Friday, November 27, 2020

ጦርነቱና ከጦርነቱ ማግስት አገሬ አዲስ ህዳር 11ቀን 2013ዓም(20-11-2020) (Ethiopian Semay)

 

ጦርነቱና  ከጦርነቱ ማግስት

አገሬ አዲስ

ህዳር 11ቀን 2013ዓም(20-11-2020)

(Ethiopian Semay)

ጦርነት ጎጂና  አውዳሚነቱ ቢታወቅም ከገቡበት በዃላ ይዞት የሚወጣው ውጤት የሚፈለግ ወይም የማይፈለግ ሊሆን ይችላል። ለጦርነት ምክንያት ብዙ ቢሆንም በሁለት መልክ ይመደባል። አንደኛው ለአገር ልዑላዊነትና ነጻነት፣ ለሕዝብ ክብርና መብት የሚደረግ  ፍትሃዊ ወይም ጀስት ዋር(Just War) የሚሉት ሲሆን ሌላው በውጭ ወራሪዎች የሚካሄድ ጦርነትና  በአገር ውስጥ ለአምባገነኖች ጥቅም ሲባል ሕዝብን በመከፋፈል አጋርና ጠላት አድርጎ ለማጫረስ የሚቀሰቀስ ኢፍትሃዊ ጦርነት ወይም አንጀስት ዋር(Unjust war) ነው።

አሁን ባገራችን ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት የሁለተኛውን የጦርነት ምክንያት የተከተለ መሆኑን የሚክድና የማያውቅ የለም።የታሪክ አምድን ወደዃላ መለስ ብለን ብናገላብጠው ከሃያ ዓመት በፊት በሻቢያና በወያኔ መካከል የተቀሰቀሰውና ለብዙ ዜጎች ህይወት መጥፋትና ለአገር ንብረት መውደም ምክንያት ለሆነው ጦርነት መንስኤው የሁለት ጸረ ኢትዮጵያ ተገንጣይና አስገንጣይ ሃይሎች የጥቅም ሽኩቻ የቀሰቀሰው ነበር።የአሁኑንም ጦርነት ከዚያ የሚለዬው ምክንያት የለም።የሁለት ጸረ ኢትዮጵያ የጎሰኛ ቡድኖች ፣የህወሃትና የኦህዴድ የጥቅምና የስልጣን ሽኩቻ የፈጠረው ጦርነት ነው።

ከሻብያም ጋር በተደረገውም  ጦርነት ስልጣን ላይ የተቀመጠው የወያኔ  ቡድን ለአገር ህልውናና ልዑላዊነት የሚያደርገው ትግል እንደሆነ በማስመሰል የኢትዮጵያን ስም ከፍ በማድረግ ስሜት በመቀስቀስ አገር ወዳዱን ሕዝብ ከዃላው ለማሰለፍ ችሎ ነበር፤በዚያም ብዙዎቹ አገር ወዳዶች ዘምተው ደማቸውን አፍሰዋል፣ ሞተዋል፣ቆስለዋል። ለተደረገው ጦርነት ምክንያቱ የታወቀው ከጦርነቱ በዃላ ነበር፤የአሁኑም ጦርነት ውጤትና ምክንያቱ የሚታዬው ጦርነቱ ከቆመ በዃላ ይሆናል። ከወዲሁ የማይካደው ግን የአንዱን የጎሳ የበላይነት አሶግዶ የሌላውን ጎሳ የበላይነት የሚያረጋግጥ ለመሆኑ አያጠራጥርም።በግልጽ አባባል የትግራይ ጎሳን የበላይነት በጋላ ጎሳ የበላይነት የመተካት ግብግብ ነው።ድርጅታዊ ስያሜም ከተሰጠው ህወሃትን በኦህዴድ የመተካት የስልጣን ትንቅንቅ ነው።

  ለዓመታት በአገራችን ላይ ለደረሰው ውድቀት፣የመበታተን አደጋ፣የሕዝብ ጭፍጨፋና መፈናቀል፣ለመጠነ ብዙ ዘረፋ እጅ ለእጅ ተያይዘው የዘለቁ ወንጀለኞች እነዚህ አሁን በጦርነት ላይ የተሰለፉ መሆናቸው እዬታወቀ የሁሉም ወንጀል ተጠያቂ ህወሃት ብቻ አድርጎ  ማቅረብ ለሌላው ወንጀለኛ ቡድን የማምለጫ መንገድ መፍጠርና በሕግ እንዳይጠዬቅ ያደርጋል።ህወሃትና መሪዎቹ ተወገዱ ማለት ህወሃት የዘረጋው አገር አጥፊ የጎሰኞች ስርዓትና  በሱ ዙሪያ የተፈለፈሉት ዬዬጎሳው የክልል  አምባገነኖች አብረው ተደመሰሱ ማለት አይደለም። ሾፌር ተቀይሮለት የሚሽከረከር መኪና ማለት ነው።ተሳፋሪዎቹም ብሔር ብሔረሰብ ክልልና ሕዝቦች እያሉ የሚጮሁ ጎሰኞች ናቸው።ይህንን  መሪ ቃል በሕገመንግሥት ስም አስከብሮ የማስቀጠሉ አቋም በገሃድ እዬተነገረ ነው።በዚህ መመሪያ የሚካሄደው ጦርነት ውጤቱ ያው በገሌ መሆኑን ለማወቅ ነብይ መሆን አያሻም።የኦህዴድ መራሹ ብልጽግና በህወሃት መራሹ ኢሕአዴግ ላይ ድል ቢቀዳጅ የብልጽግና ምስለኔ  እንደሌሎቹ ክልሎች በትግራይ ክልል በተባለው ቦታ የማስቀመጥ እንጂ ስርዓት የመለወጥ ሂደት የሚከተል እንዳልሆነ በግልጽ ሰምተናል፤ምስለኔውንም አውቀናል።

 መቼም በጦር ሜዳ ላይ የአንዱ ማሸነፍና የሌላው መሸነፍ ፣የሚጠበቅ  ነውና ያ እስኪሆን ድረስ ግን ሁሉም በዬፊናው መፈራገጡ፣አልሞት ባይ ተጋዳይ መሆኑ  አይቀሬ ነው። ከዚያ ጋር በማያያዝ የማምለጫ መንገድ መፈለጉ የተለመደ ዘዴ ነው።ከዚያም ውስጥ የሽማግሌ ያለህ ማለቱና ለሰላማዊ ድርድር መጮህ አንዱ ነው።ተሸናፊው ብቻ ሳይሆን የተሸናፊው ተባባሪዎችና ተጠቃሚ የሆኑ ሁሉ ከሚከሰተው ውድቀት ለማምለጥ ይህንኑ  የድርድር መንገድ አጥብቀው ይጠይቃሉ።እዚህ ላይ የማይካደው ነገር ቢኖር ከጦርነት በዃላ የስምምነት ድርድር ማለትም ተሸናፊ መሸነፉን አውቆ የሚቀበልበት የጠረጴዛ ላይ ስምምነት  ሊካሄድ እንደሚችል በተደጋጋሚ በታሪክ ታይቷል።ለምሳሌም የጀርመን የናዚ መንግሥት በጦርነት ተሸንፎ በተወገደበት ጊዜ ሽንፈቱን አውቆ የመቀበል ውሳኔ በናዚ መሪዎች ፊርማ ተረጋግጧል።ያ በአገራት መካከል የተደረገ ጦርነትና ውል እንጂ በወንበዴዎች ቡድን የተካሄደ ግጭትና ስምምነት  አልነበረም።ይህ በአገራችን የሚካሄደው ጦርነት ግን ህወሃትንና ዓላማውን ለማሶገድ፣የተዘረጋውን የጎሰኞች ስርዓት ለማክሰም፣በአንድነትና በጸረ አንድነት ሃይሎች መካከል የተደረገ ትግል ሳይሆን ሰላምን ባደፈረሱና  ሕግን በጣሱ ጥቂት የህወሃት “ጁንታዎች” ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሎ ስለተሰዬመ ፣የሁለት አገራትም ግጭት ስላልሆነ የእርቅና ድርድር ሂደት ሊከተል አይገባውም።ሌባና ሽፍታ ወንጀለኛ በሕግ ፊት ቀርቦ ቅጣቱን ያገኛል እንጂ በእኩልነት ደረጃ ፊትለፊት ተቀምጦ አንድ መንግሥት ነኝ ከሚል ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ የመደራደር መብት አይኖረውም። ሊኖረውም አይገባም።

የውጭ ሃይሎችም በሽምግልና ስም ጣልቃ በመግባት ህወኅትን  ለማዳን የሚያደርጉትን እሩጫ ሕዝቡ ሊቃወም ይገባዋል።ለ30 ዓመታት በተለይም ላለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት ሕዝብ በማንነቱና በእምነቱ ሲጨፈጨፍ፣ሲፈናቀል ድምጻቸውን ያላሰሙ ሃይሎች በአሁኑ ወቅት የሰላም መልእክተኞች በመሆን ለህወሃት ደህንነት ሲጮሁ ጆሮ ሊሰጣቸው አይገባም።ለእውነት የቆሙ ከሆነ የችግሩን ምንጭ የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ አውግዘው ለኢትዮጵያ አገራዊ  አንድነትና ለሕዝቡ ሰላም መቆም በተገባቸው ነበር። 

    የማይካደው ነገር ይህ አሁን በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት በአገርና በሕዝብ ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል አይሆንም። ከሚያደርሰው የህይወትና የንብረት ውድመት ባሻገር በሁለቱም በኩል የተሰለፈው ወይም በስሙ የሚነገድበት ሕዝብ ለወደፊቱ ሆድና ጀርባ ሆኖ በጥላቻና በጥርጣሬ፣በቂምና ቅርሾ ስሜት  እንዲኖር ከማድረጉ ባለፈ ለሕዝቡ የተሻለ ኑሮ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።ያንን ስሜት ለማሶገድና ቁስሉ እንዲሽር ለማድረግ የሚወስደው ጊዜና ጥረት ቀላል አይሆንም።ይህንን የወደፊት ችግር ለማሶገድ የትግራይ ተወላጆች ለጎሳ ማንነታቸው አድልተው ህወሃትን ከመደገፍ ይልቅ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር ተባብሮ በስሙ ሲነግድበት ከኖረው ቡድን እራሱን እንዲነጥል፣በኢትዮጵያዊነቱ ለሃገሩ አንድነት በጋራ እንዲቆም የማድረግ ዘመቻ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።በሌላውም በኩል ያለው አስተዋይ ዜጋ በጭፍንና በጥላቻ ስሜት የሚነጉደውን ወገን  የትግራይን  ሕዝብና ወያኔን ለይቶ እንዲያይና የሕዝቡን  አብሮነት በሚያጠናክረው መንገድ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል።ለአደጋ የተጋለጡትንም ወገኖቹን ከለላና ድጋፍ ሊያበረክትላቸው ይገባል።

 

     ለዚህ ግጭት የዳረገውን፣ለወደፊቱም ተመሳሳይ አደጋ መክንያት ሊሆን የሚችለውን የጎሰኝነት ፖለቲካና አደረጃጀት ማሶገድ  ትልቁን ድርሻ ይይዛል።ክልል የተባለ የልዮነት ግምብ ፈራርሶ የኢትዮጵያ  ሕዝብ ለዘመናት በሰላምና በአንድነት የኖረበት የክፍላተ ሃገር አገራዊ አወቃቀር እንዲሰፍን ማድረግ አንዱ መፍትሔ ነው።የክፍላተ ሃገር መዋቀሩ ለአስተዳደር አመቺ ከመሆኑም በላይ በጎሳ ማንነት ያልተመሰረተ ስለሆነ  ዜጎችን ባይተዋርና እንግዳ፣ባለቤትና ጥገኛ አያደርግም።ሁሉም ዜጋ በፈለገበት ያገሪቱ መሬት ተዘዋውሮ በእኩልነት ለመኖር፣ለመሥራትና ሃብት ለማፍራት ያለውን መብቱን ያረጋግጣል።

    የኢትዮጵያ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት የሁሉም ዜጋ የጋራ ንብረቱ ስለሆነ አንዱ ብቻውን የሚያዝበትና የሚቆጣጠረው ሊሆን አይገባም።ክልል የሚለው የጎሳዎች የመሬት ቅርምት ሽኩቻ ላለንበት ቀውስ የዳረገን ስለሆነ የከባቢ መሬቶችንና የተፈጥሮ ሃብቶችን  በጎሳ ንብረትነት ከመመደብ ይልቅ ጥንት በነበረው የክፍላተ ሃገር ያስተዳደር መረብ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ  አይነተኛ መፍትሔ ነው።ወልቃይት እና እራያ የአማራ ናቸው ከማለት ይልቅ የጎንደርና የወሎ ክፍላተ ሃገር አስተዳደር ይዞታ ናቸው ብሎ ማለቱ፣የሌሎቹም ቦታዎች የክልል ማንነትና ይዞታነት ተወግዶ ወደ ጥንቱ አስተዳደራዊ አወቃቀር ቢመለሱ ከውድቀትና ከግጭት ያድናል።ለሁሉም ቦታ ጎሳን የሚያንጸባርቅ ስያሜ ከመስጠት በነባር ስሞች ቢጠሩ የቀውስና የግጭቱ አንዱ አካል ተወገደ ማለት ነው። 

    ይህ  ጦርነት የጥቅም ሽሚያ የቀሰቀሰው ሲሆን አንዱ ሌላውን አሸንፎ ቢወጣ ለሕዝቡና ለአገራችን የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብሎ መጠበቅ ጅልነት ነው።ውጤቱ ሲሰላ አንዱን ጎሰኛ አምባገነን በሌላ ጎሰኛ አምባገነን መለወጥ ነው።በአገራችን የወታደራዊና የሲቪል የአስተዳደር መዋቅሮች  የስልጣን  ሰንሰለት ውስጥ የተሰገሰጉትን ማዬቱ ለዚያ ማስረጃ ነው።በስልጣን እርከን ላይ መሰግሰጉ ብቻ ሳይሆን ገና ከጅምሩ  በስልጣኑ ወንበር ላይ ሳይረጋጉ የሚካሄደው የገንዘብ  ዘረፋ፣ የመሬት ቅርምቱ ብሎም የተረኝነት ስሜትና ማን አለብኝነት ለዚያ ማስረጃ ነው።ይህንን እውነታ ነው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለአገርና ሕዝብ ጥቅም የሚደረግ ተጋድሎ ወይም ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ተብሎ  በጥቅምና በጎሳ አመለካከት የተለከፉ የሚነዙት የወሬ ጋጋታ።ለአንዳንዶቹም የውሸት ወሬ መቸርቸር ትልቁ የገቢ ምንጫቸው ሸቀጥ ሆኗል።እውነትና ጀንበር እያደር ይወጣል እንዲሉ፣የጦርነቱ ምክንያትና  ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከጦርነቱ ማግስት የምናዬው ይሆናል።

       የወያኔ ቡድን በአገሪቱ ለተፈጸመው ሁለንተናዊ ወንጀል ተጠያቂነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም፤ እንዲደመሰስም  ከጥቅም አጋር ከሆኑት ከጥቂቶቹ  በስተቀር በስሙ የሚነገድበትም ብዙሃኑ  የትግራይ ሕዝብ  ሳይቀር ፍላጎቱ ነው።በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ፣የጎሰኝነት ትርክት ቀፍድዶ ስለያዘውና በሌላው ጎሳ ላይ እምነት በማጣቱና የእልህና ቅርሾ ሰለባ እሆናለሁ በሚል ስጋት የተነሳ የህወሃትና መሪዎቹ ዋሻ ለመሆን የተገደደ ይመስላል።ሥራ አጡ ወጣትም በመወናበድና ከጊዜያዊ ችግሩ የሚወጣ መስሎት ለጥቂት አረመኔዎች ጭዳ ለመሆን የተሰለፈ ቢሆንም ያላማ ጽናት ኖሮት እስከመጨረሻው ይዋጋል ብሎ መገመት ያቅታል።እውነቱ ሲገለጽለት አሁንም በአንዳንድ የጦር ሜዳ እንደታዬው መሳሪያውን እያስረከበ እጅ መስጠቱ የዚያ አመላካች ነው።እስከመጨረሻው የሚዋደቁት ቁጥራቸው መጠነኛ ነው። በጦርነቱ ሳቢያ ፍርሃት ያደረበት በድንበር  አካባቢ ነዋሪ የሆነው አብዛኛው ሴትና ሕጻናት እግሬ አውጭኝ ብሎ በጎረቤት አገር በተለይም ወደ ሱዳን እዬሸሸ ነው። ከሱዳን ይልቅ ወደ ወገኑ ፣ወደ ሌላው የአገሩ  መሬትና ሕዝብ ቢሰደድ ይሻለው ነበር፤ግን የተነገረው “የእኛና የነሱ” “የይበለሀል” ትርክት ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ይልቅ ሱዳኖችን እንዲያምን አድርጎታል። ይህ ሕዝብ ዋስትና የሚሰጠው አስተማማኝ ሃይል ይፈልጋል።ከትግራይ ውጭ ያለው  ሕዝብ ይህንን በሁለት አጣብቂኝ ውስጥ ያለ ወገኑን ስንዴና እንክርዳዱን በመለዬት ሊታደገው ይገባል።ከሃያ ዓመት በፊት በንጹሃን ኤርትራውያን ላይ የተፈጸመው ስህተት እንዳይደገም መጠንቀቅ ያሻል።ብዙ በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ኤርትራውያኖች የጥቃት ሰለባ እንደሆኑ ማሰብና አሁንም በትግራይ ወገኖቻችን ላይ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጸም መጠንቀቅ ተገቢ ነው።ንብረት ለመዝረፍ ቋምጦ የሚጠባበቀውን ሌባ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ማድረግ የሕዝቡ ሃላፊነት ነው።የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል ነውና ሕዝብ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን ከሁሉም ሕግ አክባሪና ሰብአዊ ዜጋ  ይጠበቃል።

    አሁን ድምጹን አጥፍቶ የተቀመጠውና ደጋፊ መስሎ የሚታዬው ብዙሃኑ የትግራይ ህዝብ የማታ ማታ ግን በስሙ ሲነግዱበት የኖሩትን ጨካኞችና ሌቦች አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ወይም እራሱ እርምጃ ወስዶ እንደሚደመስሳቸው ጥርጥር አይኖርም፤ የአምባገነኖችና አጭበርባሪዎች መጨረሻ የሚቋጨው ይደግፈናል በሚሉት ሕዝብ እንደሆነ በታሪክ ተደጋግሞ ታይቷል።የኛዎቹም ከዚህ አያመልጡም።     

   ሌላው ክስተት የጦርነቱ ዕድሜ ከረዘመ ለውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት አመቺ ዕድል ይፈጥራል።ያ ከሆነ ደግሞ በአገራችን ብቻ ሳይሆን ቀጠናው በሙሉ ለሚያስፈራው  የረጅም ጊዜ የጦርነት አደጋ ይጋለጣል።ስለሆነም ተወደደም ተጠላም አደጋውን ለመቀልበስ፣የጦርነቱንም ዕድሜ ለማሳጠር በወያኔና ግብረአበሮቹ ላይ የተባበረ ክንድ ማሳረፍ የግድ ይላል።ይህ ትግል የአንድ ጎሳ የበላይነትን ለሚያረጋግጥ ድል ሳይሆን በቀጣይነት የጎሳ ፖለቲካንና ያለውን የመተካካት ሂደት የሚያመክን ሊሆን ይገባዋል።የመጨረሻው አስተማማኝ መቋጫ የሚሆነው ያለውን የጎሳ ፖለቲካና ክልላዊ አወቃቀር እንዲሁም ጸረ አንድነትና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ የተገንጣዮችን ሰነድ በሕዝባዊና አገራዊ ሕገመንግሥት ለውጦ  ኢትዮጵያዊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማስፈን ዓላማ በተግባር ሲረጋገጥ ብቻ ነው።ያ ካልሆነ ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ ይሆንና ከድጡ ወደማጡ የባለተረኞች አምባገነናዊ ስርዓት መዳፍ ስር ለዘለቄታው መውደቅ ይሆናል።በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ቢያበቃ ግጭቱ  ወደሌላው አካባቢ የማይዛመትበት ዋስትና የለም።ሁሉም ጎሳ የራሱን የበላይነት ለማስፈንና ለመስፋፋት ወይም የያዘውን ላለመነጠቅ ሲል የገነባው የጦር ሃይል ለሰልፍና ለጨዋታ አይደለም።የክልል ማስፋቱ፣የንብረት ዘረፋው፣የተፈጥሮ ሃብት መቀራመቱ የሚያመጣው ጣጣ ከወዲሁ እዬታዬ ነው።የፌዴራል መከላከያውም ሆነ የጸጥታ አስከባሪው፣የፖሊስ ሃይል  አወቃቀር ከዬጎሳው የተውጣጣ በመሆኑ የተንሰራፋው የጎሳ ስርዓት ካልተወገደ በስተቀር ጎሳ ለይቶ እርስ በርሱ እንደሚፋጅ በትግራይ ውስጥ በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ታይቷል።ያ እንዳይደገም ብልሃት ሊፈለግበት ይገባል።ብልሃቱም ጎሰኝነትን እስከነአካቴው አንቅሮ መትፋትና ያለውን ስርዓት ከነዝባዝንኬው ማሶገድ ነው።

   በጦርነት ሰበብ ከክልሉ የተነቃነቀው ልዩ ሃይል ወደ ቦታው ለመመለሱ ማረጋገጫ የለም፤ሰላምና መረጋጋት ለማስከበር በሚል ሽፋን የራሱን ጎሳ ተጽእኖ ለማስከበር በተሰማራበት ቦታ ቋሚ ሆኖ እንደሚቀር የሚያመላክቱ ስጋቶች አሉ።

   ጎሰኝነት ጸረ አንድነትና ጸረ ኢትዮጵያዊነት፣ከዚያም በላይ ኢሰብአዊነት ነው።ስለሆነም እስኪወገድ ድረስ በጽናት መታገል ያሻል።በአንድነት ጎራ  ዙሪያ ያለው ሃይል እርስ በርሱ እየተጠላለፈ ተከፋፍሎና ተዳክሞ፣በፍርሃት ወይም በሽርፍራፊ ጥቅም ተሸብቦ ከመቀመጥ ይልቅ የጦርነቱን ሙሉ ገጽ በመመርመር ሕዝቡን በማንቃት ልዩነቱን ወደ ጎን ትቶ በህብረት ሊቆምና  የጎሳ ማንነትን መሰረት ያደረገው ስርዓት ተወግዶ  የሕዝቡን መብትና ያገሩን ልዑላዊነትና አንድነት ለሚያስከብረው ስርዓት ሊታገል ይገባል።

 የጎሰኞች ስርዓት ይደምሰስ!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ብርታት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!!

አገሬ አዲስ

Monday, November 9, 2020

ጦርነቱን አስመልክቶ የተለያዩ ንዑስ ርዕሶች እንመልከት፡ ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ኢትዮ ሰማይ) 11/10/2020

 

 

 

ጦርነቱን አስመልክቶ የተለያዩ ንዑስ ርዕሶች እንመልከት፡

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ኢትዮ ሰማይ) 11/10/2020

1ኛ-የውጭ አገር ጣልቃ ገብነት

2ኛ፦በሃይል ወደ ትግራይ የተጠቃለሉ መሬቶችን ወደ ነበሩበት ስለ መመለስ

1ኛ- በማስታረቅ ሰበብ የውጭ አገር ጣልቃ ገብነትን በሚመለከት

29 አመት የአማራ ሕዝብ የዘር ጭፍጨፋና የክርትያኖች መታረድ ያላሳሰባቸው የውጭ አገር የዜና ማሰራጫዎች፤ የውጭ አገር ዲፕሎማቶችና የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ትግራይን ለመገንጠል እንዲያመቸው “ከመከላከያ የጦር መሳሪያ ክምችት” ላይ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ለመቀማት እሳት የለኮሰን ቡድን ለማስቆም እየተደረገ ባለው ፍልሚያ ውስጥ “የኮለኒያሊስቶች ምላሳችውን” መሰንዘር ጀምረዋል። ሩዋንዳን የሚያክል የዘር ፍጅት የሚያስንቅ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ስላለው ወንጀል አንድም ነገር ሳይሉ ዛሬ ደርሰው የሰላም መልዕክተኞች መስለው ስለ ጦርነቱ ማስቆም መለፍልፍ ለቀጠናችን አስበው እንዳልሆነ አንባቢዎቼ እውቁት።


ስለዚህ አያገባችሁም በልዋቸው። ይልቁንስ እውነት የሕዝብ ደህንነት የሚያሳስባቸው ከሆነ ‘የዘር ጭፍጨፋ ባደረጉት የወያኔ መሪዎች እና አገር እንመራለን ብለው ያለ ሕዝብ ይሁንታ  ሥልጣን የተቆጣጠሩትን የብልጽግና/(ኦሆዴድ) መሪዎች ለአማራና ለክርስትያኖች መታረድና መፈናቀል ተጠያቂዎቹ “ሽመልስ አብዲሳ፤ አብይ አሕመድና መሰሎቹ” ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲጠየቁ ኮለኒያሊስቶቹ የሚረዱበት መንገድ ካለ ይህንን ጥያቄ አጸፋዊ መልስ እንዲሰሙት ማድረግ ያስፈልጋል።


2ኛ፦በሃይል ወደ ትግራይ የተጠቃለሉ መሬቶችን ወደ ነበሩበት ስለ መመለስ በሚመለከት፤

ይህ ርዕስ ባለፈው ጠቅሸዋለሁ። በጉለብት ተነጥቀው ወደ ትግራይ ትግርኚ ምስረታ የተጠቃለሉት የጎንደርና የወሎ ለም መሬቶችና ኗሪዎች በዚህ ጦርነት በቁጥጥር እየዋሉ ያሉ እነዚህ ወረዳዎችና ከተሞች በማንኛውም ምክንያትና የሰላም ዕርቅ ድርደር “ሰበብ” አብይ አሕመድ መልሶ ለትግራይ እንዳይመልሳቸው ካሁኑኑ በግልጽ አማርኛ እንዲነገረው ያስፈልጋል።

ወያኔ ቅርቃር ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ቢሆንም አብይ አሕመድ አስተማማኝ መሪ ስላልሆነ መጨረሻም ባድሜ ላይ መለስ ዜናዊ እንዳደረገው የካሃዲ ውሳኔ ዛሬም በአጋጣሚ በሃይል ወደ ትግራይ የተወሰዱ የወልቃይትና የወሎ መሬቶችና እዛው ውስጥ በአማራነታቸው ምክንያት “የቀን ሙያተኞች ሆነን ኩንታል እንኳ ተሸክመን ስሙኒ ላለማግኘት የነገድ ልዩነት ይደረገብን ነበር” ብለው የዳንሻ ከተማ ትንናት በቁጥጥር ሲውል ኗሪዎቹ የሰጡት ቃለ መጠይቅ መሰረት ግፍ ስለተፈጸመባቸው በእነዚህ ኗሪዎች ላይ አብይ አሕመድ ስሜት ስለማይሰጠው መልሶ ለትግሬዎች በመመለስ ክህደት ይፈጽማል የሚል እምነት አለኝ። ለዚህ ነው ጦርነቱ ሲጀምር ታስታውሱ እንደሆነ በጻፍኩት ጽሑፍ የአማራ ሲቪል ሚሊሺያዎች ወደ ጦርነቱ ቅድሚ እንዳትሰለፉ ወደ እናንተ ከመጡባችሁ ብቻ እራሳችሁን ለመከለካል ተዋጉ ካልሆነ “የወታደሩ ስራ ለወታደሩ ስጡት” ምክንያቱም በሗላ ደማችሁ ፈስሶ የምትይዝዋቸው ቦታዎች መልሶ በድርድርና ሰላም ሰበብ ለወያኔዎች ሊያስረክብ ይችላል ብየ ጽፌ ነበር። ያንን አይሆንም የሚል ሰው ካለ ይንገረኝ።

 ይህ ብቻ ሰሳይሆን ወደ አስመራ ሮጦ ለኢሳያስ የገባለትን ለወዳጅነቱ መሰረታዊ ምክንያት የሆነቺውን ባድሜን ለኢሳያስ ያስረክበዋል። ይህ ቦታ ቢሰያስረክበውም ኢሳያስ ቦታውን በሰላም ማስተዳደር ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ግን አብይ ጥያቄ ነው። በዚህ ፍልሚያ ኢሳያስ እጁ ካስገባ የራሱንም ሥርዓት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይናጋል። በሗላም አብይ ሲወገድ ጦርነት ይኖራል። ምክንያቱም አብይ የባድመና አከራካሪ ቦታዎች በመተባበር ሰበብ በኤርትራ ወታደሮች እንዲይዙትና ወያኔዎችን እንዲዘጋለት ይፈቅድለታል። ያኔ ውጣ የሚለው ሃይል አይኖርም።

ዞሮ ዞሮ ወያኔ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ ወደ “የሽምቅ ውግያ” መግባቱ ስለማይቀርና ቀጠናው ወደ አደገኛ ሥርዓተ አልባነት ስለሚገባ “በመጨረሻም” አብይ አሸናፊነቱን ካረጋገጥ በሗላ ልፍስፈስና ሥልጣን ጥመኛ መሆኑና እንዲሁም አስታማማኝ መሪ ስላልሆነ፤ ሕዝብ ካስጨረሰ በሗላ የራሱን ስም በገናናነት አስመዝግቦ የጎንደርና የወሎ መሬቶች እንዲሁም የባድመ መሬቶችን መልሶ እንደሚያስረክባቸው በእርግጠኛነት እንግራችሗለሁ። በዚህም ብዙ የሰላማዊ ሰልፎችና ውጥረቶች አገሪቷ ታስተናግዳለች። አማራዎቹ ከጀግናው አሳምነው ጽጌ ሞት በሗላ ጠንካራ መሪ ስለሌላቸው በዚህ ጉዳይ የአማራ መሪዎች የተለያየ መስመር በመያዝ ይከፋፈላሉ። ይህ ሲሆን አብይ አሕመድ በለመደው መንገድ ያዳክማቸዋል።

አመሰግናለሁ’

ጌታቸው  ረዳ (Ethiopian Semay)

 

 

Wednesday, November 4, 2020

ኢሳያስ አፈወርቅ የውጭ ጉዳይ ተጠሪ አድርጎ ሹሞኛል ብሎ ያለ ሓፍረት የነገረን ኤርትራዊው አብይ አሕመድ ባድሜን የወረረ የሻዕቢያ መንጋ እንዴት እንደገለጸው ዛሬ ሰምታችሁታል? ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) November 4/2020

 

 

ኢሳያስ አፈወርቅ የውጭ ጉዳይ ተጠሪ አድርጎ ሹሞኛል ብሎ ያለ ሓፍረት የነገረን ኤርትራዊው አብይ አሕመድ ባድሜን የወረረ የሻዕቢያ መንጋ እንዴት እንደገለጸው ዛሬ ሰምታችሁታል?

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

November 4/2020

የኢሳያስ አፈወርቅ ውጭ ጉዳይ ተጠሪ ነኝ ብሎ እራሱ ሰላይነቱን ሳይደብቅ በግልጽ የነገረን “የኦነግ ኮለኔል” አብይ አሕመድ “ዘሐበሻ ኦፊሻል” በተባለ ዮቱብ ሚዲያ ላይ “Ethiopia: ሰበር - ዶ/ር ዐቢይ አሁን ወጥተው ስላለው ሁኔታ ተናገሩ | Statemnet by Dr Abiy Ahmed” በሚል የለጠፈው የስዕለ ድምፅ ርዕስ ባድሜን ወርሮ ለ70 ሺሕ ህይወት ምክንያት የነበረው ወደ ሰዎች መንደር የመጣውን ወራሪው የሻዕቢያ “የጅብ መንጋን” አስመልክቶ አብይ ሕመድ እንዲህ ይላል። ትክክለኛውን አማርኛ አጠቃቀሙን በራሴ ግልጽ ላድረግላችሁ እንዲህ ይላል፡


“ለ20 አመታት የትግራይን ሕዝብ ይጠብቀው የነበረው፤ “ከአንበሳ መንጋ” የታደገውን ሠራዊት ተተናኩሎታል…” እያለ በሰሜን የተመደበውን የአገር መከላከያ ብሎ ራሱን የሚያሞካሸው ድሮ የወያኔ ዛሬ ኦሮሙማዎች የሚያዙት ሠራዊት ለማሞገስ በሞከረበት አገላለጹ “ከአንበሳ መንጋ የታደገውን ሠራዊት” ብሎ የሚለውን “አምበሳ መንጋ” የአለቃው ሻዕቢያን ሠራዊትን ነው።


እንግዲህ ይህ ሰው አገር እመራለሁ የሚል ነገር ግን “ሲናገር ኢትዮጵያዊ በተግባር ኦነጋዊና ሻዕቢያዊ” የሆነው ይሄ ሰላይ ኢትዮጵያንን ሲገድል፤ሲረሽንና ሲያፈናቅል የነበረን የጅብ መንጋ “ወደ አንበሳነት” ቀይሮ የአንበሶች መንጋ ሲል በኤርትራዊነቱ የውጭ ጉዳይ ተጠሪነቱን ለመግለጽ ኢትዮጵያዊ ነኝ እያለ የጠላትን ሠራዊት “የአንበሶች ሠራዊት” አድርጎ በመሳል ማንነቱን በድጋሜ ዛሬም ሳያፍር ግልጽ አድርጓል።


ኢሳያስ አፈወርቅ ዕድለኛ ነው ማለት ይቻላል። ከትግራይ ያጣውን የመለስ ዜናዊ ምትክ ጂማ ያደገው ዛሬ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ነኝ ብሎ የነገረን አብይ አሕመድ አዲስ ሎሌ አግኝቷል። በዚህ ግኝት መሰረት አብይ አህመድ “ኢሱ” በማለት የሚያቆለጳጵሰው ኢሳያስ “ኢትዮጵያን ለማፈራረስ” በዕቅድ ሲሰራ የነበረውን አጀንዳው ዛሬ አብይን የሚያክል ሎሌ ኦሮሙማ በኩል በማግኘቱ የአመራንና የተቀረው የአገሪቱ ሕልውና አደጋ ላይ ነች።


ለወደፊቱ አሁን ስላለው ሁኔታ በሰፊው የምተነትነው ሲሆን፤ ትግራይ ላይ የተኮፈስ የ29 አመቱ ሽፍታ ‘ትግራይን’ ለመገንጠል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደ ሶርያነት ለመቀየር በዕቅድ ሲሰራበት የነበረ ፋሺሰታዊ ቡድን መሆኑን ብዙ ጊዜ የተናገርኩት ስለሆነ የጦርነቱ አይቀሬ ገና አብይ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊትም ሆነ ከዚያም በሗላ የሰጠሁዋቸውን ቃለመጠይቆች አፈላልጋችሁ አድምጡ (ብዙዎቹ ቃለ መጠይቆች ዲያስፖራ ያሉ ተቃወሚ ነን የሚሉ ሚዲያዎች አጥፍተዋቸዋል)። ሆኖም ዛሬ ዋናው ማተኮር ያለባችሁ፤ ይህ ጦርነት በምንም መልኩ ማስቀረት አይቻልም። ምክንያቱም ይህ ጦርነት ሁለቱም ሃይሎች “ምኒሊክ ቤተመንግሥት ያለው ኦሮሙማው ሃይል እና ወደ ትግራይ የሸሸው ሠልጣኑ በአሳፋሪ ሁኔታ ያላንዳች ጥይት የተቀማው የወያኔው ቡድን መካካል ሠልጣን የመጠበቅና ሥልጣን የማስመለስ ስለሆነ ሕዝብ ደገፈውም አልደገፈውም ብምንም መልኩ የሚቆም አይደለም።


ምክንያቶቼን ልግለጽ 

1ኛ- 

ወያኔ/ትግራይ ፐራያ (የተገለለ ቡድንና የተገለለ ሕዝብ ነው)። ይህም ማለት ወያኔ አብረው ሲዘርፉና ሲገድሉ ከነበረው የማዓከላዊው (ኦሮሙማው) ቡድን ጋር ስለተጣላ የምጣኔ ሃብትም ሆነ የፌደራል ዕርዳታዎች፤ የየብስና የጠረፍ መገናኛዎች በሙሉ ተቋርጧል። እራሱ “አገር” ብሎ ለይስሟል (ቢያነስ በለሰለሰ ቃል ዲፋክቶ ነኝ ብሏል)። አማራን በጠላትነት ፈርጇል፤ ስለዚህ የመገናኛ አውታሮችና ሲያገኛቸው የነበረው የምጣኔ ልውውጦች በጎንደርም ሆነ በወሎ የደረቀ ወንዝ ሆኖበታል። በኤርትራም በኩል እንደዚሁ።


ስለዚህ ያለው አማራጭ ያለ ምንም ጦርነትም “በፓራያነት (ታጥሯል) የመኖረም ዕድሉም” አስጨናቂ ስለሆነበት ኢሳያስ ያደረገው የባድሜ ትንኮሳ ዛሬ ወያኔም “በፓራያ እስቴት ስለተሰቃየ” ሰሜን ላይ የነበረው መከላከያ ጦር በሚባለው ላይ “የቶክስ ትንኮሳ” ማድረግ በመታጠሩ ምክንያት የጭንቅ ትንኮሳ ጀምሯል።


2ኛ- ወያኔ ይበልጥኑ ትኩረቱ ኢሳያስን በማስወገድ ላይ ያተኩራል። የባሕር ወደብ ማስገኚያ መንገዱ ኤርትራን ወደ “ከያስ” ወደ “ቀውስ” በማስገባት ጦርነት በመለኮስ ኢሳያስ የሚመካበት የጦርነት ፍላጎት የሌላቸውን የ15 አመት ዕድሜ ያላቸው ኤርትራዊያን ወጣቶች እጃቸው ለወያኔ እንደሚሰጡ በማስላት የኤርትራ ተቃዋሚ የሚባሉት “ጥርስ የሌላቸው ውጭ አገር ያረጁ ያፈጁ ኤርትራውያን ተቃዋሚዎችን” በማሰባሰብ አስመራ ውስጥ ያለው ሥርዓት በማናጋት “ትግራይ ትግርኝን” ወደ ጠረጴዛ ድርድር በማምጣት ቢያንስ የመሸሺያና የንግድ በር ማስገኛ ለመከፍት ይጥራል። ስለዚህም ጦርነቱ በሕዝብ ተደገፈም አልተደገፈም “ወያኔ” “በፓራያ እስቴት” እራሱ የቃዠበትን የእስር ሰንሰለት በማጥለቁ ወያኔ ወደ ሥልጣን መምጣት የማይተገበር ሕልም ስለሆነበት መፍቺያ መንገዱ ስለጠፋው የመገንጠልን ዓላማ “አማራጭ አድርጎታል”።


3ኛ_- አብይ ፈለገም አልፈለገም ጦርነቱ ለማስቆም አቅም የለውም። ምክንያቱም ጦርነቱ የቀሰቀሰው እንደሰማችሁት ወያኔ ነው። አብይ ጦርነት ሳይሆን ሕዝብን እያታለለ “ፓርክ” ውስጥ የሕጻናትን መኪና በማሽከርከር፤ ትራፊክ እያስቆመ “አብይ ነኝ” ማለት፤ በምያምሩ ጉንጉን አበባዎች በተዋቡ የግብዣ ጠረጴዛዎች ሆኖ “ፔንጤዋ ሚስቱ እና እርሱ” እየፈኩ “ሆዳም” ተጋባዥን በሽቶና በጠጅ እንዲዝናኑ በማድረግ እያስጨበጨበ ፤ሃብታሞች ጋር እየተሻሸ የሥልጣን ዕድሜውን በሰላም ለማራዘም ነው ዋናው ፍላጎቱ። ወያኔ ደግሞ እነዚህ በአበባና በሽቶ የታወዱ የሥልጣን ማሳያ ጠረፔዛዎች በአብይ ስለተነጠቀ ሰላም የሚባል በሕልሙም አያስበውም።


4ኛ- ወያኔ በወንጀል ስለተጨማለቀ የ27 አመት ወንጀሉ ዕርቅም ቢሆን እራሱን ማጋለጥና ማዋረድ ስለሚሆንበት ጦርነት አማራጩ አጀንዳው ነው።


5ኛ- ወያኔ አመሰራረቱ “ፋሺስት ነው”። ፋሺሰት ደግሞ ጉልበትን እንጂ ድርድርን ስለማይቀበል እርሱ በሚፈልገው መንገድ (ይህችን አስምሩልኝ) አርሱ በሚፈቅደው የዕርቅና የድርድር ስልት ካልሆነ ‘ሕዝባዊ ድረድር’ በማድረግ ሰላም ለመፍጠር ፍላጎቱም መሰረታዊ ተፈጥሮም አይፈቅድለተም። ይህ ያልኩበት ምክንያት የወለቃይትን ጉዳይ ለምሳሌ ላንሳ ።


በማርች 2016 የጻፍኩትን ልጥቀስ “ትግሬዎች እኔም ወልቃይቴ ነኝ!” እያሉ የወያኔ ወረራ በማውገዝ ለታሪክ ያስመዝግቡ! ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ) በሚል ርእስ በሚዲያ የለጠፍኩትን ጉግል ብታደርጉ ይህንን ጥቅስ ታያለችሁ፦


“የወልቃይት አማራ ወንዶች እየተገደሉ፤እየታፈኑ የወልቃይት ሴቶች “በትግሬ ወንዶች” እየታመጹ አዲስ የትግሬ ትውልድ በወልቃይት መሬት እንዲባዛ እንደተደረገ ወልቃይቴዎች እራሳቸው በተደጋጋሚ በሕዝብ መገናኛ መስመሮች እየተጋበዙ በሚያደርጓቸው ቃለ መጠይቆችና የጽሑፍ ማስረጃዎች የተገለጸ ነገር ነው። ለምሳሌ ይህንን መረጃ ይመልከቱ፤-Government carries out secret mass sterilization among Amhara womenhttps://youtu.be/2iRwEudb3NM (ከጌታቸው ረዳ -አትዮጵያን ሰማይ)።


ስለዚህ ወያኔዎች ፋሽታዊ ወንጀል ስለፈጸሙ ይህን በሚመለከት ትግሬዎች “እኔም ወልቃይቴ አማራ ነኝ የወልቃይት ደም ደሜ ነው” የሚል ደምጽ ሊያስደምጡን አይፈልጉም። ወልቃይት ወደ ቦታው ከመመለስ ይልቅ “ወደ ጦርነት” እንግባ የሚል ከእነ “አበርሃ ደስታ” ጭምር የሰማነው መስመር ስለሆነ ትግሬዎች አማራጩ “ጦርነት ብቻ” እንደሆነ ተቀብለዋል።


6ኛ- የትግራይ ሕዝብ በተለይ “ወጣቱ የትግራይ ብሔረተኛው ምሁር ክፍል” በአክራሪ ብሔረተኛነት እየተኮፈሰ በፋሺታዊ ትምክሕት ስለሰከረ ኢትዮጵያን ሕዝቧ “ሕዝባችንና አገራችን አይደለም” ብለው አገር መመስረት አማራጭ ነው ብለው ስለወሰኑ የጦርነት ከበሮ ከደለቁ አመታት አልፎአቸዋል። ስለዚህም ብዙ ገንዘብና ጥናት በማድረግ መጻኢት ትግራይን ለመመስረት ተስማምተዋል። ስለሆነም ይህ ክፍል “በትዕብት የተወጠረ ስለሆነ” አንሺውና ጣዩ “ጌዜ” መሆኑን ስለማይገባው ዛሬም የደርግን ጦርነት እንደግመዋለን የሚል ትምክሕት ይዞ በትግራይና በአማራ ሕዝብ ደም እጆቻቸው የተጨማለቁ ፍርድ ያላገኙ የወያኔ መሪዎችን በመንከባከብ የልብ ልብ ሰጥቶ የድሃ ልጆች ወደ ጦርነት እየማገዱ እንዲሄዱ ሙሉ አገልጋይነታቸው ስለገለጹለት ወያኔ ትግራይ ውስጥ ሙሉ አዛዥና ናዛዥነቱ እንዲቀጥል ፈቅደውለታል።


7ኛ- ከጫካ ሕሊና ስላልወጡ በሰብአዊትና በዘመናዊ ስልጣኔ አያምኑም ስለሆነም መለስ ዜናዊ የነገረን ላስታውሳችሁና ልደምድም። ቃለ መጠይቅ ያደረገው ከ BBC HardTalk ጋዜጠኛው Stephen Sackur ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ እንዲህ ይላል፦


“….you're also telling me that if things go wrong, as they might, you said, this country could slip into anarchy like Rwanda. You said that to me. Does that suggest you've established a level of stability and confidence in the future that can sustain this country?"

Meles - "We are not out of the woods yet..."


ሲል የባንዳዎቹ መሪ የነበረው በእግዜር ቁጣ የተቀዘፈው አሁንም ከጫካ ሕሊና እንዳልወጡ ግልጽ ያደረገው ጉዳይ ነው። ስለሆንም ከጫካ ሕሊና ያልወጣው ወያኔ በረሃ ውስጥ ሲርመሰመስ በነበረበት ባሕሪ ጦርነት እንደኳስ ጨዋታ ስለሚመከለተው በሚሊዮን ትግሬዎች ቢሞቱና አካላቸው ቢረግፍ ለወያኔዎችና ለትግራይ ምሁራን የኳስ ጨዋታ ነው ብለው ስለሚያምኑ በተለይ አውጭ ያሉ የትግራይ ምሁራን አጨብጫቢዎች የኳስ ጨዋታውን” ለማየት በጉጉት ይፈልጉታል።


8ኛ- ማጠቃለያ መልዕክቴ፡-


ስለዚህም በወያኔና በኦሮሙማ የሚካሄደው ጦርነት የሥልጣን መራኮቻ ሜዳ ስለሆነ በተለይ አማራዎች “ወደ ሥፍራችሁ ሊወጉዋችሁ ሲመጡ ብቻ እራሳችሁን ለመከላከል ካልሆነ የአብይና የወያኔ መጠቀሚያ ከመሆን ተቆጠቡ እላለሁ”። ወያኔ ከባድሜ መልስ በሗላ ጦርነቱን የረዱትን ዘጎቻችን ነበር እስርቤት አስገብቶ ለስቃይ የዳረጋቸው፡ አሁን ደግሞ አብይን ለመደገፍ ብላችሁ ወያኔን ካስቆማችሁት በሗላ አብይ ተመልሶ መለስ እንዳደረገው ስለሚያደርግ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian semay ጌታቸው ረዳ