Friday, May 13, 2016

የደርግ መንግሥት ምስጢራዊ ሰነዶች ስለ ሻለቃ ዳዊት ማንነት ምን ይላሉ? ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያን ሰማይ ብሎግ አዘጋጅ)




የደርግ መንግሥት ምስጢራዊ ሰነዶች ስለ ሻለቃ ዳዊት ማንነት ምን ይላሉ?
ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያን ሰማይ ብሎግ አዘጋጅ)



ለዚህ ሳምንት ልተችብት ያድኩት ሌላ ጉዳይ ነበር። ሆኖም ወደ እዚህኛው ጉዳይ ለማተት አዘነበልኩ።ትላንት ኢትዮ-ሚዲያ ወደ ተባለው ድረገጽ ጎራ ብዬ ነበር። ሊደመጥ የሚገባው የሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ቃለ ምልልስ የሚል ርዕስ ወደ ተሰጠው የድምፅ ሰነድ አተኮርኩኝ። ሊደመጥ የሚገባው የተባለው የሻለቃ ዳዊት ቃለ መጠይቅ የተከናወነው በኢትዮጵያ ጠላት አገር በሚደረግለት የገንዘብ ዕገዛ የሚንቀሳቀሰው የግንቦት 7 ቴ/ቪዢን ጣቢያ ነበር። ቃለ መጠይቁ ያከናወነው የግንቦት 7 ጋዜጠኛው የመቶአለቃ ሲሳይ አገና ነው።

የግንቦት 7 አባል ናቸው የሚባልላቸው የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩ እኚህ ሻለቃ  በዚህ ጣቢያ ተዘውትሮ የሚስተናገዱ የጣቢያው ደምበኛ ሲሆኑ፤እንደ ሻለቃው ተመሳሳይ መስተንግዶ እና ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣን የነበሩ ዛሬ የግንቦት 7 ድርጅት አባል ናቸው የሚባሉት “ይሁዳ” በሚል የቅጽል ሥም የሚጠሩት  ዶ/ር ካሳ ከበደም ለዚህ ጣቢያ እንግዶች አይደሉም። ሁለቱ የደርግ ከፍተኛ በቫለሥልጣኖች ፤በተለያየ ጊዜ፤ ስለ ኤርትራ ነፃነት/ባርነት/መገንጠል አምነን መቀበል እንዳለብን ደጋግመው ከሚሰብኩና ለኤርትራ/ ለሻዕቢያ ጥብቅና በመቆም የታወቁ ናቸው። በዚህ የዜና መደብር ሲስተናገዱ ሁለቱም ስለ “ወያኔ” ሥርዓት ወንጀልና ክሕደት እንጂ ራሳቸው ባገለገሉትና በመሩት የደርግ ሥርዓትም ሆነ ከወያኔ የማይለየው “ወንጀለኛው የኢሳያስ አፈወርቂ ሥርዓት” ሲተቹ ተሰምተው አይታወቁም። ሻለቃው ስለ ኮለኔል መንግሥቱ ሃይለማርያም የዓፈና ተግባር አብጠልጥለው ሲናገሩ በግንቦት 7 (የኢሳት) ቴ/ቪዢን ደጋግመን አድምጠናቸዋል።

ይህስ ባልከፋ። አስገራሚ የሚያደርገው እንግዳው በተጋበዙበት ባለፈው ወቅት በመንግሥቱ ሃይለማርያም ስብእና ላይ በተደጋጋሚ ሲያብጠለጥሉ፤ ጋዜጠኛው መቶአለቃ ሲሳይ አጋና ስለ ሻለቃ ዳዊት ስብአና እና ስለ መንግሥቱ ሃይለማርያም የነበራቸው ልዩ ፍቅር፤ሙገሳ፤ እልፎም ኮለኔሉ በሕዝብ አንደተመረጡ አድርገው ሲያወድስዋቸው የነበረውን የሚያሸማቅቅ አስተዛዛቢ እና ይሉኝታ የሌለው እስስት እና አድርባይ ባሕርያቸው እንደ ጋዜጠኛነቱ በሰነድ አስደግፎ ለምን አንደማይጠይቃቸው ሁሌም ይገርመኛል። ጋዜጠኛነት እጅግ ፈሩን የሳተበት ዘመን እና ጋዜጠኞች በራሳቸው ላይ ሃላፊነት የጎደለው አስገማች የጋዜጠኘነት ባሕሪ ለታሪክ እያዘስመዘገቡ ከሚያልፉት ጋዜጠኞች ውስጥ በግምባር የሚጠቀሰው ሲሳይ አገና እና አብረውት የሚሰሩት አብዛኛዎቹ  “የኢሳት” ጋዜጠኞች እንዲህ ያለ ወገንተኛነት/ቡድነተኛነት ካሁን በፊት በታሪካችን የታየ አሸማቃቂ የጋዜጠኛ ሥራ ተከስቶ የሚያውቅ አይመስለኝ።

ጋዜጠኞቹ፤ በዘልማድ ያገኙት የጋዜጠኛነት ሙያቸው ምን ያህል ርቀት ይዘውት እንደሚሄዱ እያየንነ ቢሆንም፤ ሊደመጥ የሚገባ ቃለመጠይቅ ብለው ስለ ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣን ሰው እንድናደምጥ አድመጭ ሲጋብዙ፤ እኝህ ከፍተኛ እንግዳ ባለፉት ሥርዓቶች የነበረው አስተዋጽኦ ምን ይመስል እንደነበረ በቂ ግንዛቤ ሳይሰጡን በደፈናው “እንድናደምጠው ይገፈትሩናል”። ለምሳሌ ሲሳይ አገና ስለ ሻለቃ ዳዊት ሲያስተዋውቅ፤ ባለፈው ሥርዓት የነበራቸው ሥልጣን እና አሁን የተመደቡበት ሥራ (መዳቢው ማን አንደሆነ እግዚሔር ይወቀው!!) ተልዕኮና ሓላፊነት እንጂ ክፉ ሥራዎቻቸውና ማሕደሮቻቸው ሕዝብ አንዲያውቀው አያደርጉም (ኦነጎች ሲጋበዙም እንዲሁ)። ይህ ደግሞ ለምን እንደሆነ የምናውቀው ነው። እንግዶቹ ከዜና ማዕከሉ ወይንም የዜና ማዕኩሉ ከሚያካሂደው የፖለቲካ ድርጅት ጋር ያላቸው ቀረቤታ ምክንያት በማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ጋዜጠኛነት ሙያ ሊያሰኝ አይቻልም። በቅርቡ የጀርምን ራዲዮ አማርኛ ክፍል (?) ባልደረባ ነኝ የሚል በነገዱ ኦሮሞ የሆነ ጋዜጠኛ ስለ ወያኔ ወንጀልና ስለ ኦሮሞ ሕዝብ መገፋት ጋዜጠኛዋን (ፈረንጅዋን) በሙዚቃ እያስደመጠ ሲተነትን ስለ ተቀሩት ኢትዮጵያ ነገዶች/ሕዝብ ተመሳሳይ ጥቃት እየተፈጸመበት እንዳለ መተንተን አልፈለገም። ይህ ስለ ኦሮሞ የሚብከነከነው ጋዜጠኛ ነኝ የሚለን ግለሰብ፤ በከፋ ሁኔታ “ጫና” እየደረሰበት ያለው “ኦሮሞ” ብቻ አንደሆነ ሲኳትት ታደምጣላችሁ።  ወይንም ወያኔን ሲያወግዝ አብረው መወገዝ ያለባቸው ኦሮሞ ድርጅቶችም የተቻቸው አንድም ነገር የለም። ጋዜጠኛ ትርጉሙ ፈሩን እየለቀቀ መሄዱን በተቃዋሚነት የቆሙ ጋዜጠኞች ለትዝብት አንደጣላቸው ካንዳንዶቻችን ልቦና የማይረሳ ትዝብት እየቀረጹብን መጥተዋል።

ይህ ካልኩኝ ዘንድ፤ ሻለቃ ዳዊት ማን ናቸው የሚለው፤ በአሳማሪ ትንታኔ ተኳኩለው በሲሳይ አገና ጋዜጠኛነት ተከሽኖ ስለቀረበላችሁ፤ ያንን መድገም አላስፈለገኝም። ሲሳይ ሊያነሳው ያልፈለገ፤ ግን ይህ የሚከተለው የሻለቃ ዳዊት ሌላው እውነተኛ ገጸ ባሕሪ ነው።

ሻለቃ ዳዊት፤ በደርግ ዘመን፤ በሱዳን በኩል አድርገው፤ ከኤርትራ ቡድኖች ጋር አየተነጋገሩ፤ ኤርትራ በረሃ ድረስ ምስጢር ሲለዋወጡ (ሃይልና እልክ የማይጠቀሙ መሪ እያሉ ሲያሞግሷቸው የነበሩትን መሪያቸውን ለመፈንቀል “ዱለታና….የመሳሰሉ” ለማካሄድ )እንደነበረና፤ በጉዞአቸውም አንዳንድ ሙርኮኛ ወታደሮች አግኝተው ሲያነጋግሩ፤ ከአንደበታቸው ሲወረወር የነበረው  ርሕራሄ ያልተላበሰ መልስ ሲሰጥዋቸው እንደነበረ የተለያዩ ሰነዶች አንብበናል። ስለ ሻለቃው ማንነትም በመጽሐፍ መልክ ተጽፎላቸዋል። ከነዚህ መጽሐፍቶች አንዱ  “አገርና ሠራዊት-ፍረጅ ኢትዮጵያ” የተሸኘ በሻለቃ ጌታቸው የሮም የተጻፈ እውነተኛ የሰነድ ክምችት ነው። የኢትዮጵያ ወታደሮች በሻለቃ ዳዊት ላይ የሰላ ሂስ ሲያሰሙ፤ ተቃዋሚ ጋዜጠኞች ስለ እነዚህ ከፍተኛ የደረግ ባለሥልጣኖች ምን እያሉ እና ምንስ እየሸጡልን ነው? 

የተዘገቡ እውነተኛ ታሪካዊ ሰነዶችን እንመልከት”። ሻለቃ ጌታቸው የሮም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1983 ዓ.ም ሓምሌ 26 (የቀኑ ትክለኛነት በግለጽ ሰለማይታየኝ ምናልበት 26 ተብሎ ይነበብ) “ከደርግ መንግሥት ምሰጢራዊ ጉዳዮች” በሚል ታትሞ ለሕዝብ ይፋ የወጣው ሰነድ ዋቢ በማድረግ ያሳተሙት ሰነድ፤ ሻለቃ ጌታቸው የሮም ፤ሻለቃ ዳዊት ውለደጊዮርጊስ ደርግን ከድቻለሁ ብለው ውጭ አገር እንደቀሩ ወደ አለቃቸው ወደ ኮለኔል መንግሥቱ ሃይለማርያም ወደ ኢትዮጵያ በእጅ ጹሑፍቸው የጻፉትን ምስጢራዊ የግል ደብዳቤ ከመመልከታችን በፊት፤ በመግቢያው ላይ ሻለቃ ጌታቸው የሮም ስለዚህ ደብዳቤና ስለ ሻለቃ ዳዊት ያለቸውን ግምገማ ያሉትን እንመልከት።
“አገሪቱንና ሕዝቦቿን በግለኛ አገዛዝ የማሰነው የደርግ መንግሥት የዚህ ዓይነት የአፋና ተግባር ሲያካሂድና ሲመራበት የቆየ የደህንነት ተቋም፤ አለው። ይህ የደህንነት ተቋም የአፈና ሥራውን እንዴት እንደሚካሄድ የሚታይ ቢሆንም፤ለዛሬው ግን በጓዳው ውስጥ ካጠራቀማቸው ሰነዶች፤ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ኢትዮጵዮጵያን ጥሎ፤ከኮበለለ በሗላ ለመንግሥቱ ሃይለማርያም የጻፈውን ደብዳቤ እናቀርባለን።

ሻለቃ ዳዊት የኰበለ ሰሞን፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብት ምን ያህል እንደታገለ በየጊዜው መድረክ በተከፈተለት በአሜሪካን ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ የአማርኛ ክፍል ብዙ ተናግሯል። በሗላም ሬድ ቲርስ (Red Tears) ወይም ቀይ እንባ በተባለው መጽሐፉ መንግሥቱን አብጠልጥሎ ለመውቀስ የማይፈራ ደፋርና ቁርጠኛ የኢትዮጵያና የሕዝብ ልጅ እንደሆነ ለማሳየት ተጣጥሯል። የደርግ ምሰጢራዊ ጓዳዎችስ ምን ይላሉ? ሻለቃ ደዊት ከተሰደደ በሗላ ወኔ እንደነበረው ያመላክቱ ይሆን?
በምድረ ኢትዮጵያ እያለሁ በምንግሥቱ ፊትም ሳይቀር የልቤን ለመናገር ደፍረቱ ነበረኝ ይል እንደነበረው፤በስደት እያለስ መንግሥቱን እውነተኛ ማንነቱ ይገልጸው ይሆን? ሻለቃ ዳዊት- ለሻለቃ መንግሥቱ ወይስ ለሰፊው ሕዝብ ተቆርቋሪነት አንደነበረው ያሳዩ ይሆን? መልሱን በራሱ በሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ የእጅ ጽሑፍ ከተጻፈው የራሱ ደብዳቤ እናግኘው።” ይላሉ።

ሻለቃ ዳዊት በራሳቸው ጽሑፍ ይህ ሁለተኛ የደብዳቤ መልዕክት ጽሑፋቸው ነው። ተከታታይ ደብዳቤ አንደሚልኩላቸውም ደብዳቤው ላይ ጠቅሰዋል። የሻለቃ ዳዊት የእጅ ጽሑፍ ሰነድ ቅጅ/ኮፒ፤(ኮፒ ስካን) ያደረግኩላችሁን ከማንበባችሁ በፊት ጹሑፉ እጅግ ሰፊ ትንተና ያያዘ ሲሆን ባጭሩ ሻለቃው ለኮለኔሉ የሚሉት ይህንን ነው፡

ከገጽ 114 ልጥቀስ “ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት አመራር ከእርስዎ ሌላ አማራጭ የለውም ብየ እኔ አምናለሁ።”

 “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃላፊነቱ የሰጠው ለርስዎ ነው።” (ገጽ 115)

 ለትንሹም ለትልቁም ነገር የእርስዎ መመሪያ በሚጠበቅበት ሁኔታ፤የእርስዎ ፈገግታ፤እየርሰዎ አዎንታ ለማግኘት ብዙ ፍትግያ ይታያል። ከነዚህ ሁሉ ሃላፊነት ሥልጣን ሽሚያ ውስጥ የሌሉ እርስዎ ብቻ ነዎት። የእርስዎ መሰረት Power one-ሕዝብ ነው። አሁን አካባቢዎ ያሉ ሃላፊዎች ግን….’BASE’ በሌላ አነጋገር የሕይወታቸው፤የሕልውናቸው ወይንም የሥልጣናቸው መጀመሪያም መጨረሻም- እርሰዎ ነዎት።…የእርስዎ ልብ ለማሸነፍ ይቀጥፋሉ፤ይዋሻሉ..”(115-116)፤
ስለ ኤርትራ ጉዳይ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡ 

“ታዲያ ኩራታችን ይዘን ልንቀመጥ? በድህነት፤በጦርነት በዘወትር ሥጋት እንኑር ወይንስ አዲሱ ዓለም-ውስጥ ገብተን ዐለም የሚጫወተውን የፖለቲካ ጨዋታ እየተጫወትን ለማሸነፍ ለማግኘት እንሞክር? (116) 

ከላይ አገላለጻቸው ሻለቃው ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልጽ ነው።ዛሬም ለተገንጣይ አረብ ደላላዎች ጥብቅናቸው እንደቀጠለ ነው። ዞሮ ዞሮ፤ ኢሳያስ ተገንጥሎም የዓረቦች ፔትሮ ዶላር እየተርከፈከፈበት ጨዋታውን በሕዝብቻን ላይ እየተጫወተ አንደሆነ ለሁላችሁም ግልጽ ይመስለኛል። ወያኔ ዓለም የሚጫወተውን ጫዋታ እንጫወት ብሎ ኤርትራን አስገንጥሎ ባሕራችንን አስዘግቶ ለዓረቦች ተሰጠ። ተከብበን አንገኛለን! ዓለም የሚጫወተው የግሎባላይዘሸን ፕሮፓጋንዳ አስራጮች እነ ሻለቃ ዳዊት እና፤ እነ ካሳ ከበደ ዓለም እየተጫወተው ያለው “አዲሱ” ጫዋታ እንቀጥልበት እያሉን ነው። ሚዲያቸውም ያው ኢሳት ነው። እየተለፈፈብን ያለውም ያው እዚያው ነው።

 ኩራት ወይንም ውርደት! አዲሱ የዓልም ጨዋታ! የፖለቲካ ወይስ የወታደራዊ መፍትሔ የሚለው የሻለቃው ጥያቄ እውነት ያስቃል።ደርግን የጣለው በወታደራዊ መፍትሔ ስለሄደ ሳይሆን ኤርትራ ልትገነጠል የበቃችው፤ “የብዙ ምክንያቶች ክምችት ነው” (መንግሥቱ የመጀመሪያው ተጠያቂ ቢሆኑም) አብረው በዙርያ ሥልጣን እና በወታደራዊ፤በስለላ መዋቅር የነበሩ ባለሥልጣኖች በተገንጣዮች የቤት ሥራ የተ-ተበተቡ ቅጠረኞች ፤አገራዊ ፍቅር የጎደላቸው ካሃዲዎች ስለነበሩ ነው። በዚያው የአሜሪካኖች የስለላ መዋቅር ተንሰራፍቶ ደርግ  እጉያውና ማንቁርቱ ውስ  ገብተው ምን ይሰሩ እንደነበርና ለተገንጣዮች የስላላ እና የወታደራዊ ዕርዳታ ሳተላይት እና ራዲዮ እርዳታ ያደረግ እንደነበር አይዘነጋም። ለዚህ ማስረጃ እነ ደረጀ ደሬሳ፤ እነ ክፍሌ ወዳጆ ከአሜሪከን ገንዘብ አየተቀበሉ ፤ በአንዱት ሴት አሜሪካዊት መሪነትና አማካሪነት ሱዳን ውስጥ ምን ይሸረብ እንደነበረ ሻለቃው የሚያውቁት ምናልባትም እጃቸው የጨመሩበት “ ዓለም ሲጫወተው የነበረው አዲሱ የዓለም ጨዋታ” ምን ይመስል እንደነበር ሻለቃው ሱዳን ኤርትራ ሲመላላሱ የሚያውቁት ጉዳይ ነው። ኤርትራ በዚህ መልክ ነበር የሄደቺው፤ወያኔም በዚህ ሽራባ ነው የገባው፤ ደርግ በግራም በቀኝም በራሱም እንደ አበደ ውሻ እራሱ እየነከሰ ለውድቀት ደርሷል። ግልጽ ግልጹን!

እንቀጥል፤

በገጽ 118 ላይ ሃይሉ ይመኑ በተባሉ የደርግ ባለሥልጣን ላይ ሻለቃው ለመንግሥቱ ሃይለማርያም ምን ብለው እንደጻፉላቸው ስትገነዘቡ፤ ሰው ለጓዱና ለዜጋው ሞት እና ግርፋት እንዴት እንደሚመኝለት ታያላችሁ። ሻለቃው እራሳቸው በካቢኔው ውስጥም ሆነ በመሪው ፊት እና በባለሥልጣናት ስብሳባ ወቅት ለመናገር ድፍረቱ ያጣ የገዛ ራሳቸው ሃሞት ሳይገመግሙ የትግል ጓዳቸው የነበሩት ሃይሉ ይመኑ ላይ “ድፍርት ለምን እንዳልኖረራቸው ለኰለኔሉ ደብዳቤ ጽፈዋል”
በገጽ 119ም እንደ እነ ጀኔራል ሃይለጊዮርጊስ ወርቅነህን ያረጁ ያፈጁ የሚያሾፉ መኮንንኖችን ትዕግስት ማድረግና መሸከምዎ አግባብ አይደለም ሲሉ ኮለኔሉን ምክር ሰጥተዋል። ለእርሰዎ threat የማይሆኑ ሰዎች ከሆኑ መምረጡ ትከክል ነው…. በጀኔራልነት ማዕረግ ያሉትን ያረጁ ያፈጁ እያሉ ሲወርፏቸው፤ በሻለቃው ዕድሜ ክልል ያሉ መኮንኖች ግን ሲያብራሩ ማባረርን ተገቢ እንዳልሆነ እና “መሰሪ” ዬሚሏቸው ሰዎች እየተሾሙ ለኮለኔሉ ታማኝ የሆኑትን ሰዎች ማራቅ ተገቢ አይደለም ሲሉ ሻለቃው ኮለኔሉን ይመክራሉ። ለእርስዎ threat የማይሆኑ ሰዎች ከሆኑ መምረጡ ትከክል ነው….  (እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስቶስ!) (118-119) 

በዛው በገጽ 119 ደግሞ በእልህና በሃይል የማያምኑ መሪ ነዎት፡ በማለት ኮለኔሉን ያሞግሳሉ። “ብዙ መሪዎች ራሳቸው ላቋቋሙት ሥርዓት መውደቂያ የሚያዘገጁት፤ የራሰቸው ዕቅድ ትክክል ነው ብለው በማመን የሕዝብን ግን ባለማመዛዘንና የሕዝብን ድምፅ ባለመመልከት በእልህና በሃይል ለማሳየት ሲሞክሩ ነው። እርስዎ እንዲህ አንዳይደሉ ይሰማኛል።”

ጓድ ሊቀመንበር!

እኔ ተንፍሻለሁኝ። በቅንነት የጻፍኩትን እርስዎን አስቆጥቼ እንደሆነ ግን በጣም ነው የማዝነው። እርስዎን የረዳሁኝ መስሎኝ ነው በቅንነት ያቀረብኩት። በዚህ ምልክ ይቀበሉኝ… ሌላ ምንም ምክንያት የለኝም። ለወደፊት በዝርዝር ስለምጽፍለዎ ይህ መግቢያ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። (119)
አብዮቱን በቅን ያገለገሉ፤ ለአብዮቱና ለአመራሩ ፍጹም ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከእርስዎ እየራቁ መሄዳቸው ያሳስበኛል። ለአብዮቱና ለእርስዎ ሁልጊዜ ታዛዥ ወንድምዎ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ።
*- ለእርስዎ ብቻ የተላከ የግል ደብዳቤ ነው፡

*በጓድ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ በኩል ስለተላከ እንደሚደርስዎት አርግጠኛ ነኝ።

ሲሉ በሰፊው የጻፉት ሰፊ የግል ደብዳቤ ለማንበብ እነሆ ከዚህ በታች ያለውን ቅጅ/ፎቶ ኮፒ አንብቡ:: በተረፈ ሻለቃው ሊቀመንበር መንግስቱ “ሃይልና እልህ” የማይጠቀሙ ናቸው በማለት ባቆለባበስዋቸው አመራር ሥር የተካሄደው በዜጎች ላይ የመብትና የጭካኔ እርምጃ ለማወቅ በባቢሌ ቶላ በእንግሊዝኛ የተጻፈው “አንድ ትውልድ ለመምተር ቀይ ሽብር በኢትዮጵያ” የሚለውን በጸጋየ ገብረመድህን (ደብተራው) ባማርኛ የተተረጎመው መጽሐፍና ሰነድ ያንብቡ።
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ
(የኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ፤ አሜሪካ ሳንሆዘ ካሊፎርኒያ) (Ethiopian Semay)  getachre@aol.com posted at welkait.com, Ethiopatriots.com, (Ethiopian Semay blogspot.com) and (Google it - Ethiopians semay face book). If you need to copy the document for personal usage/public usage- please email me you will get the unrestricted document (since this one is restricted).


No comments: