Saturday, May 22, 2010

የቀይ ሽብር ወንጀለኛዋ የመለስ ካቢኔ ፀሓፊ

የቀይ ሽብር ወንጀለኛዋ የመለስ ካቢኔ ፀሓፊ ከኢየሩሳሌም አርአያ

የኢሕአፓ አንጋፋ አባላትአሸናፊ ለማወይንም በቅጽል ስሙአሸናፊ ጐላ ጠንቅቀዉ የዉቃሉ።ታሪኩን ጠንቅቀዉ ያስታዉሱታል የሚል እምነት አለኝ። ኢሕአፓ ታዋቂ አባል እንደነበረ በስፋት የሚነገርለት አሸናፊጐላተወልዶ ባደገበት አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ቤላ ወረዳ 12 ቀበሌ 18 ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ በ1970 ዓ.ም ከመኖርያዉ አቅራቢያ በግምት በመቶ ሜትር ርቀት በደርጎች በጥይት በግፍ ተደብድቦ ነበር የተገደለዉ። በማሃል ኣናቱ በጥይት ተቦድሶና በሚዘገንን ሁኔታ አንጎሉ ተዘርግፎ በአፍ ጢሙ ተደፍቶ

የአካባቢዉ ሕዝብ ቀኑን በሙሉ እንዲያየዉ የተደረገዉ ታጋይ አሸናፊ በእስር ላይ እያለ ከፍተኛ ድብደባ (ቶርቸር) እንደተፈጸመበት በተዘረጋዉ ሬሳዉ ያለመጫሚያ ይታዩ የነበሩ የዉስጥ መዳፍ እግሮቹ ይመሰክሩ ነበር። መዳፎቹ በግርፋት ብዛት ቆስለዉ ከመገርጠታቸዉ ብዛት ኩፉኛ ተላልጠዉና ተቀራርፈዉ እንደነገሩ ተጣብቀዉ ተንጠልጥለዋል። በቅርብ የሚያዉቁት ጓደኞቹ እና የትግል አጋሮቹ “ጎላ” እያሉ የሚያወሱት ይህ ታጋይ ለሦስት ወራት አሰቃቂ ድብደባ እና ስቃይ ሲፈጸምበት አንድም ምስጢር ሳይተነፍስ እንደተገደለ የሚጠቁሙ እነዚህ ወገኖች ከዚህም ባለፈ በወቅቱ አብረዉት ታስረዉ በርካታ ወጣቶች “ከኢሕአፓ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸዉም” ሲል እንደተናገረ እና ብዙዎቹ በሕይወት ሊተርፉ እንደቻሉ አያይዘዉ ይገልጻሉ።

በተጠቀሰዉ አካባቢ የነበረዉ የኢሕአፓ እንቅስቃሴ አሸናፊ ብቻዉን ያከናዉን እንደነበረ ለሰዉ በላዎቹ ደርጎች በመግለጽ ስቃዩን እና ሞቱን ለብቻዉ ተጎንጭቶ ማለፉን የመረጠ ጀግና ነዉ ሲሉ ያክላሉ። ድንቅ እና ብሩህ ኣእምሮ ለተቸረዉ አሸናፊ ለወላጆቹ ብቸኛ ልጅ ሲሆን፤ አባቱ አቶ ለማ የልጃቸዉን ሬሳ (አሟሟት) ካዩ በሗላ ጤና በማጣታቸዉ ለረዥም ጊዜ የአልጋ ቁራኛ ሆነዉ በዛ በደርግ ስርዓት አሸልበዋል። እናቱም ተመሳሳይ የጤና መቃወስ ገጥሟቸዉ እየተሰቃዩ እና አብዛኛዉን ጊዜ በሓዘን “እህህ” እያሉ እየተብሰለሰሉ ደርግ ስርዓት ሲገረሰስ ለማየት ቻሉ። ሁለት ሴት ልጆቻቸዉ አብረዋቸዉ ይኖራሉ ።

በዘመነ ደርግ ሕዝብ ሲጨፈጭፉ የነበሩ ተጠራርገዉ እስር ቤት መግባታቸዉን ተከትሎ- በ1984 ዓ.ም አነጋጋሪ የሆነዉ የኢሕአዴግ “ድራማ” ይገለጥ ጀመረ። “ማጋለጥ” የሚል ርዕስ የተሰጠዉ ይህ ተዉኔት በየአቅጣጫዉ ሲቀጣጠል ኢላማ ያደረገዉ በደርግ ስርዓት ሲገድሉና ሲያስገድሉ የቆዩ ሹመኞች በየመድረኩ ማብጠልጠል ነበር። በተጠቀሰዉ ዓመት ጥቅምት ወር በፈረንሳይ ለጋሲዬን በሚገኘዉ በከፍተኛ 12 ት/ቤት ቅጥር ግቢ የተካሄደዉ “ማጋለጥ” አንዱ ነበር። እስከ አምስት ሺህ የሚጠጋ የአካባቢዉ ኗሪ ተገኝቷል። ከቀይ ሽብር ወንጀል ጋር በተያያዘ 40 ወረዳ እና የቀበሌ ሹመኞች (አብዬት ጠባቂ የሚባሉትን ጨምሮ) በወንጀለኛነት ተጠርጥረዉ ከታሰሩ በሗላ -ሁሉም በዛኑ ዕለት ለታዳሚ ከሚታይ መልኩ ተደርድረዉ ተቀምጠዋል፡ በስርዓቱ የተረሸኑ እና የደረሱበት ያልታወቀ የኢሕአፓ አባላት (ታጋዬች) ከመድረኩ ግርጌ ተደርድሯል። ደረት እየደለቁ (ልጄን..ልጄን..” የሚሉ ሐዘን የደቆሳቸዉ ወላጆች ከወዲያ ወዲህ እያሉ ሲያለቅሱ ይታያሉ።

መድረኩን እንዲመሩ ተመደቡት የኢህአዴግ ወኪሎች ካድሬ ሃ/ስላሴ፤ መዓሾ፤ መ/አለቃ ታደሰ ሲጠቀሱ፤ ከቀይ ሽብር ሰለባዎች ተፋራጅ ኮሚቴን በመወከል የአሁኑ የ ኢቲቪ ጋዜጠኛ በቀለ መንገሻ ተገኝቷል። ወንጀሉ ሲፈጸም ያዉቁ የነበሩ የተገረፉና ያዉቁ የነበሩ የኢሕአፓ አባላት ተራ በተራ እየተነሱ ስላዩትና እናዉቃለን ስለሚሉት ይናገሩ ያዙ። ከኢሕአፓዎች ለድረግ አድሮ የገዛ የልብ ጓደኛዉን እስከማስገደል ደረሰ ምስጢሮች አዉጥቷል የተባለና እንዳጋጣሚ ሲሰራበት ከነበረዉ የአርባ ምንጭ ክልል መጥቶ ከታዳሚዉ ጋር ተቀላቅሎ ፕሮግራሙን ይከታተል የነበረዉ ከበደ ማኦ የተባለ ግለሰብ ወዲያዉኑ በቁጥጥር ስር ዉሎ ታሳሪዎቹን እንዲቀላቀል ተደረገ። ደርግ ከፍተኛ 12 ሊቀመንበር ሆኖ ያገለግል የነበረዉ ሰለሞን ይመስገን “ የአንድም የኢሕአፓ አባል፤ አንድም ወጣት አላስገደልኩም፡የፈረምኩት ወረቀትም የለም። “አለ” ከተባለ እዚሁ ልረሸን። አንድ ሰዉ እከካም ስትለዉ እከኩን ልታሳየዉ ይገባል።” በማለት የሰዉን ቀልብ በሚችል ገለፃ ተናገረ።

እዚህ ላይ የነበረ አስደንጋጩ የማጋለጥ ክስተት የተፈጠረዉ። በቀበሌ 18 የሚኖረዉ መምህር ቢሻዉ አበጋዝ በተደበላለቀ ስሜት ተወጥሮ ወደ መድረኩ አመራ። ማይክሮፎን ጨብጦ ሲያበቃ በተረጋጋ አንደበት እንዲህ ሲል ጀመረ። “ሰለሞን በሚገባ ታዉቀኛለህ፤ታስታዉሰኛል፤የድርጅት አባል መሆን ከወንጀል ተቆጥሮ በኢሕአፓ አባለነታችን ባንተ እና አጠገብህ ባሉ ጨካኞች የቁም ስቃይ ፍዳ ከቆጠርነዉ አንዱ ነኝ። በ1969-70 ዓ.ም በከፍተኛ 12 እና በሗላም በአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ የእስር ቤቶች ግፍ ስትፈጽሙ ነበር። አስታዉሳለሁ ጋሸ ማሞ የሚባሉ አህያ ነጂ ቀን እንጨት ጭነዉ ማታ ጠጅ ቀማምሰዉ ጫካ ወደ ሚገኝ ቤታቸዉ ሲያመሩ የአንተ አብዬት ጥበቃዎች ይዘዉ እየደበደቡ እና ወዳለንበት እስር ቤት አመጧቸዉ በግምት 55 ዓመት ይሆናቸዋል። አዛዉንቱ በሚፈጸምባቸዉ ግርፋት ሳቢያ ሕይወታቸዉ አለፈች። ጭካኔዉ የት ድረስ እንደሆነ ይሄ በቂ ምልክት ነዉ።”

መምህሩ ቢሻዉ ቆፍጠን ባለ ድምፅ ወደ ዋናዉ ነጥብ ሲያመራ አንዲህ አለ “ ታጋይ አባላችን አሸናፊ ለማ ወይንም አሸናፊ ጎላ ያ ሁሉ ስቃይ እንዲፈጸምበት ያደረግከዉ አንተ ነህ። በመጀመርያ እህቱን ንግዴ ለማን እንድትታሰር አደርግክ። ከእስር ቤት በድቅድቅ ጨለማ ንግዴንና ዓይናለም የተባለቺዉ ሌላኛዋ ወጣት ልጃገረድ እስረኛ በአንድነት በአንድ አልጋ ላይ ይዘህ አደርክ። ወሲባዊ ግንኙነትም ከሁለቱም ጋር ፈጸምክ። ለአሸናፊ እሕት ማለትም ለንግዴ ለማ ቃል በገባህላት መሰረት ወንወድሟን ጠቁማ እንድታስይዝ አደረግክ። ይህችን ማፈርያ አንስት ወንድሟን አስይዛ በእርሱ ስቃይ እና ሞት አሁን ድረስ ያለችበትን የኢትዬጵያ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት መ/ቤት በቋሚ መቆናጠጥ ችላለች።” ንግግሩን ገታ አድርጎ ታዳሚዉን እየቃኘ “… እዚህ ሕዝብ መሃል ንግዴ ለማ አለች። ቅድም ስትገባ አይቻታለሁ።” ብሎ ከማለቱ “ተነሽ!.. ዉጪ.. ዉጪ” የሚል ድምፅ ከተሰብሳቢዉ አስተጋባ። አብዛኛዉ ግን ለይቶ አያዉቃትም። ከመድረኩ በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት እንደመሸጎጥ ብላ በፀጥታ ሃይሎች ተይዛ ወጣች።

ከወንጀለኞቹ አጠገብ እንድትቆም ሲደረግ ታዳሚዉ በአንድ ድምፅ “መነፀርሺን አዉልቂ! …አዉሊቂ” እያለ የዉግዘትና የስድብ ናዳ ያወርደባት ያዘ። በዛ ቅጽበት ግን አብዛኛዉ ታዳሚ ያስተዋለዉ አሳዛኙ ሁኔታ እዛዉ መድረክ ስር የታይ ነበር። የዛች አንስት አንዲሁም የሟቹ አሸናፊ “ጐላ” ወላጅ እናት የልጃቸዉን ፎቶ በደረት ጉያቸዉ ሽጉጥ እቅፍ እንዳደረጉ በሰሙትና በሚያዩት ተደናግጠዉ ክዉ እንዳሉ፤ምንም ቃል ሳይተነፍሱ ሕሊናቸዉ ስተዉ በጀርባቸዉ ተንጋለዉ ወድቀዉ ነበር። ግዙፍ ሰዉነት አላቸዉ በመሆኑ በጥቂት ሰዎች ዕርዳታ ማንሳት አልተቻለም ነበር። ዉሃ ቢፈስባቸዉም አልነቁም። “ጉዴን ያላወቅሁ! ምነዉ ለማ (ባለቤታቸዉን) አንተን ባደረገኝ!? ልጄ የተባለዉ በገዛ ልጄ ኖሯል!” በለሆሳስ ይለፈልፋ ነበር። ለተከታታይ ሕሊናቸዉን እንደሳቱ ቆዩ።

ወንድሟን እንዳስገደለች ፊት ለፊት የተነገረላት ንግዴ ለማ ከመድረኩ መሪዎች የእምነት ክሕደት ቃል እንድትሰጥ ተጠየቀች። አንገቷን እንዳቀረቀረች ዝም አለች። እንደገና ብትጠየቅም እንዳቀረቀረች ዝም አለች። እንደገና ብትጠየቅም ከማቀርቀር በቀር የተነፈሰቺዉ አልነበረም። “ዝምታ በራሱ ማመን ስለሆነ -ወንጀሉን ስለመፈሟ ያስረዳል። ይህ በሬከርድነት ተይዟል። ዉሳኔ እስኪሰጣት ድረስ ማረፊያ ቤት ትቆያለች።” አለ ካድሬ ሃ/ስላሴ። ማጋለጡም በሌሎቹ ቀጥሎ ሲካሄድ ዋለ። ለአንድ ወር ገደማ እስር ቤት ቆይታ በዋስ የተለቀቀችዉ ንግዴ እስር ላይ እያለች ለዞኑ ካድሬዎች እና ተፋራጅ ለተባሉ ወገኖች በቢሮ በሰጠቺዉ ቃል ወንድሟን በሚስጢር ይኖርበት የነበረዉን አድራሻ በመጠቆም መርታ እንዳስያዘቺዉ፤ እሱን በማስያዝ የእርሷንና የቀሪ ቤተሰቧን ሕይወት እንደታደገች መነገሯን ጋዜኛ በቀለ እና ካድሬዉ አጫዉተዉኛል።

ሌላዉ የተረጋገጠበት ጉዳይ ሰለሞን ይመስገን ከወሲብ በሗላ ወንድሟን አሳልፋ በመስጠቷ ምክንያት ሰለሞን በወቅቱ በዋና ስራ አስኪያጅነት ይመራዉ በነበረዉ የፖስታ አገልግሎት በቋሚ ሰራተኛነት መቀጠር እንደቻለች ነዉ የተመለከተዉ።

በዚህ ወደ ዋናዉ የፅሑፌ ጭብጥ ልሻገር። በ2000 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሔደዉ አስቂኝ “ማሟያ ምርጫ” ተብዮዉ የመለስ ዜናዊ የ ኢሕአዴግን በመወከል በወረዳ 12/13 ምርጫ ክልል ለክልሉ ም/ቤት እንድትወዳደር የታጨቺዉ ንግዴ ለማ ከዛ ባለፈ የአዲስ አበባን ሕዝብ እንዲመራ በተደራጀዉ አዲሱ የኩማ ደመቅሳ ካቢኔ ዉስጥ የዋና ፀሃፊነቱን መንበር እንድትቆናጠጥ ተደረገ። በ97 ምርጫና በተፈጠረዉ ሁኔታ ቆሽቱ እርር ድብን ያለዉ የአካባቢዉ ሕዝብ ንግዴ ኢሕአዴግን ወክላ ስለመወዳደሯ ሊያዉቅና ሊከታተል ቀርቶ “ማጣሪያ” ተብዬዉም የሚሰማበት ጀሮ አልነበረዉም። የታወቀዉ ሚያዚያ 2000 ዓ.ም የክልሉ ካቢኔ ሲያሰማና የዚህ ስነ ስርዓት በቲቪ ቀጥታ ሲተላለፍ ነበር። በንዴት የጦፉ የቀድሞ የኢሕአፓ አባልትና የአሸናፊ ጐላ የቅርብ ጓደኞች “አቤት” ለማለት ተሯሯጡ። የሚያሳዝነዉ ይህቺ ወንጀለኛ ሴት በወንድሟ የፈፀመቺዉ ወንጀል አልበቃ ብሎ በወላጅ እናትዋ ላይም በደል መፈፀምዋ ነበር።

ይህም በ1989 ዓ.ም ታስራ ከተፈታች በሗላ “ልጄን አስገደልሽ” እያሉ በቁጭት ሐዘን ይናገርዋት የነበሩ እናትዋን በተኙበት አልጋ ትጨቀጭቃቸዉ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜያት በዓይናቸዉ የተመለከቱ የጎረቤት እማኞች ይናገሩ ነበር። “አድኑኝ!”…ቀጥቅጣ ገደለቺኝ! የወንድሟ አልበቃ ብሎ” የሚሉ ድምፆች የአካባቢዉ ኗሪ ያሰለቹ ነበሩ። በዛ ድርብር ሐዘንና ስቃይ እንደተከበቡ ያልጋ ቁራኛ እንደሆኑ በ1993 ዓ.ም በሞት ያሸለቡት ወላጅ እናት ከሳቸዉ ሞት በሗላ የሰፈሩ ኗሪ ንግዴ ለማ በአካባቢዉ ባሉ እድር እና መሰል ማሕበራዊ መስኮች እንዳትታቀፍ (እንዳታገለገል) ቆፍጠን ያለ አቋም እስከመያዝ የደረሰበት ተጨባጭ እዉነታ ነዉ የታየዉ። ሌላ ቀርቶ የቀበሌ 18 ሕዝብ የእግዚአብሔር ሰላምታ እንዲነፍጋት ተስማምቷል።

ይህችን ሴት ነዉ እነ መለስ የአአዲስ አበባን ሕዝብ እንድትመራ ስልጣን “ያጎናጸፋት”። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ግንቦት 2000 ዓ.ም በአዉራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ “ከአሸናፊ ጐላ” በሚል ብዕር ስም “ኢሕአዴግ ለየለት ማለት ነዉ? በሚል ርዕስ ከላይ የተገጸዉን ጭብጥ በመጭመቅ ለመጋለጥ ተሞክሯል።” በድጋሚ በዛዉ ጋዜጣ “ሰሚ ያጣዉ የሕዝብ እሮሮ” በሚል ተፅፏል። የመጀመርያዉ ጽሑፍ እንደወጣ የፓርቲዉ የ አ/አ ፕሮፖጋንዳ ሃላፊ ሕላዌ ዬሴፍ ‘እንዴት” በሚል አጣሪ እስከመሰየም ደረሱ። የገዢዉ ፓርቲ ዩበኩር ልጅ የሆነዉ ተለጣፊዉ የክልሉ ወጣቶች ማሕበር አስቸኳይ ስብሰባ በወቅቱ ጠራ። የጋዜጠዉን ፅሑፍ (ጥቆማ) መነሻ በማድረግ ሰባቱ አመራር አባላት (ግልገል ኢሕአዴጎችን ወይንም ግንቦቴዎች የሚባሉ) በጉዳዩ ለአራት ቀናት ተወያዩ። በነገራችን ላይ አምስቱ አባላት ተደራቢ ስራ ይከዉናሉ። እንደ ደህንነት የስለላ ተግባር በማካሄድ ጠ/ሚ/ሩ ድረስ ዘልቀዉ መረጃ ያቀብላሉ። ከባሊስትራ ወርቅ ጋር በተያያዘ ያስያዝዋቸዉ አሉ። አንዱ አፍቃሬ ኢሕአዴግ አመራር በስብሰባዉ ከቁጥጥር ዉጭ ሆኖ “ኢሕአዴግ እንደ ሽንፍላ ነዉ ታጥቦ አይጠራም። አንዴት ወንጀለኛ ሴት…” ብሎ መነገሩንና በሗላም ስሜታዊ ንግግሩ እንዳስበረገገዉ አንዱ አባል አጫወቶኝ ነበር። በጠ/ሚ/ት/ሩ ቢሮ ስለሚወጣ እና ስለሚገባ ሌሎች ይፈሩታል። “አዉቆስ ቢሆን!?” እያሉ።

የሆኖ ሆኖ የተለጣፊዉ ማሕበር ተወካዬች ሕላዌ ዬሴፍ ጋር ተቀምጠዉ በ1984 ዓ.ም የተቀረፀዉንና በፈረንአይ ለጋሰዬን አካባቢ የተካሄደዉንና በፈረንሳይ ለጋስዬን አካባቢ የተካሄደዉን ማጋለጥ በዝርዝር የሚያሳየዉን በቪድዬ ምስል የተደገፈ ማስረጃ ከኢትዬጵያ ቴሌቪዥን ምስል ክምችት በማስወጣት ተመልከቱ። እዛ ደረጃ ቢደርሱም የመጣ ለዉጥ አልነበረም።ወንጀለኛዋም በስልጣኗ እንድትቀጥል የአዲስ አበባም ሕዝብ በነብስ በላ እንድትተዳደር ፈርደዉ ቁጭ አሉ። የነመለስ ተዉኔት በዚህ አላበቃም። አሸናፊ “ጐላ”ን ጨምሮ በርካታ ወጣቶችን በማስረሸንና በግፍ በማሰቃየት ወንጀል ተከሶ የቆየዉ ሰለሞን ተመስገን (የወሲቡን ጉዳይ ልብ ይለዋል!) በሞት እንዲቀጣ የተበየነበት በዛሬዉ ዓመት ነበር። ንግዴ ለማ በገዢዉ በታጨች ማለትም ህዳር 2000 ዓ.ም ነበር የሞት ብይኑ የተደመጠዉ። ምን ዓይነት አሳፋሪና አሸማቃቂ ተግባር እነ መለስ እየፈጸሙ እንዳሉ ይህ ጉዳይ አመላካች ነዉ።

የሚገርመዉ እነሱ የሚሾሙትና የሚሸልሙት ወንጀለኛ/ኢሰፓ “የታጠበ ንጹሕ አድርገዉ ለማሳየት መዳዳታቸዉ ነዉ። በአንፃሩ ወንጀል የሌለበት በስመ ደርግ ኢሰፓ የነበረ የተቃዋሚን አባል በመንቀስ የታቀፈበትን ድርጅት በጅምላ ሲያብለጠልጡና በአደንቋሪ ስድብ ሲያላዝኑ ጭምር መታየታቸዉ ነዉ። ጉዳዩ ግን ደርግ፤ኢሕአፓ፤ቅንጅት፤መድረክ ወዘተ…..የመሆንና ያለመሆን አይደለም ቁም ነገሩ። የትኛዉን አባልና ሹመኛ ባገኘዉ አጋጣሚ በማሕበረሰቡ ላይ ወንጀል ሰርቷል?ወይስ አልሰራም? የሚለዉ ነዉ አንገብጋቢዉ ነጥብ። ወንጀለኛ ከሆነ ባግባቡ ፍርዱ ሊቀበል ይገባል። በዚህ መነጽር ከታየ “የንግዴ” ለማ ቦታ “የካቢኔ ፀሃፊነት” አልነበረም። የክልሉን ሕዝብ ነገ ጥዋት በጅምላ ላለማስፈጀቷ ምንም ማረጋገጫ የለም። “የታጋይ ድምፅ ይጮሃል! ይጮሃል ከመቃብር!”

በነገራችን ላይ ንግዴ ለማ በ84 ዓ.ም ስትጋለጥ መድረክ ይመሩ የነበሩት ካድሬዎች ከቦታዉ የተገለሉት ብዙ ሳየቆዩ ነበር። ቀደም ሲል በዚህ ጋዜጣ የተገለጸዉ ሃ/ስላሴ የተባለዉ ከአርቲስት ኪሮስ አለማየሁ ጋር በመርዝ ሲጠፋ ፤መቶ አለቃ ታደሰ የተባለዉ “የኢዴመን” አባል ያለ አንዳች ጥፋት በ86 ዓ.ም እስር ቤት ተወርዉሯል።የት እንደደረስም አይታቀወቅም።ማዓሾ የተባለዉ የህወሓት አባልና ካድሬ “40 ሺሕ ብር ሙስና ፈጽሟል” በሚል ባልተጨበጠና ማስረጃ በሌለዉ የፈጠራ ክስ ሆለታ እስር ቤት ተወርዉሮ ሲያበቃ በዚያዉ ሕይወቱ እንዳለፈ ማረጋገጥ ተችሏል። ኢሕአፓዎች ምን ይላሉ? ለዛሬ በዚህ አበቃሁ። //-// www.ethiopiansemay.blogspot.com getachre@aol.com May 22, 2010

No comments: