Wednesday, December 23, 2015

“የነገድ ፌደራሊዝም” የግማሽ ንክ ግለሰቦች የፖለቲካ ቅዠት ነው ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ብሎግ አዘጋጅ)


“የነገድ ፌደራሊዝም” የግማሽ ንክ ግለሰቦች የፖለቲካ ቅዠት ነው
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ብሎግ አዘጋጅ)

ወደ ርዕሴ ከመግባቴ በፊት መጀመሪያ አበራታች የሆነ የምስጋና ኢመይል ለጻፋችሁልኝ ለወንድሞቼ አቶ ተድላ አስፋውና አቶ ሰመረ አለሙ እንዲሁም በርካታ እህቶችና ወንድሞች ጊዜ በማጣቴ በጊዜ መልስ ያልሰጠሁዋችሁ ወገኖቼ እንዳትቀየሙኝ እዚህ ላመሰግን እወዳለሁ።

ቀጥሎም፤ አበበ ቦጋለ የተባለው በግንቦት 7 የተጠለለው የኦነግ ፕሮግራም አራማጅና የግንቦት 7 አማራር አባል፤ ሰሞኑን እሱን በሚከተሉ ጀሌዎቹ ፓልቶክ ተጠርቶ ስለ የሰሞኑ የአሮሞ ተማሪዎች ንቅናቄ እንዲያብራራላቸው በተጠየቀበት ወቅት፤ ካሁን በፊት ደጋግሜ አንደገለጽኩላችሁ ልክ አንደ ብርሃኑ ነጋ፤ አበበ ቦጋለም ፤የመገንጠል ጥያቄ በሕግ/በፖሊሲያችን አንገድብም! መገንጠል እፈልጋለሁ የሚል የፖለቲካ ነገድ /ደርጅት ካለ፤ (ይታያችሁ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም ለሬፈረንደም የሚያቀርበው) አዲስ የሚዋቀር መንግሥት ‘አላረካኝም’ ካለ “ለነገዱ ሕዝብ” አቅርቦ “በደምፅ ብልጫ/ሬፈረንደም” ሊገነጠል ይችላል ብሏል።

እኔ ካሁን በፊት ግንቦት 7 የማልደግፍበት ምክንያት ወደ ኤርትራ ሄደ/አልሄደ ሳይሆን ዋነኛው ክርክሬ፤ መክንያቶቼ ብዙ ቢሆኑም (1ኛ) ጸረ አማራ በመሆኑ (አመስረጃ አቅርቤአለሁ) (2ኛ)-ልክ አንደ ወያኔ አንቀጽ 39ኝን ተግባራዊ ለማድረግ የፈለገ አገርና ቤተስብ አፍራሽ ሁሉ በድምፅ ብልጫ እንደ ኤርትራ የመገንጠል መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ደጋግመው ስለመግለጻቸው፦ (3ኛ) ግንቦት 7ን አምነው ወደ ኤርትራ የሄዱ ዜጎቻችን “ሄልኮፕተር” ተብሎ በሚታወቀው ኤርትራኖች ሰው የሚያሰቃዩበት እኛ “ወፌ ላላ” የምንለው የድብደባ ስቃይ እንዲሰቃዩ፤እስር ቤት እንዲማቅቁ በማድረግና ለሻዕቢያ ገራፊዎች አስተላልፎ ደብዛቸው እንዲጣፋ በማድረግ የተሰወሩ ሰዎችን በግድያ የሚጠየቅ ሰብአዊ መብት ተጠያቂ የሆነ ወንጀለኛ ድርጅት መሆኑን የመሳሰሉ ነጥቦችን፤ ግንቦት 7ን የማልደግፈው መክንያት የተከራከርኩበትን ነጥቤን ግልጽ አድረጌአለሁ። ከዘረዘርኳቸው ሦስቱ ውስጥ “በሁለተኛ ነጥብ” የተጠቀሰው “የግንጣላ ጉዳይ” ዘሬ አበበ ቦጋለ ሳይደባብቅ ግንቦት 7ትም ልክ እንደ ወያኔ እንደሚያምን ግልጽ አድሮጎላችኋል። አሁን ግንቦት 7 እና ወያኔ መምረጥ ምን እሳት አንደሚጭርባችሁ መገንዘብ ካልቻላችሁ፤ የራሳችሁ ጉዳይ!

በተያያዘም፤ ምስኪኗ ጋዜጠኛዋ ርዕዮት፤ ግንቦት 7ን  መቀላቀሏን ነግራናለች። ግን….ግን…. በተቀላቀለችበት ድርጅት ውስጥ ደብዛቸው የጠፉና የተደበደቡ፤ ኢሳት በፍርሃት ምክንያት ለአለቆቹ ወግኖ እንዳያቀርባቸው አምቢ ብሎ፤ “ከድብደባው” እንደ ዕድል ያመለጡ ታጋዮች “ግንቦት7 ዲ” በማለት ድረገጽ ከከፈቱ በኋላ የግንቦት 7 መሪዎች “ጉድ” ያስነበቡን ግለሰቦች ፤……. ፤ ኢሳትን በደብዳቤ “ሕዝብ እንዲፈርደን ከግንቦት 7 መሪዎች ጋር በራዲዮናችሁ፤ ቴሌቪዢናችሁ አገናኝታችሁ አነጋግሩን፤ ብለዋቸው “መድረክ” ስለ ተነፈጉ ሰዎች አንደ ጋዜጠኛነቷ እና ተጋይነቷ ኤርትራ ድረስም ሄዳም ሆነ  አውሮጳ ያሉትንም “ሃቁን” አጣርታ ታቀርብልን ይሆን? የሚል ጥያቄ አቀርብላታለሁ። ከዚህ ጸረ አማራ ድርጅት ሆኜ ለመታገል “ተቀላቀያለሁ” ብላለችና  ኤርትራ ከሄደችም ፤ እሷንም ከዚያ ማኣት ማርያም ትጠብቃት ከማለት ሌለ ምን ይባላል። አስገራሚ ጊዜ። ከድጡ ወደ ማጡ!

ወደ ርዕሴ ከመግባቴ በፊት በሌላ ቀን፤ በዚህ ጉዳይ እስክመለስበት ጊዜ አስገራሚው የሆነ ብዙዎቻችሁ ስትሞኙና ስታሞኙ የነበራችሁ ጀሌ“ግርምቢጦች” አበበ ቦጋለ ግልፅ ያደረገላችሁን ልንገራችሁ። ግንቦት 7 ፖሊሲ/ፕሮግራም የለውም፤ ምንግሥትነት/ለሥልጣን አይደለም እየታገለ ያለው ሲሉ ደጋግመው ሲዋሹዋችሁ፤ እናንተ ጀሌዎቹም ተቀብላችሁ ስታስተጋቡ ነበር። አበበ የነገርን ግን፤ ግንቦት 7 “ፖሊሲን አስምልክቶ የፖቲካ ድርድር ማድረግ እንደሚችል” ፤ “የመገንጠልን ያክል አንገብጋቢ ፖሊሲ” ሳይቀር “በሬፈረንደም” መግንጠል አንደሚቻል ድርጅቱ የሚፈቅድ መሆኑ፤ ወዘተ ወዘተ ነግሯችኋል። ግንቦት 7 ወያኔ ለመጣል እንጂ “የፖለቲካ ፍላጎትም ሆነ፤ፖሊሲ/መመሪያ ፕሮግራም የለኝም” እያለ ሲዋሽ ቆይቶ፤ ሬፈረንደም ሁሉ እስከመፍቀድና፤ ከማንኛውም ተደራዳሪ “የሚጠይቀው ሁሉ ‘ግንቦት 7 ኮምፕሮማይዝ” የሚያደርግ “ተደራዳሪ ድርጅት” እንደሆነ ዛሬ ግልፅ አድርጓል።  ካሁን በፊት ለተጃጃላችሁ ምስኪኖች፤ ደርጅታችሁ “ድርጅቱ የሚመራበት ፕሮግራምና ፖሊሲ” የለም ሲል፤ ሲያጃጅላችሁ ከርሞ፤ ዛሬ ሳያስበው ድንገት አበበ ቦጋለ “በድንገት ባርቆበት” ፖሊሲያቸውን ግልጽ አድርጎላችኋል። በዚህ አጋጣሚ ኦነጎችና መሰል ተገንጣይ ፋሺስቶች ወያኔ ተክቶ ሲመጣ ግንቦት 7 የወያኔን ኮፒ/አንቀጽ 39ኝን ተግባራዊ እንደሚያደርግላችሁ ቃል ስለገባላችሁ “አንኳን ደስ አላችሁ!” እላለሁ። ለዚህም ነው ኦነጎችና ኤርትራኖች ግንቦት 7ን ከሌሎች ድርጅት የሚደግፉት ዋናው ነጥባቸው።

ይኼ ፖለቲካ ራስ ምታት ነው ጃል! አይደል? ወደ ርዕሳችን እንግባ።

ፖለቲካው ስንገባ ፖለቲካ ማለት በቀለለ ትርጉሙ “የአስተዳዳር ዘይቤ፤የቅስቀሳ ዘዴ” ብዬ ተርጉሜዋለሁ። በራሳችሁ ትርጉምም ሂዱበት፡ ግድየለኝም። ዛሬ ለማሳየት የፈለግኩት ግማሽ ዕብድ ፖለቲከኞች የሚወዱት ፖለቲካ ነው። ፌደራሊዝም የሚባል ፖለቲካ!

ለበርካታ አመታት “ፌደራሊዝም” የውጭ ቋንቋ ሆኖ፤ ትርጉሙም በትክክል ባይታወቅም፤ ያገራችን ታዋቂው “ቀልድ ነጋሪው” ታማኝ በየነ ካልተሳሳትኩ “ፌዝ-ራሊዝም” የሚል ትርጉም የሰጠው መሰልኝ (በደምብ ትዝ አላለለኝም ተሳስቻለሁ መሰለኝ አርሙኝ) አውነትም ቀልድ ነው። ከዚህ ቃላት ጀምሮ ማለትም  “ፌደራሊዝም”፤ “ዲሞክራሲ”፤ “ብዙሃን/ማጆሮቲ”፤ “ጥቂት/ ንኡሳን/ማይኖሪቲ”፤ “ሕዝበ ውሳኔ”፤ “ብሔር/ብሄረሰቦች/ሕዝቦች”…. የመሳሰሉ፤በቃላት እንጂ “በተግባር ሲተረጐሙ” ትርጉመ ቢስ ወይንም ስራ ላይ ሲውሉ “ዲክታቶሪያላዊ” ውጤት ሆነው እየታዩ ነው።

“ማርና ወተት” የሚያምበሸብሹ “እስከሚመስሉ” ድረስ “ተደጋግመው” ሲነገሩ ሰምታችኋል። እነኚህ የተጠቀሱት “አስተዳደሮችና ትርጉሞች” “ለሰው ልጅ” መብት ሰላምና ብልፅግና “በር ከፋች” መንገዶች ናቸው ብለው ባብዛኘው የሚነግሩን ክፍሎች ደግሞ እነማን ናቸው ብላችሁ ብትጠይቁኝ፤ ለግለሰብ ሰብአዊ መብት የቆሙ ክፍሎች ሳይሆኑ “ለብዙሃን መብት” ቆመናል የሚሉ “ኮለክቲቪስት” የሚባሉ ክፍሎች ናቸው። ኮለክቲቪስቶች ደግሞ “ፋሺዝምን”  “ሶሺያሊዝምን/ኮሚኒዝምን/የብዙሃን ዲክታቶር-ሺፕ/ የሚያራምዱ ሰዎች/ድርጅቶች/ ናቸው።” ማጆሪቲ ጋቨርንስ ዘ ማይኖሪቲ/” ብዙሃን ይመውኡ”፤ ንኡሳን ማለትም ግለሰብንም ያጠቃልላል፡ መብቱ ተረግጦ ለብዙዎቹ ተገዥ ይሆናል ማለት ነው። አንድ አማራ ወይንም ጥቂት አማራዎች፤ ብዙሃን ኦሮሞ ወይንም ብዙሃን ነገዶች ክልል…. በሚኖሩበት ክልል ውስጥ ከኖረ፤ ግለሰባዊ/ዜጋዊ መብቱ በብዙሃኑ ፍላጎትና ውሳኔ ይነጠቃል ማለት ነው። ይህ ደግሞ “ዲክታተሪያል” ይባላል።

የኮለክቲቪስት ፖለቲካ ርዕዮት የጀመረው ‘ከሶቭየት ሶሺያሊስት/ከቻይና/” እስከ ሂትለራዊት ጀርመን እና ሞሶሎኒትዋ ጣሊያን እና የነዚህ ክፍሎች ርዕዮት ተቀብለው ያራመዱ በየአገሩ እሰከ አሁኗ የወያኔ ኢትዮጵያ እና እስከ ኦነግ/አብነግ ወዘተ የመሳሰሉ በብዙሃን እና በነገድ (ለፖለቲካ) የተሳባሰቡ ክፍሎች ብዙ ሕዝብን ያበጣበጠ ርዕዮት ያጠቃለለ ነው። እነዚህ ክፍሎች የቆሙት” ለግለሰብ ነፃነት ሳይሆን “ለብሔራቸው፤ለሃይማኖት ድርጅታቸው፤ለቤተሰባቸው፤ለክልላቸው፤ለፖለቲካ ድርጅታቸው፤… መብት” የቆሙ እንጂ “ለሰውልጅ/ለግለሰብ” መብት ቀዳሚ ትኩረታቸው አይደለም። ይህ ሲሆን፤ ከስብስቦቹ/ከኮለክቲቪስቶቹ/ “ማሕበር ውጭ” የሆነ “ግለሰብ” (የሰው ልጅ) እነሱን ካልመሰለ፤ ለማሕበራቸው የተከራከሩለትን “መብት/ነፃነት” ተጋሪ አያደርጉትም።

 ስለሆነም፤ ኮለክቲቪስቶቹ (በነገድ (ጎሳ) ተከልለው የራሳቸው አስተዳደራዊ መዋቅር፤ ባንዴራቸውና ቋንቋቸው ዘርግተው….) የተዋቀሩ ክፍሎች የግለሰብ መብት ተፃራሪዎች በመሆን፤ እነሱን የማይመስል ግለሰብ “ከማሕበሩ ባይተዋር እንዲሆን በማድረግ፤የቆየ የበሰበሰ የተረሳ፤መሰረተ ቢስ የሆነ ታሪክ እየመዘዙ ዘላቂ ፀብ ለመጫር አንዲመቻቸው “ኦነሌ የመሳሰሉ ሃውልቶችን በመትከል” ወይንም እስከ ግዲያ እስከ ማባረር፤ንብረቱን እስከ መዝረፍ፤ማንገላታትና ማሰር በሚደርስ” ወንጀል ተዋናይ ይሆናሉ (በሌላ አነጋገር ከዱር እንሰሳት ሕሊና ያልወጡ ተበቃዮች ይሆናሉ ማለት ነው)። ተዋናዮቹ ‘ማሕበረሰባችን/ነገዳችን/ክልላችን’ ብለው ከከለሉት አጥር ውጭ ተሻግሮ/ዘልሎ የሚመጣ “እነሱን የማይመስል” ሁሉ እንደ ‘ጠላት/ወራሪ/ በማየት ‘የንብረት፤የመሬት ተቀናቃኛቸው’ አድርገው እንዲመለከቱት ያደርጋሉ።

ሕዝባቸውን በቁጥጥር ለማድረግ አደራጂዎቹ የሚጠቀሙበት ዘዴ “እንወክለዋለን የሚሉትን ማሕበር” በወንጀል ባሕሪያቸው ተካፋይ እንዲሆን፤ እነሱን በማይመስሉ ነገዶች ምክንያት “ማንነቱ/ባህሉ፤ቋንቋው፤ንብረቱ/መሬቱ/ሚስቱ/ተራራው/ወንዙ/ሃይማኖቱ/ባህሉ…” እንደተነካ ወይንም ሊነጥቀው አንደመጣ “ወራሪ” አስመስለው በመቀስቀስ ‘በመጤዎች’ ላይ አመፅ እንዲያስነሳ በመገፋፋት፤ ለረዢም ጊዜ ጠብ አንዲኖረው በማድረግ “ነገዳቸው በአንድነት/በጋብቻ’ “ከመጤዎቹ” ጋር እንዳይቆራኝ አድርገው “ነገዳቸው በማንነት ክር” ተብትበው “በቁጥጥራቸው” ሥር ያደርጉታል።

የነገዶቹ ግለሰብ አባላት ከሌሎች ጋር የነበራቸው ማሕበራዊ ግንኙነቶች በሙሉ “ለዓይን በማይታይ ሕሊና ውስጥ የሚፈነዳ ቦምብ በማቀጣጠል” አፈንድተው እንደማይሆን አድርገው ይበታትኑታል። ሕብረተሰቡ ውሎ አድሮ “ከቅዠቱ ሲባንን”፤ ደራሲውና የ ኢሕአፓ መስራች መሪ “ሃማ ቱማ” (ኢያሱ ዓለማየሁ) “GIVE ME A DOG”S LIFE ANY DAY” African Absurdities II” በሚባለው ድንቅ መጽሐፉ እንደገለጸው ‘ነፃነት’ ብለው የደገፉት *ነፃነት* ተስፋ በሚያስቆርጥ ውጤቱ *ባርነት፤ችጋር፤ኢፍትሓዊ በደልና ውርደት ነግሶ* እነኛ በማስገንጠልም ሆነ በኤትንክ ፌደራሊዝም ማርና ወተት ታገኛለህ ብለው ያሞኙት “የክልል መሪዎችና ገንጣዮች “ዙፋን” ላይ ተቀምጠው የባሰውኑ “ጨቋኞችና ብጥብጥ አስነሺዎች” ሆነው ያገኛቸዋል። ኗሪዎቹ ሕይወት አዳጋች ሆና ያገኟታል። ኤርትራ የተጓዘችበትና የታየው ክስተት፤ እንዲሁም “ሶማሊያ” የተጓዘቺበት መንገድ ስትመለከቱ የሊሂቃን/የጎሳ/ክላን አባቶች/መሪዎች (ዋር ሎርድስ) የቀረጹት “የኮለክቲቪስት ርዕዮት” ውጤት ነው።

ፌዴራሊዝም በስያሜውና በስነ ትርጉም “የመብት አጎናጻፊነትን ልብስ የሚያለብስ ይመስላል። ሆኖም ከማንኛውም ‘አሃዳዊ/ፓርላሜንታዊ ስርዓት’ ይልቅ በነገድ/ በኮለክቲቭ/ በቋንቋ የተዋቀረ ፌደራሊዝም “ሥርዓተ አልባነትን” በሰፊው ያሰፍናል። ሶማሌ ውስጥ ስትመለከቱ “ሰቴት-ለስ/መንግሥት አልባ” የሆነችበት መንገድ ሲመረመር፤ አንዳንድ ኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች፤ የሶማሊ ኤሊቶች እና የውጭ ተንታኞች “የውጭ ጣልቃ/ፕሮክሲ” “ኢትዮጵያ በወረራ ስለገባችት ነው” የሚል ምከንያታዊ ሽፋን ቢሰጡም፤ አሃዳዊው “የስያድ በሬ” መንግሥት ከፈረሰ በላ፤ ማሕበረሰቡ “ገደብ የለሽ የራስ ገዝ አስተዳደደር መብት” እናመጣልሃለን ብለው ፖለቲካውን ብጥስጥሱ አውጥተው አገሪቱን ያናጓት የሥልጣን ጥመኛ ሊሂቀን ክፍሎች፤ ጫና በመበርታቱነው።
ይህ ደግሞ “በናሺናለዝም ሽፋን” (የባዕድ ወራሪ መጣብን ሽፋን) “ግማሽ ዕብደት” የተጠናወታቸው በሶማሊ ውስጥ  የሚገኙ የተለያዩ “የወታደራዊ፤ የጎሳ፤ የዓብደል ውሃብ ሃይማኖት አቀንቃኝ “ውሃባይት’ መሪዎች፤ በየመአዝናቱ ተበትነው “በሰለጠነ ሕግ ያልተዋቀረ/ቁጥጥሩ የላላ፤ ስርዓተ አልባ የሆነ ፤ “የራስ ገዝ/ፌደራሊዝም” ግማሽ ንክ በሆኑ ክፍሎች መሪነት ትርጉም ላይ ሲውል ያስገኘው አሳዛኝ ውጤት ነው።

የሶማሌ ውድቀት ላገራችን ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይገባል። ክላኖች/ነገዶች በቋንቋቸው፤በሃይማኖታቸው የራሳቸው አስተዳዳርና ተከታዮች ኖሯቸው “ሙሉ ነፃነት” አውጀው፤ እርስ በርስ በጠላትነት እየተያዩ፤ እስከ አልሸባብ ድረስ “የተጓዙበት መንገድ” ምክንያት የሆነው “የጎሳ መሪዎች/ፖለቲከኞች” ማአከላዊ መንግሥት በቅርበት የማይቆጣጠረው “ገደብ የለሽ” (ወያኔዎችና ኦነጎች “ያልተሸራረፈ” መብት የሚሉት ዓይነት) ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት “የክልል-አምባገነኖችን” እያራባ መፈልፈል እንጂ ማስወገድን የማይችል በመሆኑ ነው።

አምባ ገነኖችን ማራባት ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሶማሌ “በይፋ ያልታወጀ” ይሁን እንደ ኢትዮጵያ በይፋ በመንግሥት የተዋቀረ አዋጅ የተዘረጋ “ቋንቋን/ጎሳን መሰረት ያደረገ “ፌደራሊዝም” ሥራ ላይ ሲውል፤  እንደ “ጎበጠ ምስማር” ለማስተካካል እጅግ የሚያስቸግር “ጠማማ” ስርዓት ነው። ለማስተካካል ሲሞከርም ‘እሳት ጭሮ’ በማሕበረሰቡ ውስጥም ሆነ ባካባቢው የሚኖሩ ነገዶች የማያባራ ብጥብጥን ያስከትላል። ፌደራሊዝም ዕብዶች የሚከተሉት የኮለክቲቪስት ርዕዮት ነው የምልበት ምክንያትም ይህ ነው። ሰሞኑን በጉልህ የወጣው የወልቃይት አማራዎች የጥጥቅ ንቅናቄ ስትመለከቱ “Hegemony/ሄጀሞኒ/ወይንም አኔክሰሺን/ በትግርኛ “ጉብጣን” የምንለው፤ አማርኛ ምን አንደሚባል አላውቀውም (ምናልባት ‘መዋጥ/መውረር’ (?)) ያስከተለው ‘ኮሊክቲቪሰት ፋሺሰትቶች” የዘረጉት “ኤትኒክ ፌደራሊዝም” ብሎ የሰየመው አስተዳዳራዊ “የሄጀመኒ” ውጤት ነው። የነገድ ፖለቲካ ማለቂያ የሌለው “ውረር ተዋረር” አቤቱታና ግጭትን የሚያስከትል “ጤነኛ” የነበረ ማሕበረሰብ ወደ “ዕብድነት” ለውጦ “ንክ” የሆነ ማሕበረሰብን የመፍጠር በር ይከፍታል። 

ኤትኒክ ፌደራሊዝም ፋሺስታዊ ነው ብለን መደምደም ብቻ ሳይሆን “አስጎምጂ” መስሎ፤ “ስትይዘው” ግን “ከእጅ አምልጦ” የሚሰበር “ዕንቁላል” ነው። “አስኳሉ” ከፈሰሰ በላ፤ ዕንቁላሉ “መልሼ ልጠግን” ብትል ውጤቱ ፍፁም የማይቻል “የፈሰሰ ውሃን የማፈስ” ከንቱ ሙከራ ይሆናል። አገር ለማፍረሰም ፌደራሊዝም ጥሩ የማፍረሻ ዘዴ ሆኖ የተገኘ “ግማሽ ንኮች/ዕብዶች” የሚከተሉት የአስተዳደር ዘዴ ነው። የውጭ ሃይላትም ወዳጅና አማካሪ መስለው፤ ይህ ሥርዓት እንዲስፋፋ በጉጉት የሚፈልጉትና እጅግ የሚደግፉበት ምክንያታቸው አገርን ያለ ውጊያ በቀላሉ ለማምበርከክ ሲፈልጉ የሚጠቀሙበት ቀላል ዘዴ ስለሆነ ነው። እንድንጠነቀቅ ሁሌም ደጋግሜ የምገልጸው ቃል “ሳብቨርዢን” የምለውም ይህንን አዳጋ የሚያስከትል በመሆኑ ነው።
ይህ አደጋ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከተለው የጎሳ ፌደራላዊ አስተዳዳር “መገንጠልን” ሕጋዊ ያደረገች ብቸኛ  አገር እንደመሆኗ መጠን “የጣሊያን ፋሺስት ወራሪዎች ኢትዮጵያን ለቀው ከሄዱ በላ፤ ለመተግበር አቅደውት ዕቅዳቸው ተቀጭቶ ባጭር የቀረው የመጨረሻ ግባቸው፤ ዛሬ በትግሬዎች መሪነት ግቡን በመምታቱ አንጀታችን እየተቃጠለም ቢሆን ፤ግባችሁ እንደማንኛውም ስርዓት ቀኑ ደርሶ፤ አርጅቶ ራሱ እስኪፈራርስ ድረስ “ፋሺስቶችና የፋሺስት ጀሌዎች እንኳን ደስ አላችሁ” እንላችለን ።

እጅግ የሚገርመው ክስተት ደግሞ፤ ፌደራሊዝም የሚያራምዱ ሊሂቃን፤ ለተመልካች በአካል ጤነኞች ይምሰሉ እንጂ “አገርን የማፍረስ፤ነገድን ከነገድ ማናከስን” የሚያረካቸው እንደ “ልዩ ጀብድ” አድርገው ይመለከቱታል። ስለሆነም በስነእምሮአዊ ጤንነታቸው “ግማሽ ንክ” ናቸው። በተለይ “ኤትኒክ ፌደራሊዝም” (ብሔር/ነገድ ብለው የሚጠሩት የራስ ገዝ ፌደራሊዝም) የሚከተሉ ሰዎች (ኦነግ እና የወያኔ ጀሌዎች ንግግራቸውና ጽሑፋቸውን ስመለከት) “ፋሺዝምን” በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በቀላሉ የሚተረጎምበት አስተዳዳራዊ ስልት መሆኑንም የተረዱ አይመስሉም። እንደምገምተው “ጎሰኛነት አስካሪ ስሜት ስላለው” ፤የሚራመዱት የተወላገደ እርምጃ የት አንደሚረገጥ አይታያቸውም።

 ጎሰኞች ሊፈላሰፉ ፤የኔን አባባል ሊያሳንሱ ይሞክሩ ይሆናል። ሃቁ ግን ፌደራሊዝም ምንም በሉት ምንም፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ “ከሌሎች ጋር ተዋህዶ ላለመኖር” ፋሺስቶች የሚመርጡት ‘የመከላከያ ምሽግ’ ነው። አሜሪካም ሆኑ ሌሎች በፌዴራል የሚተዳደሩ አገሮች መነሻቸው “ጥበትን የሚያተኩር/አካባቢያዊ” ስርዓትነው። ለምሳሌ አሜሪካ ስትምለከቱ “ደቡብ/ሳውዝ/” ያሉት የፌዴራል መንግሥታት/ስቴቶች’ የጋራ እይታ፤የጋራ ብልጽግና/አስተዳዳር/… የሚሉ ቃላቶች በሕልማቸውም የለም። ኮለክቲቪስቶች/አካባቢያን/ቡድንተኞች ሆነው ነው የምታይዋቸው። ሆኖም እንደ  ወያኔዎችና ኦነጎችና ኦብነጎች “ጸረ ኢትዮጵያ” አፍራሾች ሳይሆኑ፤ ለአገራቸው ለአሜሪካ የቆሙ፤ በአሜሪካ ላይ ‘ያነጣጠረ’ የፕሮፓጋንዳም ሆነ የአካል ጥቃት ሲመለከቱ አጅግ ላገራቸው ለአሜሪካ የሚብከነከኑ “ናሺናሊሰቶች/ብሔረተኞች” ናቸው።

ሆኖም፤ ፌደራሊዝም አካባቢያዊነትን ስለሚያጎለብት፤ ለተወሰኑ አካባቢ የሚኖሩ “ነጮችን” መብት የቆመ፤የሚከራከር አግላይ የፌዴራል መብት የሚደግፉ ናቸው። ፌዴራሊዝም ያንን አግላይ/ዘረኛ ባሕሪያቸው አንዲጠብቁበት ሙሉ መብት ሰጥቷቸዋል። “Fire Eaters” የተባሉ በፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር በ1861 አካባቢ የተነሱ ተገንጣዮች (ካልተሳሳትኩ 13 መንግሥታት ነበሩ ግንጣለን ያቀነቀኑ) መነሻቸው ዛሬ እነ ኦነግ እነ ወያኔ እነ ኦብነግ ወዘተ…..የሚቃዡት “ራስ በራስ ማስተዳዳር” የሚባለው የጎሳ/ዘር አስተዳዳር ተሞርኩዘው “የራስ ገዝ /ፌደራል አስተሰዳዳርን ተቀብለው” ቀስ ብለው፤ ወደ “ግንጣላ ጥያቄ” ያቀነቀኑ የደቡቦች ተገንጣይ ንቅናቄ ክፍሎችን ስናስታውስ፤ የዚህ ቡድን ንቅናቄ አነሳስ ስትምለከቱ ፌደራሊዝምን እንቀበል ከዚያ ግን ጉዱን መርምረን ካልተመቸን ከሰሜኖቹ ‘እስቴቶች’ እንገነጠላላን የሚል ታክቲክ ያዙ።

 አንዳንዶቹ ደግሞ፤ “መነሻቸው” የሆነው “ባርያን/አፍሪካኖቹን” አንደ ንብረት የመቁጠር መብታችን ልንነጠቅ ነው፤ ስለዚህ የእንግሊዝ ኮሎኒ ነበርን፤ ብለው “አንደንትን በማንኳሰስ” እንገንጠል ብለው ወደ ግንጠላ ሄደዋል/ተዋግተዋልም።

ወደ አገራችን ተገንጣዮች ስንመለስ ደግሞ፤ “የጥቁር ሕዝቦችን ክብር” ከትቢያ አንስተው “በወርቅ መንበር እንዲቀመጥ” ዓለምን ያስገደዱ የጥቀር ሕዝቦች ባለውለታ የሆኑት፤ ንጉሳችን አፄ ሚኒሊክን ዛሬ  ተገንጣይ ኦነጎች “Holy War! “the Bloodthirsty Tyrant in Human History. Menlik II of Ethiopia!  (አፍሪካዊ ሂትለር) በማለት የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግምባሮችና መሰል ኦሮሞ ድርጅቶች፤ በዩቱብ ቪዲዮ የዘረጉት፤ ፕሮተስታን አስፋፊ ጀርመኖችና፤ ‘ፋሺስት ጣሊያኖች’ የፈጠሩላቸው ፈጠራ ተመርኩዘው፤ አሁን የደረሱበትን ንግግርና መፈክር ስትመለከቱት፤ አዲስ አበባ ውስጥ እየኖሩ “ፌደራል መንግሥቱ እና እኛ የተለያየን አካሎች ነን” አንተዋወቅም/ጎረቤታሞች ስለሆንን ‘መሬታችን’ እሱ አያዘውም በማለት “ነገዳዊ የሆነ ፌደራሊያዊ የራስ ገዝ ቢቀበሉም“ እራሰቸው የቻሉ የተገነጠሉ አገሮች” ሆነው ስለሚቆጥሩ ኦሮሞዎቹ “ፌደራል መንግሥት” ተብየውን “ድምበራችንን አልፈሃል” በማለት “አናውቅህም ብለውታል”። በጣም አስገራሚ ዘመን!

ወደ “ፋየር ኢተሮቹ” ታሪክ ከመመለሳችን በፊት ‘ሰሞኑን’ ባየነው የኦሮሞዎቹ “ድምበራችንን አትዝለል” ተቃውሞ አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ።

በቀለ ገርባ ይባላል። ኦሮሞ ፌደራል ፓርቲ ብሎ ራሱን ከወያኔ እውቅና ያገኘ ‘የነገድ ድርጅት’ አማራር ቢሆንም፤ ሲፍቁት ግን ድብቅ  የሆነ “ኦነግ” የሚል ቆዳው ላይ ማንበብ ይቻላል። አስገራሚው ደግሞ፤ ተቃወሚዎችና ሚዲያዎቻቸው ይህ ገንጣይና አፍራሽ ግለሰብ በወያኔ ታስሮ በነበረበት ወቅት “ሃቀኛ ኢትዮጵያዊ” “ለአንድነት የቆመ ነው” እያሉ “ኡ ኡ ሲሉለት ነበር”። ኡኡ እንዲሉለት ሲያሞኟቸው የነበሩ ክፍሎች ደግሞ “ተግንጣይ ቡድኖች ናቸው”። ልክ ታስሮ አንደተፈታ፤ እዚህ አሜሪካ አገር መጥቶ እሳት ላይ ተጋብዞ “አማራዎች አሮሞዎችን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው” ሲል አላመፈር “ፀያፍ ትፋቱን” ተፍቶብን የሄደ “ውለታ ቢስ” ግለሰብ ነው።
 ሰሞኑን የኦሮሞ ተማሪዎች “Burayub KeNga (ቡራዩ የኛ) Sebeta SKenGa!  (ሰበታ የኛ!)” ሆሆታው አስመልክቶ እንዲያብራራ ቃለ መየጥቅ ተደርጎለት እንዲህ ሲል ተናግሯል፦

መጀመሪያ ማኀበረሰብ..ሕዝብ..ብሔርና ብሔረሰብ ሀገርና ክልል የሚለውን ማወቅ አለባችሁ!!
የኦሮሞ ጥያቄ የብሄር ነው…ባሕል ቋንቋችን ክልላችን ከሌላው መደባለቅ የለበትም። አሜሪካ የምትከተለው ፌደራሊዝምና የከተማ መስፋፋት ከእኛ ጋር አንድ አይደለም። እነሱ “አንድ ሕዝብ ናቸው አንድ ቋንቋ ይናገራሉ…” እኛ ግን “ልዩ ህዝቦች ሆነን ኦረሚያና ፌደራሉ መንግስት ጎረቤታሞች ናቸው።”
   ይላል፤ በቀለ ገርባ።

እንግዲህ እንደ ምታውቁት አሜሪካ ከኢትዮጵያ በሰፋ መልኩ “የተለያዩ ነገድ/ቀለም/ባሕል/ባሕሪ/ዘር/እምነት፤ቋንቋ/ፆታ፤ድረጅቶችን” ያቀፈ አገር ነው። ተገንጣዩ በቀለ ገርባ ተከታዮቹን ለማመቻቸት ሲል ግን አሜሪካ “አንድ ሕዝብ” ናቸው፤ “አንድ ቋንቋ” የሚናገሩ ናቸው፤ እኛ ግን “ልዩ ሕዝቦች ነን” “ጎረቤታሞች ነን” ሲል ልዩ አገርና ሕዘብ መሆኑን ግልጽ አድርጎ ነግሮናል።
 “ኦሮሚያ” የተባለ “ክልል” እንደ የአገር አካል/ግዛት ሳይሆን “ልዩ ሕዝብና ጎረቤት” አድርጎ እራሱንና ኦሮሚያን ከኬኒያና ከሱዳን ጋር በማመሳሰል “ያልታወጀ የራሱን ኦሮሚያ የተባለ አገር ቀርፆ መከራከሩን የሚያሳየው “ልክ “ፋየር ኢተሮቹ/ እሳት በሊታ” የተባለው በ1861 አሜሪካ ደቡባዊው ግዛት ክፍል ውስጥ የነበረው ተገንጣይ “ዘረኞች ክፍሎች” ያነሱት የነበረው ጥያቄ ይመሳሰላል። በቀለ ገርባ እና የመሳሰሉ ተገንጣይ ኦሮሞ ኤሊቶች “በወያኔ ማዕቀብ” ውስጥ በመሆናቸው “ጥያቄአችን ግንጣላ ሳይሆን የክልል/ስቴት ራይትስ/ State’s rights ነው” ቢሉም፤ ቀጥተኛ ትኩረታቸው እና ንግግራቸው የሚያመላክተን ‘ቋንቋን፤ባሕልን፤መሬትን” አስታክኮ “ግንጠላን ማራመድ” ነው።

“ፋየር ኢተሮቹ/Fire Eaters” ሲሉት የነበረው፡ ልክ እንደ ወያኔና ኦነግ እንዲሁም መሰል ተገንጣዮች ፌደራሊዝም ለረዢም ጊዜ ተቀብልን “ነፍጠኛን ካባረረን በኋላ፡ “የተወረረብንን መሬትም ካለ እያስመለስን፤ድምበራችን እያስፋፋን እየከለልን ከቆየን በኋላ” አንቀጽ 39ኝን ተጠቅመን ቀስ በቀስ ወደ ግንጣላ እናመራለን እንደሚሉት ሁሉ፡-

“እሳት የላሱ” በመባል የሚጠሩ የደቡብ ነጭ ዘረኞችም በተመሳሳይ ያራመዱት ሂደት አሰሜነኞች ልንዋጥ/ልንተዳዳር ነው፤ “ንብረቶቻችን የሆኑ “አፍሪካኖች” ለኛ እንዳይገዙ፤ በኛ ላይ እንዲነሱ ለማድረግ በሴራቸው ውስጥ አንዲተባባሩ በማድረግ ‘ነፃ’ እንዲወጡ ሊያደርግብን ነው፤ ሰፋፊ ለም እርሻ መሬቶቻችንንና ዓሳ መፈልፈያ ሃይቆቻችን፤ወንዞችና የባሕር ውሃዎቻችን ሊሻሙን ነው። ስለዚህ ፌደራል መንግሥት የተባለው የሰሜኑ ክፍል፤ ወደ ደቡባዊ ድምበር ተሻግሮ “ልማትን ማስፋፋት፤ አስተዳዳራዊ መዋቅርን ጣልቃ መግባት፤ድምበራችንን መነካካት” የለበትም ባይ ናቸው። እኛ ከሰሜኑ የሚለየን ልዩ ባሕል አለን።አንድ ያደረግን ነገር ቢኖር በእንግሊዝ ቅንመበር “አገራችን” ተይዞ በኮሎኒ ተይዘን የነበርን ነን” አሁን ግን ከሌሎች አካባቢዎች እየፈለሱ እየተዳቀሉ መሬቶቻችን ሊሻሙን ነው ባዮች ነበሩ።

Professor Charles B Dew’s የተባሉ ‘Apostles of Disunion” በሚል መጽሐፋቸው በትክክል የሚሉት “race and slavery, not States’ rights, were what motivated Southerners to secede.ይላሉ። በቀለ ግርባም ሆኑ ኦሮሞ የጎሳ ኤሊቶችም ያሳሰባቸው ነገር “የክልል መብት ሳይሆን፤ ባሕላችን፤ቋንቋችን በሌሎች መጤዎች ሊዋጥ ነው፤ሊበላሽ ነው” ሲሉ በግልጽ እየተናገሩ ነው/ሳይሸሽጉ!!!!።  ይህንን አበክራችሁ አስተውሉ። ፋሺስዝም ‘የጎሳ ጥራትን” ያቀነቅናል የምለውም ለዚህ ነው።

ደቡቦቹ ያሳሰባቸው በፌደራሉ ስርዓት ተደማጭነትና ቦታ ያላቸው መሆኑን ቢያውቁም ደቡቦቹ  ወደ መገንጠሉ ያቀነቀኑበት ምክንያት ይላሉ ፕሮፌሰር ቻርለስ፤-

With the above brief historical sketch one can understand why Southerners in the mid-nineteenth century were on the defensive. Their economy was extremely strong and their power in the US Federal Government was impressive yet their position was being gradually undermined by the North’s fast-growing (due to immigration) population and western expansion. Southerners saw a time approaching when they would be unable to stop anti-Southern legislation in the US Congress. The prospect of this was frightening given the increasingly radical political noises that came out of the Northeast and Upper Midwest. The Era of Good Feelings was over; the North and South were locked in a struggle for political supremacy, control of the Union and, ultimately, cultural and economic survival.”

የሚገርመው ነገር በፌደራላዊ ሥርዓት ሆነውም “ነጮቹ ባርነትን እንደ ሕጋዊ ንብረት የመያዛቸው መብታቸው የጠበቀላቸው የፌደራል ስርዓት ነበር” ይህ በላ አነሳዋለሁ። እንዲያም ሆነው፤ በፌደራል ሥርዓት መኖር አልረኩም። ምከንያቱም፤ ከላይ ያያችሁት አንዱ ምክንያት፤ የሰሜኑ ክፍል በልማትና በሕዝብ ወደ ደቡቡና ማዕከላዊ ምዕራባዊ አሜሪካ ግዛት ፍልሰት መቀጠልን ሲገነዘቡ፤ እንዲሁም “ሥር ነቀል” ፖለቲካዊ ንቃት የማደጉ ጉዳይ ወደ እነሱ እንዳይዘመት በመስጋት “ከዚህ ወዲህ አትለፍ” “ይህ “የኛ ድምበር ነው” ፤ “እኛና ፌደራሉ ጎረቤታሞች ነን”፤ አንተ እዚህ መገንባት አትችልም፡” በማለት ነው ግንጣላቸው መነሻ የሚያደርገው። ይህንን ስትመለከት፤ የነ በቀለ ገርባና ኦሮሞዎቹ ንቅናቄ/ተቃውሞ ልክ አንደ “እሳት የላሱ” ዘረኛ ነጭ ተዋጊዎች የኛዎቹ “ኦሮሞ ለኦሮሞ!” ኢትዮጵያ አውት ኦፍ ኦሮሚያ” ፈካሪዎች “በግልጽ አንዳስቀመጡት፤ Burayub KeNga (ቡራዩ የኛ)  Sebeta SKenGa!  (ሰበታ የኛ) የሚለው መፈክር በግልጽ ከተቀሩት የግንጣላ አቀንቃኞችና ፋሺዝምን በሕገ መንግሥት ሕጋዊነት እንዲኖረው ያጸደቀውና የጻፈው መንግሥት ቡድን ጋር “በድምበር መሳሳብና በልማት ሰበብ” ግብግብ መግጠማቸው የሚያሳየን “They are locked in a struggle for political supremacy”.

 ሁለቱም (ወያኔና የተቀሩት አሁን በሥሩ ያሉት የክልል ነገሥታቶች)  አገር በሚያፈርስ የፋሺስት ዲዛይን/ክልል ተሞርኩዘው በግብግብ ትግል በሚገኙበት በዛሬው ወቅት፤ “the Responsibility of intellecctuals” የኢትዮጵያ ምሁራን ሃላፊነት፤ በተለይም “አንድነትን” የሚከተሉ “ኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ” ምሁራንና ሚዲያዎቻቸው፤ “ከዚህ ድምበር ወዲያ እኛና ፌደራሉ ጎረቤታሞች ነን፤ ማንም ኢትዮጵያዊ  በሱሉልታ፤በቡራዩ፤ በመላ ኦሮሚያ ክልል ‘ማረስ፤ መገንባት፤መራመድ፤መስፋፋት፤ ሰርቶ ገንብቶ መኖር፤የተከለከለ ነው’” በማለት እንደ ዶናል ትራምፕ” ድምበራቸው ዙርያ ላይ “ግንብ ለሚያጥሩት” የዘመናችን “Fire Eaters” ፋሺስታዊ ንቅናቄ አራማጆች፤ መልስ ብለው በየድረገጹ የሚጽፉላቸው ጽሑፍና “እሰጥ አገባ” መልስ ፈራ ተባ በማለት ‘አድርባይነታቸው” ዛሬም እንዳልለቀቃቸው በግልጽ ማየት ችያለሁ።

የኦሮሞ ምሁራን ተብየዎች የሚያቀጣጥሉት ትግል የኦሮሞ ገበሬዎች መብት ለመከላከል በሚል ሽፋን እያስተጋቡት ያሉት ነጥብ፤ ቢመረመር (እነ ጃዋር መሐመድ እስከ ጅማ ድረስ ትናንት ድረስ ወጣቶችን ሳነጋግር ነበር የዋልኩት፤ እያለ የልጅነት ጀብደኝነቱን ለማሳየት ወጣቶች በወያኔ ሰንሰለት ሥር እንዲገቡ ምክንያት እየሆነ፤ በግልጽ በሚዲያ የሚናገረው ምራቁ ያልዋጠ ጀብደኝነት ባሕሪው ወደ ጎን ትተን) የኦሮሞ ገንጣዮች በጉልህ የምናየው ፍላጎታቸው የታዘብነው ነገር አለ።  እሱም፦

 “ኦሮሞዎች፤በሕዝብ ብዛት ተመሳሳይ ከሆነው ከአማራው ነገድ እጅግ የተሻለ /መጠነኛም ቢሆን ‘የራስ ገዝ’ አስተዳደር መጎናጸፋቸው አሌ የማይባል ነው (ወያኔ በበላይ ሆኖ ቢያዘቸውም፤ አማራን/”ነፍጠኛን”/ ማባረርን በሕግም በንግግርም ከወያኔዎችና ከኦነጎች የተላለፈላቸው መብት ተሰጥቶአቸዋል።) ስለሆነም ነው ጥያቄአቸው፤

 “ኦሮሞ ከሌላ ማሕበረሰብ ጋር አንዳይቀላቀል ፍራቻ አለን፤ባሕላችን እንዳይበረዝብን ፍራቻ አለን፤በላቲን የምንጽፈው ቋንቋችን በኢትዮጵያዊያ ፊደል እንዳይበከልብን ስለሰጋን አዲስ አበባ ወደ እኛው እየተስፈፋች ከመጣች ማቆሚያ ስለማይኖራት “መጤዎች ደማችን፤ፖለቲካችን፤ፍትሓዊ ስርዓታችን፤ ባሕላችንን ያቆሽሹብናል” ሲሉ በአደባባይ የሚሟገቱት ምክንያት ግልጽ ነው።

*፡ዘራችን፡* የተለየ ስለሆነ “ኦሮሞ ያልሆነ” “ማንም” እየመጣ፤ እየገፋ ድምበር በጣሰ ቁጥር፤ ማንነታችን ከሌሎች ጋር እየተቀላቀለ “የቆሸሰ ማንነት/ባህልና ደም” ለመቀበል እንዳንገደድ “ከቡራዩ፤ከሱስሉልታ” ወዲያ ማለፍ በጥብቅ የተከለከለ ነው” ማለታቸው  ፋሺስቶች/የኢጣሊያን ሙሶሊኒዎች/የአሜሪካ ደቡባዊ ግዛት ‘ነጮች’ ከጥቁር ዜጎችና ፈልሰው ከየዓለማቱ ወደ ደቡብ ክፍል በሚፈልሱ ስደተኞች ጋር ደማችን ባህላችን ቋንቋችን እንዳይበከልብን “ድምበራችን መከለል/መዝጋት” አለበት ሲሉ racial amalgamation / መቀላቀሉን መቀበል ማለት ለኦሮሞዎቹ (which would mean the end of… ) የኦሮሞ ህልውናን የመጻረር ነው ሲሉ ደምድመዋል።

ፋሺስቶች ራሳቸውን የሚመለከቱት “as a distinct ethnic group” ስለሆነ፤ ከሰዎችነት የተለየ ከመጤዎች ጋር መቀላቀል የማይገባው ‘ልዩ’ የሆነ ማሕበርሰብ ነው” ብለው ስለሚያምኑ፡ ኦሮሞዎቹ “በግማሽ ንክ” ምሁራኖቻቸው በሚመሩት በሚመራ ጠባብ “የጎሳ ፍቅር” እየተመረዙ በእንዲህ ያለ scenario ትዕይንት ገብተው ግብግብ ገጥመው በምንም መልኩ አንቀበልም የሚሉበት ምክንያታቸውም “ደማቸውን ላለማቆሸሽ” ነው።ራት ነጥብ!

 ከተቀላቀሉ “ባህላችን፤ቋንቋችን፤ማንንታችን ይበከላል” የሚሉት ሲተረጎም “ንፁህ ኦሮሞኣዊ ደም ከቆሸሸው የሌሎች ነገድ ደም ጋር በማቀላቀል አናቆሽሽም” የሚለው ግልባጭ ትርጉም ይሰጠናል። ኮለክቲቪስት ማሕበረሰብ፤ ከግለሰቦች/ የሚለያቸው ኢንዲቪጂዋልስቲክ አራማጆች ጋር ከተዋሃዱ “ማንነታችን እናጣለን” የሚል ክርክራቸው፤ ሲጤን የሰው ልጆችን መዋሃድ የሚቃወሙ መሆናቸው አያከራክርም።

 racial amalgamation ወይንም ሌላ ነገድ ላለመዋሃድ የሚደመጠው የነ በቀለ ገርባ ክርክር ሲጤን፤ወይንም ኦሮሞ ተማሪዎቹ Burayub KeNga (ቡራዩ የኛ)  Sebeta SKenGa!  (ሰበታ የኛ) በሚለው መፈክርራቸው የተደገፈው “የድምበር ይያቄ ግጭት”   በገቤሬዎች የመሬት መብት “ሽፋን” ቢንጸባረቅም ኢትዮጵያዊያን አይደለንም ነው የሚሉት። ሲጀመር እስኪያልቅ በወያኔ ስርዓት የኔ ነው ብሎ ገበሬው የራሱ የሚሸጠውና የሚለውጠው መሬት የለውምና!!! ስለዚህ ክርክሩ አጉል ሆኖ “ለግንጣላ ዓላማ ቅስቀሳ እንዲመች” ግን እንደ በንዚን ሆኖ አገልግሎአቸዋል።

በሚቀጥለው ስለ የጎሳ ፖለቲካ ወያኔና ኦነግ ለምን እንደሚጋጩ በጥልቀት አቀርባለሁ። ከዚያም ጊዜ ከተገኘ “ጸጋዬ አራርሶ” የተባለ የፌደራል አቀንቃኝ ቅስቀሳው እንመለከታለን። ይህ ግለሰብ የሕግ ምሁር ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና የሕገመንግሥት መምህር ነበርኩ የሚል ነው። ይህ “ኦነግ” ያልሆነ “አዲስ ኦነግ” ደግሞ ብቅ ብሎላችልና ለፍልፎ እስኪተነፍስ ድረስ አዲስ የሕግ ተንታኝ ብለው “ቪ ኦ ኦ ዎች” ሰሞኑን “እየወለወሉልን” ነው።

ሰውየው ካሁን በፊት ከተዋጣለት ጋዜጠኛው ወንድም ካሳሁን (የአውስትራልያ S B S ራዲዮ አዘጋጅ) ጋር ባንድ ወቅት አንቀጽ 39ኝ ዙሪያ አስመልክቶ ጋዜጠኛ ካሳሁን “ፀጋየ አራርሶን” ሲጠይቀው “አንቀጽ 39 ወደፊትም ዛሬም መኖር ያለበት የኢትዮጵያ አንድነት የዋስትና አርማ ነው” ሲል ፋሺሰታዊ አንቀጽ ሲከላከል አድምጣናል። አዲስ በመሆኑ፤ ማሕደሩና ማንነቱ ባናውቀውም፤ይህ “ኒሂሊስቶች ርዕዮት” የሚከተል ወጣት፤ ወያኔ በሚቆጣጠረው ትምህረት ተቋም በሕግ ትምሕርት ሲያሰተምር የነበረ ዛሬ ለዶክተሬት ትምሕርት እዚህ ተልኮ “እሳት የላሰ ኤክስፐርት” ለመሆን እየተሯሯጠ ነው። በዚህ እምለስበታለሁ።

ጸጋዬ አራርሶ አንቀጽ 39 በመጪው ስርዓት የሚደነገግ ሕገመንግሥት እንዳይፈርስ ሲከራከር፤ “የጎሳ ፌደራሊዝም” አቀንቃኞች፤ “Burayub KeNga (ቡራዩ የኛ)  Sebeta KenGa!  (ሰበታ የኛ)” የሚለው የነ ጃዋር መሓመዳዊያን መፈክር የሚደግፍ መሆኑን ሰሞኑን በቪኦኤ ተደምጧል።  “ኢትዮጵያዊ ዜግንትን ለመንጠቅ “በመከለል”፤ አገር ለማፍረስ ደግሞ “ሬፈረንደም” ተጠቅሞ ማስገንጠልን” ለሰው ልጆች እድገትና ጤነኛ ፖለቲካ ነው ብለው የሚሰብኩ ምሁራን “ግማሽ ዕብደት” የተጠናወታቸው ፖለቲከኞች ናቸው፤ የምለውም ለዚህ ነው። ወያኔ መሬታችሁ ነው ብሎ ኦሮሞዎችን ከሰጣቸው “ማንም ሰው ከዚህ ድምብር ማለፍና ማልማት ክልክል ነው” ብለው ቢሉ ጥፋቱ የነሱ ሳይሆን “ፌደራል” የሚባለው “ወያኔም” ሙሉ በሙሉ የራሱ ጥፋት መሆኑን እንመለከታለን። ዝርዝሩ በክፍል 2 እንመለከታለን፡….. ይቀጥላል፡
አመሰግናለሁ፤
ጌታቸው ረዳ Ethiopian semay ብሎግ አዘጋጅ ( getachre@aol.com )


 

  



No comments: