የረሳናቸዉ ሰማዕታት
(ከወያኔ ገበና ማህደር)
ጌታቸዉ ረዳ
“ሞኝና ወረቀት የያዘዉን አይለቅም” እንዲሉ በወረቀት ከመመዝገብ ያመለጡ አያሌ የወያነ ትግራይ ነጻ አዉጪ ድርጅት ወንጀሎች እንዳሉ ሁሉ ፣ወረቀት የመዘገባቸዉ በተባባሪዎቹና በመሪዎቻቸዉ የተፈጸሙ ወንጀሎችም አሉ። ከዚህ የተነሳ፣ ወያኔ የብዙ አመታት ወንጀሎቹን ልደብቅ እንኳ ቢል “ሞኝና ወረቀት የያዘዉን አይለቅም” ነዉና የተዘገበ ስለሆነ ፣ በጊዜ ጉዳይ ይዘገይ እንደሆን እንጂ ይጠየቅበታል።
ይልቅኑ የብዙ አመታት በርካታ ወንጀሎቹ በየቀኑ ይፋ ሆነዉ በየሚዲያዉ እንዳይሰራጩ ፣ተቃዋሚ ነን የሚሉን ክፍሎች ፣ በየወቅቱ ከሚቀያየሩ ሁኔታዎችና በአዳዲስ የፖለቲካ ተዋናዮች እየተማረኩ፣አዳዲስ የድርጅት አርበኞቻቸዉን ዝና ለማስቀደም ሲሉ “ለአንድነትና ለሃገሪቱ ክብር ሲሉ መስዋዕት ሆነዉ ብዙ አመታት አልፎአቸዉ በየጉድጓድ እስር ቤቶች ተወርዉረዉ አስቸጋሪ ሕይወት እየገፉ ያሉት እና በሕይወት የሌሉ ከሕዝቡ ሕሊና እየተረሱ-የመጡ ብዙ እጅግ በርካታ የሆኑ ወጣቶችና አዛዉንቶች ኢትዮጵያዉያን እንዲረሱ አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸዉ።
በየእስር ቤቱ ሆነዉ የድርጅት አባሎች ያልሆኑ የ“አድኑን” ድምጽ ካስሰሙ ብዙ አመታት ላለፋቸዉ ዜጎች በሻማ መብራት የመዘክር መድረክ ሳያሰታዉሷቸዉ ዛሬ የምናያቸዉ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ክፍሎች ለድርጅታቸዉ ቅርብ የሆኑት መሪዎቻቸዉ ሲታሰሩ ብቻ “ነጋ ጠባ ካለመታከት” ሲጮሁላቸዉ ስንመለከት፣ ይህ “የድርጅት ፍቅርና ወገንተኝነት” *በሽታ* ሳይታወቃቸዉ የወያኔዉን-ያህል “የወገንተኝነት” የስበት ሃይል እነሱም እየተጓዙበት ይመስላሉ።ጎሰኛነት፣ጎጠኛነት ወገንተኛነት “ለነገድ”ፍቅር ብቻ የሚገለጽ ጠባብ የሕሊና ፍቅር ቢሆንም ፣ “የድርጅት ተከታዮች”-ለመሪዎቻቸዉ ካላቸዉ “ልዩ ፍቅር እና አክብሮት” የተነሳ መስዋዕት ለሆኑት ከድረጅታቸዉ ዉጭ ለሆኑ ለሌሎች ዜጎች ያለቸዉ ፍቅር በጣም “ደካማ”ስለሚያደርገዉ “ከድርጅታቸዉ ዉጭ ለሕዝብ መብት ሲሉ ለሚሰቃዩ እና መስዋዕት ለሆኑ ሀገራዊ ዜጎች”እኩል አክብሮት ካልሰጡ፡ በተቃዋሚነት ቢንቀሳቀሱና ቢጮሁም “የድርጅት ወገንተኛነት-ስሜት”-“ከጎሳ ወገንተኛነት ስሜት” ስለማይለይና ለትግሉ ጎጂ ስለሚሆን ፣ ለተወሰኑ የወያኔ ሰለባ ለሆኑ ግለሰቦች ብቻ “ጥብቅና ቆሞ -ወያኔን ከስልጠኑ እስወግዳለሁ ማለት የ ”ፋንታሲ” ጉዞ ስለሚሆን ዛሬም ይታሰብበት እያልኩ ወደ ዛሬዉ ከሰማዕታት ማህደር የመረጥኩላችሁ በወያኔ ትግራይ መንግስት የተገደሉት “መስዋዕቱ ባህታዊ ፈቀደ ስላሴን” በዚህ ዓምድ እናስታዉሳቸዋለን።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የገደልዋት እንደነበሩ ሁሉ፣ የሞቱላትና ዛሬም የሚሞቱላት አላጣችም። አገራችን በአረመኔዎች በተስፋፊዎች ሴራ ምክንያት ሃይማኖቷን ለማስለወጥ አንድነቷን ለማፈራረስ አያሌ ጊዜ አስቸጋሪ ወቅቶችን ተጋፍጣለች። በዘመናችን እንኳ በግምባር ቀደም የሚታወሱት እፁብ ኢትዮጵያዊያን መካከል መስዋዕቱ “ፕሮፌሰር ዶ/ር አስራት ወልደየስ” እና ከሞት በር በሕዝብ ብርታት ተጎትቶ የወጣዉ አሁንም አርአያነቱ እየቀጠለ ያለዉ ወጣት ሙሁሩ “ፕሮፌሰር ዶ/ር ታየ ወልደሰማያት” ፈታኝ በሆኑ ወቅቶች ያገር ጠላት የሆነዉን ባንዳዉ ወያኔን ተጋፍጠዉ አኩሪ ታሪክ ካስመዘገቡት “ኩሩ” ዜጎቻችን ጥቂቶቹ ናቸዉ። እነ ፊታዉራሪ ጎሪ እና ኤርትራ ኢትዮጵያዊዉ አቶ አበራ የማነአብ እና በሺዎች ሳንረሳ ማለቴ ነዉ።
በሃይማኖት መሪዎቻችን በኩል ወያኔን በመቃወም ብዙ ጳጳሳት ካህናትና ድያቆናት ለሞትና ለስደት ተዳርገዋል። ወያኔ የኢትዮጵያን ተዋህዶ ቤተክርስትያን ለማዳከም በረሃ ዉስጥ እያለ በካህናትና በዲያቆናት እንዲሁም በመነኮሳት ላይ አሰቃቂ ግፎችን መፈጸሙ ከአንድ ሁለት ጊዜ በወያኔ የገበና መህደር ላይ ለህዝብ አቅርቤ እንደነበር ይታወሳል። ጣሊያኖችና ግራኝ መሐመድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ላይ ሲፈጽሟቸዉ የነበሩት ግፎች ዛሬም ወያኔ በግልጽና በተዛዋዋሪ እየፈጸማቸዉ ይገኛል። ጣሊያን “አገሬን አልክድም” ባሉት በመስዋዕቱ ጴጥሮስ ላይ የፈጸመዉን ግፍ፣ ወያኔ ደግሞ ዓለም በቃኝ ብለዉ በመነኮሱ ባህታዊያን ላይ የጥይት ቃታ ስቦ ፋሽስታዊ ግፍ ፈጸሟል። በወያኔ ጥይት ከተረሸኑት መነኮሳት/ባህታዉያን መካከል አንዱ “ብህታዊ ፈቃደ ስላሴ” ናቸዉ።
በጥር 1 ቀን 1989 ዓ/ም የኚህ ባህታዊ ሞት በተሰማ ወቅት፣ ለባህታዊዉ ሞት ቀጥተኛ ተጠያቂ የሚሆኑት የወያኔዉ ጳጳስ ጳዉሎስ እና መንግስታቸዉ ፋሽስታዊነታቸዉ ያረጋገጠበት እና የወያኔ ፋሽስታዊ ባሕሪ ሲጠራጠሩ ለነበሩት ሁሉ ማንነቱ ያሳየበት አሳዛኝ ድርጊት ነበር። በወቅቱ ብዙ ጋዜጦችና መጽሄቶች በዚህ አሳዛኝ ድርጊት ላይ ዘግበዉ እንደነበር ይታወሳል። ከዘጋቢዎቹ አያሌ መጽሄቶች መካከል “ላንዳፍታ” ተብሎ ሲጠራ የነበረዉ አሜሪካ አገር ዉስጥ ሲታተም የነበረዉ በወቅቱ የዘገበዉን “ሰላምታ ከወደ አገር ቤት ከወርቃየሁ” በሚል የቋሚ አመደኞቹ የደብዳቤ ልዉውጥ አምድ ላይ ስለ ባህታዊዉ አሟሟት ዘግቦት ነበር። እናስታዉሳችሁ።
“ …ጥር ከመግቢያዉ ጀምሮ የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንና ምዕመናኑ ሲታመሱ ነዉ የከረሙት። ጥር 1 የልደታ ዕለት ባህታዊ ፈቃደ ሥላሴ በእስጢፋኖስ ቤተክርስትያን መገደል ትልቅ ሽብር ፈጠረ። ጥር-4-ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስትያን በዓሉን ለማክበርና ቃለ ቡራኬ ለመስጠት በፖሊስ ታጅበዉ በቦታዉ የተገኙት አባ ጳዉሎስ “ቡራኬ” ሲሰጡ ሕዘቡ እጁን እያወዛወዘባቸዉ ተቃዉሞዉን በመግለጽ “ሃይል የእዚአብሔር ነዉ ቡራኬዉን አንቀበልም” የሚል ከፍተኛ ጩኸት ተሰምቷል።
በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ብጥብጥ ተነስቶ ብዛት ያላቸዉ ምዕመናን በፖሊስ ታፈሱ። ጥር 7 የሥላሴ ዕለት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን ከተገኙ ምዕመናን መሐል ፖሊስ ወደ 20 የሚጠጉ የቤተክርስትያኑን ወጣት መዘምራን አፍሶ በመዉሰድ እንዳሰራቸዉ ጋዜጦች ዘግበዋል። ጥር 11 ቀን የጥምቀት ዕለት ጃልሜዳ አባ ጳዉሎስ አሁንም በፖሊስ ታጅበዉ ቡራኬ ለመስጠት ከቦታዉ ሲደርሱ ሕዝቡ ቡራኬያቸዉን ላለመቀበልና ተቃዉሞዉን ለመግለጽ ምዕመናኑ ጠቅላላ ጃንሜዳ ለሳቸዉና ለደቀመዝሙሮቻቸዉ ትቶላቸዉ ሄዷል። እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነዉ በዘህቹ በጥር ወር ግማሽ ጊዜ ነዉ።
እንግዲህ ወዳጄ ይግለጡ “ይሰዉረን ከመዓቱ” ብለን እግዚኦታ ከመግባት በቀር ምን ምርጫ አለን። ይሄ በኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እየታየ ባለዉ ሁኔታ አንዳንድ መጤ ሃይማኖት የተደሰቱበት ይመስላል። እንደዉም እንደሚወራ ከሆነማ ያባ ጳዉሎስ የቅርብ አማካሪያቸዉ ጴንጤ ነዉም ይባላል። ምናልባት እሳቱን የሚጭሩ እነሱ ይሁኑ ሌላ ሰይጣን ሁሉም የሚያይ አምላክ ያዉቃል።ለማንኛዉም ያገራችን ነገር፣ ከመቼዉም ጊዜ በላይ እየከፋ ሄዷል። ሲከፋን ጊዜ ሳንመርጥ ከአምላካችን የምንነጋገርብት ደጀ ሰላም እያስፈራን ከመጣ ሌላ ምንቀረን እንላለን። ቢሆንም የተስፋ አገር ልጆች ነን እና በክረስቶስ ተስፋ አንቆርጥም። አንድ ቀን አንዴ ሁሉ ነገር ይስተካከል ይሆናል። የዛ ሰዉ ይበለን!”
በማለት ሃዘኑን ሲገልጽ፡ በወቅቱ የባህታዊዉ አገዳደል የቀረበዉ ዘገባ በዜና መህደሩ እንደሚከተለዉ ዘግቦት ነበር።
ባህታዊ ፈቀደ ሥላሴ በጥይት ተገደሉ
ጥር 1ቀን 1989-ዓ.ም.አዲስ አባባ መስቀል አደባባይ በሚገኘዉ ቅዱስ አስጢፋኖስ ቤተክርስትአን የንግሥ በዓል ይካሄዳል። በመጀመርያ ታቦቱ መጥቶ ሁለት ጊዜ ቤተክርስትያኑን ዞሮ እንደቆመ ያሬዳዊ ዜማና የሰንበት ተማሪዎች ዝማሬ ተሰምቶ እንዳበቃ የደብሩ አለቃ ንግግር በማድረግ የዕለቱን ትምህርት እንዲአደርጉ ፓትርያሪኩ ጋብዘዉ አቡኑ ለንገግርና ለስበከት ሲዘጋጁ አራት ባህታዉያንና ሕዝቡም አብሮ እጅ በማዉጣት “ያቀረብነዉ 21 ጥያቄ ይመለስልን” ሲሉ ይጠይቃሉ። በበዓሉ ላይ የተገኙትን አቡነ ጳዉሎስ፣- የኦርቶዶክስ እምነት መሪነትን የሚቃወሙና የማይቀበሉ ባህታዉያን በወቅቱ በሃይማኖቱ ላይ እየደረሰ ያለዉ መከፋፈል ለመግታት ፣ ‘እምነታችን ላይ ሃይማኖታችን እየተደፈረ ነዉ’-በማለት ‘ማሕበረ ሃዋርያት” በሚል ስም የተቋቋመዉ አዲሱ ማሕበር ያዘጋጀዉን 21 ነጥብ የያዘ የጥያቄ ጽሑፍ ለመስጠት ባህታዉያኑ ቀረብ ለማለት ይሞክራሉ።
በዚህን ጊዜ አንድ ፖሊስ “ጥያቄዉን በጽሕፈት ቤታቸዉ እንጂ መጠየቅም መመለስም አይቻልም ብለዋል”። ሲል መልስ ይሰጣቸዋል። ከዚህ በመቀጠልም የማሕበረ ሐዋርያት በአቋም ደረጃ ያስተላለፉትን 10 ገጽ የያዘ ወረቀት ለፖሊሱ ወርዉረዉ ለፓትርያሪኩ ስጥልን እንዳሉትና እንደተቀበላቸዉ ባህታዊ ሃይለሚካኤል የተባሉ ገልጠዋል። ወዲያዉ ግርግርና ጫጫታ ተፈጥሮ- በዚህ ጊዜ ስለተፈጸመዉ ነገር የተለያዩ ነገሮች ተሰምተዋል። ባንድ በኩል ፓትርያሪኩ ከጎናቸዉ ሽጉጥ በማዉጣት በታቦቱ ትክክል ወደ ሰማይ አንድ ጥይት እንደተኮሱና ከዚያም በመቀጠል አጠገባቸዉ የነበሩ ሊቀ ብርሀኑ የተባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትአን የቅርብ አለቃ ሽጉጣቸዉን አዉጥተዉ ሲተኩሱና ሌሎቹም ከየነጠላቸዉ ስር ሽጉጥ በማዉጣት እየተኮሱ ሳለ ባህታዊ ፈቃደ ሥላሴ መዉደቃቸዉ ሲወራ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአባ ጳዉሎስ ጠባቂ የሆነ ፖሊስ ተኩሶ እንደመታቸዉ ተወርቷል።በዚህ መሃከል ባህታዊ አባ ፈቃደ ሥላሴ ፓትርያሪኩ አጠገብ በቅርብ ዕርቀት ተመትተዉ ራሳቸዉ በፅላቱ ስር አግራቸዉ በፓትርያሪኩ ሰር ሆነዉ ወድቀዉ መንጋለላቸዉን ያዩ መሆኑን እኚሁ ባህታዊ ገልጸዋል።
እንግዲህ በአሁኑ ጊዜ ይህ ጥያቄ ለማቅረብ ለምን አስፈለገ ተብሎ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ባህታዊዉ ሲመልሱ “በመጀመርያ ጥያቄአችንን በሰላማዊ መንገድ በተለያዩ ወቅት ለፓትርያሪኩ አቅርበን ነበር። ነገር ግን በጥያቄዉ ምክንያት ባህታዉያን ቤተክርስትያን እንዳንገባ እንዳንሳለምም ታግደናል። ፓትርያሪኩ ጽህፈት ቤትም ስንሄድ እያባረሩ ይደበድቡናል።ስለዚህ ጥያቄ ለማቅረብና መስተካከል ያለበትን ለመጠቆም አማራጩ ፓትርያሪኩ የሚገኝትን ክብረ በዓል መጠቀም ብቻ ስለነበር ነዉ” ሲሉ መልሰዋል። በመጨረሻ ላይ ምዕመናን እንዳይንቀሳቀሱ ተደርጎ አባ ጳዉሎስ (“ፓትርያሪኩ”) በጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች ታጅበዉ ከቤተክርስትያኑ መዉጣታቸዉ ተስተዉለዋል።
በዚህ ጉዳይ የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም በቅርቡ በአሜሪካ ና አዉሮፓ ጉብኝት አድርገዉ የተመለሱት ባህታዊ ገብረመስቀል በፖሊስ ተይዘዉ በ እስር ላይ ያሉ መሆናቸዉን ዘግይቶ የደረሰን ዜና ገልጿል። ባህታዊ ገብረመስቀል በእስር ላይ እንዳሉ መታመማቸዉና አለመፈታታቸዉንም ተዘግቧል። ሲል በጥር 1 ቀን 1989 ዓ.ም. በወያኔ ጥይት ስለ ተገደሉት ስለ ሰማዕቱ ባህታዊ ፈቃደ ሥላሴ አገዳደል ዘግቦ ነበር። በእኛም የእነኚህ የሃይማኖት መሪዎች ገድልና መስዋዕት ዛሬም በሕሊናችን እና በታሪካችን የሰማዕታት ማህደር ህያዉ ናቸዉ። ኢትዮጵያ በነጻነት ትኑር!ጌታቸዉ ረዳ መጋቢት 2001 ዓ.ም www.Ethiopiansemay.blogspot.com
No comments:
Post a Comment