Tuesday, April 7, 2009

ለደረሰብኝ የሞራል ዉድቀትና የንብረት ዉድመት

ለደረሰብኝ የሞራል ዉድቀትና የንብረት ዉድመት ተጠያቂዉ ማን ነዉ? ጌታቸዉ ረዳ

(መጋቢት 2002) ዛሬ ቀን የህዋ ሰሌዳዎችን ስጎበኝ ኢትዮጵያ-ዉስጥ-ይታተማልተብሎ በተቃዋሚነት ስም የሚታወቅ ጋዜጣ ባወጣዉ ዜና አቶ በረከት ስሞኦን “መንግሥት በሰብአዊ መብት ላይ አሳፋሪ ሪኮርድ-የለዉም”-ሲሉ ለጋዜጠኖች መግለጫ ሰጡ፡ ሲል የዘገበዉ ዜና ሳነብብ፤ አጋጣሚ ሆኖ ሰብአዊ ጉዳዮችን በመዘገብ ዜጎች ብሶታቸዉን የሚያሰሙበት ጦቢያ ጋዜጣ ላይ “እንነጋገር”የሚል መድረክ ሳነብብ ነበር። ታዲያ በዛ አምድ የተዘገበ ያንድ ዜጋ እሮሮ አንብቤ ስጨርስ ሕሊናየ ተቃጥሎ እንዳለ ፡የበረከት ስሞኦን የ “ህወሓት መንግሥት” አኩሪ ሰብአዊ መብት ሪኮርድ እንዳለዉ የሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሳነብብ ይበልጥኑ የተቃጠለዉን ሕሊናየ ተቃጠለ። እወቁ ያገራችን ዘፋኝ ጥላሁን ገሰሰ የዘፈነዉ “ፍጡር ካላዘነ ለፍጡር ስቃይ ከቶ ጤና የለም በዚች ምድር ላይ…”እያለ አንጎራጎረዉን ትምርታዊ ዜማ አስታወሳኝ። በረከትም መለስም ስብሐትም እነ ገብሩም እነ አዉዓሎም ወልዱ እነ አበበ ተክለሃይማኖት እነ አረጋሽ አዳነና… እና እነ እነዎቹ…የዜጎች እሮሮ የረገጡበትን ማሕደር ወረቀቱ ነክሶ ይዞታልና ለመዋሸት ቢዳዳቸዉም፤ ማሕደሩ አይለቃቸዉም። ያነበብኩት በወረቀት ላይ ተዘግቦ የቆየ የዜጎችን እሮሮ አብራችሁ እንድታነብቡ የወያኔ መንግሥት “ለደረሰብኝ የሞራል ዉድቀትና የንብረት ዉድመት ከማን እካሳለሁ? በማለት እሮሮአቸዉን በማሰማት “ኤርትራዊዉ የህወሓት መንግሥት” በሰመ ሞክሼነት አስሮ ያንገላታቸዉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በረከት ስሞኦን እየዋሸ ያለዉ ቡክን ሕሊናዉ መጪዉ ፍትሕ ምን እንደሚጠይቀዉ ላስገነዝበዉ እወዳለወሁ። “የወያኔ ገበና ማሕደር” ዓምዳችን የመዘገበዉ አሳዛኙ የዜጎች እሮሮ እነሆ።- “ለደረሰብኝ የሞራል ዉድቀትና ንብረት ዉድመት ከማን እካሳለሁ?” (ከበደ ገርቢ) - ጦቢያ (ጋዜጣ) ሰባተኛ ቁጥር19 ነሓሴ 11 1999 ዓ.ም. ሥራየ ንግድ ነዉ። በናዝሬት ከተማ ትዳር መስርቼ ፤ንብረት አፍርቼ ከመኖር በስተቀር በፖለቲካ ሥራ ዉስጥ ምንም ተሳትፎ አልነበረኝም፡ አሁንም የለኝም። በዘር ማጥፋት ወንጀል ሕዳር 15 ቀን 1990 ዓ.ም ተይዤ፤ በአቃቂ መታጎርያ ካምፕ ለ2 ዓመት ለ7 ወር ታስሬ የአካልና የሞራል ጉዳት፤ የንብረት መዉደም ጉዳት ደርሶብኛል። የእሥራቱ መንስኤ “የሻሸመኔ” ወረዳ አስተዳደር በነበርክ ጊዜ ሰዎችን በሥልጣን አስረህ በደርግ አባሎች እንዲገደሉ አድርገሃል” የሚል ነዉ። እኔ በሻሸመኔ ከተማ ኖሬም አላዉቅም። ከንግድ ሥራ ዉጭ የመንግሥት ሹም ሆኜም አላዉቅም በማለት ደጋግሜ አቤት ብልም የልዩ ዓቃቤ ሕግ ባልፈጸምኩት ወንጀል አገር ሰላም ነዉ ብየ ከተቀመጥኩበት ቤቴ አዉጥቶ ይህን መሰሉን አሳዛኝ ድርጊት ፈጽሞብኛል። እኔ አስከማዉቀዉ ድረስ የታሰርኩበት የሻሸመኔ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበረዉ አቶ ከበደ ገብሬ ነዉ በማለት ነዉ። በስመ መኩሼና በይመስላል። በእሱ ቦታ እኔን ለጭዳ ያቀረቡኝ ሰዎች ይህንን ወረዳ አስተዳዳሪ ወደ አልሰራበት አካባቢ ወስደዉ ሕዝቡም እና እንኳን ወንጀሉን ቀርቶ ሰዉየዉንም ራሱን አናዉቀዉም አሰኝተዉ በነፃ እንድሰናበት ማስደረጋቸዉን በአሉኝ መረጃዎች አማካይነት በማጣራት ላይ እገናለሁ። እስቲ አንባቢ ይፍረደዉ! “ከበደ ገርቢ” እና “ከበደ ገብሬ” በእዉነት የስም ሞክሼነት አላቸዉ?የአባት ስም እንዲህ ተለያየቶ እያለ በእዉነት የስም ሞክሼነት አላቸዉ? የአባት ስም እንዲህ ተለያይቶ እያለ የአያቶቻችን ስም ሳይፈተሽ ልዩ ዓቃቤ ሕግ የትኛዉን መረጃ ሰብስቦና የትኛዉን ጭብጥ ይዞ እኔን በወንጀለኛነት እንደፈረጀ ለማወቅ በእጅጉ ግራ ያጋባል። የልዩ አቃቤ ሕግ አሠራር እንደዚህ በዘፈቀደ ከሆነ በይሆናል የተከሰሱትን ሰዎች ብዛት ቤት ይቁጠረዉ ብሎ ዝም ማለቱ ይሻላል። ያም ሆነ ይህ እኔም በዘር ማጥፋት ወንጀል በመዝገብ ቁጥር 925/89 በልዩ ዓቃቤ ክስ ቀርቦብኝ ያላንዳች ጥፋት ሁለት ዓመት ከሰባት ወር በእሥር ፍዳዮን ቆጥሬ መፈጠሬን ጨርሶ በጠላሁበት ወቅት ጉዳዬ የቀረበለት የፌደራሉ የከፍተኛ ፍረድ ቤት የወንጀል ችሎት የቀረበብኝን የዉንጀላ ክስ ዉድቅ በማድረግ ሰኔ 29/92 ዓ.ም. በነፃ አሰናብቶኛል። እንግዲህ ምንም ወንጀል ሳልሰራ ወይንም ወንጀል ለመስራቴ በፖሊስ ምርመራ ተጣርቶ መረጃ ተሰብስቦ ሳይቀርብለት ከሜዳ ላይ እንደከብት ነድቶ በእሰር ያማቀቀኝ የልዩ ዓቃቤ ጸ/ቤት ነዉ ወይንስ መንግሥት የአካልና የሞራል ካሳየን የሚከፍሉኝ?ይህ ተጠያቂነት በማን ላይ እንደሚያርፍ ተለይቶ አስካልታወቀ ድረስ በደል የደረሰበትና እየደረሰበት ያለዉ ኢትዮያዊ ሁሉ እየተበራከተ ሊሄድ ነዉ። በዚህ እሥር ሳቢያ በንብረቴ ላይ የደረሰዉ ዉድመት ደግሞ በእጅጉ የሚሰቀጥጥና የሚያስደነግጥም ነዉ። እኔ 52 ዓመት አስኪሆነኝ ድረስ በየቦታዉ ተንከራትቼ ንብረት አፍርቼ ነበር። ልዩ ዓቃቤ ሕግ እኔን ከመኖርያየ ጨምድዶ ወህኒ ቤት የወረወረኝ በድነገት ስለነበረ ንብረቴ በየቦታዉ ተዝረክርኮ የሚጠፋ ሆነብኝ። ይህንን ለመከላከል ባለቤቴን ወ/ሮ መቅደስ ወልዴን ለንብረቴ አስተዳደር ወኪልና ሙሉ ነገረ ፈጅ አደርጌ መሾም ግድ ሆነብኝ። ባለቤቴም በዘር ማጥፋት ወንጀል ተይዘዉ ፍርድ ቤት እንኳን ሳይቀርቡ 9 ዓመት በእስር የሚማቅቁ ሰዎች መኖራቸዉን ስለምታዉቅና የእኔም ጉዳይ እንደዚያዉ ይሆናል በማለት ገንዘቤን መዝረፉን ተያያዘችዉ። አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አስቀምጨዉ ከነበረዉ ገንዘቤ ዉስጥ በቼክ ቁጥር ኢ.ቢ.ዋይ101622 በአንድ ቀን ብቻ 56፣000 ብር አዉጥታ ወስዳለች። ዳግመኛም በአቶ ክፍሌ ተፈራ ዳኝነት ከሚሰበሰብ ዕቁብ 31,000 ብር ተቀብላለች። ከአቶ ሰይድ ራሕመቶ እጅ 30,000ወስዳለች። በተጨማሪም ወ/ሮ ብዙነሽ ገብረ ሚካኤል10,000በደረሰኝ ተረክባለች። እንግዲህ የምወዳት ባለቤቴ ይህንን 127000 ብር በጥሬ ገንዘብ በእጇ አድርጋ ልዩ ዓቃቤ ሕግ አይለቀዉም በሚል እምነት እርግፍ አደርጋ ተወቺኝ። ከዚያም ያለ ጥያቄ እስር ቤት ወድቄ ቀረሁ። ይህ ብቻ አይደለም። የ3መኪናዎች ገቢ የ31 ወር (የ2 ዓመት ከ7 ወር ገቢ) እንደተዘረፍኩኝ ነኝ። እንደገናም ሙሉ የቤት ዕቃ፤የምግብ ጠረጴዛ ፎቴ፤ማቀዝቀዣ፤ቴሌቪዥን፤ቴፕሪኮርደር በርካታ የሱፍ ልብሶች በአጠቃላይ ከ35000 ብር የሚበልጥ ንብረት ተዘርፌአለሁ። ሌላዉ ቀርቶ ባለቤቴ መኖርያ ቤቴን ሳይቀር በኮንትራት አከራይታ አንዱን የጋራ መኪናችንን ከዉጭ በወለደቺዉ ልጅ ስም አዙራ ለዕለት መዉደቂያ እንኳን አሳጥታኝ በአሁኑ ጊዜ የ የማድረዉ ከዘመድ ቤት ተጠግቼ ነዉ።የዘረፈቺኝ ባለቤቴ መፈታቴን ስትሰማ የት እንደደረሰች አላዉቅም። ፈልጌ አፈላልጌ ላገኛት አልቻልኩም። ስለዚህም በምስራቅ ሸዋ ዞን ፓሊስ መምሪያ ክስ መስርቼ ወ/ሮ መቅደስ እየተፈለገች ነዉ። እንግዲህ ከሕፃንነት ጀምሮ በመታሰሬ ተዘርፌ የቁም ሙት ሆኛለሁ። በዚህ መልክ በልዩ ኣቃቤ ያልተጣራ ክስ የስንቱ ቤት እንደፈረሰ፤የስንቱ ቤት እንደተዘረፈ መገመት ትችላላችሁ። ይህንን ጉድ እያዩ ሰዉ አገር አለኝ፤ሰብአዊ መብቴ ይከበራል፤የሕግ ጥበቃ ይደረጋል ብሎ መናገር ይቻላል?በሕግ ከለላ ቤቴ ፤ንብረቴ፤ሕይወቴ ከአደጋ ተጠብቆ እኖራለሁ ብሎ ይተማመናል? በአጠቃላይ ከእሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ለወደመዉ ንብረቴ፤በእስራት ለተሰቃየዉ ሰዉነቴ፤በሚያሳዝን ሁኔታ በደል ለደረሰበት ሞራሌ ካሣ የሚከፍለኝ ማነዉ?” በማለት ዜጎች በራሳቸዉ ቃል “ይህንን ጉድ እያዩ ሰዉ አገር አለኝ፤ሰብአዊ መብቴ ይከበራል፤የሕግ ጥበቃ ይደረጋል ብሎ መናገር ይቻላል?በሕግ ከለላ ቤቴ ፤ንብረቴ፤ሕይወቴ ከአደጋ ተጠብቆ እኖራለሁ ብሎ ይተማመናል?” በማለት የጠየቁትን የስንቱን ቤት እንደፈረሰ የስንቱን ዜጋ መብት እንደተረገጠ “በረከት ስሞኦን” ተጎትቶ ለፍረድ ሲቀርብ የሚመልሰዉ አንዱ ጥየቄ ይኼኛዉ ይሆናል። በረከት ስማኦን “አኩሪ የሰብአዊ መብት ሪኮርድ አለን” በማለት ፋሽስታዊ ግፍንና ብልሹ አስተዳደርን አኩሪ ሪኮርዱ ይሄንን የዜጎችን ግፍ ነዉ! የዜጎች እሮሮ በጊዜ እርዝመት ምክንያት ተድበስብሶ እንዳይቀር ሁሉም ዘብ ይቁም ፤ማሕደሮቻቸዉን እንቆፍር፤ህያዉ ይሁን፤ይመዝገብ፤ይወራ፤ይሰራጭ!አዳዲስ ግፎችን ለጊዜያዊ የፖለቲካ ማስጠበቂያ እያወራን ከባድ ፤ከባድ ወንጀሎቻቸዉ እንዳይረሱ እንጠንቀቅ ። ጌታቸዉ ረዳ www.Ethiopiansemay.blogspot.com

No comments: