ይደርስ መልእክቴ ለአቶ (ሰላ አባሞስ)
ጌታቸው
ረዳ (የEthiopian Semay ድረገጽ አዘጋጅ)
Photo-Getachew Reda (Editor Ethiopian Semay |
) በቅርቡ ለተከበሩ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሐይሌ በማለት በየድረገጹ ሲልኩ ለኔም በአድራሻየ ልከውልኝ በአግራሞት
ተመልክቸዋለሁ። ያስገረሙኝ ነገረችዎንም አንዳንዱ እጠቅሳለሁ። በቅድሚያ ግን ስለ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እና ስለ ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ
አንድ ነገር ብየ ወደ እርስዎ አልፋለሁ።
ሁለቱም የቅርብ ወዳጆቼ
ናቸው። ሁለቱም በየሙያቸው የተከበሩ ምሁራን ናቸው። በቅርቡ ዶ/ር ፍቅሬ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ”በጻፈው መጽሐፍ ላይ ተንተርሰው
ፕሮፌሰር ጌታቸው የተገነዘቡዋቸውን ጉዳዮች በጥያቄ መልክ ለደራሲው አቅርበዋል። ፍቅሬም የተቻለውን ያህል መልስ ለመመለስ ሞክሯል።
በነዚህ በተከበሩ ሁለቱም ውድ ምሁራን ወዳጆቼ መካከል ገብቼ በሰፊው እንዳልተች የተጠቀሰውን መጽሐፍ አላነበብኩትም፤ ያም ሆኖ ለመተቸት
የሚያስችሉኝን ሁኔታዎች ከተሰነዘሩት ትችቶችና መልሶች የታዘብኳቸው ጉዳዮች አሉ። ከተሰነዘሩት ትችቶችና መልሶች ብዙ ሰዎች እመሃል
ገብተው ያልበሰለ የጽሑፍ ገንፎ ሊያስውጡን ሲሞክሩ ተገንዝቤያለሁ። ሳይንስ እና ሃይማኖት እንደማይጣጣሙ ስለማውቅ በሰፊው ከመተቸት
ይልቅ ስለተባለው መጽሐፍ (ትንሽ ጠቅሼ ወደ ጽሑፌን እደመድማሁ።
አሁን ወደ እርስዎ
ትችት ልግባ።
እርስዎን ለመተቸት ያስገደደኝ ነገር፥ እንደ እርስዎ ያሉ ጸሐፊዎች የሚጽፉትን
ጥቂት ጽሑፎች ባነብብም ለርስዎ ልመልስ ያሳሰበኝ ጽሑፎን በቀጥታ ወደ የግል መላክያ ሳጥኔ ስለላኩልኝና ካነበብኩትም በኋላ ትንሽ ስለገረመኝ ነው፤ አንዳንዱ ደግሞ ጥያቄ ነው።
በቢጫ ቀለም የለበሰው የእርስዎ ሲሆን የኔ በሌጣ ጽሑፍ ቀርቧል። እርስዎ
ስለፕሮፌሰር ጌታቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል።
<<የኢትዮጵያ ታረክ የመቶ አመት ታሪክ እያሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሚያደነቁሩን ወቅት በሺህ ዘመን ታሪክ ያላት አገር መሆኗን የሚገልጹ ታሪኮች ሲወጡ የሚያኮራን እንጂ የሚያሳፍረን መሆን የለበትም። መደረግ ያለበት የተረጋጋ ሁኔታዎች በሚፈጠሩ ወቅቶች ወደምርምር ተቋም በመውሰድ አለማቀፍ እውቅና የሚያገኝበትን መንገድ መስራት እንጂ እኛ የማናውቀው ታሪክ ከሚጻፍ የመቶ አመት ታሪክ አላት ብለው ደንቁረው የሚያደነቁሩንን መምረጥዎ ባላስፈለገ ነበር። ውሸት የራሱ የሆነ አስተዳደግ ይፈልጋል። በቤተክርስትያን ታርሞ ያደገን ሰው ውሸታም ነው ብሎ መሳደብ እግዚአብሔርን አለመፍራት ነው። በዚህ ንግግሮዎ መሪራስ አማን በላይን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል።እኛም የእናንተ ልጆች ነንና ጥሩ ስነምግባርን ልታስተምሩን ይገባል።>>
<<ውሸት
የራሱ
የሆነ
አስተዳደግ ይፈልጋል።>>
ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? የራሱ የሆነ አስተዳደግ ያለው “ውሸት” እንዴት ያለ ነው። እንዲህ እያልክ ዋሽ እያሉ የሚያሳግዱ
ቤተሰቦች አሉ ማለትዎ ይሆን? አስገራሚው ነገር ደግሞ ፕሮፌሰሩን በዚህ ሁኔታ ካረሙዋቸው በኋላ፤
<<በቤተክርስትያን ታርሞ ያደገን ሰው ውሸታም ነው ብሎ መሳደብ እግዚአብሔርን አለመፍራት ነው።>> ባሉበት አንደበትዎ ትንሽ እልፍ ሳይሉ፤- <<ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ በእዚህ እድሜዎ እንዴት ይዋሻሉ?>> በማለት ፕሮፌሰሩን “ውሸታም” ሲሉ እርስዎስ
ቢሆን በቤተክርስትያን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ባህል ተኮትኩተው ያደጉትን ምሁር “ውሸታም” ማለትዎ ተገቢ ነው? ለመሆኑ
በቤተክርስትያን ትምህርትና ወግ ተኮትኩቶ ያደገ ሁሉ አይዋሽም ብሎ የነገረዎት ማነው? ወያኔን እያገለገሉ ያሉት ታላላቅ ካህናት
በዚያው ትምህርት ተኮትኩተው አልነበርም ያደጉት? ቤተክርስትያን ውሸታም አይወጣባትም የሚል ምንጭዎ ቢነግሩን? ትችት በእርስዎ
ላይ እንጂ የማላውቃቸውን ክቡር መሪራስ አማን በላይን እንዳልሆነ ይገንዘቡልኝ።
እኛ
የሰው ልጆች መዋሸት የጀመርነው ገና በህጽናንታችን ነው። ህጻን ሆነን በቃላት መናገር ከማወቃችን በፊት ማልቀስ
የተንከባካቢያችንን ልቦና እንደሚስብ ስንገነዘብ ‘በማልቀስ’ የፈለግነውን እንደምናገኝ እና ቃላት መናገር ስንለምድም ለደፋነው
ወተት ወይንም ለሰበርነው ብርጭቆ ከወላጅ ቁጣ ለማምለጥ የምንሰጠው ምክንያት እያንዳንዳችን ያለፍንበት ይመስለኛል። ማንም ሰው
አይዋሽም፤ ሁሉም ከኃጢያት የጸዳ ንጹህ ነው የሚሉ ከሆነ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ በደለኛ ነው የሚለውን አለመቀበል ይሆናል።
ፕሮፌሰሩ
መሪራስ አማን በላይ የተባሉትን ያላልኩትን/ያልተነገረ ነገር ለምን አንደሆነ አድርገህ መልስ ትሰጣለህ ብለው ነው በውሸት የጠቀስዋቸው።
እንዲያ ሉሉዋቸው ያስገደዳቸውም ፕሮፌር ጌታቸው ለመሪራስ እንዲህ ሲሉ መልስ ጽፈውላቸዋል፦
“ከመሪራስ አማን በላይ ያመጣህልኝ
መልክትም አለህ። የተጋለጠ ሰው ስድብ ሆነ እንጂ፥ መልእክቱስ ያልተጠባበቅሁት አይደለም። ሰውየው ውሸተኛ አደረከኝ ብሎኝ ተቆጥቶ
ሳለ፥ አለመዋሸቱን በማስረዳት ፈንታ፥ በውሸት ላይ ውሸት አከለበት። አንደኛ፥ “ፈንታሁን ጥሩነህን አማላጅ ልከህብኝ ነበር” ብሎ፥
እውነቱ ሲገለጥ የሚያሳፍር አዲስ ውሸት ጨመረበት። ለነገሩማ፥ አዲስ ጽሑፍ ተገኘ ሲባል የኔ ብጤው ተመራማሪ ለማየት ቢጓጓ አያስገርምም።
ግን መሪራስ አማን በላይ አገኘሁት ስላለው የብራና ጥቅል መጽሐፍ ጉዳይ አቶ ፈንታሁንን እንኳን አማላጅ ልልከው፥ በጉዳዩ ጨርሶም
አልተነጋገርንበትም። ለማረጋገጥ የፈለገ አቶ ፈንታሁንን መጠየቅ ይችላል። ይህም ጽሑፍ በይፋ ሲወጣ አቶ ፈንታሁን ያየዋል።”
አማላጅ ሳልልክ እንዴት አቶ ፈንታሁን
የተባሉትን አማላጅ እንደላኩብህ አድርግህ የፈጠራ/ውሸት ትጽፋለህ? ነው። አሁን እርስዎ የተጠቀሱ ግለሰብ እንደ አማላጅ መላካቸው
ምን ማስረጃ አለዎት? መሪራስም ለመልሱ መልስ አልሰጡም።
ሌላው መከራከሪያ ነጥብዎ ደግሞ
እርስዎ የሚከተለው ብለዋል፡ ማለትም ፕሮፌሰሩ በቅርቡ
ባሰራጩት ጽሑፍ
ላይ እንደገለጹት፥ እርስዎም እንደጠቀሱት፥
“በመጨረሻም ምንም ስድብ ቢበዛብኝ “ሳባ” የንግሥቲቱ ግዛት እንጂ የንግሥቲቱ ስም
አለመሆኑን በጽሞና መቀበልህን ሳይ ጥረቴ በከንቱ እንዳልቀረ ተረዳሁ” (ፕሮፈሰር ጌታቸው) ይላል። በመቀጠል
“ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በመጽሐፉ ውስጥ በገጽ 213 ላይ “ሳባ” ኢትዮጵያ ውስጥ
በአጼ እስያኤል የተመሰረተች ከተማ ነበረች ቢልም፥ አልፎ አልፎ የንግሥቲቷ ስም ያደርገዋል። ስለዚህ ወቀሳው ምኑ ላይ ነው? እንዳውም ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው። በዘሀበሻ ጋዜጣ ላይ ለእርስዎ እንደገለጸሎት የንግሥተ ሳባ ስም ኢትያኤል እንጂ
ሳባ እንዳልሆነ ነው። በመጽሀፉ ውስጥም እውነተኛ ስምዋን ደጋግሞ አብራርቶታል።
ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ
በእዚህ እድሜዎ እንዴት
ይዋሻሉ?
ፕሮፌሰሩ አልዋሹም። ሳባ የከተማ
ስም ነው ብሎ ቢልም እርስዎ እንዳመኑትም “አልፎ አልፎ የንግሥቲቷ ስም ያደርገዋል።” ብለዋል እኮ! ዶ/ር ፍቅሬ አልፎ የከተማው/የግዝትዋን ስም አልፎ
“የንግሥቲቷ ስም” አድርጎ ጽፎ ከሆነ ፕሮፌሰሩ ውሸታም የሚያስብል ነገር የለም። የውም ፕሮፌሰሩ እንዲህ ሲሉ ደ/ር ፍቀቅሬን
አርመውታል፡
<<“ባንተ ተስፋ ባልቈረጥኩበት ዘመን
ስለ ክብረ ነገሥትና ስለ ንግሥተ አዜብ የጻፍኩት አጪር ድርሰት
ሲታተም፥ የታሪክና የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ተመራማሪዎች እርስ በርሳችን እንደምናደርገው አንድ ቅጂ ልኬልህ ነበረ። በዚያ ጽሑፍ ያሰፈርኩትንና አሁን ደግሞ ስሕተትህን ስዘረዝር የጻፍኩትን በማጣመም፥
“ርስዎ ሳባን ስምዋን ቀይረው «ቢልቂስ« ብለው፣ በሃሰት ሳባ የኛ ቢልቂስ ናት ለሚልዋት ለአረቦች «ደ»ይሸልሙዋታል” ብለኸኛል።
እኔ እንደዚህ ዝብርቅርቁ የወጣ ዐረፍተ ነገር አልጻፍኩም። “ሳባን ስምዋን ቀይረው” የሚለው አነጋገር የአላዋቂ ሐረግ ነው። “ሳባ”
የመንግሥቷ፥ የግዛቷ ስም እንጂ አንተንና የታሪክና የግዕዝ መሃይምናንን እንደመሰላችሁ፥ የንግሥቲቱ ስም አይደለም። ስለማያውቁት
መስክ መጻፍ ነፋስ ያለመንሽ የሚያነሣው ገለባ ያደርጋል።
እኔ ያልኩት እንደዚህ ነው፤
ብሉይ ኪዳን ስሟን ሳይጠራ “የሳባ
ንግሥት” (በዕብራይስጥ “ማልከት ሽባ”) ብሎ ነው ያለፈው። ዐረቦች “ቢልቂስ” ይሏታል። ክብረ ነገሥቱ “ማክዳ” የሚለው እሷን
ሊሆን ይችላል፤ ግን አጥጋቢ ማስረጃ የለንም። >>
ከላይ የተመለከትነው “ሳባን ስሟን
ቀይረው” የሚለው የዶ/ር ፍቅሬ አገላለጽ ከሆነ ከመጽሐፉም ውጭ በሚዲያም መልስ ሲሰጣጡ ፍቅሬ የንግሥቲቱ ስም ‘ሳባ” ብሎ አስቀምጦታል።
ዶ/ር ፍቅሬ “ሳባን ስሟን ቀይረው” ሲላቸው/ማለት/ ምንን ያመለክታል? ይህ አባባል፤ ባብዛኛው ኢትዮጵያዊያን “ሳባ” Queen
Sheba/Saba እያሉ ይጠርዋታል፤ በተለይ ትግሬዎች በዚህ ስሟ
አብደውበታል። ፕሮፌሰሩ “የግዕዝ መሃይማን” የሚለው አባባላቸው፤ ግዕዝ ለማናውቅ ዜጎች እውነትም ስለ ተባለው ስያሜ ግንዛቤ ጎድሎብናል።
ስለዚህ ውድ ወንድሜ ሆይ፤ ዶ/ር ፍቅሬ ያልጻፍሉትን አትጻፍ ብለው ያረሙት ብቻ ሳይሆን የንግሥቲቱን ስም ‘ሳባ’ ሳልል አንተነህ
‘ሳባ’ እንደምትባል ጽሑፍህ አረፍተነገርህ የሚያስረዳው ስላሉ “ፕሮፌሰሩን “በእዚህ
እድሜዎ እንዴት ይዋሻሉ? ማለትዎ
አግባብነት የጎደለው ነው።
ሌላው ያሳሰበዎትና አስተያየት የሰጡበት ደግሞ “ የጠነዛ” ማለቱ ነው። እርሶ ከዚህ በፊት ከጻፉትና አስተያየት የጻፉበትን ደቂቀ እስጢፋኖስን “ በህግ አምላክ” በሚል ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙትን እንመልከት። ይህን መጽሃፍ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲይ የመጸሃፍት መደብር በመሄድ ገዛሁት። በገጽ 23 እንዲህ ይላል “ ታረካቸውን እዚህ የማቀርበው አባ እስጢፋኖስ ተከታዮቻቸው(ደቂቀ እስጢፋኖስ) የእትዮጵያ ቤተክርትያን የማትቀበላቸው እንዲያውም የተወገዙ አድርጋ የምታያቸው በዓስራ አምስተኛው ምእተ አመት ያበቡ የተሓድሶ እንቅስቃሴ መሪዎች ናቸው። አሕይዎና ተሐድሶ(Revival and Renewal
or Reformation) ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠው ስርአት(Establishment) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ ነገር የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተስጥዎ ካላቸዉ ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሓሳቦች ናቸው” ይላል።
ሌላ ደግሞ እትዮጵያ የራሷ እምነትና ክርስትናን ቀድማ የተቀበለች መሆኑ ይታወቃል። እርሶ ከግእዝ ወደ አማርኛ በተረጎሙት ደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ በጀርመን የተነሳውን ማርቲን ሉተርን ሃሳብ ከእትዮጵያ ካለው ንቅናቄ ጋር በማመሳሰል በገጽ 24-25 እንዲህ ብለው ጽፈዋል
“ደቂቀ እስጢፋኖስ የተነሱት በአጼ ይስሃቅ (1406-1421) ዘመን ሲሆን ማርቲን ሉተር ጀርመን ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ ይዞ ከመነሳቱ ከሰላሳ አመት በፊት ነው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውጉዛን ታድርጋቸው እንጂ ተልኳቸውን ውስጥ ውስጡን በጽሙና እየተቀበለችው በመሄድ ላይ እንዳለች ስነ ጽሁፍ ይመሰክራል። እንደሚባለው ሳይሆን ሁልጊዜ ሰላማዊና የማይቈረቁር ተሃድሶን የሚቀበል መሪዎች አሏት” ይላል።
እነዚህ ከላይ የገለጿቸው አስተሳሰብ በቀደመው ቤተክርስትያን የበለጸገውን ሃይማኖታዊ እድገት እንዴት ሊወክል ይችላል? የዛገና የሚራገፍ የሚለው ቤተክርስቲያንን ይወክላል?
ሲሉ ፕሮፌሰሩን ወቅሰዋል/ተገቢ አባባል አይደለም ብለዋል። እርስዎ
ያልገባዎት በግር እንዳለ ገምቻለሁ። ቤተክርስትያን / ወይንም
ቤተክርስትያኒቱን የሚያስተዳድር አካል/ክፍሎች የዛገ አስተሳሰብ እንዳለቻው የሚክዱ ይመስለኛል። የቤተክርስትያን አስተዳዳሪዎች ሁሉ እንደማንም ሥርዓት
ይታደሳሉ/ይበሰብሳሉ/ይታደሳሉ፡ ሰዎች ናቸው፤ ሕሊናቸው ባንድ ዘመን ወይንም ውቅት አዲስ አመለካካት ሲመጣባቸው ነገሩን
አስላስለው ከመቀበል እና ከመከራከር ይልቅ ወደ ውግዘትና አለፍ ሲልም መሪያቸው እስጢፋኖስ እና “ደቂቀ እስጢፋኖስ”
እንደደረሰባቸው የቅጣት ግፍ ድረስ ይደርሳል/አድርሰዋልም። አስተዳዳሪዎች ይዝጋሉ (አስተሳባቸው የዛገ እና ከወቅቱ ግጭቶች ጋር
ለክርክር ዝግጁ አይሆኑም ማለት ነው) “ዲክታተሮች/አምባገነን አባቶች/ ይሆናሉ። የወያኔ የቤተክህነት መሪዎች የምናየው ምሳሌ
ነው። በጣም ግልጽ እኮ ነው።
የሚከተለውን ጽሑፍዎን ይመልከቱ፦ እንዲህ ብለዋል፦
<<ሌላው ደግሞ በቅርቡ በጻፉት ጽሁፍ “ይህ የሃሰት ታሪክ የእትዮጵያ አንድነት በሚያንሰፈስፋቸው እትዮጵያውያን ስሜት ከመቀለድና ከመጠቀም አልፎ በክልልና በጎሳ ፓለቲካ የሚያምን አንድ የኦነግ ሰው ነፍስ አይማርክም። የተረቱ ሰለባ የሆኑት የአንድነት ተስፋ የናፈቃቸው ምስኪንና አንድነቶችን ብቻ ናቸው” ይላል። በእውነቱ ከሆነ ኦነግ የእትዮጵያ ኦሮሞዎችን ወኪል ነው ያለው ማነው? እርሶስ ቢሆኑ የአማራ ወኪል ማን አደረገዎት? ይህ አገላለጸዎ የእትዮጵያን ዜጎች በክብር አለማስቀመጥዎን ያመለክታል።>>
በማለት ፕሮፈሰሩን በሃሰት የአማራ ወኪል ነኝ እንዳሉ አስመስለው አቅርበዋቸዋል።
ሁለት ነገሮችን ጠቅሰዋል ለነዚህ መልስ ይስጡ፡ 1) ፕሮፌሰሩ ኦነግ የኢትዮጵያ ኦሮሞዎች ወኪል ነው ያሉበትን ይጠቁሙ፡ 2)
እርስዎስ ቢሆን የአማራ ወኪል ያደረገዎት ማነው ሲሉ ፕሮፌሰሩ ወኪል ነኝ ያሉበትን ጽሑፍ ያቅርቡልን።
የዶ/ር ፍቅሬ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” ብሎ ስለጻፈው አዲስ መጽሐፍ ፕሮፌሰሩ <<በክልልና በጎሳ ፓለቲካ
የሚያምን አንድ የኦነግ ሰው ነፍስ አይማርክም።>>
ማለታቸው አልተሳሰቱም። መሪዎችም ሆኑ ተከታዮቻቸው የፍቅሬን መጽሐፍ እንደ አዲስ ዜና ወስደው ‘ግንጠላቸው እና ጥላቻቸው”
ይተዋሉ ብሎ ማለት “ቀልድ ነው”። የኦነግ መሪዎችም ሆኑ ተከታዮቻቸው ከማን ዘር እንደተደበላለቁ ስላለወቁ ኖሮው ነው “ግንጠላ
እና ጥለቻ” ውስጥ የገቡት የሚል ብሎ ማለት ቅዠት ነው። ደ/ር ፍቅሬም ቢሆን ውሃ አንዲት ሴት ሃይቅ ውስጥ ስትዋኝ እባሕሩ
ውስጥ በታአምር ሲዋኝ ከነበረ የውሃው ጨው/ሌላም ንጠረነገር/የውሃ ኬሚካሎችን እና የሃይቁን ሞገድን/ሾክ ተጋፍጦ አንድ ሞገደኛ
የወንድ ሃጢያት (Sperm) ወደ ማህጸንዋ ሰርስሮ በመግባቱ ‘ደሸት’
የተባለ ሰው ተወልዶ ሁለቱ አማራ እና ኦሮሞ ተወለዱ ይለናል። አስገራሚው ደግሞ ደሸት አሁን ላሉት ሁሉም የኢትዮጵያ
ነገዶች ወላጅ እንደሆነ በቃለ መጠይቁ ሰምቸዋለሁ። አሁን ላሉት ነገዶች ከመወለዳቸው በፊት እዛው የሃይቁ መጎድ
(ሾክ/ነውጥ እና ጨዋማ ውሃው? salty ዋተር)ተጋፍጦ የኖሮው የወንድ ዘር/ human sperm/ የማን ዘሮች ወይንም የማን
ነገዶች ነበሩ? እጅግ አስገራሚ ነው! ደሸት የተባለው ሰው እና የመልከጸዴቅ ልጅ ኢትኤል/ኢትዮጵ በምን በምን እንደሚገናኙ ለኔ
ግልጽ አልሆነልኝም። ማብራሪያ እፈልጋለሁ።
ወደ ነገሩ ልመለስና አሁን በግንጠላ እና በግድያ ወንጀል የተሳተፉት የኦነግ
መሪዎች በእናታቸው ወይንም በአባታቸው አንዳንዶቹ
ጎጃሜዎች/ሸዌዎች እና ወሎዎች ወዘተ ናቸው። እነ ጃዋር እነ አሚን እነ ስንቱን እንጥራ? የአማራ ዘሮች ናቸው። ወደ
4000/3000 አመት ወደ ኋላ ዘመን ተመልሰው ማንነታቸው የሚያስመረምራቸው አንዳችም ምክንያት የለም። መቶ
አመት በሚሉት የተረት ተረት ሙግታቸው እንኳ ብንመለከት በመቶ አመት ውስጥ ሳይሆን በ60 እና በ30 አመታቸው ውስጥ
ያሉት መሪዎቻቸው ናቸው ከአማራ እናት ወይንም አባት ተውልደው ኮለኒ ተደርገናል/ባዕድ ነን “ኦነግ” ነን የሚሉን። ኦነግ
ነን የሚሉ በሺዎች ምናልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግራ የገባቸው ጀሌዎች “አባት/እናት/አያት/ሚሰት/ልጅ… ቢጠየቁ አማራ በእናት/አባት/አያት/ሚሰት….የተከለሱ እንደሆኑ እነሱም ሆኑ
እኛ የምናውቀው ሃቅ ነው። አይደለም እንዴ? ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንሰራፍቶ ያለው ኦሮሞ የአማራ ዘር የለውም ብሎ የሚል ማሃይም
ብቻ ነው ።
ስለዚህ የመሪ ራስን
(ምንጩ የማን እንደሆነ ባላውቅም) ተንተርሶ ወደ 3000 አመት የሚጎትት ውሃ ውስጥ የተጸነሱ ወንድማማቾች ናቸው የሚለውን ሊያሳምናቸው
ቀርቶ፤ ከ60/30/40/20 አመት በፊት እናታቸው አማራ መሆኗን ጡቷን ጠብተው ያደጉ የጠቀስኳቸው ኦነጎች አማራን እንደጠላት ከማየት
አልፈው አማራን ከምድረገጽ ወደ ማጥፋት የተሳተፉበት ወንጀልና አናካሸስና በቀል አስነሺ የሆነ አስገራሚ የአኖሌው የውሸት ሃውልት ማቆማቸው የምናውቀው ጉዳይ ነው። ወንድም እህት ኣባትና ልጅ
የሚገዳደሉበትና ክሕደት ውስጥ የሚገቡበት ዓለም አደለም ያለነው? ማንነታቸው አጥተውት አይደለም ግድያና ክሕደት ውስጥ
ገቡት። ’እኛ
እና
አማራ
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደዚህ ጤፍ የተቀላቀልን ነን’ ብለው
ኦሮሞዎችንም ሆነ ጣሊያኖችን ያስተማሩ ታላቁ የኦሮሞው “አባ ዶዬ” የተባሉትን ታሪክ አናወቅም ወይንም ኦሮሞዎች አያውቁም ሆነው ነው ወደ 3000 አመት
ወደ ጎጃም ዉሃ እርግዝና የሚጎተቱት?
በመጨረሻም እባካችሁ ሳይንስ እና ሃይማኖት ቀመስ ታሪኮች የተለያዩ መሆናቸውን እና
እንደማይጣጣሙ እያወቅን እራሳችንን በማይሆን ሙግት ባናስገባ የተሻለ ነው። ወዳጄ ፍቅሬ ቶሎሳ አማሮች እና ኦሮሞዎች
‘መልከጸዴቅ’ ከተባለ ከፍተኛው ቄስ (ከፍተኛ የዓለም ቄስ) እኔ አይሁድ/እስራላዊ (?) እለዋለሁ (አፍሪቃዊ ግን ሊሆን
አይችልም፤ ከእየሩሳሌም ልጁን ልኮ ፈጠረን ነው የሚለን፤(ሰለሆነም እኛ ኢትዮጵያ ነገዶች የመልከጸዴቅ የልጅ ልጆች ነን
ነው/መልክጸዴቅ ሁላችን አባት ነው፤ ሲል ፍቅሬ በቃለ መጠይቁ ሰምቼዋለሁ።) ስለሆነም እኛ መላው ኢትዮጵያዊያኖች አይሁዶች ነን
ማለት ነው (በደሼት እና ኢትዮ አማካይነት)። መልከጸዴቅ ሰው ነው፤ ሰው ከሆነ የራሱ ነገድ አለው እና ነገዱ እስራኤላዊ ነው።
እኛ የሱ የልጅ ልጆች ከሆንን ሁላችንም መጤዎች ነን ወይንም ክልሶች ነን ማለት ነው (ከደሼት/ከኢትዮጵ)። በ13/በ15/በ16
ክፍለ ዘመን ወደ መሃል ኢትዮጵያ ተስፋፍተው/መጥተው ወረራ ፈጸሙ የሚባሉት የድሮ ጋሎች በዛሬው አጠራር ኦነግ “ኦሮሞ” እንጂ ‘ጋላ’ ማለት ምኒልክ እና ሃይለስላሴ ያወጡልን
ስድብ ነው (ብሎ የሚዋሸው ውሸታሙ ኦነግ) እየተባሉ የሚጠሩ ነገዶችም የመለክጸዴቅ የአይሁድ ክልሶች ናቸው ማለት ነው። ግራ
የገባ ሁኔታ ነው ያለነው። ተገኘ የተባለው መጽሐፍ ኦሮሞዎችን ምን በሚል ስም ይጠራቸዋል? በጋላ በኦሮሞ ወይንም በሁለቱም
ወይስ በሌላ ስም?
እንዲህ ከሆነ፥ እኛ
የሰው መገኚያ አንሆንም ማለት ነው። የኛ ትልቁ አባት ከመልከጸዴቅ የተገኘን ዘሮች ነን ማለት ነው (በፍቅሬ/ተገኘ በተባለው
መጽሐፍ አገላለጽ)፤ ምክንያቱም ‘መልከጸዴቅ” እና ልጁ ከኛ በፊት የነበሩ እስራኤላዊያን (?) ናቸው እና። ከእባሕር ውስጥ
ሲዋኝ የከነበረ አመጸኛው የወንድ ዘር/ Sperm ደሸት የተባለው አባት ተጸንሶ የተገኘን ነን ከተባለ፤ እኛ ከመገኘታችን በፊት
የነበሩ ነገዶች እነማን ሲባሉ ነበሩ? ወይንም የማን ነገዶች እንደነበሩ ፍቅሬ/ወይንም ተገኘ የተባለው መጽሐፍ የነገርን ነገር
ይኑር አይኑር አላወቅኩም (ደ/ር ፍቅሬ የሚለን እኛ የሰው ዘር መገኛ ነን ይላል። እንደገና አሁን ያሉት ኢትዮጵያዊያን
የመልከጸዴቅ የልጅ ልጆች (?) ናቸው ይላል። ሃይቅ ወስጥ ሲዋኝ ነበረው የወንድ ዘርም የማን ነገድ የማን ሰው እንደነበረ
የነገረን ነገር/የሚታወቅ ነገር የለም (የውስጥ ሰውም የውጭ ሰውም ሊሆን ይችላል አደለም አንዴ?)።
ያ ብቻ ሳይሆን
የመልከጸዴቅ ልጅ ወደ ጣና ከመምጣቱ በፊት የነበሩ ኗሪዎች የራሳቸው ንጉሥ /መሪ/ነገሥታት/መሪዎች/በላያቸው ላይ እንዲጫናቸው
እግዚሔር ለምን ትዕዛዝ ሰጠ? አልገባኝም። እዛው ጣና ይኖሩ የነበሩ ጥንታዊያን (ኢንዲጂነስ) የራሳቸው ነገሥታት (12?)
ሰዎች/ነገሥታት እየሱስ ሲወለድ በከዋክብት እየተመሩ ወደ በቤተላህም በመሄድ ‘ብስራት ለማበሰር’ የሚያንሳቸው ምክንያት እየሱስ
ያስቀመጠው ምክንያት “ተገኘ የተባለው መጽሐፍ ነግሮን ይሆን?” በእግዚአብሔር ቃላት አጠቃቀም ‘ዮፕ’ ማለት ወርቅ ማለት ከሆነ
ወርቁም አገራችን ውስጥ ነበር፤ ከውጭ አልመጣም፡ ስለሆነም ለምንድነው የመለክጸዴቅ የልጅ ልጆች ተመርጠው ነባሮቹ ሊመርጣቸው
ያልተፈቀደው? የእግዚአብሐርን ትዕዛዝ አትጠይቅ ካልተባለ፤
ለምንስ 12 ወንዶች ብቻ ተወለዱ? ሴቶችስ ለምን አልተመረጡም? የሚል ጠያቂ ቢመጣ መጽሐፉ የሚያውቀው ነገር ይኖር ይሆን? ተገኘ
የተባለው መጽሐፍ ስለዚህ ያለው ጉዳይ አለ? ሃይማኖት ውስጥ
ብንገባ ብዙ አነጋጋሪ ነገሮች ውስጥ ያስገባናል፤
ምክንያቱም እየሰሱ/እግዚአብሔር እንደገና ሲወለድ ወደ ቤተላህም የሄዱት 12
(ነገዶች/በፍቅሬ አገላለጽ እነ ‘መጋል’ ኦሮሞ ወክሎ እነ ‘ሙር’፤አፋሮችን፤‘መቃዲሽ’ ኦጋዴኖችን ወክሎ አማሮችም እንዲሁ
ሁሉም 12 ነገሥታቶች ክልሶች ወይንም …. (?) እነዚህ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ኢንዲጂነስ/ጥንታዊያን/ኦሪታዊያን ኗሪዎች
አላደረጋቸውም (የአይሁዱ/የሳሌም ከተማ/አገር ተወላጅ የመልከጸዴቅ የልጅ ልጆች ነን ናቸውና)
ወዳጄ ዶ/ር ፍቅሬ አጅግ የማከብረው ምሁር እና እውነተኛ ወዳጄ ነው። ግን ብዙ
ተሳስቷል። ለምሳሌ ግሪኮች ኢትዮጵያ የሚል ስም አላወጡልንም የሚል ክርክሩ የሚያሳምነ ቢሆንም፤ ክርክሩ ግን <<እኛ
ከመፈጠራችን በፊት አልተፈረጠሩም ልጆች ለወላጆቻቸው ስም ሊያወጡላቸው አይችሉም፤ ወላጆች ናቸው ለልጆቻቸው ስም
የሚያወጡላቸው>> በመለት “ሂፕክሪት” ክርክር ያቀርባል። ስሞች በውጭም በውስጥ ሰዎችም ይሰጣጣሉ። አሁን ያለው
ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ ውስጥና (ዞን…ወዘተ) የሚጠቀምባቸው የውጭ ቃላቶች፤ትምሐርት ቤቶች ንግድ ቤቶች፤ የጎዳና ስሞች
የወጣቶች ስም ሁሉ የውጭ /የባዐድ ስም ሆኗል። ነይህ የሚያሳየን ቀድሞ የተፈጠረ እና ሗላ የተፈጠረ ሳይሆን የ
“ሳብቨርዥን”/የብከላ ውጤት ነው። “ፈላሻ” እየተባሉ በተለምዶ የሚጠሩት “አይሁዶች/እስራላዊያን/ እንጂ “ኢትዮጵያዊን
አይደለንም” ብለው ወደ እስራላቸው የነጐዱት ወገኖቻችን “እስራሎች” ከኛ በፊት ስለፈጠሩ ሆነው አይደለም። የብከላ እና
የቅጥፈት ሴራዎች ጉዳይ ነው። እንዲህ ከሆነ እኛ የሰው ልጆች ዘር መገኚያ ነን የሚል አምነት ካለው (እሱም ያምናል) ከኛ
በፊት ያልነበሩት እነ መልከጸዴቅ የተባለው ካሕን በልጁ በኩል ስማችን አስሰጥቶናል፡ አይደለም እንዴ? 12 ነገዶች እነ መጋል
እነ …..ስማቸው ያወጣላቸው ማን ነው? እነ መጋል እነ አማራ እነ ሙር፤ እነ መቃድሽ…….. ከመፈጠራቸው በፊት የነበሩ
ያገራችን ጥንታዊያን ሰዎች የነበራቸው ስም ተውጦ በነ መጋል፤
በአማራ፤መቃዲሽ፤በሙር……… የተጠሩ ጥንታዊያን አልነበሩም ልንል ነው?
ለማጠቃለል፤ ተገኘ የተባለው ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ ተንተርሶ ዶ/ር ፍቅሬ
የጻፈው/የሚያቀርበው ክርክር “የክርሰትያን/አይሁድ? የፈለጋችሁ በሉት ብቻ ክረስትያናዊ የሆነ ሃይማኖታዊነት የተሞረኮዘ/
የተጻፈ ተንተርሶ ነው እየተከራከረ ያለው (አማራና ኦሮሞን በሚመለከት ብቻ ማለቴ ነው) እና የወዳጄን የዶክተር ፍቅሬን መጽሐፍ
አንብቤ መተቸቱ ይሻላል እና እኔ እንደገባኝ ግን እባካችሁ ሳይንስን እና ሃይማኖት ባናምታታቸው ይሻላል። ይህ ጽሑፍ ላለማውጣት
እንደለመዳችሁት የመናገር ነፃነት የምታፍኑ የወያኔን ፈለግ የተከተላችሁ የዲያስፖራ ተቃዋሚ ድረገፆች አውጡት አታውጡት እኔን
ሳይሆን የምታፍኑት የሕዝቡን የማወቅ መብትን ነው።
ከአክብሮት ጋር። ጌታቸው ረዳ (የኢትዮፕያን ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ) getachre@aol.com
(Ethiopian Semay)
No comments:
Post a Comment