ይድረስ ለጎጠኛው መምህር(አማርኛ) $25.00 እና ሓይካማ (ትግርኛ) $15.00 መጽሐፌን ለመግዛት ዕድሉን ያላገኛችሁ ካላችሁ በሚከተለው አድራሻ ደውላችሁ ማግኘት ትችላላችሁ Telephone (408) 561 4836 (Getachew Reda P.O.Box 2219 San Jose, CA 95109) getachre@aol.com http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/
“ትግሬ” ማለት ስድብ ከሆነ “አምሓራይ” ብሎ ለመጥራትሳ መብቱ ማን ሰጣችሁ?
(ትግራይ - ትግሬ)
ጌታቸው ረዳ www.ethiopiansemay.blogspot.com
“ኢትዮፕያን ካረንት አፈይርስ ፎረም” የተባለው ጸረ ትግራይ ሕዝብ የሆኑ አዳዲስ ወጣት ፋሺስቶች የተሰባሰቡበት ፓል ቶክ ገብቼ ባለፈው ወር ያዳመጥኩትን ያበሻጨኝ ሳይበቃኝ ትናንት ደግሞ በትግራይ ተወላጆች የሚካሄድ “አሉላ አባ ነጋ” እየተባለ የሚጠራ “ፓል ቶክ” እግር ጥሎኝ ዘው ብየ ስገባ፦አንድ የመለስ ዜናዊ ሥርዓት ተቃዋሚ ነኝ የሚል (የትግራይ ሰው) ነገር ግን “ማሕበር ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ” በሗላ “ህወሓት” ብሎ ራሱን የሚጠራ ጠባብ ብሔረተኛ ያስፋፋውን የተሳሳተ የማንነት ትርጉም ሳይታወቀው በሕሊናው ሰርፆ “የድምፅ ማጉያውን” በመያዝ “ትግሬ” ማለት ስድብ ነው! ማንም ሰው “ትግሬ” ብሎ እንዲጠራኝ አልፈቅድም! አማራዎች ትግሬ ብለው የሚጠሩን እንደ እነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዓይነቶቹ እኛን ለማንኳሰስ ሲሉ ሁሌም “ትግራይ” ከማለት “ትገሬ” ይሉናል! ካሁን ወዲህ ማቆም አለባቸው! ስማችን “ትግሬ” አይደለም! ትግሬ ማለት “የዴግሪዴሽን” አጠራር ነው! ሲል አዳምጬው፦ይህ ሞኝነት ከ1966 ዓ.ም በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ስንቱን ገራገር ብሔረተኛ እያሞኘ እንደሆነ ዛሬም መቀጠሉ ስለገረመኝ አማራዎቹ ሳይሆኑ እኔው የትግራይ ተወላጅ ባንደበቴ ለጠባቦቹና ገራገር የህወሓት ሰለባዎቹ አንዳንድ ጥያቄ ላቅርብና መልስ ካላቸው ለመስማት ፈልጌ ነው ይኼን አንድ ልላችሁ የፈለግኩት። ባይሆን መሪያቸው መለስ ዜናዊ ቢመለሰው ደስ ባለኝ-ሆኖም እሱም ያገሩን ሰንደቅና ታሪክ የሚያጣጥል “ግብዝ” ሰውና መልስ እንደማያገኝለት ስለማውቅ በግረ መንገዴ በዚህ ጽሑፍ አንዳንዶቹን ገራገሮች ማስተማር ይጠቅም እንደሆነ እነሆ።
“ትግራይ” እንጂ “ትግሬ” አይደለንም የሚለው ሞኝነት የተጀመረው ዛሬ ሳይሆን ቀደም ብሎ በራስ መኮንን ጊዜ እንደሆነ ይነገራል( ምን ያህል ልክ መሆኑን ግን እርግጠኛ አይደለሁም)። ትግሬ አትበሉን ትግሬ ማለት ስድብ ነው ካላችሁ “ችግሩ ምን ላይ እንደሆነ ባይገባንም” ትግሬ ማለቱን ትተን ትግራይ እንላችሗለን ብለው ጃንሆይ እንደተናገሩ አንዳንድ መጻሕፍተ ያነበብኩ መሰለኝ። ሁኔታው ጎልቶ በይፋ የወጣው ግን እኔ በተማሪ ዓለም በነበርኩበት ወቅት ነው ማለትም በ1961-2 (?) ዎቹ አካባቢ ነው። በታሪክ አጋጣሚ በአካል የተከራከርኩበት ወቅት ስለነበር ላበራራራ።
ነገሩ እንዲህ ነው።የተማሪዎች ረብሻ እና የትግራይ ብሔረተኛነት ጎልቶ እና ትኩስ ሆኖ የተፋፋመበት ወቅት ነበር እና እኔ በወቅቱ ትግራይ ውስጥ ለብሔራዊ ቡድን ከሚጫወቱ ታይድል/መሰቦ.…በሚባሉ የትግራይ እግር ኳስ ተጫዋች ስለነበርኩ፦ በወቅቱ ትግራይን ወክለው ወደ አዲስ አበባ ላገር አቀፍ ዋንጫ ውድድር ከሚሄዱ ውስጥ ስም ዝርዝራችን በሚስጥር ተይዞ የተመረጥንም ያልተመረጥንም (በኳስ ውድድር ምክንያት የተበጣበጥንም የተደባደብንም የተሰዳደብንም..) አብረን ለጥንካሬ እና አንድነት ተብሎ የጋለ የክለቦች ወንድማዊ ግንኙነት አንድ ወር ሙሉ በፍቅር ስንጨዋወት ድንገት ካዲስ አበባ “ለትግራይ ጠቅላይ ግዛት እግር ኳስ መምርያ/ፌደረሽን (?) የሚል የመጥርያ ደብዳቤ እንደደረሰ፦ በወቅቱ የእግር ኳስ አሰልጣኝና እና የአካል ጥንካሬ አስተማሪ የነበረው አቶ አራም ማሩ (የአፄ ዮሓንስ 4ኛ ወንድም የልጅ ልጅ ልጅ ….የደጃች ማሩ- የሆነ “ተምቤን” ) በጣም ማራኪ፤ ፈጣን ተጫዋች፤ ነግር ግን ምስፍናዊ ባሕሪው እጅግ ተናካሽ ውሻ የሚያስመስለው ተነታራኪ/አስቸጋሪ ጸባዩ “ትግሬ” የሚለው ቃል ወደ “ትግራይ” ካልተለወጠ ወደ አዲስ አበባ አንሄድም ብሎ (የስፖርት መሪና አምበል በመሆኑ) አድማ እንዲመታ ሲያደርግ፤- እኔ እና እሱ ከዚህ በታች የምዘረዝረው ሙጉቴ ምክንያት ከሱ ጋር ክርክር ገጥሜ አድማው መስፍናዊና ውሃ ያማይቋጥር አንደሆነ በመቃወሜ ዱላ ቀረሽ ስድብ በመግባት አስከ መጨረሻ ድረስ ከአራም ጋር ሳንዋደድ እንደተለያየን አንድ ጊዜ ብቻ አዲስ አበባ ከገዛ ወንድሙ ባር/ሆቴል ውስጥ ተገናኝተን መሳሳማችን እና ይቅር ይቀር መባባላችን ትዝ ይለኛል።
እነሆ ይህ የማንነት ቁርቁስ ያዘለ የተሳሳተ ብሔረተኛነት የጀመረው በዛ ውቅት ሲሆን ዛሬም ይህንኑ ቀጥሎ ማየቴ በጣም አሳዛኝ ድንቁርና መሆኑን ስገልጽ፤ ክርክሩን እነሆ ልለግስ። ትግሬ የሚለው ቃልም ሆነ ትግራይ ሁለቱም መጠርያችን እንጂ ማንኛቸውም ቢሆኑ የስድብ ምልክቶች /ቃናዎች የላቸውም። ትገሬ ማለት የተጀመረው በዘመነ ቀ.ሃይለስላሴ ወይንም በፕሮፌሰር መስፍን ወይንም አማርኛ ቋንቋ ሲጀምር ብቻ ሳይሆን ግዕዝ መጻፍ ሲጀምር “ትግሬ” የሚለውም ጭምር መጠርያችን ሆኖ እንደነበር ከመቶ አመታት በፊት የተጻፉ የግዕዝ መጻሕፍቶችና ደብዳቤዎች ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ በ15ኛው ክፍለ ዘመን በአባ ባሕሪ የተጻፈው የግዕዝ “ዜናሁ ለጋላ” በክቡር ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ የተጻፈው “የአባ ባሕሪ ድረሰቶች” በገጽ114 ስንመለከት ማለትም በአፄ ሠርፀ ድንግል ታሪክ የተቀዳ እንዲህ ይላል “ ወለአከ ሃቦ ኮሙ ጨዋ ወሃበ ሠየምተ ትግሬ ከመ ይብጽሑ በዕድሜ ዘአደሙ”። ይላል። ይህ በጣም በጣም ሩቅ ዘመን ወደ 500 ዓመት ገደማ የሆነው የግዕዝ ጽሑፍ ነው። ትርጉሙ (ወታደሩ ሁሉና የትገሬ ሹሟምንት ከቀጠራቸው ቦታ ድረስ እንዲመጡ ላከባቸው) ይላል ወደ ማርኛው ሲተረጎም።
በዚህ የግዕዝ ጽሑፍ መረጃ “ሠየምተ ትግሬ ከመይበጽሁ) ብሎ በግዕዝ በዘመኑ ይጻፍ ከነበረ ዛሬ አማራዎች “ትግሬ” ብለው ቢጠሩን በምን መለኪያ ነው ስድብ ሊሆን የሚችለው? እንዳውም ለቀቅ አድርጌ ልተንትን። ቋንቋችን ምን ይባላል? “ትግርኛ”። ትግር “ኛ” ህጋዊ ነው ብለን ከተቀበልን፤ ካነሳሱ ልብ ብለን ስንገነዘበው “ኛ” የሚለው ፊደል የተገኘው ከአማርኛ መሆኑ ነው (ግዕዙ ከፈጠራቸው ሌላ አማራ የጨመራቸው ፊደሎችና የዜማ ምልክቶችም (የዜማ ኖታ) እንዳሉ ይነገራልና) ምክንያቱም “ይ” ለሚለው ፊደል (ትግራ“ይ”) “ኛ” የሚለው ያማርኛ ፊደል ተክቶታልና ነው። ምክንያቱም በትግርኛው አጠራር (ቀዳማ “ይ” ካልኣ “ይ” ሳልሳ “ይ” አምሓራ “ይ” ትግራዋ “ይ”…) የሚሉ ተከታታይ ቁጥሮችና ስያሜዎችን ስንመለከት በአማርኛው (አንደ “ኛ” ሁለተ “ኛ ሦስተ “ኛ” አራተ “ኛ”.. አማር “ኛ” አንግሊዝ “ኛ”…አሮም “ኛ” ትግር “ኛ”….ይላል) ቋንቋችን ትግር”ኛ” ነው ብለን ህጋዊነቱን ካረጋገጥን ካማርኛ የወሰድነውን “ኛ” ሕጋዊ ሆኖ “ሬ” ሕጋዊ አይደለም ማለት አንችልም። “ሬ” ካስጠላን እና “ይ”ን የተካው “ኛ” ማስወገድ ሊኖርብን ነው ማለት ነው።
አማርኛ ተናጋሪው ክፍል ሊሰድበን ሲፈልግ “ትግሬ” ይለናል ስለዚህ ስድብ ነው ካልን፡ ለመሆኑ አማራን የውጥንቅጣችሁ ማምለጫ የምታደርጉ ጠባብ ብሔረተኞች ለሆናችሁ ሁሉ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁና ልሰናበታችሁ። እኛ ትግሬዎች አማራውን ምን ብለን ነው የምንጠራው? ምንስ እያልን ነበር (አስካሁንዋ ደቂቃ ድረስ) በሺ የትግርኛ መጻሕፍቶችና ፓንፍሌቶች (በድርጅትም በመንግሥትም) ተሰንደው የሚነበቡት? “አምሓሩ” እያልን አደለም የምንጠራቸው? እኛ ትግሬዎች አማራውን “አማሓራይ” (ለነጠላ) አምሓሩ (ለብዙ ቁጥር) ብለን እንጠራለን። አማራዎቹስ ራሳቸውን ምን ብለው ይጠራሉ? አማራ (ነጠላ) አማራዎች (ለብዙ ቁጥር)። ታዲያ እኛ ትግሬዎች “አማራ” ብሎ ራሱን ለሚጠራ “አምራዎች” ብለው ራሳቸውን ለሚጠሩ ዜጎች “አምሓራይ” “አምሓሩ” ብለን እንድንጠራቸው ማን ነው መብቱ የሰጥን? ወይንም ማን ነው መብቱ የሰጣችሁ? በምን ሞራላችሁ ነው እንዲህ ያለው ትምክሕት እያንጸባረቃችሁ አማራውን “ትግሬ” እያለን ነው ብላችሁ መክሰስ የምትችሉበት አንደበት ከየት አገኛችሁት? እስከ መቸ የጠባብ ቡድኖች እና መሳፍንቶች መጫወቻ ሆናችሁ ልትዘልቁት ነው?አምላክ ይቅር ይበላችሁ። //ጌታቸው ረዳ “ይድረስ ለጎጠኛው መምህር” መጽሐፍ ደራሲ getachre@aol.com editor Ethiopian Semay www.ethiopiansemay.blogspot.com
No comments:
Post a Comment