Wednesday, February 18, 2026

ከፊት ሆኖ ይምራን እኛ እንከተለው ሻለቃ ዳዊት እና ብርሃነመስቀል ነጋ የሰለሞን ተካልኝ ቅጂዎች ጌታቸው ረዳ 2/18/26 Ethiopian Semay

 

ከፊት ሆኖ ይምራን እኛ እንከተለው ሻለቃ ዳዊት እና ብርሃነመስቀል ነጋ የሰለሞን ተካልኝ ቅጂዎች

ጌታቸው ረዳ

2/18/26

Ethiopian Semay

በፎቶግራፍ ላይ የምታይዋቸው ሁለት ሰዎች ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ እና አምባሳደር ብርሃነመስቀል ነጋ ናቸው። ብርሃነመስቀልን አላውቃቸውም (ማወቁን እንኳን ቀረብኝ!!!) ፤ ሻለቃ ዳዊት ግን በርካታ ሃገራዊ ስሕተቶች አንዳንዱም በባንዳነት ለሻዕቢያ ፐሮፓጋንዳ ድጋፍ በሆነ መልኩ የተከራከሩ እና የጻፉ፤ ሲነሽጣቸውም በታሪክ የሚመዘገቡ መልካም ሰነዶችንና መጻሕፍቶችን ጽፈው ያበረከቱ  ፤በዚህም ክንያት በድጋፍም በተቃውሞም ብዙ መጣጥፎች የጻፍኩላቸው ታዋቂ ምሁር ናቸው።

ሰላም እንደምን ሰነበታቸሁ!

በአጣዳፊ ሥራ ተወጥሬ ስለነበርና በወቀቱ አልመጣሁም። ዛሬ ስለ እነዚህ ሰዎች እና ሰለ የፋኖ ዘረኛነትን እንመለከታለን።

በቅርቡ እነዚህ ሁለት ሰዎች እና ጀርመን ሃገር የሚኖሩት ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ ጋር ሆነው፤ የጫካ ዱርየነት ባሕሪ በመከተል ወደ አስራ ምናምን ተበታተኖ እርስበርስ ሲታኮስ የነበረ የአማራ ፋኖ ታጣቂዎችን አንድ አድረገን መጣንላችሁ ብለው በሚዲያ ሲጎረኑ ሰምተናቸዋል።   

አሰገራሚ የሆነኝ ነገር «ንጹሃንን በመረሸንና በመግረፍ የታወቁ እነዚህ ግባ የማይባል የፖለቲካ እና የሽምቅ ተዋጊነት ስልቶችና የፖሊሲ አወቃቀሮች የሚከተሉ ፥ በአብዛኛው በጎጃም ፋኖ መሪዎች የሚቦወዝ «የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ/አፋብን/AFNM) የተባለው ታጣቂ ድርጅት ወርቅ ቀባበተው ፥ ሰማይ ሰቅለው ተፋላሚዎችን ለማስታረቅ በሰለጠኑበት ሙያቸው ተመድበው በየዓለማቱ በተላኩበት የአስታራቂነት  ሙያቸው እንዲህ ያሉ ተፋላሚዎች ፈጽሞ ያላዩ እና በኢትዮጵያ ታሪክም እንዲህ ያሉ ምጡቃን ነፃ አውጪ መሪዎች ያላጋጠማቸው መሆናቸውን ከሰማየ ሰማያት የተላኩ  ሙሴዎች አስመስለው ሲያደንቋቸው ሰምቸ፤ “እንዲህ ያሉ የተማሩ ሰዎች ወደ ትንሽነት የጎተታቸው ግፊት ምን ይሆን?” የሚል ጥያቄ ጭሮብኛል።

 በነዚህ ሰዎች የተደነቁት በተለይ «ያ ደም የጠማው አስርሰ ማረ የተባለ በብዙ ወንጀሎችና ንግግሮቹ በጥቁር መዝገብ የመዘገብኩት የሕሊና ቀውስ ያለው የሚያስመስለው “አስረስ ማረ” የተባለው የዚህ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪ”  በሻለቃ ዳዊትና በአምባሳደር ብርሃነመስቀል ተደጋግሞ ሲሞገስ የሚነግረን ነገር ሁለቱም የዚህ የጎጃም ፋኖ አባሎች መሆናቸውን ነጋሪ ነው። ለዚህ ማሳያም “ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ እራሳቸው «እነዚህ መሪዎቻችን» እያሉ  ሲናገሩ ሰመተናቸዋል። ስለዚህም  ሁለቱም አባሎች እንጂ ገለለተኛ ታዛቢዎች አለመሆናቸውን ነው እየነገሩን ያሉት

አስገራሚው ደግሞ ‘የፋኖ የመድረኩ ዋና አወያይ የጎጃሙ አስረስ ማረ መሆኑን ስንሰማ ስቀን ማለፉ የሚመረጥ ነው።

 ታስታውሱ እንደሆነ  የመጀመሪያው የፋኖ አንድነት ሙከራ ስንት ተንኮል ጎንጉነው ቢመጡም በመጨረሻ ታላቁ እስክንድር ነጋ በድምጽ ሲበልጣቸው ፤ ዘመነ ካልመራ አንቀበልም ብለው ስብሰባው ሲበትኑት ታስታውሳላችሁ? ከዚያ የተከተለው ግድያና ሰዶ -ማሳደድ ያሳዩን የጫካው እውነታዊ ቲያትራቸው የምታውቁት የትናንት ማታ ትዝታ ነው። አሁንስ የአንድነት ተብየው ጉባኤ ማን ነበር መድረኩን ሲመራው የነበረው? አሁንም ያው ጎጃም ነበር (ደም የጠማው የዳዊትና የብረሃነ መስቀል አርበኛ ‘’አስረስ ማረ’’)!!!

ለምን የመድረክ መሪነቱን ለመያዝ ፈለጉ? ያቺን የሚጋደሉላት የመሪነት ቦታ ለመያዝ ማለት ነዋ!! አሁን ፣በፖለቲካ ፥ በሕዝብ አደረጃጀት ፥ በጽናትና ሁሉንም  በመታገስ ፥ በፖሊሲ አቀራረጽና ለሕዝብ መስዋዕት በመሆን ዓለም የመዘገበለትን ባለ ታላቅ ማሕደሩ ‘’ታላቁ እስክንድር ነጋ’’ ፈቅዶ ቦታውን ሲለቅላቸው እንደ ጅብ ተንግገተው መሪነቱን ያዙከዚህስ በኋላስ?

ከዚህስ በኋላ የሚከሰተው ከደቡብ አፍሪካው ስምምነት ማግስት (ልክ በማገስቱ!!!) በወያነ ካምፕና አመራር ውስጥ ምን እንደሚከሰት እንደተነበይኩትና እውነታ እንደሆነው ሁሉ ፤ በነዚህ ፋኖዎችም የመገዳደልና የመከፋፈል የመክዳትም (የመሰለምም) ክስተት ጭምር የሚሆነውን በማስረጃ ለወደፊቱ አስነብባችኋለሁ።

 ይህ ታጣቂ ቡደን ከመሪዎቹ ጀመሮ እሰከ ተራ ተዋጊዎቹ በርካታ አከራሪ ብሔረተኞች «ሃይማኖት እና ነገድ ነክ አክራሪዎች» የተሰገሰጉበት ነው።

ሻለቃ ዳዊትም ይሁን ብርሃነመስቀል ነጋ መሪዎቻቸን ሲሉ የሚጠሯቸው ፋኖዎች ላንድ ዓላማ የወጡ ናቸው> ሲሉ ሰምተናቸዋል። እንዲህ ከሆነ አመራሮች እርስ በርስ ለምን ይገዳደሉ ነበር? ብለን ብንጠቃቸው መልስ አይኖራቸውም። ለዚህ መልስ የሰጠ አንድ ምስኪን ሰው ግና አለ። እሱም ፤ ዳዊት እና በረሃነመስቀልን በማወያየት ጎጃሞቹ ከመረጡዋቸው የጎጃሞቹ (የፋኖዎቹ) ሚዲያ ቡድን  አማረ አሰፋ” የተባለ የጣና ቲ ቪ አባል ነው። እንዲህ ይላል፡

« የአማራ ሕዝብ  (ፋኖ) አንድ እንዳይሆን የተሰራበት መንገድ ስላለ ነው» ። የላል። ሰነፍ ሰው ጥፋት አለኝ አይልም፤ጣቱን የሚቀስረው ለስንፍናውና ለመውደቁ ምክንያት ሌላ አካል ነው ብሎ ያመካኛል።የፋኖ ታጣቂ እርስ በርሱ የመገዳደሉ መስጢር  አንድ እንዳንሆን ሰለተሰራብን ነው፡ ይላሉ።

አንድ እንዳይሆኑም ይሁን ወንጀል ለመፈጸም የተሰራባቸው ክታብ እና  የተሰራባቸው ድግምት ለማወቅና ለመፍታት ከጎጃሞቹ ባለይ የተሰወረ ዕውቀት ይኖር ይሆን? ሕጻናትን መረሸን፤ መምሕራንን መረሽን ፥ የተያዘ ምርኮኛን ቅንድብ መላጨትድሆች እናቶች ሲጋራ እና   አረቄ እየሸጡ ልጆቻቸው እንዳያስተምሩ ማገድ ፥ የተማረከውን ማዋከብና ማሸማቀቅ... ለምን እንዲያ ያለ ነውር እድትሰሩ የተሰራባችሁ መንገድ ካወቃችሁት፤ በማን እንደተሰራባችሁ ለምን አትነገሩንም?

ይህ ሁሉ ግደል ተገዳደል ፤ይህ ሁሉ ዘረኛ ስድብ መሰዳደብ እስክንድር አማራ አይደለም ኢትዮጵያዊ ነው” ፥ «ግምባሩንና ቅንድቡን በለው»፤ የሚለው «የአስረስ ማረ» እና የመሰሎቹ ትዕዛዝ  በመጨረሻው ለፍርድ ቀን ስትጠየቁ «ወንጀል እንድትሰሩ የተሰራባችህ ድግምት» ማስረዳት ትችላላችሁ?

መሪዎቻችን አንድ አድርገናቸዋል ብለው እነ  ሻለቃ ዳዊት ለሕዝብ ሲያውጁ ፤ በሚገርም ነገር እርስ-በርሳቸው ይገዳደሉ እንደነበር ቢያውቁም ያንን የመሪዎቻቸውን ወጀንጀል ለመደበቅ ሲሉ በማደባበስ እንዲህ ፤ ለምሳሌ ሻለቃ ዳዊት እንዲህ ይላሉ፦

«አለ መነጋገርና አለመደማመጥ ነበር፡ መደማመጣና መነጋገር ሲያደርጉ “መፈትሔ አገኙለት” ፡ በማለት «መገዳደሉንና ዘረኛነትን እንደ ቀላል አይተውታል»፡

 ሻለቃ ዳዊት ከታወቀ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በከፈተኛ የሕግ ዲግሪ የተመረቁ የሕግ ምሁር ናቸው። “ሲገዳደሉት የነበረው የመገዳደል ወንጀልን” አለመደማመጥና አለመነጋገር ነበር” ወደ ማለት የዳዳቸው እኝህ ምሁር ተራ የዕቁብ (የዕድር) ሰዎች ንትርክ አደርገው ሲያቀርቡት፤ የኛን የመታዘብ ብቃታችንን  በንቀት መዝነውታል

የሽምግልና እና የሰብአዊ መብት ነክ ልምድ ያለን አመባሳደሮች ነን እያሉ ሲጎረኑበት የነበረው ልምዳቸው ፋኖ ላይ ሲደርሱ ተፈትነው ወደቀዋል። አስገራሚው ደግሞ ገለልተኞች ነን ይሉና ሰከንድ ሳይርቁ “እነዚህ መሪዎቻቸን” እያሉ በጫካ አጉራ ዘለልነታቸው እና በአክራሪነታቸው የምናውቃቸው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ  ምጥቀት የጎደላቸው  የፋኖ መሪዎችን መሪዎቻችን ሲሉ ይደመጣሉ

ያንን ሲያጠናክሩትም «እነዚህ መሪዎቻችን ታላቅዋን ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ የወስዷታል፤ አዲሰ አበባም ያስገቡናል” እያሉ ሳይሸማቀቁ ይነግሩናል።

እገሌ አማራ እገሌ ደግሞ ኢትዮጵያዊ  የሚሉ ኢትዮጵያዊን የሚያጥላሉ የፋኖ ኢንተርሃሙዌ ታጣቂ መሪዎችን ‘መሪዎቻችን’ እያሉ በማሞካሸት የወደቁበት የፍቅር ጥልቀት “በብሔረተኝነት መለከፋቸው ማሳያ ነው”።

ብሔረተኝነት ከፉ ፍቅር ነው። አንዴም ይሁን ተደጋጋሚ ፍቅር ያልያዘው ሰው መቸም የለም (መናልባት ጠቂቶች)፤ ፍቅር ስሜትን ከቁጥጥር ውጭ አድርጎ የሕሊና እና የነርቭ የሕዋሳት መቀያየርን የሚያስከትል ነው። ፍቅር ብዙ ገጽታ አለው። የሰው ፍቅር፤ የንብረት ፍቅር ፥ ለራስ ፍቅር የሃይማኖት እና የፖለቲካ ፍቅር ወዘተ... ፍቅሮች አሉ።

ሰዎች በፖለቲካ ፍቅር በፖለቲካ ታዛዥነት (ለመሪዎች ያላቸው ፍቅር) Politics Obedience” ሲወድቁ  ራሳቸውን እስከመሰዋት እና ማስገመት ይደርሳሉ።

ራሳቸውን ያስገመቱ በቅርቡ “በአናርኮ ፋሺቱ ፋኖ” ፍቅር የወደቁ ሰዎችን አይተናል። ብዙዎቹ ውጭ አገር የሚኖሩ “በጣም ጥቂት የአማራ ” ምሁራን ናቸው። 

ፋኖ የተባለው “አክራሪ በሔረተኛ” የሚመሩት ሰዎች ደም በጠማቸው ብዙዎቹ ኤርትራ ውስጥ የአንዳርጋቸው እና የብርሃኑ ነጋ ጭፍራ የነበሩ ታጣቂዎች ናቸው።

ይህንን ታጣቂ የሚመሩት ዓድዋዎች ወያነን ሲመሩት እንደነበሩት ሁሉ  ፋኖንን የሚመሩትም በዙዎቹ ጎጃሜዎች ናቸው። ይህንን ድርጅት በቀዳሚነት የሚያንቀሳቅሱትና ግምባር የሚታዩት ጎጃሜ ግለሰቦችን እንጥቀስ ቢባል አንደኛው፤ አስረስ ማረ” የተባለው  የሰው ነፃነትን የሚጋፋ ፥ የያስረሸናቸው ደም የሚያክለፈልፈው ፥ ዘረኛ ፥ በጣም ናርሲትና ትዕቢተኛው አስረስ ማረ ሲሆን፤ አብሮት የበላዩ የሆነው «የነጋሽ እና የአንጋሽ ዘር የሆንኩኝ ፥ ከእናቴ ማሕጸን ሆኜ ያገኝሁትን የታላላቅ ሕለመኞች ልጅ የሆንኩኝ ፥ በታሪክና በዲኤንኤ የተላለፈልኝን ሕልሜን  «እስክንድር ነጋ ሕልሜን ነጠቀው» እያለ በሚዲያ በግልጽ ለሥልጣን ሲቃዥ የነበረበትን ሕልሙን ተሳከቶለት የበላይ ሆኖ የወጣው ዘመነ ካሴ የተባለው የሥልጣን ቅዠታም የፋኖ ታጣቂዎችን በመሪነት የሚመራ እና የመሳሰሉ ታዛዦቹ የሚመሩት ድርጅት ነው።

 እነዚህ ደግሞ ለፍትሕ የቆሙ ሳይሆኑ ጸረ ፍትሕ የሆኑ፤  ትችት የማይፈቅዱ የጫካ አጉራ ዘለል የሆኑ፤ ተራ ዝርፍያ ውስጥ የገቡ ድብደባ (ቶርቸር) ፤የባንክ ዝርፍያ የሚያካሂዱ፥ ሕጻናትን ተመራዎችን እና የመምህራንን ግድያ ትዕዛዝ የሰጡ አክራሪ ብሄሔረተኝነት እና ወንጀል መስራትን የሚደፍሩ ናቸው።

በሚገርም ነገር ከላይ ከተጠቀሱት የሻለቃ ዳዊት እና የብርሃነመስቀል ነጋ “መሪዎች” ከሆኑት  “እስክንድር ኢትዮጵያዊ እንጂ አማራ አይደለም” ከሚሉት በተጨማሪ የፋኖ መሪዎች አንዱ ድሮ የወያኔ ባሕላዊ ጄነራል የነበረ «ተፈራ ማሞ» የተባለው በቅርቡ  በዙዎቻችንን ያስደነገጠ ዘረኛ አዋጅ አውጇል።

 ተፈራ አስገራሚ ሰው ነው። በቅጽል ስሟ “መነን ሃይለ” እያለች ራሰዋን የምትጠራ ወሎየዋ ሚስቱ ወደ ኤርትራ እየተመላለሰች ከሻዕቢያ መሪዎች ጋር ፎቶ እየተነሳች   እኛን ትግሬዎችን “ቅማላምአጋሜ” እያለች የሻዕቢያ ተልዕኮ ለማስፈጸም <<የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ከወሎ  ተጠራርገው ወደ አገራቸው ወደ ትግራይ ይባረሩ>> እያለች “ኢንተርሃሙዌዊ የዘር ቅስቀሳ” ማድረግዋን እየገረመን አሁን ደግሞ ተፈራ ማሞ እራሱ የአማራ ስም በያዝን ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊቶች ላይ የሚያስደነግጥ ዘረኛ አዋጅ አውጆብናል።

«የአማራ ሥም የያዙ አማራ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን የአማራ ስም መጠቀም ማቆም አለባቸው» ሲል አውጇል።

የነ ሻለቃ ዳዊት እና የነ በርሃነመስቀል ነጋ መሪዎች አንዱ የሆነው ተፈራ ማሞ እየነገረን ያለው ‘’የፋኖ ዋና ተልዕኮ አማራ ያልሆኑ የአማራ ስም የወሰዱ ሁሉ ክእንግዲህ ወዲህ እንዳይጠሩበትና በልዋጭ በየነገዳቸው ስም እንዲጠሩ ለማስገደድ “ፋኖ” በትጋት እንደሚሰራ ነው ከወዲሁ እየነገረን ያለው”።

እነዚህ የእነ ዳዊት መሪዎች ናቸው።ይህንን ዘረኛ ቅስቀሳም ለታጣቂ ሰልጣኞችና እሱ ለሚያዋጋቸው ታጣቂዎቹ እንዲሁም ለአማራ ሕዝብ ይህንን ዘረኛ ፖሊሲው እያስተማረ ነው።

ይህንን አዋጅ በተፈራ ማሞ በኩል  እንዲነገር የተደረገው ዘረኛ ቅስቀሳ በፋኖ አማራር እውቅና የተደረገ ነውእውቅና ባይኖሮው ኖሮ ድርጅቱ ተሎ ብሎ በማውገዝና ተፈራን ከሥልጣኑ በማውረድ ድርጀቱ “የኢትዮጰያን ሕዝብ ይቅርታ መጠይቅ ነበረበት»

ሆኖም በድርጅቱ ፖሊሲ እውቅና ስለተነገረ ፤ እሰካሁን ድረስ ምንም ያሉት የለም።

የፋኖ ደጋፊዎች ያልሆኑ የአማራ ምሁራንም ዝምታን መርጠዋል

ይህ ዘረኝነት ወያኔዎችም ትግራይ ውስጥ የአማራ ስም የያዙ የትግራይ ተወላጆች እና በአማርኛ ስም ያላቸው ንግድ ቤቶች ወደ ትግርኛ እንዲለወጥ በድምጺ ወያነ ራዲዮ እና በትግርኛ ቋንቋ ምሁራን (ሁለት የዩኒቨርሲቲ መምህራን) በኩል ሲነጋገሩበት እንደነበር እና ለሕዝቡ የስልክ ጥሪ መነጋገሪያ መድረክ ክፍት ተደረጎ ውይይት ሲደረግ መቀሌ ከተማ  ትግራይ ከተማ ሳትሆን የአማራዎች ከተማ ሰለመሰለች የአማራ ስም ያላቸው እና ኗሪዎችዋ የሚንነጋገሩበት ትግርኛም አማርኛ የተቀላቀለበት «ዲቃላ-ትግርኛ» በመሆኑ ትኩረት እንዲደረግበት ሲያሳስቡ እንደነበር ካሁን በፊት አንድ መጣጥፍ አቅርቤ በድረገጾች ተለጥፎ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ተፈራ ማሞም ዕድሜውን ሙሉ ወያነ ያስተማረቺውን የጥላቻ ትምሕርት ፋኖ ውስጥ ይዞት ስለገባ «አማራ ያልሆነ ሰው የአማራ ስም መጠቀም  የለበትም» ማለቱ በናዚ ጀርመን ዘመንም በደም የአርያን/ኖርዲክ/ ጀርመን ደም ያልሆኑ ሰዎች  የቤተሰብ እና የግል ስሞችን የመቀየር ሕግ 1939-1938 ውስጥ ወጥቶ ነበር።

የቤተሰብ እና የግል ስሞች መቀየር ሕግ ላይ ያለው አስፈፃሚ ትዕዛዝ የሚያሳየው "አይሁድ ያልሆኑ" የጀርመን ስም ያላቸው  አይሁዶች ከእውነተኞቹ  የደም ጥራት ካላቸው ጀርመኖች ለመለየት ሲባል ተጨማሪ ስም እንዲይዙ በማስገደድ "እስራኤል" ለወንዶች እና "ሳራ" የሚለው ስም ለሴቶች እንዲሰጥ ሆኗል።

 ሁሉም የአይሁድ ፓስፖርቶች "J" በሚለው ቀይ ፊደል ታትሞባቸዋል።

በዚህ መልክ የፋኖዎቹ የነ ተፋራ ስማችን ተጠቀማችሁ የሚለው ስሞታና ሰበብ ከናዚዎች ፖሊሲ ጋር ሰናስተያየው የናዚ መሪዎች የጦርነት ዝግጅታቸውን ሲያፋጥኑ፣ በጀርመን እና በኦስትሪያ ፀረ-ሴማዊ ሕግ በአይሁዶች ላይ የበለጠ ሥር ነቀል ስደት እንዲፈጠር መንገድ ጠርጓል።

የሕጉ ዓላማ የጀርመን አይሁዶች በግልጽ እንዲታወቁ ማድረግ እና ከጀርመን ኮሚኒቲ (ሕዝባዊ ማሕበር) መለየት ነበር።

በተመሳሳይ መልኩ በፋኖ መሪዎች ናዚያዊ ንግግር መሰረት «እስክንድር ኢትዮጵያዊ እንጂ አማራ አይደለም» «አማራ ያልሆኑ በአማርኛ ስም የሚጠሩ ሰዎች ስማቸው ይለውጡ ሐጎስ፤ ፣ ነመራ፤ ኦባንግ ኔቶ፤ ታዲዮስ፤ ታንቱ ......ወዘተ (የቶች ስምም ሓዳስ..... ወዘተ በየነገዳችሁ ጨምሩበት)የሚል በመታወቂያ ስማችን ላይ ይጠቀስ ብሎ  «ፋኖ አዲሰ አበባ ገብቶ 4 ኪሎ ሲቆጣጠር፤ በሚደነግገው ሕገ-መንግሥት ላይ ናዚዎች “ጀይ/J/” የሚል ፊደል በአይሁዶቹ መለያ ካርድ እንዳተሙበት ሁሉ “የሚለው ፊደል እንዲሁ ለጠሩ ለነጠሩ አማራዎች ሲሆን “” የሚል ፊደል ደግሞ አማራ ላልሆኑ ወይም “ዘርን ላደፈረሱ” (ለተዳቀሉ)  ኢትዮጵያዊያን በመታወቂያ ካርዳችን እንደሚያሰፍሩበት ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

ምክንያቱም ይህንን የተፈራ አዋጅ በይፋ ድረጅቱ አላዋገዘውምና ይህንን አዋጅ እውን ያደርገዋል ብየ በድፍረት እከራከራለሁ።

 በዲያስፖራ የሚኖሩ የዚህ ድርጅት (ሃርድ ኮር ደጋፊ) የሆኑ በጣት የሚቆጠሩ ሄደውም መጥተውም የማይጠቅሙ የአማራ መሁራን ተብየዎቹ እና በዘረኝነት እየጨቀዩ ያሉት መሪዎቻቸው (ፋኖዎች) እና የነሱ ቱልቱላ ሚዲያዎቻቸው ከነዚህም አብረው በየቲክታክ መስኮቶች ተቸከለው ይህንን ዘረኝነት ወደ አየር የሚያስተጋቡ መንጋዎቻቸው  ከወያነ ውድቀት ማግስት የተከሰቱ አዳዲስ ዘረኞች ናቸው።

 የአማራ ስም የኔ እንጂ የማንም ኢትዮጵያዊም ይሁን ኢትዮጵያ ያደገ ፈረንጅ ሊጠቀምበት አይፈቀድም <<አምሐራ ለአማራ ብቻ>> የሚል አደገኛ ቅስቀሳ በምሁራን ዘንድ ትኩረት ሳይደረግበት ማየት ወያነና ኦነጎች በአማራዎች ላይ ያደረሱት ግፍ የአማርኛ ስም በያዝን በኢትዮጵያዊያትና ኢትዮጱያዊያን ላይ እየተዘመተብን ያለው ይህ የፋኖዎች ዘመቻ በቀላሉ እየታለፈ ቢሆንም ለወደፊቱ እግር እየተከለ ስለሚሄድ ስጋት የሚጭር ንግግር ነው።

እነኚህ የፋኖ መሪዎችና ተከታዮቻቸው ካንደበታቸው የሚያሰራጩት መልዕክት  እውቁ ኢትዮጵያዊው የሎሬት ጸጋዬ /መድህንንግግር አስታወሰኝ።

እንዲህ ይላል፡

<<ሐይቅ ዳር ተሰብስበው እንቁራሪቶቹ አብዝተው ስለጮሁ ሐይቁ የእንቁራሪቶች ነው ማለት አይደለም። ለክብራቸው ሲሉ ዝም ያሉ ብዙ ዓሳዎች ሐይቁ ውስጥ አሉ>> ይላሉ።

የነ ሻለቃ ዳዊት መሪዎች እገሌ ኢትዮጵያዊ እንጂ አማራ አየደለም ፥ የአማራ ስም የያዙ አማራ ያልሆኑ ሰዎች ስማችንን አስረክበው በራሳቸው ስምና አገር ይጠቀሙ ወደ እሚል ጭራሽ ወደ  ዕብደት የደረሱ የፋኖ መሪዎችን ስንመለከት ነብሱን ይማረው የዶ/ር ደረጀ አባባል ነው ዓይኔ ላይ ድቅን ያለው። እንዲህ ብሎ ነበር፦

<<የአማራ ብሔረተኛነት ድግሞ ጭራሽ ወደ ዕብደት የደረሰ ነው -Almost ወደ near madness የደረሰ ነው» አሁን የአማራ ናሺናሊዝም የሚባል የለም ነው የምለው >> << ከኖረ ግን እግዚአብሔር አይቅናው ቀንቶት ሥልጣን ከያዘ የአማራ ናሺናሊዝም የሂትለርን የሚመስለው ፋሺዝም ነው እዚች ሃገር የሚያሰፍነው!>> ብሎ ነበር፡ ነብስ ይማር ኢትዮጰያዊው ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ። አሁን ያንን የተነበየውን ትንቢት እውን ሆነ።

የነ ሻለቃ ዳዊት እና የነብርሃነመስቀል መሪዎች ዕበደትና ዘረኛነት በተጠቀሱት መሪዎች ብቻም አልተወሰነም። እሰላምና አማራ አበረው ቁርስ መካፈልም ይሁን ሥልጣን ላይ እስላም መውጣት የለበትም የሚሉ እንደ እነ መሳፍንት ተስፉ የመሳሰሉ በጎንደር የፋኖ መሪዎችም ለድርጅቱ ዘረኛነት ማዳበሪያዎች ናቸው።

 ሻለቃ ዳዊትና አምባሳደር በርሃነመስቀል ነጋ እነዚህን የፋኖ መሪዎችን “መሪዎቻችን” እያሉ በአድናቆት ሲፈነድቁና  በእንዲህ ያለ መሃይምነት ሲቸነከሩ ማየት ይገርማል።

 ሻለቃ ዳዊት ከደስታቸው ብዛት

«ታላቋን ኢትዮጵያ ማስወለድ የሚችሉ በይዘት የተለዩ፥ እንደዚህ ያለ የተለየ ውይይት ተሳትፌ እና መስክሬ አላውቅም አልሰማሁም ።  መጨረሻም ዕምባ ነው የተናነቀኝ፡....» ሲሉ በረሃነመስቀል ነጋም እንዲሁ ያለ ማፈር እነዚህን አዳዲስ ናዚዎች ሲያቆለጳጵሱ መስማት እኛን ኢትዮጵያዊያኖችንም ይሁን እግዚአብሔርን አልፈሩም። እዚህ ላይ ያስታወሰኝ ነገር አሁንም የጦቢያው ጸሐፊ ሙሉጌ ሉሌን   ነው።

ጸሐፊው እንዲህ ይላሉ፤

‘አቤቱ የሚፈሩት ስጣቸው!’ « እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አይደለም። እኛም ብንሆን ኢትዮጵያን አይደለንም። ወደ ትግሬነት፣ ወደ አማራነት፥ ከምባታነት፥ ሐዲያነት፥ ኦሮሞነት፥ ወዘተ፤ ተሸሽነናል። 80 ቤቶች ስርተናል። ኢትዮጵያዊነት የሚባል ነገር የሌለና ያልነበረ መሆኑ በሚነገርበት አገር ፤ እግዚአብሔር ብቻውን ኢትዮጵያዊ ሊሆን ነው? ወይስ ከክፍፍሉ (ከጎሳዎቹ) የትኛውን ይምረጥ?» ብለው ነበር።

ታዲያ «ከፊት ሆኖ ይምራን እኛ እንከተለው» እያሉን ያሉት “የሰለሞን ተካልኝ ቅጂዎቹ እነ ሻለቃ ዳዊት እና አምባሳደር ብርሃነመስቀል ነጋ ሁሉም እየወጣ የፈለገውን ዘረኛ ንግግር እንዲናገር የሚፈቅድ በሥርዓት የማይመራ ከዚህ ታጣቂ ቡድን ጋር የሚያቁነጠንጥ “እፍ ፥ እፍ ፍቅር!” የያዛቸው እነዚህ ሰዎች  

«እልፍ አእላፍ ኢትዮጰያዊ ይህችን አገር ተመልሶ ላለማየትና እየተፈጠመ -ቃል እየገባ- ሲወጣ እግዚአብሔር ኢትዮጰያዊ የሚሆንበት ምን ምክንያት፤ ምንስ ግዴታ አለበት? ታላቁን ጌታ ክእነ መለስና ከነ ነጋሶ ጋር በአንድ አገር የኖር ዘንድ እንፍረድበት?» እንዳሉት ታላቁ ጸሐፊ 

 ታላቁን ጌታና ታላቁ የአማራ ሕዝብ ከነዚህ መንፈሳዊ ባዶነትና የሕሊና እራቁትነት ከተጠናወታቸው ከአዳዲሶቹ የፋኖ ዘረኞች ክእነ አስረስ ማረ እና ከነ ተፈራ ማሞ ባንድ አገር ይኖሩ ዘንድ እንፍረድበት?እንዴትስ በዚህ የዘረኛነታቸው ባሕሪ ሕዝቡን እንዲመሩት እንፈቅዳለን?

ሰላም እንስንብት

ጌታቸው ረዳ

Thursday, February 12, 2026

ዶ/ር ጸጋ መላኩ ኢትዮጵያን ለምን ጠሉ? ሰመረ አለሙ Ethiopian Semay 2/12/2026

 

 

ዶ/ር ጸጋ መላኩ ኢትዮጵያን ለምን ጠሉ?

ሰመረ አለሙ

Ethiopian Semay

2/12/2026


ከላይ ምስላቸው የሚታየው ትውልደ  ኢትዮጵያውያን ታላቁ  ዶ/ር ኢንጀነር ቅጣው እጅጉና ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በእጅጉ ያንገሸገሻቸው ዶ/ር ጸጋ መላኩ ናቸው፡፡  በወ/ሮ ጸጋ በኩል የተለየ ማብራሪያ ቢሰጠውም ሁለቱም ለተሻለ ህይወት ወደ ባህር ማዶ ያቀኑ የኢትዮጵያ ልጆች ነበሩ፡፡ ነብሱን ይማረውና ቅጣው እጅጉ በህይወት በነበረበት ዘመን ከግል ኑሮው በላይ ስለ ሃገሩ ኢትዮጵያ የሚብሰከሰክ መልካም ዜጋ ነበር፡፡ በኑሮ ደረጃውም  ልጅ ቅጣው እጅጉ ከወ/ሮ ጸጋ በላይ በአሜሪካ ቁሳዊ  ጥቅሞች ተመቻችቶለት በታላቅ እንክብካቤ የሚኖር የተዋጣለት ሳይንቲስት ነበር፡፡  ይህ ወንድማችን በአንድ ወቅት የወያኔን መንግስት ለመጣል ሃይል አቀናጅቶ ከፍተኛ ጥረት አድርጎም ነበር  በዚህ የተከፋው ቴዎድሮስ ጸጋዬ የርእዮት ሚዲያ ባለቤት አፍቃሪ ኢትዮጵያ በመሆኑ  ጥርስ ነክሶበት  ሲያብጠለጥለውም ነበር፡፡ ዶር ኢንጅነር ቅጣው እጅጉ ቢሮ በቀኙ የኢትዮጵያ ባንዲራ በግራው ደግሞ የተቀማጠለ ኑሮ የሰጠችውን የአሜሪካን ባንዲራ በማቆም ለሃገሩ ያለውን ክብር አሳይቷል፡፡

ስለ ፎቶግራፉ  በዚህ መልኩ ካብራራን በኋላ  በቅርቡ አስተዋዩ፤ሞጋቹ ትንታጉ ጋዜጠኛ ተክለ ሃይማኖት አዳነ ወደ ሃገረ እስራኤል አቅንቶ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷን ዶር ጸጋ መላኩን አነጋግሮ ነበር፡፡ ተ/ ሃይማኖት ጥያቄውን ሲሸክፈው 1/ ኢትዮጵያ ውስጥ የቀሩ ቤተ እስራኤላውያን እርሶ ይህንን ወምበር ከያዙ በኋላ ጉዳያችን መንቀሳቀስ አቁሟል እያሉ ቅሬታቸውን ያሰማሉ 2/  የኢየሩሳሌም ይዞታችን የዴር ሱልጣን ገዳም  ሊፈርስ መቃረቡንና በዚያ የሚኖሩት ገዳማውያንም መንገላታቸውን 3/ ኢትዮጵያ በኖሩበት ዘመን የኢትዮጵያ ትዝታቸውንና 4/ በቱርክ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የዋሃቢ ሰው በእስራኤል ጉዳይ የሰጠውን ግንዛቤ እንዴት ይመለከቱታል የሚል ይገኝበታል፡፡

ጋዜጠኛ ተክሌ የስልጣን ርቀቱን ጠብቆ ብዙ የሚያውቀውን ለራሱ ይዞ  እሳቸው ብቻ የሚሰጡትን መልስ ሳይሞግት እንዳለ አስተላልፎልናል፡፡ አንዳንዴ ብቻ ወ/ሮዋ ገደብ ሲጥሱ እርምት ለማድረግ  ቢሞክርም ሴትዮዋ መናገርና የራሳቸውን ሃሳብ ከማስተጋባት ውጭ የሌላውን ስለማያዳምጡ አንዳንዴም ከጥያቄው ጋር ያልተገናኘ መልስ በመስጠታቸው አድማጭ ይፍረድ በማለት ቃለ መጠይቁን እንዳለ አቅርቦታል።

 https://www.youtube.com/watch?v=YgI 

 ወ/ሮ ጸጋ ኢትዮጵያ በሚኖሩበት ጊዜ የምድር ሲኦል ይኖሩ እንደነበር መገለል ይደርስባቸው እንደ ነበር  በተጨማሪም  ሸክላ ሰሪ ፤ ካይላ፤ ቡዳ ፤ፈላሻ ይባሉ እንደነበረና መሬት መግዛት እንደማይፈቀድላቸው ከፕሮፌሰር ሃይጋ የተጋቱትን  ከፈረንጅ መጽሃፍ አንብበው መበደላቸውን ቱግ ግንፍል እያሉ ሲያወሩ ሰማናቸው፡፡ አንባቢ ሴትዮዋ ኢትዮጵያን ሲለቁ 16 አመታቸው መሆኑን ከግንዛቤ ይውሰድ፡፡ ያሳዝናል እንደሳቸው በዶክትሬት ደረጃ የተማረ ነገርን በጥልቀት ሳያገናዝብ የፕሮፌሰር ሃይጋን የማጠብ ፖለቲካ ሳያላምጥ የበላበትን ወጭት መስበሩ በእጅጉ ያስተዛዝባል ፡፡ እውቁ ኢትዮጵያዊ መንግስቱ ለማ በሎንዶን ሲማር በህመም ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ አንዱ መደዴ እንግሊዝ ልብስ የለበስከው አየር ማረፊያው ላይ ወደ እንግሊዝ ስትመጣ ነው፤ ሃገርህ ዛፍ ላይ ነበር ተንጠልጥለህ የምትኖረው ይህንን አስረዳን በማለት በመቶ በሚቆጠሩ መደዴ  የእንግሊዝ ህሙማን ወጥረው ቢጠይቁት  ነገሩ ገርሞት "ከየት ልጀምረው ብሎ ጥልቅ ሃሳብ ውስጥ የገባውን ያህል ለወ/ሮ ጸጋም ለመመልስ ከየት ልጀምር ብሎ በእጅጉ ያስጨንቃል፡፡  መንግስቱ ለማ ግን ቆፍጣና ኢትዮጵያዊና የተዋጣለት ምሁር በመሆኑ የተጠየቀውን  አንዱንም ሳይክድ እነዛን መደዴ እንግሊዞች በምሁራዊ ትንተና አላዋቂነታቸውን አረጋግጦ ኢትዮጵያን አስከብሮ ታሪካዊ ተልእኮውን ተወጥቶ ነበር  ወደ ውድ ሃገሩ የተመለሰው፡፡

 በጎንደር፤በጎጃም፤በወሎበሸዋ፤በከፋ፤በትግራይ፤በአሩሲ፤በሲዳሞ፤በሃረር፡፡ አንዱ አንዱ ላይ መቀለዱ የታወቀ ነበር  ያም ካለመማር የመጣ እንጅ ቂም ታስቦ ታልሞ ሌላውን ለማቁሰል በኢንስቲቱሽኖች የተባለ አባባል አልነበረም፡፡  ጋዜጠኛው እራሱ በቤተ ሰቡ ሳይቀር የደረሰበትን በደል ከዚህ በፊት አቅርቦልናል እሱም ከግንዛቤ ማጣትና ባለመማር ነው በማለት ነገሩን ቂም ሳይቋጥርበት አልፎታል፡፡ ጎጃሜ ቡዳ ነው እየተባለ በዘፈን ሳይቀር ይቀለዳል ወ/ሮዋም ይህን ነገር ያውቃሉ ወይም ከቤተሰባቸው ይሰማሉ፡፡ጎጃሜ ግን ሃገሩ ኢትዮጵያ ላይ እንዲህ ተባልኩ ብሎ የጥላቻ ሰይፉን እንደ ወ/ሮ ጸጋ አልመዘዘም ስቆ ያልፈዋል እንጅ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ከቤተ እስራኤላውያኑ በላይ በትግሬ፤በአማራ፤በኦሮሞ፤በደቡብ ይቀለዳል እንደውስ ማን የማይቀለድበት ጎሳ አለ?  ህብረተሰባችን ባለመማሩ አርሶ የሚያበላውን ገበሬ አፈር ገፊ፤ ማረሺያውን የሚሰራለትን ቀጥቃጭ፤ ሸምኖ የሚያለብሰውን ሸማኔ፤ ፍቆ አቅማዳ የሚሰራለትን ፋቂ ሌላም ሌላም ስም  ሲሰጠው ኑሯል፡፡ ባለውለታውን በዚህ መልኩ የሚጠራ ህብረተሰብ ባለመማሩ አላዋቂ ካለመሆኑ በስተቀር ምን ምክንያት ሊሰጥበት ይችላል? ቤተ እስራኤላውያን ነን ብለው ራሳቸውን የጠሩት በዚህ ልክ ተበድለው ነበር ወይ? ዛሬ አገራችን እስራኤል በሚሉት አገር ከዚህ ያነሰ መገለል አልደረሰባቸውም ወይ? በእርግጥ በየስርአቱ ከገዥዎች ጋር  እንደ ዶር ጸጋ የሚሞዳሞዱ  ይህ መገለል ላይደርስባቸው ይችላል፡፡ ወሮ ጸጋ  እንዳናውቅ ቢያድበሰብሱትም በሃገረ እስራኤል በትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው በደል በመላው አለም የሚገኙ ሚዲያዎችን ቀልብ ስለሚስብ በየእለቱ እየሰማነው ነው፡፡  እንደውም ይህ ጽሁፍ ሲዘጋጅ ቤተ እስራኤላውያን ላይ የሚደርሰውን በደልና አድልዎ  አስመልክቶ የእስራኤል ፓርላማ ውይይት ያደርጋል ዶር ጸጋ  የማገጃ ትእዛዝ ካላወጡበት  በስተቀር፡፡ዶር  ጸጋ አክቲቪስት ሁነው የእስራኤልን ፓርላማ ደጅ ይጠኑ የነበረው ቆሻሻ ነው ተብሎ በተደፋው በኢትዮጵውያን ደም ምክንያት መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ ቤተ እስራኤላውያን ከጠቅላላው የእስራኤል ህዝብ በንጽጽር በግምባር ላይ ከሚሰለፉ የእስራኤል ወታደሮች ከፍተኛውን ቁጥር ሲይዙ ሞታቸውም በዚያው ልክ ያሻቅባል ይህ ዶር ጸጋን አያሳስብም ባላቸው ንክኪ ልጆቻቸው ወደ ውጊያ ስላማይሄዱ፡፡ በኦፊሰር ደረጃ ያሉ እጅግ በጣም ጥቂቶችና ለንጽጽርም የሚበቁ አይደሉም፡፡ ወ/ሮ ጸጋ ማርች 15 2023 ለኪኔሴቱ ባደረጉት ንግግር ተቃውሟቸውን ሲገልጹ   ቤተ እስራኤላውያኑ በቂ መተዳደሪያ ያለ ማግኘታቸው፤በመንፈሳዊ አባቶቻችዉ ላይ የሚደርሰው ንቀት፤በቂ የሆነ ህክምና ያለማግኘት፤ልጆቻቸው የከፍተኛ ትምህርት እድል ያለማግኘት፤የሚመደቡበት የትምህርት ዘርፎች ወደፊት በቂ መተዳደሪያን የማያገስገኝ መሆኑ በመግለጽ ነበር፡፡ እንደውም በ2022 በሃላፊነት ሰራ የተመደቡት 2% መሆናቸውንና በትምህርት ረገድ ከፍተኛ መድሎ እንደተደረገባቸው ዛሬ በጣም ሰልጥነናል በሚሏት እስራኤል ላይ እየተደረገባቸው መሆኑን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ ስምና አዲስ ማንነትን የመቀየሩን ነገር ከግምት ሳንከት ማለት ነው፡፡ የአረብና ሌሎች ወደ እስራኤል የፈለሱት ቤተ እስራኤላውያን ቀድሞ የነበራቸውን ስምና ማንነት ሲይዙ ከኢትዮጵያ የሚሄዱት ግን አዲስ ስም ወጥቶላቸዋል አዲስ የሃይማኖት ስልጠናም ተቀብለዋል፡፡ኢትዮጵያ ግን በልጆቿ መሃል ልዩነት ሳታደርግ በድህነቷ እኩል አስተናግዳቸዉ ነበር  የኢትዮጵያ በደሏ ደሃ መሆኗ ነው ደሃ እናት ደግሞ ለምን ደኸየች ተብላ በጠላትነት ልትታይ አይገባትም፡፡

ከ9 ወር በፊት እዚሁ እግረኛው ሚዲያ ላይ ብርቱካን የተባለች መልከ መልካም ወገናችን በትግራይ  "ቡዳ ነሽ" ፤ "ወደ ጅብነት ትቀየሪያለሽ" ሌላም ሌላም  እያሉ መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተውኛል"<<ከትግራይ-አውጡኝ>> በማለት ተማጽኖዋን ለኢትዮውጵያውያን አቅርባለች፡፡ መረጃውም እነሆ።

https://www.youtube.com/watch?v=tgpLyHmkBdg   

ብርቱካን ምንም እንኳን የኦርቶዶክስ ተከታይ ብትሆንም ልጅሽን ክርስትና አናነሳውም፤ ልጆችሽም ከልጆቻችን ጋር አይማሩም ተብላ በሚያሳዝን ሁኔታ የተገለለች ወጣት ነች፡፡ ብርቱካን ፈላሻ  ሁና አይደለም ይህ ሁሉ መገለል የደረሰባት፡፡  ለዚህ ተጠያቂው የትግራይ ህዝብ ሳይሆን እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገር  የእውቀትና የግንዛቤ ችግር  በማህበራችን መንሰራፋቱ ነው፡፡ እስቲ ወደ ወሮ ጸጋ ህይወት እንመለስ ወ/ሮ ጸጋ ጎንደር በልጅነታቸው ብስክሌት እየጋለቡ የምድር መንግስተ ሰማያት ይኖሩ የነበር ሲሆን ቤተሰባቸው በጎንደር ቤት ንብረት ያላቸው ነበሩ አባታቸውም በወቅቱ ለሌሎች ህልም በሆነው በመብራት ሃይል ተቀጥረው ይሰሩ ነበር፡፡  ወሮ ጸጋ መበደላቸውን ያወቁት ከቤተሰባቸው ሳይሆን በሰሚ ሰሚ  ከፈረንጆቹ ነበር፡፡ ብዙ ጎንደሬዎች ከቤተ እስራኤላውያን ጋር ተጋብተው በፍቅር እየኖሩ ነው ከቤተ እስራኤላውያንም ለመጋባት ከፍተኛ ፍላጎትም  እንዳለ ጋዜጠኛ ተክሌ በቦታው ተገኝቶ የአይን ምስክርነቱን ቢሰጥም ሴትዮዋ ለመስማት ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ቤተ እስራኤላውያኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በውትድርና፤  በአስተዳደር፤ በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ነበሩ የወ/ሮዋ በሬ ወለደ ተረት አንድም ተጨባጭነት ያለው ማስረጃ ሊቀርብለት አይችልም ከአፈ ታሪክ በዘለለ፡፡

ዶር ጸጋ አንዱ አምርረው ከገለጹት በላይና ሊረሱት ያልቻሉት ፈላሻ እየተባሉ መጠራታቸውን ነው ይገርማል በዚያው ቃለ ምልልስ ማንኛውም ቤተ እስራኤላዊ ህልሙና ጸሎቱ ከ2500 አመት በፊት ከመጣባት ከፈለሰባት ሃገሩ ወደ እስራኤል መመለስ ነው ብለውናል፡፡ ይህ የዶ/ር ጸጋ ማብራሪያ የሚያሳየውና ዶር ጸጋም የተቀበሉት ከውጭ ፈልሰው የመጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ታዲያ ይህ ስም በሌሎች ሲጠራ ወንጀል መሆኑ ምኑ ላይ ነው? በእርግጥ ይህንን ስም አንወደውም ተብሎ ስምን መለወጥ ይቻላል  የጥል መንስኤ ግን መሆኑ አግባብነት የለውም ፡፡ (በጌምድር ወደ ጎንደር፤ ጋላ ወደ ኦሮሞ፤ አሩሲ ወደ አርሲ፤ሀረር ወደ ሃረሪ ተለውጧል ሌላም ሌላም)፡፡ ቤተ እስራኤላውያን ኢትዮጵያ በነበሩበት ጊዜ በእኩልነት አንዱ ከአንዱ ሳያንስ የሚኖርበት በመሆኑ ዶር ጸጋና ቤተሰቦቻቸው ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በላይ የቅንጦት ኑሮ  መኖራቸውን አባባላቸው የፈጠራ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ማሳያውም  " እናቴን ነገ ወደ ኢትዮጵያ ልንሄድ ነው ብዬ አሁን ብደውልላት ልዘጋጅ እንኳን አትለኝም ለኢትዮጵያ ካላት ፍቅር የተነሳ" በማለት ኢትዮጵያ ያለመበደሏን አረጋግጠውልናል፡፡ በእርግጥ ወያኔ ከገባ በኋላ ሂደው ቢሆን ኑሮ በጎሳዬ ተበደልኩ ብለው ሊነግሩን ይችሉ ነበር የወቅቱ ፋሽን በመሆኑ፡፡ እንደዛም እንዳንል ጌታቸው ረዳ የ TPLF መሪ ሁኖ ወደ እስራኤል ተጉዞ እንዳነጋገራችውም እናውቃለን፡፡ እንደ ወ/ሮ ጸጋ ገለጻ  ጀርመን ካደረሰባቸው በላይ ኢትዮጵያውያን ያደረሱባቸው በደል ይበልጣል ባይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያውያን መልካምነት ግን በእናታቸው በኩል ተንጸባርቋል፡፡  ዮዲት ጌዴዎን የአይሁድ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰችው ጥፋትና ሰቆቃ ጀርመን በሚኖሩት አይሁዳውያን ላይ ከደረሰው ይበልጥ እንደሆን እንጅ የሚተናነስ አልነበረም መልካሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን በዚህ ቂም አልያዘም ተፈጥሮውም አይደለም፡

ዶር ጸጋ የእስራኤል ወዳጅ ናቸው ብሎ ፣መገመት ይከብዳል፡፡ በውነት ለቤት እስራኤሎች ከኢትዮጵያውያን በላይ ወዳጅ ከየት ይመጣል? 80% ያህል ኢትዮጵያዊ ለእስራኤል በአንድም ሆነ በሌላ ስስ ልብ አለው፡፡ " የእስራኤል ወዳጇ ለኔም ወዳጄ ነው ቤተኛ መሆኔ ታዲያ ምኑ ላይ ነው?' እያልን እንዳላዜምን እኝህ ሰው በእብሪት ጉድ ሰሩን ፡፡ ወሮ ጸጋ የወደፊት ህልማቸውን ሲጠየቁ  ለጊዜው ከነኳታር ጋር ተስማምተናል ሳውዲ አረቢያና የተለያዩ ቦታዎች በነጻነት መሄድ ነው የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል ኢትዮጵያ ግን ዝርዝራቸው ውስጥ አልተካተተችም፡፡ ወሮ ጸጋ ኑሮና ታሪክ ብዙ አስተምሮናል ቁሚያለሁ ያለ በእግዚአብሄር የቆመ ነው አሜሪካ አውሮፓን አላውቅህም ብላዋለች ነገ ነገሮች ምን አቅጣጫ እንደሚይዙ የሚያውቅ ፈጣሪ ብቻ ነው አይበለውና ለጥቂት ሰከንድ እስራኤልን ከአሜሪካ ነጥለው ይመልከቷት፡፡ ባለፈው በኢራን የሚሳዬል ውርጅብኝ ሲወርድ ባንድ እግራችን እየቆምን ነበር ምህላ ያደረስነው ዛሬ እርሶ ግን ይህ የመከራ ጊዜ ያለፈ ሲመስሎት ገደብ በሌለው እብሪት ያብጠልጥሉናል፡፡  እንደ እርሶ አይነት ፖለቲከኛ ለእስራኤል ጠላት እንጅ ወዳጅ አያበዛላትም መሰረተ ኢትዮጵያውያን ለሚቀጥለው የፓርላማ ምርጫ ይህን ነገር ከግምት ይከታሉ ብለን እናምናለን፡፡

ወሮ ጸጋ ወደ እስራኤል የወሰዶት የእምነትም የመገፋትም ምክንያት አይደለም ኢትዮጵያ ደሃ አገር በመሆኗ  ጥሩ ኑሮን ፍለጋ በማለም ነው፡፡ እኔም ሃገሬን ጥዬ ወደ አሜሪካ የተሰደድኩት የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ነው እኔም ዜግነቴን ቀይሪያለሁ ሃገሬ በነበርኩበት ጊዜም መናጢ ደሃ ነበርኩ ሃገሬ ካላት በላይ ልትሰጠኝ ስለማትችል ዛሬ ላይ እንደ እርሶ ኢትዮጵያን ሳብጠለጠል አልውልም እንደውም ሃሳቤና መንፈሴ ከኢትዮጵያ ተሰፍቶ ከእንቅልፍ የምባንንበት ጊዜም አለ ስለ መጭው ዘመኗ በማሰብ፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሚጎርፈው ቤተ እስራኤል እንደ እኔና እንደእርሶ መልካም ኑሮን ፍለጋ ነው፡፡ በሊቢያ፤ በየመን፤በሱዳን፤በሳውዲ አረቢያ  ነብሱን አስይዞ ተዋርዶ የሚጎርፈው የተከበረው ኢትዮጵያዊ  በተመሳሳይ ምክንያት ምክንያት ኑሮን ለማሸነፍ ነው   ማለባበስና ምክንያት መደርደር አያስፈልግም፡ በአውሮፓና በአሜሪካ እጅግ ብዙ የሃገሩ አይሁዳውያን ይኖራሉ በኢትዮጵያውያኑ ልክ እራሳቸውን ለአደጋ ሰጥተው ወደ እስራኤል ለውትድርና ግልጋሎትና ለመኖር ሲጓዙ  አላየንም ምክንያቱም እስራኤል ሊያገኙ ከሚችሉት ጥቅም በላይ ባሉበት አገር ስለሚያገኙ ነው፡፡  በተቃራኒው ብዙ እስራኤላውያን  ወደ አውሮፓና አሜሪካ ይጎርፋሉ( ይፈልሳሉ የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ነው እንዳያስቆጣዎት)፡፡ በቃለ ምልልሶ እንዳስተዋልነው ያቀረቡት ሃተታና ምክንያት ሁሉ ውሃ የሚቋጥር አይደለም ምሁራዊ ትንታኔዎም እጅግ ቀላላ ነው፡፡ ዛሬ አለም እርሶ ኢትዮጵያን ሲለቁ የነበረበት ዘመን አይደልም የመረጃዎች ፍሰት በእጅጉ ጨምሯል ምናልባትም እዛው እስራኤል ውስጥ ሁነው እርሶ ያልደረሱበት ዜናዎች የኢትዮጵያ ወጣቶች እጅ ሊደርስ ይችላል የእውቀት ሞኖፖሊነትም ስላበቃ ሌላውን አሳንሶ ማየት አላዋቂነት ነው፡፡

ወ/ሮ ጸጋ ከእስራኤል ባለስልጣን ጋር በተለያየ ሁኔታ  መገናኘታቸውና ፎቶ መነሳታቸው እራሳቸውን እንደ ነጮች ሳይመለከቱ አልቀሩም፡፡  ወሮ ጸጋ እርሶ እስከ ቤተሰብዎ  ጠቅልለው ስለመጡ እርሶ ያገኙትን እድል ኢትዮጵያ ለቀሩት ቤት እስራኤላውያን አይነፈጓቸው ጥረትም  ያለማድረግዎን ፍንጭ ሰጥተዋል  ከ3 ትውልድ በላይ አናመጣም የሚሉት ለኢትዮጵያውያኑ አይሰራም እዚህ ከ3 ትውልድ በላይ ስላልተጨፈጨፋችሁ፡፡  በኢየሩሳሌም ስላለው ይዞታችን የግብጽ ነው ብለው ቃሎን ስለሰጡ ምን ማለት እንችላለን አፍቃሪ ኢትዮጵያ የፓርላማ አባል ሲመጣ ጉዳዩን ህይወት ይዘራበት ይሆናል፡፡ የፓለስታይኑ እስላሙ ንጉስ ይዞታችንን ሲያጸኑልን በሳለሃዲን ጊዜ ኢትዮጵያውያን ተጓዦች ልዩ ጥበቃ ተደርጎላቸው ወደ እምነት ቦታቸው ሲጓዙ  በነ ዶር ጸጋ መላኩ የስልጣን ዘመን ይዞታችን መነጠቁ ልብ ያደማል ጊዜ ይፍረደው፡

በመጨረሻም ለእስራኤል መራጭ ህዝብ በተለይም ቤተ እስራኤላውያን

ወሮ ጸጋን በዚያ ወምበር ያስቀምጥካቸው አንተ ነህ ሴትዮዋ አፈትልኳቸው እንደገለጹት ክፉ የኢትዮጵያ ጥላቻ አላቸው ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን በዚያ ለሚኖሩት ቤተ እስራኤላውያንም ክብርና ፍቅር የላቸውም  በዚያ ያላችሁ ወገኖቻችን ኢትዮጵያ አገራችሁ ነች ኢትዮጵያ መሸሻችሁ ነች ዶር ጸጋ ግን በዚህ ወምበር  እስከተቀመጡ ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላችሁ ቁርኝት መፋቁ አይቀሬ ነው፡፡  የኢትዮጵያ ህዝብ ለናንተ ያለው ፍቅር ወደር የለውም ነገር ግን እናንተን በዶር ጸጋ አይን ካያችሁ አትራፊ አትሆኑም፡፡ በእርግጥ እንደ ወንድማችን ዳጊ መሰለኝ ወደ ፓርላማ ሲገባ የእናቱን ጉልበት የሳመው፤እነ ዶር አምባሳደር አብረሃም ንጉሴ አይነቱን በወሮ ጸጋ አይነት ማየት ቢከብደንም በዚህ ሃላፊነት የሚሰሩ ሰው ያደረሱት ጥፋት በእናንተው ካልሆነ በሌላ ሊፋቅ አይችልም፡፡ የሴትዮዋ ኢትዮጵያን  ጥላቻ የጀመረው ከፕሮፌሰር ሃይጋ ትምህርት ይሁን ወይም የትግሬ ራዲዮ በሚሰሩበት ጊዜ ወይም ደግሞ ጌታቸው ረዳ የ ቲ ፒ ኤል  ኤፍ መሪ ሁኖ በጎበኛቸው ጊዜ ትክክለኛ ምንጩን ለጊዜው ማወቅ ቢከብደንም ወደፊት መድረሳችን ግን ጥርጣሬ የለውም፡፡ በነገራችን ላይ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ የዘር ሃረጉ ከአይሁድ እምነት ተከታዮች ቤተሰቡ ይመዘዛል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

ሰመረ አለሙ semere.alemu@yahoo.com

 

 

 

 

Thursday, February 5, 2026

ለአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እኔም የምለው አለኝ! ይኄይስ አእምሮ 2/5/26 Ethiopian Semay

ለአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እኔም የምለው አለኝ!

ይኄይስ አእምሮ

2/5/26

Ethiopian Semay

በቀጣዩ ዐረፍተ ነገር የምለውን ለማለት በርግጥም የተወሰነ ጥናትና ምርምር አስፈላጊ መሆኑ አይካድም፡፡ [ይሁንና] ካነበብኩትም፣ ከሰማሁትም፣ ፈጣሪየ ረዘም ያለ ዕድሜ ሰጥቶኝ በሕይወት ተሞክሮየ ከታዘብኩትም፣ በተለይ ደግሞ ያለፉት ስምንት ዓመታት የአቢይ አህመድ ጭራቃዊ አገዛዝ አእምሮየን ካሸከመው ሥነ ልቦናዊ ቀውስና አእምሯዊ ህመም በመነሳት “በዓለማችን ታሪክ እንደአማራ ጠላት የበዛበትና በዚያም ምክንያት እንደአማራ የተበደለ ሕዝብ (ነገድ) የለም” የሚል ግለሰብኣዊ ምሥክርነት ብሰጥ ስህተቴ ያን ያህል ለከፉ የሚሰጥ አይመስለኝም፡፡ የአማራ ጠላት እንደመብዛቱ እስካሁን አለመጥፋቱ ደግሞ የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት እንዳለ መገመት አይከብድም፡፡ ለምን ቢባል ሌሎች መሰል ነገዶች ጠፍተዋልና፡፡ አማራ ግን ትንሣኤው እንደተጠበቀ ሆኖ እየተንጠራወዘም ቢሆን አለ ለማለት ያህል እስካሁን አለ፡፡

የአማራ ጠላቶች ቆጥረው አይዘለቁም፡፡ ጭንቅላቱ በውጭ ሀገር ሆኖ በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ ዓለምን እየገዛ የሚገኘው የአፍራሹ ኃይል ምድራዊ ወኪል (Ambassador of the Negative Energy) አንደኛው ሲሆን ሁለተኛውና የዚህ ኃይል የሀገር ውስጥ ታዛዡ ደግሞ በዚሁ አሉታዊ ኑባሬ ተኮትኩቶና በመርዛማ ትርክት አንጎሉ ተሞልቶ ያደገውና አንዱ አንዱን እየተካ የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥትን ሲቆጣጠር በሚገባ የምናውቀው ዘረኛና ሆዳም ትውልድ ነው፡፡ እነዚህ ዋነኞቹ የአማራ ጠላቶች ሲሆኑ ከዋና ጠላትነት ባልተናነሰ የአማራን ከርሰ መቃብር እየቆፈረ አማራን በመጨረስ ላይ የሚገኘው ደግሞ ከአማራው አብራክ የወጣ ሆዳምና ባንዳ አማራ ነው፡፡ የአማራ ክልል ሚሊሻና አድማ በታኝ ከመከላከያ ጋር ጥምር ጦር በሚል መጠሪያ ተባብሮ ፋኖን በመውጋት የራሱን አጥፊ ኦሮሙማን ሲታደግ ይታያችሁ፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ነጥብ ዙሪያ ትንሽ ተጨማሪ ነገር ማለት አስፈላጊ ነው፡፡ በቅድሚያ ግን በክርስትና ሃይማኖቴ አንድ ትልቅ አስተምህሮ ያለው ክስተት ባስታውስ ደስ ይለኛል፡፡ እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር እንደሰው ሲመላለስና ተልእኮውንም ጨርሶ በስቅላት ሕይወቱን ለሰው ልጆች ሲገብር ለዚያ ኹነት ያበቃው ይሁዳ የሚባል የራሱ ደቀ መዝሙር መሆኑ ነው፡፡ ገንዘብ ያዥ የነበረው ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር አበደና ጌታውን በ30 አላድ ሸጠ፡፡ ጉንጩን በመሳም አሳልፎ ከሸጠውና እንዲሰቀል ካደረገው በኋላ ግን ተፀፀተና የሸጠበትን ገንዘብ ሳይበላው ራሱን ሰቅሎ ሞተ፡፡ አማራን የከዱ አማሮች ሁሉ ክርስቶስ “የሰውን ልጅ አሳልፎ የሚሰጥ የወፍጮ መጅ ባንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል” ሲል ያ ሆዳም ገብጋባ፣ ያ የዲያቢሎስ ልዑክ ይሁዳ መዳረሻው ሲዖል እንጂ ገነት እንደማይሆን በግልጽ እንደተናገረ ሁሉ እነዚህ አማራን የከዱ አማሮችም በታሪክ ጥቁር መዝገብ ስማቸው ሰፍሮ ወደፊት ለሚነሱ ከሃዲዎች መቀጣጫ እንደሚሆኑ አንጠራጠርም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡

አማራን ገባ ብለን ማየቱ ስለአማራ ጠላት አማራዎች መጠነኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስችለናል፡፡

በአማራ ስም የሚነግደው አማራ ነኝ ባይ እጅግ ብዙ ነው፡፡ በመሠረቱ አማራነት ክፍት ነው - በተለያዩ ምክንያቶች፡፡

አንደኛ - አማርኛ ቋንቋ ባለቤትነቱ አማሮች ተብለው ለተፈረጁት ዜጎች ብቻ የተተወ ሣይሆን የገዢዎችም ቋንቋ ነው፡፡ ገዢዎች ደግሞ ከየትኛውም ነገድ ወይም ብሔር/ብሔረሰብ የሚመጡ ናቸው - አማራውም፣ ትግሬውም፣ አገውም፣ ኦሮሞውም … ኢትዮጵያን እየተፈራረቀ ገዝቷል፡፡ ስለዚህ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አማርኛ ባለቤት አልነበረውም - ግን ያስገድል መጀመሩ ከጊዜ ወደጊዜ ግንዛቤ እያገኘና አማርኛን በአፍ መፍቻነት የሚናገሩ ተጠቂዎችም የአክራሪ ዘረኞች ዒላማ እየሆኑ መጡ፡፡

ሁለተኛ - አማራ የሚባለው ነገድ ከአካባቢና ከክፍለ ሀገር ልጅነት ባለፈ በጎሰኝነትና በዘረኝነት እንዲሁም በአንድ ቋንቋ ተናጋሪነት የፍረጃ ደዌ የተለከፈ ባለመሆኑ ከሁሉም የኢትዮጵያ ነገዶች ጋር ተዋልዷል፤ ተካብዷል፡፡ ስለዚህም በዘረኝነት ልክፍት ተጠምዶ በወንዝና በሸንተረር ራሱን አጥሮ የጋራ መሰባሰቢያ ጎሣዊ ማንነት ሊፈጥር አልቻለም፡፡ ይህም አንዱ የችግሩ መንስዔ ነው፡፡

ሦስተኛ - በብዙ የመቶኛ ስሌት “ጥርት ያለ” አማራ የሚባለውን ዜጋ ከዜሮ በላይ እስከሚገኙ ጥቃቅን የመቶኛ ሥሌቶች ድረስ “በአባቴ እናት ትግሬ ነኝ፤ በሴት አያቴ አባት ኦሮሞ ነኝ” የሚለውን ሰው ሁሉ አማራ በአማራነት ይቀበላል፤ አማራ የመሳብና የማቀፍ እንጂ የመግፋትና እደጅ አቁሞ አጥንትና ደም የማጣራት ጠባይ የለውም፡፡ ስለሆነም ይህ ለማንም እጅግ የተለጠጠ አማራዊ ክፍተት ለአሰለጦችና ለጠላቶቹ ቦርቃቃ መግቢያ በር እየከፈተ አማራን አስጠቅቶታል፤ እያስጠቃውም ነው፡፡ አማራ የአማራነትን ነገዳዊ የማንነት ሥልጣን የመስጠት ወይ የመንፈግ መብት እንደሌለው ይገነዘባል፡፡ ሌሎች ግን ይህ መብት እንዳላቸው ይሰማቸዋል ብቻ ሣይሆን ተግባራዊ ሲያደርጉም ይስተዋላል፡፡ ለምሣሌ አንድ ሰው ኦሮሞ ነኝ ቢልና ኦሮምኛ ቋንቋንም ከኦሮሞ ነኝ ባዩም በበለጠ ጥንቅቅ አድርጎ ቢናገር ዘር ማንዘሩንና የትውልድ አካባቢውን ተናግሮ በተገቢው መንገድ እንዲጣራና ትክክለኛ ኦሮሞነቱ እንዲታወቅ ካልተደረገ በስተቀር ባህሉንና ቋንቋውን በማወቁ ብቻ ከታወጀው ጄኖሣይድ አይተርፍም፡፡ ለዚህ ነባራዊ እውነት የወለጋ አማራ-ኦሮሞዎች ኅያው ምሥክር ናቸው (ከዚህ ነጥብ አኳያ ትግሬዎች እንደሚሻሉ እኔ አውቃለሁ)፡፡ አማራ ግን አማርኛን ሁሉም ስለሚናገረው መልክህ ጠቆረ ቀላ፤ ቁመትህ ረዘመ አጠረ፣ ሰውነትህ ከሳ ወፈረ … አማራ ነኝ ካልክ አማራ ነህ - አበቃ፡፡ ሁሉም ነገ ጥርግርግ ብሎ ወደማይቀረው ቤቱ ሊጓዝ አሁንና ዛሬ አንተ አማራ ሆንክ አልሆንክ ለአማራ ጉዳዩ አይደለም፡፡ በሦስት ቀናት የሚፈርስ ሰውነት በነዚህ ምድራዊ ልዩነቶች ሲናከስና ሲበላላ ይታያችሁ፡፡ ይህም አንደኛው አማራን የሚያስጠቃ ነጥብ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስንሞት እኮ ቋንቋም በለው ሃይማኖት፣ ሀብት በለው ንብረት አብሮ አይሄድም፡፡ በምን ዓይነት ድንቁርና ውስጥ እንደምንኖር ሳስበው ይገርመኛል፡፡

 አምስተኛ - ራሱን በአማራነት የተቀበለ ዜጋ ሳይቀር ለሆዱ ተገዝቶ ከአማራ ጠላቶች ጋር በማበር አማራን ለማጥፋት ይሰማራል፡፡ ለዚህ ትልቁ ምሣሌ አቢይ አህመድ ራሱ ነው፡፡ ብዙ ሰው አቢይን በኦሮሞነት ነው የሚያውቀው፡፡ ግን ስህተት ነው፡፡ አቢይ በኦሮሞ ላይ ማሾፉ እንዳለ ሆኖ እናቱ ወሎዬና አባቱ አማራ ወይም ጋሞ እንደሆነ ይነገራል - ቅንጣት ኦሮሞነት የለበትም፡፡ ምንም እንኳን ተበርዘን ተከልሰን አንድኛችንን ከሌላኛችን በመልክና በቁመት መለየት ብንቸገርም የአቢይ መልክ ሲታይ ግን ይበልጥ የሚቀርበው አማራ ወደሚባሉት ኢትዮጵያውያን ነው ወይም ይመስለኛል፡፡ የሥልጣን ወንበሩን በምንም ዓይነት መንገድ ለድርድር የማያቀርበው አቢይ ግን የመጣበትን ነገድ ክዶ ኦሮሞ በመምሰል አማራን እያጠፋ ይገኛል፤ ነገ ኬንያ ውስጥ ሌላ ዕድል ቢሰጠው ኪኩዩ ነኝ ብሎ እነሉዎንና ካሊንጂን፣ እነካምባና ሉያን ከማጥፋት አይመለስም፡፡ የቆረበው በጥፋት ነውና፡፡ ይህ የሰንበት ጽንስ አቢይ አህመድ መላውን አማራ ሳይቀብር የአእምሮ ዕረፍት እንደማያገኝ ሁሉም የሚመለከተው ወገን ካልተረዳ አደጋው በ60 ሚሊዮን አማራ ብቻ ተወስኖ እንደማይቀር መታወቅ አለበት፡፡ ለማንኛውም አማራነትንና ኢትዮጵያዊነትን የካዱት እነተመስገን ጥሩነህና ዳንኤል ክብረትም ሆኑ ሌሎቹ በአእምሮ የቀነጨሩና ለሆዳቸው ሲሉ ለአጋንንቱ ዓለም ያደሩ በላዔሰቦች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ የፍርድ ቀናቸውም  በብርሃን ፍጥነት እየመጣ ነው፡፡ አፋብን ከዚህ አንጻር ብዙ ይጠበቅበታል፡፡ ራሱን ግን በደምብ ይፈትሽ!!

በላይኛው አካሄድ ከተጓዝኩ መቆሚያ የለኝምና ወደተነሳሁበት ላምራ፡፡

1. አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ከፍ ሲል በአጭሩ ያስቀመጥኩትን እውነታ በማጤን የትግል ሥልቱን በአስቸኳይ ይለውጥ፡፡ ለውጦም ትግሉን ከአማራ ክልል አሁኑኑ ያውጣ፡፡ አለበለዚያ በዚህ መልክ ከቀጠለ አማራ ክልል ይጠፋል፤ የትም ሥፍራ የሚገኝ አማራም ያልቃል፡፡ አሁን ራሱ አማራ አለ ማለት በማንችልበት ሁኔታ ተቋማቱና ኢኮኖሚው እየወደሙበት ነው፡፡ የተነሱበት ጠላቶች ዋና ዓላማ አማራን መጨረስ ብቻ ሳይሆን የአማራ ነው የተባለ ነገርን ሁሉ እንስሳትንና ዛፎችን ጭምር እየረመረሙ አማራን ባዶ ማስቀረት ነው፡፡ የፋኖ ትግል ከአማራ ክልል ካልወጣ የአማራ ችግር በቶሎ ዕልባት አያገኝም፡፡ አቢይ እንደሆነ የማይነጥፈውን የኢትዮጵያ ሰብኣዊና ቁሣዊ ሀብት ስለተቆጣጠረ የሚያሰማራው ሰውና ድሮን የሚገዛበት ገንዘብ እስኪያጥረው ድረስ ለመቆየት ማሰብ ጅልነት ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ይቀራል እንጂ አቢይ የሚያሰልፈው ወታደርና የሚተኩሰው ጥይት ወይም የጦር መሣሪያ ግብኣት ሊያጣ አይችልም፡፡ ሺህ ዓመት እዋጋለሁ የሚለው እዚህ ላይ እውነቱን ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝብ አታስጨርሱ፤ ሀብት ንብረት አታስወድሙ፤ በቶሎ ከአማራ ክልል ውጡ፡፡ አቢይን አደህይቼ አራት ኪሎን እይዛለሁ ማለት ቅዠት ነው፡፡

 አቢይ የሚቀናጣበትንና ጦርነት የሚያካሂደበትን ገንዘብ በፍጹም አያጣም፡፡ እደግመዋለሁ ከአማራ ክልል ቶሎ ውጡ!! አቢይ አማራን ለማጥፋት የሚተባበረው የውጭ ኃይልም እንደዚሁ እጅግ ብዙ ነው፡፡

2. ውስጣችሁን አጥሩ፡፡ “ሳል ይዞ ስርቆት፤ ቂም ይዞ ጸሎት” የለም፡፡ እርስ በርስዋ የተከፋፈለች መንግሥትም አትጸናም፡፡ ስለዚህ አንድ ሁኑ፡፡ ላልተጨበጠ ሥልጣንም አትራኮቱ፡፡ ገና ነው፡፡ ምኑም አልተያዘም፡፡ ለተረት ከአማራ በላይ ያለ አይመስለኝም - “የምትስቅ ሴትና የሚነቃነቅ ዛፍ” የምትሉት እናንተው ናችሁ፡፡ የምትስቅ ሴት ሳቀችልኝ ስትል እያሾፈችብህ ሊሆን ይችላልና ያኔ መጠንቀቅ ነው፡፡ የሚነቃነቅ ዛፍም ከአሁን አሁን ተነቀለልኝ ስትል ውሸቱን ነው - ሊያደክምህ፡፡ ይህን ምሣሌ ወደፋኖ ስናመጣው አንድ ሺህ ወታደር ተሰማርቶብህ ስምንት መቶውን ስትማርክና ሃሴት ስታደርግ በማግስቱ ሃምሣ ሺህ ወታደር ይለቀቅብሃል፤ ምክንያቱም አቢቹ የሰው ችግር የለበትማ! አንተ ጦሩን ማርከህ የምታቀምሰው ስታጣ፣ አንተ በየቀኑ መከላከያን እየገደልክ ጣትህ ሲዝል፣ አንተ የሞተን በመቅበር አቅልህን ስትስት … አቢዩ ግን የሀገሪቱ ተጨባጭ ችግሮች ምንም ሳይመስለው በብልጭልጭ ኮሪደር ዓለምን እያታለለ የሥልጣን ዕድሜውን ያራዝማል፡፡ ይህንንም ሂደት እንኳን አቢይና መንጋው ከፋኖ አመራሮች ውስጥም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የሚወዱት አይጠፉም፡፡ ጦርነቶች የድሃ ጠላቶች እንጂ የባለጌዎች መፈንጫ የሀብት ምንጭ ናቸው፡፡

ልጆቻቸውን በመቶ ሚሊዮኖች ወጪ እየዳሩና ውጭ ሀገር አንቀባርረው እያስተማሩ የሚገኙ ጄኔራሎችና ሚኒስትሮች ዕድሜያቸው በአሥራዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የሚገኙ የድሆች ልጆችን ግን ከትምህርት ቤት እያፈሱ ያለበቂ ሥልጠናና ያለበቂ ደሞዝ ወደሞት ቀጣና ያሰማራሉ፡፡ በሀገራችን የተንሰራፋው ይህን መሰሉ ግፍ ያሳብዳል፡፡ የኑሮ ውድነቱና መፈናቀሉ፣ ቤት ፈረሳውና ለከት የለሽ ቀረጥና ግብሩ፣ ሙስናውና ሌላ ሌላው መከራና ስቃይማ ሆድ ይፍጀው፡፡ ኢትዮጵያ እግዚአብሔርም የረሳት የምንዱባን ምድር ሆናለች፡፡ እንጸልይ፡፡ ምህላም እንያዝ፡፡

3. በሰበር ዜናዎች ተሰላችተናል፡፡ ሰበር ዜና ጥሩ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች እርግጥ ነው ይኖራሉ፡፡ ሲበዛ ግን ይሰለቻል፤ ማርም ሲበዛ ይመራል ይባላል አይደል? ሦስትና አራት ዓመት በዘለቀ ሁኔታ በጥቃቅን ሰበር ዜናዎች የሚሊዮኖችን ተስፋ ለማለምለም መሞከር እየቆዬ የሚያመጣው አሉታዊ ጎን ለጥገናም አዳጋች ነው፡፡ ከፋኖ ጎን ቆመው በወፌ ቆመች ወፌ ቆመች ትግሉን በተለያዩ መንገዶች ለመደገፍ የሚተጉ ሚዲያዎችን በዚህ አጋጣሚ ባመሰግን ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን በጎመን የተደለለ ሆድ አቀበት ላይ ቢለግም ጥፋቱ የማን እንደሆነ ይታወቃልና ከዚህ ዓይነቱ አካሄድ ቆጠብ ማለቱ አይከፋም፡፡ ለአብነት ያህል ቀደም ሲል የነበረው የሕዝብ ብሩኅ ተስፋና ጉጉት የተሞላበት ጥባቆት (expectation) አሁን ከሞላ ጎደል የለም፡፡ የሰነፉ እረኛ ታሪክ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ አላውቅም አሁንም በግልጽ እየተስተዋለ ነው - እውነቱን ተናግሮ እመሸበት ማደር መልካም ነውና አንወሻሽ፡፡ ሕዝቡ ሰፍ ብሎ ፋኖን የሚጠብቅበት ጊዜ ነበር፤ ነበር ስል አሁን የለም ማለቴ ግን አይደለም፡፡ የጠቀስኩት ሰነፉ እረኛ በጎቹን ቀበሮ በላብኝ እያለ በመጮህ መንደርተኛውን ሁሉ በውሸት ሲያሯሩጥ ቆይቶ በሦስተኛው ዙር የቀበሮ መንጋ መጥቶ በጎቹን ሲያረትምለትና ያነዜ ቢጮህ ማን ይድረስለት? እንደዚያ ነው የኛ ነገር እየሆነ ያለው፡፡ ፈረንጅ ምን ይላል? አንብብልኛ! “Hit the iron when it is hot.” ለዚህ አማርኛም አይሰንፍም - “ዱላ ይዞ እባብ…” ይለዋል፡፡ ዱላ ይዘሃል - አጠገብህ እባብ አለ፡፡ እስኪነድፍህ ምን አስጠበቀህ? በያዝከው ዱላ መቀጥቀጥ ነዋ! (እማሬያዊ ፍቺው ነው)

4. አምባገነናዊነት የራስን መቀበሪያ ጉድጓድ ከማቃረብ ውጪ ምንም እንደማይፈይድ ፋኖም ሆነ የፋኖ ቤተሰብ ይገንዘብ፡፡ ቀን ሰጠኝ ብሎ፣ አንድን ነገር የማድረግና ያለማድረግ ዕድል እጄ ላይ ወደቀ ብሎ ኢፍትኃዊና ኢሞራላዊ ነገር ማድረግ ይዋል ይደር እንጂ ወደባለቤቱ መዞሩ ገሃድ እውነት ነው፡፡ ለዚህ ብዙ ሩቅ ሳንሄድ እኔ እንኳን በቅርበት የማውቃቸውን ደርግንና ወያኔ/ኢሕአዴግን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ሕዝብን ልትንቅ፣ ድሃን ልትጠየፍ፣ ደካማን ልታንኳስስ ትችላለህ፡፡ የሥራህን የዞረ ድምር ግን ከታሪክና ከሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ተረዳ፡፡ ጉልበትና ኃይል ይከዳሉ፡፡ ዝናና ባለጸግነት እንደጉም ይተናሉ፤ እንደጤዛም ይረግፋሉ፡፡… ስለዚህ ፋኖ አንድ መግለጫ ከማውጣቱ በፊት በቡድን ሆኖ በደምብ ይምከርበት፡፡ አስፈላጊ ከሆነም ከሽማግሌዎችና ከጤናማ የሃይማኖት አባቶች ጋር ይወያይበት፡፡ ከአፍ ከወጣ አፋፍ ነው፡፡ አሸናፊው ፍቅርና መተሳሰብ እንጂ ኃይልና ጉልበት አይደለም፡፡ ቆም ብሎ የመከረ፣ ታገስ ብሎ ያማከረ ብዙ ወንዞችን ይሻገራል፤ ብዙ ተራሮችንም ይወጣል፡፡ ብልኅነት ጀብደኝነትን ይገራል፤ አስተዋይነት ዘመን ተሻጋሪ ስብዕናን ያላብሳል፡፡ ለዚህም ነው ጥበብን የተጎናጸፉ ዜጎች በትውልዶች መካከል በበጎ አርአያነት የሚታወሱት፡፡ ኔልሰን ማንዴልን አስብ፤ ማኅተመ ጋንዲንና ማዘር ተሬዛን አስታውስ፡፡

ዙሪያ ጥምጥም መሄዱን ጋብ ላድርገውና አንድ ሰሞነኛ አውነት ልናገር፡፡ በዚያን ሰሞን ፋኖ በሚዲያዎች ላይ ያወጣው መግለጫ በበኩሌ አላስደሰተኝም፡፡ እቤታቸው ጎመን ሰልችቷቸው ለወጥ ያለ ነገር ባገኝ ብለው ጓደኛቸው ቤትም ሲሄዱ ያው ጎመን ሲቀርብላቸው “በየት ዞረሽ ቀደምሽኝ” ያሉትን የአለቃ ገ/ሃናን ታሪክ ነው ያስታወሰኝ፡፡ ይህን ስል በግሌ መግለጫውን አልደገፍኩትም ለማለት አይደለም - በብዙ ጎኑ የምደግፈው ነው፡፡ ነገር ግን በድርጅታዊ አቋምነት በዚያ መልክ አይወጣም፡፡ ከአንድ አባል እንደግል አስተያየት ቢቀርብ ምንም ባልነበረ፡፡ ብዙ ውዝግብ ማስነሳቱንም ታዝቤያለሁ፡፡ ያኔ ታዲያ የሚመለከተው አካል ብቅ ብሎ ማብራራትና እንዳስፈላጊነቱም ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው በዝምታ ነው የታለፈው፡፡ የትኛው ማኅበረሰብ ነበር “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” ያለው? አዎ፣ ለኔ ብሎ የቆመ ስለኔ ፍላጎትና ድምጽ ግድ ካልሰጠው የኔ አይደለም ማለት ነው፡፡ አይደገም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በትኅትናው የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል - ራሱን ዝቅ አድርጎ፡፡ ሩቅ ሳልሄድ እንደ አስቴር በዳኔ አገላለጽ “ውድ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቢይ አህመድ እንኳን ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አቅርበው የለም አንዴ?” (ቀለደችብን አስቱ) ወይ ኢትዮጵያ፡፡ የማንሰማው እኮ ላይኖር ነው፡፡

5. ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ የትውልድ አካባቢ፣ ወዘተ. ምንም ማለት አይደሉም፡፡ ከሁሉም ሰው ወይም ሰውነት ይበልጣል፤ ቀጥሎም የአንዲት ሀገር ዜግነት፡፡ ስለሆነም እነዚህን ነገሮች ለባለቤቱ ማለትም ለግለሰቡ መተው እንጂ ተቋማዊ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፤ ፋኖ በመሣሪያና በሰው ብዛት ብቻ ሳይሆን በዕውቀትና በጥበብም ታላቅ ከፍታ ላይ መገኘት አለበት - በራሳቸውና በቅርብ ሰዎቻቸው ላይ ሳይቀር ትክክለኛ ፍርድ የሚሰጡት የነአፄ ምኒልክ፣ የነአፄ ቴዎድሮስ ዘር አይደለም እንዴ? አንድ ሰው ደረቱ ላይ ያሻውን ያህል መጠን ያለው መስቀል ቢያንጠለጥል፤ የጨረቃን ወይ የቀይ መስቀልን ምስል ትከሻው ላይ ቢያስቀምጥ፣ የሰው ቀርቶ የወፍ ቋንቋ ቢናገር መብቱ ነው - የሰውን መብት እስካልነካ ድረስ፡፡ በሌላ በኩል ግን የአንድ ተዋጊ ሠራዊት ሥነ ሥርዓትና ደምብ ሊኖረው ይገባልና በዚያን መሰሉ ሁኔታ በመተዳደሪያ ደምብና በተቀረጸ ህግና ሥርዓት መዳኘት አግባብ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ መሥሪያ ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ወዘተ. በዚህ መሠረት የሚገዙ ስለመሆናቸው እንረዳለንና አባላትም ለደንቦች ተገዢ መሆን እንደሚኖርባቸው ይገንዘቡ፤ ለተቋማዊ ህግና ደምብም ይገዙ፡፡ ፋኖ አሁን ባለበት ደረጃ እንደነዚህ ያሉ ልዩነቶችን በጥበብና በአስተዋይነት በሆደ ሰፊነትም ጭምር ማለፍ እንጂ ወደኃይል እርምጃ መሄድ ራሱን ይጎዳዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ ከአቢይ ልዋስና “መግደል መሸነፍ ነው” እያልኩ ነው፡፡

6. ፋኖ ጥይት ማባከን ያለበት ጠላቱ ላይ እንጂ በቅጣት መልክም እንበለው በብቀላ ወይም በሌላ መንገድ ወገኑ ላይ መሆን የለበትም፡፡ ግድያ እርኩሰት ነው፤ ግድያ ከሰው ማነስ ነው፤ ግድያ ከእንስሳዊነትም በታች ነው፡፡ ግድያ በምንም መልኩ አንድን ችግር ያባብስ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም፡፡ በጦር ግምባር የሚታየው መገዳደልም አማራጭ በመጥፋቱ እንጂ የሚመረጥ ሆኖ አይደለም፡፡ በግድያ የሚፈታ ችግር ያለ ይመስላል እንጂ እንደኔ በጭራሽ የለም፡ግድያ የጫጫን አእምሮ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ምሉዕ የምናደርግበት ሰይጣናዊ እርምጃ ነው፡፡ ስለዚህ ፋኖ የውስጥ ችግሩንና አለመግባባቱን በውይይትና በሽምግልና እንጂ በግንፍለተኝነት ወደጥይት ካመራ ትግሉ ከመጀመሩ ከሸፈ ማለት ነው - ለውስጣዊ ግድያዎች ነው እንዲህ እምቧዘራፍ የምለው፡፡

ኦህዲድን በህልምም በእውንም የምንገድለው እኮ እኛን ካልገደለ እንቅልፍ እንደማይወስደው ስለምናውቅ ነው፤ በስድስቱም አቅጣጫዎች ሌላ የተሻለ አማራጭ ብንፈልግ ምንም በማጣታችን ነው እነሱን ካልገደልን እኛ መኖር እንደማንችል አምነን ከኦሮሙማ ጋር የምንዋጋው፡፡ ስንሻው አምባቸውን መግደሉ ግን የቂልነት መጨረሻ ነው፡፡ ሥልጣን እንደሆነ ይደረስበታል፡፡ ዝናና ታዋቂነት እንደሆነ በራሱ ጊዜ እኛኑ ፈልጎ ይመጣል፡፡ ሳይቀመጡ እግርን መዘርጋትን ምን አመጣው? ለመፈንገል? ገና ምኑም ምኑም ሳይጨበጥ ለሥልጣን መራወጥና ለበላይነት መሟሟት በተለይ ሥልጡን ከሚባለው አማራ በጭራሽ አይጠበቅም፡፡ “ለዚህ ለዚህማ ምናለችኝ ጣቴ” ተብሎ እንዳይተረትብንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ከአይተ ሐጎስ አንዳችም ነገር ያልተማረው ኦቦ ገመቹ ምን እያደረገና በዚያም ምክንያት በጫካም በከተማም ምን እየደረሰበት እንደሆነ ምንም እንዳይገባው አቶ ደስታ ጆሮውን በጨርቅ ጠቅጥቆ ራሱን ካደነቆረ እግዜር ይሁነን ከማለት ውጪ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ወንበሪቱ ደግሞ ፈርዶባት አንዲት ብቻ ናት፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠረው የፋኖ ሠራዊት አባላትና በሺዎች የሚቆጠሩ የፋኖ አመራሮችን ልትሸከም ቀርቶ ልታስጠጋቸው አትችልም፡፡ ከዚህ አኳያ ራሳችንን ለትዝብት መዳረግ የለብንም፡፡ አለበለዚያማ ከጮርቃው አቢይ በምን ተሻልን? እናም ፋኖዎች ጊዜ አታባክኑ፤ ራሳችሁን አስተካክሉና በቶሎ ኑልን፤ እኔም ፍቼ ወይም ሸኖ ድረስ መጥቼ በደስታ እቀበላችኋለሁ፡፡ ለዛሬ ይብቃኝ፡፡ እንደሁኔታዎች አስገዳጅነት መመለሴ ግን አይቀርም፡፡

Ethiopian Semay 

Tuesday, February 3, 2026

በታላቅዋ ትግራዋይነት ድምፅ የሚጮህ የትግራይ “ናዚትራ” ርዕይዮተ ዓለም ‘የናዚ ጀርመን “ሊበንስራም” ቀጥተኛ የመስፋፋት ቅጂ ጌታቸው ረዳ (ETHIOPIAN SEMAY) 02/03/2026

 

በታላቅዋ ትግራዋይነት ድምፅ የሚጮህ የትግራይ “ናዚትራ” ርዕይዮተ ዓለም ‘የናዚ ጀርመን “ሊበንስራም” ቀጥተኛ የመስፋፋት ቅጂ

ጌታቸው ረዳ

(ETHIOPIAN SEMAY)

02/03/2026

በሙሶሎኒ እና በጀርመን ናዚ ርዕዮተ ዓለም የሚመራው የወያነ ትግራይ የመገንጠል ዕቅዱን ለማስፈጸም የቦታ ማስፋፋት ፍለጋ አያቆምም ብለን ጉንጫችን እሰኪደክም ድረስ ተናግረናል።እነሆ ሰሞኑን ካደፈጠበት በመንቀሳቀስ  አየሩን “መጠነኛ” የባሩድ ሽታ አውዶታል።

ይህ እያነከሰ ያለ ዝግምተኛ ግን አይቀሬ የመስፋፋት ጦርነት ሰሞኑን ወደ ጠለምት (ወልቃይት) እና ራያ አካባቢ የመንቀሳቀሱን ክስተት  ዋና የሚዲያዎች ትኩረት ሆኖ ስንብቷል። ለዚህ ሁሉ ለወያነ ሞቶ መነሳት ዋናው ተጠያቂ ደጋግሜ እንደጻፍኩት አፓርታይዱ የአብይ ኦሮሙማ ቡድን ነው።

አብይ አሕመድም ደጋግሞ ባንደበቱ እንደገለጸው “ወያኔ እንዲጠፋ ፍላጎት የለኝም” ሲል ነግሮናል። ስለዚህም «ነካ ለቀቅ» እያደረገ በሞተች አይጥ እንደምትጫወተው አይነት ድመት እየተጫወተ ያለው አብይ አሕመድ ለወያነ “ሞቶ መነሳት” ዋናው ተጠያቂው ሰው አብይ አሕመድ  ነው

  በምስል የቀረቡ ሁለቱ ካርታዎች የመጀመሪያው “የናዚትራ” መንጋዎች (የትግራይ ናዚ መንጋዎች) የፈጠሩት የትግራይ ነባር ካርታ ነው የሚሉት በ2014 ዓ.ም (በ2022) “የተፈበረከ” ከላይ የለጠፍኩት ካሁን በፊት ያልተጨመሩ በጠቀስኩት ዓ.ም. የተጨመሩ አዲስ “የዓባይ ትግራይ” ካርታ “አብርሃ ጂራ”“አብደራፍዕ”“ራዕሲ ደጌና” (ራስ ደጌና) ፥ “ዓዲ አርቃይ ፥ በነሱ አጠራር “ለማልሞ” (ለማሊሞ) ፥ “አለውሃ” ያጠቃለለ አዲሱ “የዓባይ ትግራይ” (የታላቅዋ ትግራይ) ካርታ ሲሆን (ምንጭ Ethiopian Semay)

ሁለተኛውና በክብ የተመለከተው የትግራይ አውራጃዎችና ወሰኖች በነባሩዋ ትግራይ

የነበሩ አውራጃዎችን እና ይዞታዎች ከመጽሐፈ አከሱም የተገኘ የካርታ ማስረጃ ነው (ምንጭ አቻምየለህ ታምሩ) ።

 ነባር የሚለው ካርታ በነባርነት የሚታወቀው “ትግራይ” በክብ “መልክኣምድርዋ” የተመለከተው በ8 አቅጣጫዎች/መዓዝኖች/ የተጎራበተና ወሰኖችዋንም ማመሰከሪያ የቀረበ “ነባር” የትግራይ ይዞታ ነው።

የትግራይ ተስፋፊ ናዚዎች የፈጠሩት መልክአምድር እና የቦታ ስሞች በነባሩ የትግራይ ካርታ ከሚለው ብምዕራቡም ሆነ ደቡባዊ ከሚሏቸው ቦታዎች  “አንዳቸውም” ለማስረጃ  አይገኙም።

ከፎቶዎች መጨረሻ ያለው የ1 ሚሊዮን ብር “ቸክ” ምንነት ልግለጽላችሁ።

በኮረና ወረርሺኝ ምክንያት በመላ አገሪቱ እንዳይደረግ የታገደው የምርጫ ሂደት በመጣስ ትግራይ ውስጥ በ2020 እሁድ ነሐሴ የተካሄደው የትግራይ ፖለቲካ  ምርጫ ተወዳዳሪዎች ቀርበው ለነበሩ  «ትግራይ ሃገር ሆና እንድትመሰረተት» የሚታገሉት 4ቱ ተገንጣይ ፓርቲዎች ፤ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባይቶና ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ፤ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳውት)፤ ውድብ ናፅነት ትግራይ (ውናት) በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ የትግራይ ነጋዴዎች ማሕበር 4 ቱ   ድርጅቶች «የግንጠላ አጀንዳ በማራመዳቸው» ለ 4 ቱ ሃገር ገንጣይ ድርጅቶች እያንዳንዱ 1,000,000.00 ብር እና የየራሳቸው አርማ ያሉባቸው የግድግዳ ሰዓቶች፤ በጠቅላላ 4,000,000.00 ብር በሽልማት ያበረከቱላቸው ቸክ ነው።

 የሽልማቱ አስረካቢ የምርጫው “ኮሚሽነር” ተደረጎ የተመረጠው ዶ/ር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም ነው።

የትግራይ ንግድ ማሕበረሰብ ያደረጉት ልክ የኢጣሊያ የንግድ ማህበረሰብን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ግዙፍ ኩባንያዎች እና የባንክ ባለሙያዎች እንዳደረጉት ለቤኒቶ ሙሶሎኒ እና ለፋሽስት ፓርቲያቸው በተለይም በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሥልጣን ላይ በወጡበት ወቅት እና አገዛዙ በተጠናከረበት ወቅት ወሳኝ የገንዘብ፣ የሎጂስቲክስና የፖለቲካ ድጋፍ ያደርጉ የነበሩት እነዚህ ማሕበረሰብ ክፍሎች ናቸው። ይህ ድጋፍ በአብዛኛው ያነሳሳው ምክንያት አክራሪ ብሔርተኝነት ያነሳሳው ድጋፍ ነው።

ለወደፊቱ በዚህ ድንኳን በተተከለበት የሽልማት ወቅት በተደረገው መስከረም አንድ ቀን (ቅዱስ ዮሐንስ ዕለት) የተከበረው ሃይማኖታዊ በዓል ላይ መላው የመቀሌ ሕዝብ በተሰበሰበበት ከመድረኩ ምን ይነገር እንደነበር ሌላ ቀን አቀርባለሁ።

አንድ ነገር ሳልጠቅስ የማላልፈው ግን ከተጠቀሱት ፓርቲዎች ውጭ የመገንጠል አጅንዳ የማያራምደው “ዓሲምባ” የተባለው ፓርቲ ሳይሸለም ቀርቷል (!!)።

ይህ ካልኩ ዘንድ ወደ ርዕሱ ልግባ።

የመስፋፋት ውትወታው ምክንያታቸው በተጠቀሱት ቦታዎች የሚኖሩ ትግሬዎች ብዛት ሰላላቸው (ማጆሪቲ) ሆኖው ሳይሆን እነዚህ ቦታዎች በሁለት መንገድ ጠቀሜታዎች ስላላቸው ነው።

 1ኛው- ትግራይ ወደ ሃገርነት ለመመስረት ባላቸው ዕቅድ “የተጠቀሱት የውልቃይትና የመተማ ወዘተ. . . ልክ እንደ ባሕር ወደብ” መሸጋገርያ በማድረግ ወደ ውጭ አገር መውጪያ በር ስለሚሆንላቸው፡

2ኛ- የተጠቀሱት አካባቢዎች ለም መሬት ስለሆኑ ለሚመሰርቱት “ሃገር” ሕዝባቸውን ለመመገብ ስለሚያስችላቸው ነው።

3ኛ- ትምክሕት የወጠረው ያልሆኑትን “ለመሆን” ያመጣው ተስፋፊ ባሕሪ ነው።

ይህንን የመስፋፋት አጀንዳ ቀጣይ ለማድረግና ሃገር ለመመስረት እንዲያመቻቸው፤ በማንነት ቀውስ የሚሰቃዩት፤ ያልሆኑትን “ለመሆን” ከሚከጅላቸው ፤ እንደ “ሰው ሳይሆን እንደ ጎሰኛ” የማስብ ባሕሪ ከፉኛ የተጠናውታቸው ናቸው።

  ይህንን በቀጣይነት የምናየው በሰው ልጅነት ማሰብ ያቆሙ ብዙ ትግራይ ምሁራን እና “ወያኔዎች የወለዱዋቸው አዲስ ውልደት የሆኑ የግንጠላ “መርህ” (አጀንዳ) የሚያራምዱ በርካታ የናዚትራ (የትግራይ ናዚ) ድርጅቶች ተፈጥረዋል።

ከነዚህ ውስጥ እላይ በጨረፍታ ስማቸው የጠቀስኳቸው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ ወ ሓ ት) ባይቶና ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ፤ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳውት)፤ ውድብ ናፅነት ትግራይ (ውናት)... እና 99.999% የትግራይ ምሁራን የዚህ የግንጠላ እና የመስፋፋት አጀንዳ አራማጆች ናቸው

እንደሚታወሰው በኮረና ቫይረስ ወረርሺን በሽታ ወቅት በነሓሴ 23/2020 ትግራይ ውስጥ “መረጻ ትግራይ” (የትግራይ ምርጫ) እናካሂዳለን ብለው ከተሳተፉት 6 ፓርቲዎች  ውስጥ ልፍስፍሱ «ዓረና ለዲሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ» (ዓረና) ፤ እና “ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ዓዴፓ)  (ተገንጣይ ስላልሆነ ከላይ አልጠቀስኩትም) በስተቀር ከላይ የተጠቀስኳቸው 4 ድርጅቶች ስለ ትግራይ ሃገርነት ፕሮግራም አዘጋጅተው እርስበርስ ሲከራከሩ “በትግራይ ቲቪ” አድምጠናቸዋል።

  ሁሉም የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች  ስለ መጪዋ ታላቅዋ ትግራይ የሚያሳይ እኔ እበልጥ እኔ ልመረጥ የትግራይ መልክአ-ምድር ከዚህ ጽሁፍ ጋር የተለጠፈው ምስል ነው።

ይህ “የናዚትራው” ቡድን መከራከሪያቸው “ትግሬ በተፈጥሮ ከአማራ ጋር አትዋሰንም” በማለት ያንን እውን ለማድረግ እንደ የርዕዮተ ዓለም አባቶቹ እንደ “ናዚ ጀርመኖች እና የጣሊያን ፋሺስቶች” እንደ ቡልኮ   ከዚህም ከዚያም ያጣቀሱዋቸው የተለያዩ የቦታ ስሞችን ቀለሞች ቀባብተው “ትግሬ በተፈጥሮ ከአማራ ጋር አትዋሰንም” የሚሉባቸው ሦስት ነጥቦች ከትግርኛ ወደ አማርኛ ልተርጉምላችሁ።

 እንዲህ ይላል፦

በተፈጥሮ ትግራይ ከአማራ ጋር አትዋሰንም። ከአማራ ጋር እንድትዋሰን ያደረጋት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ሦስት ናቸው።

1-ትግሬ ሆኖ በአማራ አስተሳሰብ የተጠመቀ

 2-አማራዎች እራሳቸው   ታላቅዋ አምሐራን ለመፍጠር ያቀዱት ስትራተጂ በመቀዳጀታቸው ምክንያት

3-   በተራ ቁጥር 1 የተጠቀሱ ትግሬዎች (የትግሬ ገበሬና የአማራ ገበሬ አንድ ናቸው፡ ሁሉም ብሄረሰቦች እኩል ናቸው፤ ሕዝብ ከሕዝብ አይለይም፤ሁሉም ሕዝቦች አንድ ናቸው…ወዘተ) የሚሉ “የአማራ አስተሳሰብ” ተሸክመው በተራ ቁጥር 2 ጋር ከተጠቀሱት ከአማራዎች ጋር ግምባር በመፍጠር ያጸደቁት ፀረ ትግሬ የሆነ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ማለትም “ሽጉጥ የምትመስል ምጢጢዋ ትግራይ በመፍጠር (ባይቶና የተባለው ፓርቲ እዚህ ላይ እነ መለስን እየወቀስ ነው) የጥንታዊ ነባርዋ የትግሬን ድምበሮች ቆራርሰው ታላቅዋን አምሓራ በመፍጠር ስለተቀዳጁ ነው።” ይላሉ።

ዚህ ሰነድ ግምባር ቀደም አቀንቃኝ ደግሞ የባይቶና ትግራይ መሪ የሆነው “ናዚትራዊው ቲኦሪሰት” እንደ ጀርመናዊው “Alfred Rosenberg” የሌሎች አጎራባች ሕዝብ መኖርያ ቦታዎችን በመውረር (ስፔስ ፍለጋ) (ቦታ ፍለጋ) መዋዠቅን ያማረው “ሕልመኛ ተስፋፊ” አማራን በመውቀስና በመዝለፍ የሚቀናው “ኪዳነ አመነ” ነው።

 “ቦታን ማስፋፋት ሁሉም የኛ” የሚለው ስግብግብ የናዚ ልክፍት የተጠናወታቸው ይትግራይ ምሁራን ከፈጠሩት አዲስ ካርታ እና የትግራይ ድምበርና ካርታ ለማሳየት የትግራይ “ነባር” ድምበሮች ስሞች እና አካባቢዎች ከስዕሉ ያቀረብኩት ከመጽሐፈ አከሱም የተገኘ መጽሐፍ በማስረጃ ስታነጻጽሩት “ወያነ ሰራሽ” ካርታ ውሃ አይቋጥርም

ትግሬዎች ለምን የመስፋፋት ፍላጎት እንዳደረባቸው በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ያነበበናቸው ሰነዶችን ስንመረምር ድርጊታቸው ከናዚ ፍልስፍና ጋር ተመሳሳይነት እናይባቸዋለን።

ይህንን እንመልከት።

ሂትለር በ1933 ልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ Lebensraum (ሊበንስራም) በተባለው መርሃግብር የአካባቢ ጎረቤት አገሮችን መሬት በማግበስበስ ላይ ያተኮረ የናዚ ዕቅድ ሲሆን፡ በዚህ መርሃ ግብር “ቦታን የመፈለግና የመውረር ዘመቻ” ብዙ ስራ ተሰርቷል።

መርሃ ግብሩ በአንደኛ የለም ጦርነት(1914–1918) መጀመሪያ ላይ ሌበንስራም የኢምፔሪያል ጀርመን የጂኦፖለቲካ (የቀጠና አሰላለፈና የፖለቲካ-ግንዛቤ ክንውን) ግብ ቀዳሚ ቢሆንም ፤ መሬትን (ስፔስ) የማስፋፋት ዕቅድ እጅግ የተደገፈው ደግሞ (ኤን ኤስ ዲ ኤ ፒ- National Socialist German Workers' Party -) ፓርቲ እና የጀርመን ናዚ ፓርቲ እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ ተግባራዊ ሆኖ ሲገፉበት ነበር።

አዶልፍ ሂትለር ወደ ልጣን ከመምጣቱ በፊት አዳዲስ የማስፈሪያ ቦታዎችን በቅኝ/ በጉልበት/ የማስፋፋት መርሃ-ግብሩን የጀርመን ግዛት ወደ መካከለኛው እና ምስራቅ አውሮፓ እንዲስፋፋ የሊበንስራም ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ (1914–1918) መንቀሳቀሱ ይታወሳል።

 የናዚ አጠቃላይ ‘ማስተር ፕላኑ’ በመሠረታዊ ሥርዓቱ ላይ ሌሎችን ሕዝቦች ከቦታቸው በማስለቀቅ (ወያኔ ለ27 አመት ሲያደርግ እንደነበረውና አሁንም በከፋ መልኩ ለማስፋፋት በወያኔዎቹ “ከላይ በጠቀስኳቸው” ድርጅቶች እና በመሳሰሉት «የትግራይ ፋሺስትና ናዚ ምሁራን»  በመሪ ድርጅታቸው በ’ህወሓት’ እና ባዘጋጃቸው ታጣቂዎቹ በኩል እንደታቀደው ሁሉ ጦርነት ከፍተው ለሃገረ ትግራይ ህልውናችን ያስፈልገናል ብለው ባሰመርዋቸው አጎራባች ድምበሮች የጎረቤት ነባር ኗሪዎችን ከቦታቸው በማስለቀቅጀርመኖች እንዳደረጉት ሁሉ ትግሬዎችም ያንን ተግባራዊ አድርገዋል

ትግሬዎች በወልቃይትና በመሳሰሉ የወሎ ግዛቶች ወርረው ነባሩን ሕዝብ አማርኛ እንዳይናገር በማድረግ አብዛኛዎቹንም በመግደልና በማስወጣት፤ሴቶችንም በትግሬዎች እየታመጹ ትግሬዎች እንዲባዙ በማድረግ እና አማራ በሚበሉት መሬቶችም “ሴቶች የአማራ ትውልዶች እንዳይወልዱ በወሊድ መቆጣጠሪያ መርዞችን ወደ ማህጸናቸው በማስገባትና በመውጋትና እንዲሁም በዘር ፍጅት እና በመሳሰሉ የአማራ ዘር በሚሊዮኖች አንደተሰወረ/እንደቀነሰ (በወያነ ፓርላማም ጭምር ባመነው ዘገባ) ብዙ ሺሕ ታጋዮቻቸው በሃይል በተነጠቁ ለም መሬቶችና ከተሞች አስፍረው እንዲበለጽጉ እንዳደረጉት ሁሉ ጀርመንም “በሊበንስራም አቅድ” የጀርመን ዝርያዎች (ኖርዲኮች) ያለምንም ስጋት በምቾት ለመኖርና ለመመገብ ለራሳቸው የእርሻ ትርፍ እንዲያገኙ ሞክሯል።

ይህ የሂትለር ስልታዊ ስግብግነት መርሃግብር የአለም የበላይነትን ለመቀዳጀት “ቦታዎችን/ስፔስ” በማግበስበስ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በተያዙ ቦታዎች “አሃዳዊ ብቸኛ የዘር ወጥነትየላቀ የጀርመን ማህበረሰብ ለማሳደግ ሲባል “በሊበንስራም ዘመቻ የተነጠቁ አገሮችና ጎረቤቶች ውስጥ” ፣ “አሪያን ያልሆኑ ዘሮች” የጀርመን ማሕበረሰብ አካል እንደሆኑ የሚታሰቡ ቦታዎችን በመለየት የአርያን ዝርያ ያልሆኑትን እየለቀሙ ማባረር ወይም የአካል የንብረት ውድመት እንዲደርሳበቸው በማድረግ (ወያኔዎች በጉልበት በያዝዋቸው ቦታዎች እንዳደረጉት) በዓለም ውስጥ racially superior society የአርያን ዝርያዎች ልቀው ብብዛትና በሃያልነት እንዲወጡ የሚረዳ የናዚዎችና የፋሺሰት ጣሊያኖች “የቦታ ፍለጋና መስፋፋት” መርሃ ግብር ታቅዶ በተግባር እንደዋለ ታሪክ ይነግረናል።

ሲጠቃለል የመርሃግብሩ ሁለት ገጽታዎች የሚከተሉት ናቸው።

(1)    ናዚዎች በሚይዙት ቦታዎች ሁሉ ትላልቅ የግብርና እና ኢንዳስትረያል ንጠረ ዕቃዎችን ለጀርመን ህዝብ ፍጆታ ማዋልናዚዎችና/ፋሺስቶች በሚይዝዋቸው ቦታዎች የዘር ማጽዳት በማድረግ የተደላደለ ኑሮ ለአርያን ዘሮች መፍጠር።

(2) የሊበንስራም ሁለተኛው መርሃ ግብር ደግሞ የሌሎች ሕዝቦችን ቦታዎች “የኛ ነበሩ” በሚል ትርክት በወረራ ቦታዎችን በመያዝ በዛው ቦታ የነበሩ “ነባር ተወላጅ ሕዝቦችን” በደምና (በዘራቸው) አርያን ያልሆኑትን እየለቀሙ ማጽዳት ወይንም ከቦታው በማባረር፡ በምትካቸው በሚያዙ ቦታዎች ሁሉ አርያኖችን እንዲባዙ በማድረግ የአርያን ዘር እንዲባዙና ሃያልነታቸው በዓለም መጥቆ እንዲወጣ ማድርግ ላይ የተመሰረተ ዕቅድ ነበር።

   

(3) በዚያም አስታክኮ ናዚዎች Nordicism (ኖርዲክ/ጀርመኒክ) በቆሸሹ ዘሮች እየተዋጠ ከምድረገጽ እየጠፋ ያለ የዓለም ምርጥ ዘር በመጥፋት ያለ ነው የሚሉት ናዚዎች እና ትግሬዎች “በጉርዲ” (የትግራይ ዘፋኞችና ገጣሚዎች ቃል) በቆሻሻ ዘሮች በተለይ ከአማራ ጋር የተዳቀሉ ትግሬዎች “ትግራዋይነትን” እያቆሸሱት ስለሆኑ ከጉርዲ (ከገለባ) የጸዳ ትግራዋይነት “የተባለ “አዲስ የትግራይ ሃይማኖት በመፍጠር እንደሚንቀሳቀሱት ሁሉ፥

(ፋኖ ስጥም ተፈራ ማሞ የተባለው “የብአዴን ባህላዊ ጀነራል” ዛሬ “የአማራ ፋኖ ታጣቂ አዋጊ የሆነው «ኢትዮያዊያኖች የአማራ ስም ሰለያዙ ስማችንን ስላቆሸሹብን ለባለቤቶቹ ለኛ ለንጹሃን ለአማራዎች መልሰው በራሳቸው ስም ይጠቀሙብሎ እንዳለው ማለት ነው። በዚህ ጉዳይ ራሱ የቻለ ርዕስ እያዘጋጀሁ ነው በሚቀጥለው ጊዜ እመለስበታለሁ)።

እነሆ የትግራይ ምሁራን እና በርካታ ድርጅቶቻቸው የማስፋፋት መዝሙር በማስተጋባት ለብዙ አመታት የሕዝብ እልቂት ምክንያት እንደሆኑት ሁሉ ከዚያ ሳይማሩ ሰሞኑን ደግሞ አድፍጦ የነበረው ወያነ ወደ እሚያልማቸው ቦታዎች እየተንቀሳቀሰ ነው።

ጥጋብ አላስቀምጥ በሎት ራሱ በለኮሰው ጦርነት ጫካ እያለ ጀምሮ በጉልበት የያዛቸው የነ ጠለምት እና የመሳሰሉ ወደ በባለቤቶቹ በመግባታቸው ያንን እንደገና ለማስመለስ ጦሩን ወደ ተጠቀሱት ቦታዎች (ጠለምት....) በማንቀሳቀስ ቶክስ ክፍቶ አልሆን ሲለው ተመልሶ ወደ ትግራይ አፈግፍጓል ይባላል።

ጫካ እያለ የዘር ማጽዳትና ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ይዟቸው የነበሩት ቦታዎች ተነጥቅኩ በማለት ተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራ እያደረገ ያለው ምክንያት ያንን ኢትዮያን የማዳከመና የማፍረስ «የታላቅዋ ሃገረ ትግራይ ምስረታ ዕቅዱ» እውን ለማድረግ ነው።

 አስገራሚ ትረካቸው ከነጭራሹ “ጎጃም ጎንደር ሽዋ እና ወሎ እንጂ “አማራ” የሚባል ዘር የለም “አማራ” ብሎ የፈጠረው “ወያኔ’ እንጂ አማራ የሚባል ሥፍራ/ማሕበረሰብ በታሪክ ተሰምቶ አይታወቅም፡ ‘አማራ” የተፈጠረው በ27 አመት ውስጥ ነው፤ ያውም “በወያኔ ዘመን ይላሉ። ስለዚህ አመራ ከትግሬ ጋር ተካልሎ አያውቅም የምንለው ለዚህ ነው ይላሉ።

ይህ የሚያሳየን ምንድነው? ስንል ከላይ የጠቀስኩት የናዚው ሊሂቅ “Alfred Rosenberg” እንደሚለው አይሁዶች ሰው ሳይሆኑ ከአርያን/ ከኖርዲክ ሕዝብ እኩል እንደ ሰው ወይንም እንደ ሕዝብ መጠራት አይቻልም” ባይ ሲሆን እንደ ጀረመኖቹ ከኖርዲክ ዝርያ ውጭ ወይንም እንደ ተስፋፊዎችና ተገጣዮቹ ትርክት «ከትግራይ ውጭ ያለው ሕዝብ እኩል እንደ ትግራይ “ሰው” ሰው ነው ማለት አይቻልም” ይላሉ።

እነዚህን ሰው ያልሆኑትን ሰዎች ለማንበርከክ “Total alienation እና “Total humiliation” ማድረግ ነው። የላሉ ። ይህንን ከሚሉት የትግራይ ናዚ ድርጀት መሪዎቹ አንዱ የሆነው ባይቶና የተባለው ተስፋፊና ተገንጣይ ቡድን መሪ «ኪዳነ አመነ እና ድርጀቱ» ነው።

የትግራይ ተስፋፊ ምሑራን እና ድርጅቶቻቸው ይህ አዲስ ካርታቸው እውን ለማድረግ ያቀዱት መንገድም “በጦርነት” ነው። ይህንን ለማከናወን በሱዳን ውስጥ እያሰለጠኑዋቸው ያሉት ከ3 አመት በፊት የከፈቱት ጦርነት ወልቃይት ውስጥ ጀነሳይድ ፈጽሞ ወደ ሱዳን የሸሸው «ሳምረ» የተባለው የትግራይ-«ኢንተርሃሙውዌ»-ቡድን» ከሱዳን ድምበር እያሾለከ በማስገባት ከውስጥም “ቲ ዲ ኤ ፍ” በሚል አዲስ ሰም የሚጠራው “የህ ወ ሓ ት” ታጣቂ ጦር በማዘጋጀት ነው።

ይህ “ጦርነት” ደግሞ የሚያየው እንደ ቦታ ማስገኚያ እና ከተሰመሩ አዲስ ካርታዎችና ድመበሮች “አማራን የማጽጂያ/የማጥፊያ” ምቹ መንገድ መሆኑን የትግራይ ተስፋፊ ምሑራን እና ድርጅቶቻቸው ልሳኖች የሚስተጋባ ነው

በመጨረጻም ይህንን ልበልና ልደምድም፡

ናዚ ከተሸነፈ በኋላ “Alfred Rosenberg ጠረጴዛ ሲፈተሽ በጠረጴዛው ውስጥ የተገኘው የእጅ ጽሑፉ እንህ ይላል።

 I welcome the war. It is necessary to exterminate directly all those racially inferior germs of Jewry and its bastards as a final solution to the problem unsolved for ever two thousand years …”

 “(Alfred Rosenberg- by Fritz Nova P-120 published 1986)

 ትርጉም

“ጦርነቱን በደስታ እቀበላለሁ። ለሁለት ሺህ ዓመታት ላልተፈታው ችግር የመጨረሻ መፍትሄ ሆኖ እነዚያን በዘር ዝቅተኛ የሆኑ የአይሁድ “ጀርሞችን/ትል/” እና መናኛ ፍጡራን ሁሉ በቀጥታ ለማጥፋት ጦርነት አስፈላጊነት ነው…።” (Alfred Rosenberg- ደራሲ Fritz Nova ገጽ-120 ሕትመት 1986) ይላል የተገኘው ጽሑፍ።

እንግዲህ የትግራይ ነባር ደቡባዊና ምዕራባዊ የትግራይ መሬትና ድምበር ብሎ የፈጠረው ካርታ እውን ለማድረግና አማራን ለማጥፋት ጦርነት አስፈላጊነቱን በግሃድ ሲናገሩና ሲጽፉ እያየን ነው።ይህንንም እውን ለማድረግ

“ድል ለታሪካዊና ሕጋዊ መሬታችን!”

“ድል ለታላቅዋ ትግራይ!”

የሚለው  ድምፅ የትግራይ “ናዚዎች” ርዕይዮተ ዓለም ‘የናዚ ጀርመን “ሊበንስራም” ቀጥተኛ የመስፋፋት ቅጂ ነው።

ሰላም እንሰንብት  

ጌታቸው ረዳ (ETHIOPIAN SEMAY)