ያልተወራረደ የወላጆቻችን ሂሳብ አለ፤ እሱን የሚያወራርድልን ኢትዮጵያዊ መሪ ማን ይሆን?
ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 4/8/26
እንደምን ሰነበታችሁ? እንደ ሁሌም Ethiopioan
Semay ድረገጽ
ላይ በMarch 2026 (31 ቀን ውስጥ) ጠቅላላ 297,715 አንባቢዎች
እንደተጎበኘ ለመግለጽ እወዳለሁ።
አሁን ወደ ጉዳያችን እንግባ።
ያልተወራረደ የወላጆቻችን ሂሳብ ስናስብ የምናድር እና ሳያሳስባቸው የሚያድሩ ለጥ ብለው የሚተኙ
ቢኖሩም እኛ ግን ያልተወራረደ የወላጆቻችን የሂሳብ አደራ አለብንና አልተኛንም! በቅርቡ የባሕር ወደባችንን እናስመልሳለን ብሎ አብይ አሕመድ
ለራሱ ታሪክ መጠሪያ ያድርገው አያድርገው ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ መጠቀሚያ ይሁን አይሁን ሞቶ የነበረና እንዳናነሳው ስንወገዝ የነበርን
ኢትዮጵያዊያን ድንገት ሳናስበው በዚህ ሰዓት ርዕሱ መነሳቱ ብቻ የሚበረታታ እንጂ የሚኮነን አይደለም።
ጠቃሚ ሀገራዊ
ጉዳዮች በተደጋጋሚ ካልተወያዩ ብዙ ጊዜ ይረሳሉ ወይም ወደ ጎን (sidelined) ይደረጋሉ። አንገብጋቢ ብሔራዊ ጉዳዮች በሻጥርም ይሁን በተፅዕኖ
ወይንም በእንዝህላልነት እንዳይወሱ ሲደርጉ ሕብረተሰቡም ይሁን ምሑሩ ክፍል "የዝምታ ሽክርክሪት" (spiral of silence) ወይም
"የፖለቲካ ትውስታ
መርሳት" (political amnesia) የክስተት
ደረጃ ሲደረስ ዋናው የፖሊሲ ክርክሮች በፍጥነት እንዲደበዝዙ እና እሰከወድያኛው
ድረስ ዋናው ጉዳይ እልባት እንዳያገኝ ያደርጋል።
ለ35 ዓመት የተሰራብን "የዝምታ ሽክርክሪት" (spiral of
silence) እና "የፖለቲካ ትውስታ መርሳት" (political amnesia) ሂሳብ እንዳናወራርድ አድርጎናል።
ሃያሉ አክሱም ሃያልነቱም ሆነ ሞቱ ከባሕር ወደብ ጋር የተያያዘ ነበር። እትብታችን ከባሕር
ጋር ይተያያዘ ነበርና ያንን ቆርጡና ገደሉን። የሂሳብ ማወራረዳችን ከዚህ ይጀምራል።የመጨረሻዎቹ የአክሱም ነገሥታት የሞቱትን ዘላለማዊ ሞት እንዳንሞት ለሃያለንታችን እና ላለሞታችን
የሚደረግ ትግል ከተሰራብን "የዝምታ
ሽክርክሪት" እና “ትውስታን ከመርሳት” የመወጣቱ ትግል በይደር የሚቆይ ጉዳይ አይደለም።
የሙሶሎኒ ልጆች! የባሕር ወደባችንን ምፅዋን ከተቆጣጠሩት እነሆ 35 አመታቸው ነው። አገራችን
ውስጥ እንዳንኖር “አማራ” ከአገራችን አስለቀቀን እያሉ አማራን በውሸት ሲከሱና ሲያደነቁሩን እንደነበር ታሪክ ዘግቦታል።
አማራ ከሀገራችን አስለቀቀን ብለው ወደ ሳሕል በረሃ ገቡ።
መሪያቸውም ኢሳያስ አፈወረቂ ይባላል። ኢሳያስ “ወዲ ኣርብዓ” (በቆየ ሕግ 40 አመት የኖረ
እንግዳ ኤርትራዊ የሚያደርግ ሕግ) እንጂ በሥጋ ትውልድ ብጣሽ ኤርትራዊነት
የለውም ብለው እራሳቸው የሙሶሎኒ ልጆች ይናገራሉ።
የኢሳያስ ትውልድ ወሎ ውስጥ የሚመዘዝ ትውልድ አለው የሚሉ ቢኖሩም፦ከቤተሰብ ጋር የተደረገ የውይይት ማስረጃዎች የሚያሳዩት ሰነዶች ግን የሚከተለው ነው።
የኢሳያስ እናት እናት “አያት” (ወ/ሮ መድህን ) ዓድዋ "ይሓ" ናቸው። የኢሳያስ አባት አቶ አፈወርቂ አብርሃ እናታቸው አውራጃ “ዓጋመ” በጋንታ አፈሹም ወረዳ “ቅልአት” ሲሆን በአባታቸው በኩል ደግሞ ለዩ ስም ባልተገለጸ ተምቤን ውስጥ ነው።
የሳሕል በረሃ ባርያዎች ነፃ ወጣን ሲሉ ጨፍረው ፥ ጨፍረው ስካራቸው ሲበርድ ወደ እውነታው ዓለም ሲመለሱ የኢሳያስ ባርያዎችና ሥራ ፈቶች ሆነው በመላ የዓለም ምድር ተበትነው ራሳቸውን በስደት አለም ውስጥ አገኙት።
ሲሰለቻቸው ድምበር ሰብረው በመሮጥ አክብራ ሰታንደላቅቃቸውና ስታስተምራቸው ወደ ነበረቺው “ሲሰድቧት”
ወደ ነበረቺዋ ወደ የእነ ጀነራል ተሾመ ተሰማ እናትአገር ኢትዮጵያ ጥገኝነት እየለመኑ ተንደላቅቀው ይኖራሉ።
እንዲያም እየተደረገላቸው የሐፍረት ትርጉም የማያውቁ «ምስጋና ቢሶቹ» የሙሶሎኒ ልጆች አሁንም ኢትዮጵያን
ሲሳደቡ እንሰማቸዋለን።
ኢትዮጵያን መስደብ ብቻ ሳይሆን በየአመቱ ባርነታቸውን እንዲያከብሩ በየቀበሌው እየታዘዙ እንዲጨፍሩ
ሲደረግ ሰንደቅ ዓላማችንም ጭምር በሰልፈኞች እንዲረገጥ መደረጉን ነውር
የማያወቁት ታሪክ የሚደፍሩ የሙሶሎኒ ልጆች ዱርየ ባሕሪያቸውን ላስታውሳችሁ እና ወደ ዋናው ሂሳብ ማወራረድ ጥይቄ ለምን እንደምንጠይቅ
እገባለሁ።
ትውስታችንን አሁናዊ እያድረግን ካልጠበቅነው ትውልዱ ትውስታውን እየረሳ ለጥቃት ተጋልጦ ለመጥፎ
ሞት ሞቱን ይጋብዛል።
ወቅቱ በሙሶሎኒ ልጆች ዘመን አቆጣጠር በ2017 ነው። የሰልፉ ትዕይነተ ስም “የኤርትራ
ካርኒቫል” ብለው ሰይመውታል። “ካሬቢያን ካርኒቫል” እንደማለት!! ደግነቱ የወንድን ላሃጭ የሚያዝረከርኩ እንደ
ካረቢያኖቹ “ሰውነተ ምልምል” አንስት ኮረዳዎች እርቃናቸው
ወጥተው የሚወዛወዙ ሰልፈኞች አልነበሩበትም።
አሳዛኝ የሚያደርገው
የትዕይንቱ ጉልህ ትዕይንት ጎልማሳ ወጣቶች ከኢሳያስ ነብሰገዳዮችና ገራፊዎች እየሸሹ ወደ ስደትና ሞት በመሄዳቸው፤ 85% የሰልፉ ተካፋዮች አቅመ-ሄዋን ለመድረስ
ብቅ ያሉ እምቡጥ ወጣት ሴቶች፤ መካከለኛ እና አዛውንት ሴቶች ነበሩ።
የሰልፈኛው
ትዕይንት የጀመረው እንደተለመደው ብዙዎቹ የአምባገነኖች ሰርዓት እንደሚያደርጉት፤ ይህ ትዕይንትም ለአምባገነኑ ኢሳያስ በሚሰግዱ
ጋዜጠኞች ፕሮፐጋንዳ መግቢያ ነበር የተከፈተው። እንዲህ በሚል፦
“የቅኝ ገዢዎችን በማስወገድ በዚህ ታሪካዊ በዓላችን ኤርትራ በሕይወትዋ አይታው የማታውቀው የሰላም፤ የደስታና የብልጽግና አየር እያስተነፈሰች ባለችበት ወቅት መከበሩ ልዩ በዓል ያደርገዋል!” በሚል ገና በወጣትነቱ ዕድሜ ሽበት በወረረው ወጣት ጋዜጠኛ ፕሮፓጋንዳ አስተናጋጅነት ነበር የጀመረው።
ቀጥሎ፤ሞጀሌ
ያሸፈፈው እግር የሚመስል የ “ቻርሊ ቻፕሊን” ሸፋፋዊ የእግር አረማመድ በሚራመድ የሙዚቃ ባንድ መሪና ድንክየዎች የሚመስሉ ካለልካቸው
የተሰፋ ቀይና ጥቁር ወታደራዊ ደምብ ልብስ የለበሱ የሙዚቃ ባንድ ሰልፈኞች፤ ‘ኮምቢሽታቶ’ ብሎ ጣሊያን በሰየመው ጎዳና እየተመሙ ትዕይንቱን ለማድመቅ ወታደራዊ ማርሽ ያስሰማሉ።
ትዕይንቱ የተከናወነው
በማታ ሲሆን፤ ጎዳናዉ በኮርያዎች ተሳታፊነት የተቀረጹ ‘ቦግ-ጭልም’ በሚሉ መካከለኛ መብራቶችና ቅርጾች አሸብርቀውታል። አሳዛኙ
ግን በዓሉ እንዳለቀ ለኗሪዎች ተለቅቆ የነበረው አስጎምጂው የኤሌክትሪክ የቤት መብራት ፤ ለእራት የጣዱትን ድስት ሳይበስል ‘እንዲጠፋ’
ተደርጎ፤ እንደተለመደው ወደ ‘ፈረቃው’ የጭለማ ህይወት እንዲደናበሩ ተደርጓል።
ይቀጥልና፤
አሁንም ከሙዚቃው ባንዱ የከፋ እየተወላገዱ ለመውደቅ የሚዳዳቸው ከቅርጽ ውጭ የሆኑ ሽማግሌ ባለስልጣኖች ‘የክብር ሪባን በመመቀስ
የካርኒቫሉን በዓል መርቀው ሲከፍቱ ያሳያል።
በጎዳናው ግራና
ቀኝ በዓሉን ለማክበር ተገደውም ፈርተውም ወድደውም ሆነ ለጉብኝት ከውጭ አገር የሄዱ ተመልካቾች፤ ይታያሉ። ቅጠላ ቅጠል እንዲሁም
በፕላስቲክ የተሰራ ‘የሟሽላና ስንዴ’ እሸት’ ቅርጽ እያውለበለቡ፤በሴቶች ብዛት የታጀበው ሰልፈኛ፤ በአጉል ጉራና ውሸት በተሞላ
በተለቀቀላቸው አስጨፋሪ ሙዚቃ እየጨፈሩ፤እየዘለሉ፤ ያልፋሉ።
እንዲህ፤ እንዲህ…
እያለ አንባቢዎቼ በዓይናችሁ ለማየት የማትሹትን የሚያስቆጣ እንደ ካሁን በፊቱ በንግሥተ ሳባ መሰብሰቢያ
‘ስታድዮም’ በተከበረው በዓላቸው በ2004 (ካልተሳሳትኩ) የኢትዮጵያን ሰንደቃላማ ኢሳያስ ቆሞ እያየ አንዲቦጫጨቅ እና አንዲረገጥ
እንደተደረገው ሁሉ፤ ዛሬም ‘የሙሶሎኒ ልጆች’ ያንኑ ያደጉበትን ጋጠወጥ ባሕሪያቸውን በመድገም የኢትዮጵያን ሕዝብ ምልክት የሆነው
አርማችንን ቦጫጭቆ በመጣል፤ በሰልፈኞች ጫማ እተረገጠና በታዳጊ ወጣቶች መጫማያ እየተቀላ ሲጨፍሩና ሲተፉበት ወደ እሚያሳየው የዱርየዎች
ግብረ ትዕይንት ትደርሳላችሁ።ይህንን ለማየት 2017 Eritrean Independence Carnival Show ምርኢት ካርኒቫል
(May 22, 2017) በዩቱብ የተለጠፈውን ከ49 እስከ 55 ‘እስትሪም’ ርዝመት ስትደርሱ ታዩታላችሁ
(የሙሶሎኒ ልጆች ወደ ኢሳያስ
ባርነት የገቡበት 26ኛውን የባርነት አመታቸውን ስያከብሩ ማለት ነው)።
ኢሳያስ ለወላጆቹ አገር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው ጥልቅ ጥላቻ ያን ያህል እንደሆነ የገለጸበትን ማስረጃ በቀላሉ ማየት ያስችላችኋል። «ኢሳያስ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነው» ከሚሉ በረካታ ሃገራዊ ባንዳዎች ጋር እልክ ገጥመን በዙ ታግለናል። ታሪክ በባንዳነታቸው የዘገባቸው ብዙዎች ናቸው። ጥቂቶቹን በምሳሌ ላስታወሳችሁ። እስራኤላዊ ነኝ ባዩ አምባሳደር ካሳ ከበደ ፥ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ፥ ብርሃኑ ነጋ ፥ አንዳርጋቸው ጽጌ ፥ ንአምን ዘለቀ ፥ ጋዜጠኛ ሲሳይ አገና እና “አስመራ ደርሶ መልስ” ብየ የምጠራቸው (የኢሳት ጋዜጠኞች) ወዘተ...... የባንዳው ብዛት ብዙ ነው።
ከላይ በጸሑፌ ርዐስ አንደገለጽኩት ይህ ሁሉ አስገራሚ ወንጀልና በ125 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ ጥላቻ እንዲሰፍን ፥ ሕዝብ ለሕዝብ እንዲጣላ ትዕዛዝ የሰጠው ኢሳያስ እና አሽከሮቹ ሰንደቅ ዓላማችን በሰለፈኞች ሲረገጥ ‘ይህ አስነዋሪ ድርጊት’ ጥላቻን ከማስፋፋት በቀር፤ ምን ጥቅም ያመጣል ተብሎ ተደረገ? ብለው ባንዳዎቹ እንደማይጠይቁ እናውቃለን።
ሰንደቃላማ
ተቀዳድዳ ምንም በማያውቁ ታዳጊ ህጻናት መጫሚያ ሥር መሬት ላይ ተወርውራ አፈር ጋር እንደትረገጥ ዱርየነቱን ዓለም እንዲያየው ሲያደርግ በ204
እና በ2017 (በሙሶሎኒ ልጆች ዘመን አቆጣጠር) ለሁለተኛ ጊዜው ነው።
ባንዳዎቹ ስለ ወደብ ጉዳይ ሲነሳ «በተባበሩት መንግሥታት ያለቀለት ፥ የጸደቀ ጉዳይ ነው! አይሆንም! ያለቀለት ነገር ነው! » እያሉ እነ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስና መሰሎቹ ወጣቱን ለማጃጃል እየሞከሩት ያለውን ባንዳዊ የሕሊና አጠባ እንደሚሉት ‘ያለቀለት’ አይደለም።የኤርትራ (የወደብ ጉዳይ) ጉዳይ አላለቀም፤ ይደረጋል ያልነውን ይደረጋል! የጊዜ ጉዳይ እንጂ ያልተወራረደ ሂሳብ አለን ፣ ይወራረዳል! ጥያቄው ሂሳቡን የሚያወራርድልን ኢትዮጵያዊ መሪ ማን ይሆን? የሚለው ነው።
በዚህ አጋጣሚ በምሳሌ እንድታነቡት የምጋብዛችሁ፤ የክራሚያና የሩስያ ጉዳይ
ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ያልተዘጋ አጀንዳ ምንን
ያስተምረናል? (አክሊሉ ወንድአፈረው - የግል አስተያየት መስከረም 2, 2007 (ስፕተምበር 12 2014)፡
(Ethiopian Semay) የሚለውን አንብቡ።
ኢትዮጵያዊያኖች
ሰንደቃላማችን ተረግጦ ባሕራችን ተዘግቶብን መተኛት እንደሌለብን ራሳቸውን ሲሰው ጀግኖቻችን
በአደራ ያስተጋቡትን ቃላቸው ዛሬም ሕያው ነውና ‘አለቅላቂዎች’ ከዚህ በታች ያለውን ቃል እንዲያነቡት እያስታወስኩ በዚህ የጀግኖች ታሪካዊ ግብግብና ልሳን ልሰናበታችሁ።
አይ ምጽዋ ከሚል ነብስ ይማር በጀግናው መቶአለቃ ታደሰ ቴሌ ደራሲነት ለታሪክ የተዘገበ መጽሐፍ
(ገጽ 187 አስከ 198) በዓይናቸው ያዩትና በግብር ጦርነቱን የተካፉሉበትን እምባና ቁጭት በሚጭር አሳዛኝ ፍጻሜና ጀግንነት ላስታውሳችሁና ልሰናበት፡
“የካቲት
9 ቀን 1982 ዓ.ም ምፅዋ ከተማ ለተከማቸው አብዮታዊ ሠራዊትና አመራሩ ክፉ ቀን ነበረች። ሻዕቢያ ደግሞ እንደ ልደት ቀን ይቆጥረዋል። ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ
ምፅዋ ከተማን የረገጠዉ በዚች ዕለት ነዉና።
ሻዕቢያ በ1970
ዓ.ም ከጀብሃ ተዋጊዎች ጋር በመሆን አብዛኛውን የኤርትራ ግዛት ተቆጣጥሮ ነበር። አሥመራ፤ባሬንቱ፤ምፅዋና
ዓዲቀይህ ከተማ የነበሩትን የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት ደምስሶ እነዚህን ከተሞች መቆጣጠር ግን አልቻለም። በመሆኑም የሃያ
የ6ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ጀኔራል ተሾመ ተሰማ ካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡30 ሰዓት ላይ በምፅዋ ከተማ ‘ርዕሲ ምድሪ’ በተባለ አካባቢ በከባድ መሣሪያ በፈራረሱ ቤቶች ጥግ ሆነዉ የተወሰኑ የጦር መኮንኖችን እና ባለሌላ ማዕረግተኞችን ሰብስበዉ ንግግር አደረጉ። እንዲህም አሉ፤-
“ሻዕቢያ ያለ የሌለ ሃይሉን ተጠቅሞ በእጅ ቦምብና በክላሽን በአሁኑ ሰዓት የከተማ ዉስጥ ዉጊያ በማድረግ ላይ ነዉ። ሻዕቢያ ከባድ መሣሪያ ድብደባ አቁሞ በእግረኛ ብቻ ለመዋጋት አዲስ ተዋጊ ሃይሉን በመኪና እያመላለሰ ዕዳጋ ከተማ ላይ እያከማቸ ነዉ። በአዲስ ጉልበት ተዋግቶ ምጸፅዋን ለመያዝ ቆርጦ ስለመነሣቱ ጥርጥር የለዉም።… “እኔ የሚፈለግብኝን አደራ ተወጥቻለሁ። ከጥር 30ቀን 1982 እስከ ዛር የካቲት 9 ቀን 1982 ሞት ሽረት ትግል አድረጌአለሁ።የሻዕቢያን የጥፋት ዓለማ ለመግታት ያላደረግኩት ጥረት የለም። ከዚህ በኋላ ግን የራሴን ሕይወት በክብር ከማጥፋትና ለኢትዮጵያ ጀግኖችና ታሪክ ፀሐፊዎች ታላቅ ተምሳሌት ከመሆን ሌላ አማራጭ የለኝም። ጀግንነት ማለት በሁሉም መልክ ለጠላት አመች ሆኖ አለመገኘት ማለት ነዉ።…
“በዚች የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በርና ዓለም አቀፍ ወደብ በሆነችዉ በምፅዋ ከተማና በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ቆሜ ሽጉጤን ለመጠጣት ዝግጁ ሆኜአለሁ። በ እዉነት እኔ ዛሬ በሞት ብሸነፍም በታሪክና በመጭዉ የኢትዮጵያ ትዉልድ ፊት አልሸነፍም። የአፄ ቴዎድሮስን ዕድል በማግኘቴም በጣም እኮራለሁ። እኔ አሁን የተዘጋጀሁለት ሞት ዘለዓለማዊ ክብርና ሕይወት ይሰጠናል። በሻዕቢያ እንደ እነ ጀኔራል ጥላሁን እና ጀኔራል ዓሊ ሓጂ ተማርኬ የሻዕቢያን መሪዎች ዓይን ማየት ግን የሞት ሞት ነዉ። አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች እጅ ወድቀዉ ከመዋረድ ሞትን መርጠዉ የራሳቸዉን ሕይወት መቀቅደላ ላይ አጠፉ።
እኔ ደግሞ በተራየ ከኢትየጵያ ሕዝብ መንግሥት የተሰጠኝን የጄኔራልነት ማዕረግ ሳላስደፍር ለመንግሥትና ለሕዝብ በገባሁት ቃል ኪዳን መሰረት አስቀድሜ የፈቀደዉን ያህል ተዋግቼና አዋግቼ ሻዕቢያን አራግፌአለሁ። እንደ ጦር መሪም እንደ ተራ ተዋጊም ሁኜ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዤ ተፋልሜአለሁ። አሁን ግን ለመጨረሻዋ መስዋዕትነት ህይወቴን ለማጥፋት የቀሩኝ ጥቂት ደቂቃዎች ናቸዉ።… “ጎበዝ ስሙኝ! ይህ አደራ መልዕክቴ ነገ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይደርስ ይሆናል። ምናልባት አምላክ ካለ ከእናንተ አንዱ መልዕክቴን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አደርስ ይሆናል። ዛሬ ሻዕቢያ ምፅዋን ተቆጣጥሬአለሁ በማለት የዓለምን መገናኛ ብዙሃን እንደሚያጨናንቅ ጥርጥር የለዉም። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሀገርና ሕዝቧ ትልቅ አደጋ ነዉ። በቀይ ባሕር በራችን በኩል ብዙዉን ጊዜ ወረራ ፈጽመዉብን በተደጋጋሚ የሳፈርናቸዉና ፊት ለፊት ያልቻሉን ምዕራባዉያን ሀገሮችና ዓረቦች ዛሬ የሻዕቢያን ጊዜያዊ ድል ሰምተዉ ይፈነጥዛሉ። ምናልባትም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ድንበር የሆነዉንና ለዘመናት በአባቶቻችን የደም ዋጋ ፀንቶ የቆየን የባሕር በራችንን በመዝጋት እንዲሁም ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ባሕር አይደለም በማለት በምድር ተወስነን እንድንቀር ይደረግ ይሆናል። ይህ ደግሞ የሞት ሞት ነዉ። “ይሁን! ምንም ማድረግ አልችልንም። ሁሉም ነገር ከቁጥጥሬ ዉጭ ሆኗል። ከሙታን ዓለም መጥቼ ማረጋገጥ ባልችልም የፈለገ ጊዜ ይጠይቅ እንጂ ጀግናዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር አልባ ሆኖ በኢምፔርያሊስቶችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸዉ ተሸንፎና እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም። ይህ ከሆነማ የአፄ ዮሐንስ የቀይ በሕር ተጋድሎ እና የጀግናዉ ራስ አሉላ አባነጋ አጥንት እንዲሁም የእኔን ጨምሮ የአበዮታዊ ሠራዊት አባላት አጥንትና ደም የኢትዮ ያን ትዉልድ ሁሉ እሰከዘላለሙ የፋረዳል። ኢትዮጵያ ሀገሬ የጀግኖች መፍለቅያና ገናና ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በመሆኑም ጀግናዉ ሕዝቧ ሕዝባዊ የባሕር በሩ በሻዕቢያ ተይዞና የጠላቶቹ መፈንጫ ሆኖ አይኖርም። የፈለገ ጊዜ ይቆይ እንጂ ሻዕቢያ ምፅዋን እንደያዛት ለዘላለሙ አይኖርም” ። ጊዜዉ ጠብቆ የኢትዮጵያ ጀግና ጠላትን ደምስሶ ምፅዋን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስረክብ እምነቴ የፀና ነው!”
አሉና ትንፋሽ ዋጡ: የትንሽ ፋታ ወሰዱ። የጀኔራል ተሾመ ዓይን የቆሰለ የነብር ዓይን መስሏል፡ ከንፈራቸዉ በዉሃ ጥም ደርቆ ቅርፊት ይዟል። ፊታቸዉ በደረቅ ላብ ዥንጉርጉር ሆኗል። ሆዳቸው ከወገባቸው ተጣብቋል። በተሰበሰበው አባል ውስጥ በሰፈነው ጸጥታና ዝምታ መሃል “እናንተ አብየታዊ መኮንኖች ባለሌላ ማዕረጎች! ስሙኝ፤ አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ።” አሉ ጀኔራል ተሾመ ቆጣ ብለው። “አንድ ሰዉ ቤት ሲሰራ የሚሠራዉ ቤት በርና መስኮቶች አሉት። አንድ ሰዉ ደግሞ ሞተ እንበል። መቃብር በርና መስኮት የለዉም። በርና መስኮት የሕይወት ምልክቶችናቸዉ። በመሆኑም ያለሀገር ነፃነትና ያለባሕር በር ብልጽግና ስለሌለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር ተነጥቆ የሚኖር ሕዝብ አይደለም። ከሻዕቢያ ጀርባ ሆነው ቀይ በሕር የኢትዮጵያ አይደለም የሚሉ ሀገሮችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ሁሉ በቀጥታም ሆኑ በተዘዋዋሪ ፍላጎታቸዉ የኢትዮጵያ ሞት ነው።
“ይህ ምሳሌ ከገባችሁ የባሕር በር የሌላት ሀገር ሞቶ ከተቀበረ ግለሰብ የምትለየዉ በትንሹ ነዉ። ምክንያቱም የባሕር ሀብት ከማጣቷ በላይ ምርቷን ወደ ውጭ ለመላክ የግዴታ ወደብ ስለምትከራይ ለወደብ ክፍያ የምትከፍለው የገንዘብ ወጪ ዜጎቿን ያደኸያል። በአኳያው ጠላቶቿን ባለወደቦቹን ያበለጽጋል።
ይህ ዕድል ለኢትዮጵያ እንዳይደርሳት ቀይ ባሕር የኢትየጵያ ትውልድ ይፋረድ።ቀይ ባሕር ለእኔ ዘላለማዊ ቤቴ እንዲሆን ወስኛለሁ። ደስተኛ እና ዕድለኛ ጀኔራል ነኝ። እኔ ብሞት ታሪኬ አይሞትም። የእኔ ታሪክ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕሊና ዉስጥ እንደሚኖር አምናለሁ። ቻዉ! ቻዉ! ቻዉ!” አሉና ጀኔራል ተሾመ ፤መኮንኖቹን ከሰበሰቡበት ቦታ ተፈናጥረው ወደ ቀይ ባሕር ጠረፍ አመሩ።
የባሕሩ ጠረፍ ከስብሰባው ቦታ በግምት ከስልሳ ሜትር አይበልጥም። በፍጥነት ወደዚህ በሕር ጠረፍ ገሰገሱ። ክላሺንኮቭ ጠመንጃቸውን አቀባብለውና አውቶማቲክ ላይ አድርገዉ በቀኝ እጃቸዉ ጨብጠዋል። ከምፅዋ ወደብ በስተቀኝ ከሚገኘው ወታደራዊ ወደብና መደብር ላይ ሲደርሱም ለቀይ ባሕር ውሃ መገደቢያ በተሰራ ግንብ ጠርዝ ላይ ጀርባቸውን ወደ ቀይ ባሕር ፊታቸውን ወደ ምፅዋ ከተማ አድርገው ቆሙ። ቀጥሎ በእጃቸው የነበረውን ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ወደ ቀይ ባሕር ወረወሩት። ከዚያም በወገባቸው ታጥቀዉት የነበረውን ኮልት ሽጉጥ አወጡና የሽጉጡን አፈሙዝ በአፋቸዉ ጎርሰው የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጥወቱ 2፡10 ሰዓት ሲሆን ቃታዉን ሳቡት። የሽጉጥ ቶክስ ድምፅ እንደተሰማ ወደ ጀርባቸው በቀይባሕር ውሃ ላይ ወድቀው ሰጠሙ። ከጭንቅላታቸው የሚፈስ ደም በቀይ ባሕር ውሃ ላይ ቀልቶ ይታይ ነበር።
ወዲያውም ይህን የጀኔራል ተሾመ ሞት በምስክርነት ቆመው ከአዩት መካከል ከ150 የማያንሱ የጦር መኮንኖች ባለሌላ ማዕርጎች በሽጉጥ፤ በእጅ ቦምብና በክላሽ ጠመንጃ ሕይወታቸውን አጠፉ። ከእነዚህም መካከል ሻለቃ ሮሪሣ ዳዲ በእጅ ቦምብ፤ሻምበል ሸዋንታዮ ዓለሙ በማካሮቭ ሽጉጥ፤ሻምበል አዲሱ በማካሮቭ ሽጉጥ፤ሻምበል ባሻ አማረ ናጂ በክላሽ፤ሻምበል ወንድወሰን በሽጉጥ የሃምሳ አለቃ ፈቃዱ ቦጋለ በክላሽ፤ ወታደር ሽንገረፋ በክላሽ ሕይወታቸውን ያጠፉ በስም የሚታወሱ ናቸው። ሌሎችም በብዛት ራሳቸውን ገድለዋል። በአጭር ደቂቃ ዉስጥ አካባቢዉ ሬሳ በሬሳ ሆነ።”…
ካሉ በኋላ ኮለኔል በላይ አስጨናቂ ስለተባሉ ሌላ ጀግና ወታደርና የቀኑን እጅ ለእጅ አስጨናቂና አኩሪ የገድሎ መሞት ውግያን በሚመለከት ደራሲው በሰፊው ይተነተኑታል።
“ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ የኢትዮጵያን ሰንደቃላማ ለብሰው ከቀይ ባሕር ሆቴል በረንዳ ላይ በአንዲት ጥልፍልፍ የቃጫ ወንብረ ላይ ተቀምጠዉ አጠገባቸው ለነበሩት ጥቂት አባላት መልዕክት ያስተላልፋሉ። “ጀግና ቢሞት በእልፍ እአላፍ ጀግና ይተካል።የእኔ ታሪክ ለትዉልድ ይቀራል። ታሪክ ይናገራል እንጂ እኔ አልናገርም።” የምትል መልዕክት እያስተላለፉና …..ራሰቸውን መስዋዕት አደረጉ።
“ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ ክላሽንኮቭ ጠመንጃቸዉ እንደያዙ ወንበር ተደግፈዉ ተዝለፍልፈዋል። የለበሱት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ባንዴራ በላያቸዉ ላይ ደምቆ ይታያል።ይህነን ትዕይንት ሻዕቢያ በፎቶግራፍ አንስቶታል።በቪዲዮ ካሜራም ቀርጾታል፡ የወታደዊ ሸሚዝና ሱሪያቸውን ኪስ ሻዕቢያ ሲበረብርም ከንጽህና ወረቀት በስተቀር ምንም አላገኘም።
አንድ የሻዕብያ ተዋጊ ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ ለብሰዉ የተሰውትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ባንዴራ ካላያቸዉ ላይ ገፈፈና ክብሪት ጭሮ አቃጠለዉ። የኮሎኔሉ አስከሬን ከወንበሩ ላይ ገፍትሮ በመጣልም በደም የተጨማለቀውን ወንበር በአንድ እጁ ወደ ላይ አነሳው። ይህ ድርጊት ጋብ ያለውን ተኩስ በመጠኑ ቀሰቀሰው። ከአንድ አቅጣጫ የተተኮሰች ጥይት ያን የሻዕቢያ አባል ከወንበሩ ጣለችው።ከዚያ መሬት ቀውጥ ሆና የጨበጣ ውግያው እንደገና ተፋፋመ፤….”
በማለት የጀግንነት ገድላችንን ሲያስታውሱን ለጠላት ያደሩ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ ከፍተኛ የሰራዊቱ ቁንጮ አዛዦች የነበሩ ሰላዮችም አብረው ለምጽዋ መውደቅ የተጫወቱት ሚና በመጽሐፉ በሰፊው ይገልጻሉ።
ሰለሆነም ያልተወራረደ የወላጆቻችን የደም ሂሳብ አለ፤ እሱን እናወራርዳለን የምለው ለዚህ ነው።ያልተወራረደ የወላጆቻችን ሂሳብ
የሚያወራርድልን ኢትዮጵያዊ መሪ ማን ይሆን? የሚለው ትልቁ ጥያቄ ግን እስካሁን ድረስ መልስ አላገኘም።
ለጊዜው ኤርትራ
«ግድያ፥ዘር-ማጥፋት፥ሕዝብን ወደ ባርነት መለወጥ፥ጥቁር ገባያ፤ሌብነት፥ ስም ማጥፋት፥ ውሸት ፥ ጉራ ፥ ወንጀል ፥ ጦርነት ፥ ሽብር፥ ስደትና ዕብደት፥ ሁሉንም ሞክራዋለች። ከዚህ ወዲያ የሚቀራት መደምደሚያዋ ወደ አመድነት መጓዝ ነው።ከዚያ ጣረ ሞት መዳን ከፈለገች “የቀራት አማራጭ” ኢትዮጵያዊነትዋን “በቁርባን” ተቀብላ ከዘላለማዊው ቅዠት (ደሉዥን) እና ሞት መዳን ነው።
ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay
