጊዜያዊ ችግሩ የሚወጣ መስሎት ለጥቂት አረመኔዎች ጭዳ ለመሆን የተሰለፈ ቢሆንም ያላማ ጽናት ኖሮት እስከመጨረሻው ይዋጋል ብሎ መገመት ያቅታል።እውነቱ ሲገለጽለት አሁንም በአንዳንድ የጦር ሜዳ እንደታዬው መሳሪያውን እያስረከበ እጅ መስጠቱ የዚያ አመላካች ነው።እስከመጨረሻው የሚዋደቁት ቁጥራቸው መጠነኛ ነው። በጦርነቱ ሳቢያ ፍርሃት ያደረበት በድንበር  አካባቢ ነዋሪ የሆነው አብዛኛው ሴትና ሕጻናት እግሬ አውጭኝ ብሎ በጎረቤት አገር በተለይም ወደ ሱዳን እዬሸሸ ነው። ከሱዳን ይልቅ ወደ ወገኑ ፣ወደ ሌላው የአገሩ  መሬትና ሕዝብ ቢሰደድ ይሻለው ነበር፤ግን የተነገረው “የእኛና የነሱ” “የይበለሀል” ትርክት ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ይልቅ ሱዳኖችን እንዲያምን አድርጎታል። ይህ ሕዝብ ዋስትና የሚሰጠው አስተማማኝ ሃይል ይፈልጋል።ከትግራይ ውጭ ያለው  ሕዝብ ይህንን በሁለት አጣብቂኝ ውስጥ ያለ ወገኑን ስንዴና እንክርዳዱን በመለዬት ሊታደገው ይገባል።ከሃያ ዓመት በፊት በንጹሃን ኤርትራውያን ላይ የተፈጸመው ስህተት እንዳይደገም መጠንቀቅ ያሻል።ብዙ በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ኤርትራውያኖች የጥቃት ሰለባ እንደሆኑ ማሰብና አሁንም በትግራይ ወገኖቻችን ላይ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጸም መጠንቀቅ ተገቢ ነው።ንብረት ለመዝረፍ ቋምጦ የሚጠባበቀውን ሌባ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ማድረግ የሕዝቡ ሃላፊነት ነው።የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል ነውና ሕዝብ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን ከሁሉም ሕግ አክባሪና ሰብአዊ ዜጋ  ይጠበቃል።

    አሁን ድምጹን አጥፍቶ የተቀመጠውና ደጋፊ መስሎ የሚታዬው ብዙሃኑ የትግራይ ህዝብ የማታ ማታ ግን በስሙ ሲነግዱበት የኖሩትን ጨካኞችና ሌቦች አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ወይም እራሱ እርምጃ ወስዶ እንደሚደመስሳቸው ጥርጥር አይኖርም፤ የአምባገነኖችና አጭበርባሪዎች መጨረሻ የሚቋጨው ይደግፈናል በሚሉት ሕዝብ እንደሆነ በታሪክ ተደጋግሞ ታይቷል።የኛዎቹም ከዚህ አያመልጡም።     

   ሌላው ክስተት የጦርነቱ ዕድሜ ከረዘመ ለውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት አመቺ ዕድል ይፈጥራል።ያ ከሆነ ደግሞ በአገራችን ብቻ ሳይሆን ቀጠናው በሙሉ ለሚያስፈራው  የረጅም ጊዜ የጦርነት አደጋ ይጋለጣል።ስለሆነም ተወደደም ተጠላም አደጋውን ለመቀልበስ፣የጦርነቱንም ዕድሜ ለማሳጠር በወያኔና ግብረአበሮቹ ላይ የተባበረ ክንድ ማሳረፍ የግድ ይላል።ይህ ትግል የአንድ ጎሳ የበላይነትን ለሚያረጋግጥ ድል ሳይሆን በቀጣይነት የጎሳ ፖለቲካንና ያለውን የመተካካት ሂደት የሚያመክን ሊሆን ይገባዋል።የመጨረሻው አስተማማኝ መቋጫ የሚሆነው ያለውን የጎሳ ፖለቲካና ክልላዊ አወቃቀር እንዲሁም ጸረ አንድነትና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ የተገንጣዮችን ሰነድ በሕዝባዊና አገራዊ ሕገመንግሥት ለውጦ  ኢትዮጵያዊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማስፈን ዓላማ በተግባር ሲረጋገጥ ብቻ ነው።ያ ካልሆነ ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ ይሆንና ከድጡ ወደማጡ የባለተረኞች አምባገነናዊ ስርዓት መዳፍ ስር ለዘለቄታው መውደቅ ይሆናል።በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ቢያበቃ ግጭቱ  ወደሌላው አካባቢ የማይዛመትበት ዋስትና የለም።ሁሉም ጎሳ የራሱን የበላይነት ለማስፈንና ለመስፋፋት ወይም የያዘውን ላለመነጠቅ ሲል የገነባው የጦር ሃይል ለሰልፍና ለጨዋታ አይደለም።የክልል ማስፋቱ፣የንብረት ዘረፋው፣የተፈጥሮ ሃብት መቀራመቱ የሚያመጣው ጣጣ ከወዲሁ እዬታዬ ነው።የፌዴራል መከላከያውም ሆነ የጸጥታ አስከባሪው፣የፖሊስ ሃይል  አወቃቀር ከዬጎሳው የተውጣጣ በመሆኑ የተንሰራፋው የጎሳ ስርዓት ካልተወገደ በስተቀር ጎሳ ለይቶ እርስ በርሱ እንደሚፋጅ በትግራይ ውስጥ በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ታይቷል።ያ እንዳይደገም ብልሃት ሊፈለግበት ይገባል።ብልሃቱም ጎሰኝነትን እስከነአካቴው አንቅሮ መትፋትና ያለውን ስርዓት ከነዝባዝንኬው ማሶገድ ነው።

   በጦርነት ሰበብ ከክልሉ የተነቃነቀው ልዩ ሃይል ወደ ቦታው ለመመለሱ ማረጋገጫ የለም፤ሰላምና መረጋጋት ለማስከበር በሚል ሽፋን የራሱን ጎሳ ተጽእኖ ለማስከበር በተሰማራበት ቦታ ቋሚ ሆኖ እንደሚቀር የሚያመላክቱ ስጋቶች አሉ።

   ጎሰኝነት ጸረ አንድነትና ጸረ ኢትዮጵያዊነት፣ከዚያም በላይ ኢሰብአዊነት ነው።ስለሆነም እስኪወገድ ድረስ በጽናት መታገል ያሻል።በአንድነት ጎራ  ዙሪያ ያለው ሃይል እርስ በርሱ እየተጠላለፈ ተከፋፍሎና ተዳክሞ፣በፍርሃት ወይም በሽርፍራፊ ጥቅም ተሸብቦ ከመቀመጥ ይልቅ የጦርነቱን ሙሉ ገጽ በመመርመር ሕዝቡን በማንቃት ልዩነቱን ወደ ጎን ትቶ በህብረት ሊቆምና  የጎሳ ማንነትን መሰረት ያደረገው ስርዓት ተወግዶ  የሕዝቡን መብትና ያገሩን ልዑላዊነትና አንድነት ለሚያስከብረው ስርዓት ሊታገል ይገባል።

 የጎሰኞች ስርዓት ይደምሰስ!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ብርታት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!!

አገሬ አዲስ

No comments: