Thursday, July 19, 2018

አክራሪ ብሄረተኛነት ምንድነው? ተከታዮቹ በሆኑት የአንድ ነገድ ተወላጆችስ ላይ የሚያስከትለው ስነልቦናዊ ለውጥ ምን ይመስላል? በዶክተር አሰፋ ነጋሽ --› አምስተርዳም (ሆላንድ) – ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ. ም.posted at Ethiopian Semay

አክራሪ ብሄረተኛነት ምንድነውተከታዮቹ በሆኑት የአንድ ነገድ ተወላጆችስ ላይ የሚያስከትለው ስነልቦናዊ ለውጥ ምን ይመስላል?

በዶክተር አሰፋ ነጋሽ --› አምስተርዳም (ሆላንድ) – ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ. ም.
የኢሜይል አድራሻ ---› Debesso@gmail.com
posted at Ethiopian Semay

አክራሪ ብሄረተኛነት በሰዎች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ - የፕሮፌሰር ገብሩ ጽሁፍ እንደማሳያ
ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በ1932 ዓ. ም. አክሱም ውስጥ የተወለዱ ሲሆን በንጉሱ ዘመን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኑቨርሲቲ በሚባለው ዩኑቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተምረው በ1956 ዓ. ም. (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ከጨረሱ በኋላ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኑቨርሲቲ ቅርንጫፍ በነበረው የጎንደር የጤና ጥበቃ ኮሌጅ፤ እንደዚሁም አዲስ አበባ በሚገኘውም የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኑቨርሲቲም በታሪክ መምህርነት ያገለገሉ የ78 ዓመት እድሜ ባለጸጋ ናቸው። እኚህ ሰው ከአብዩቱ በፊት ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ከተላኩ በኋላ በ1969 ዓ. ም በኢትዮጵያ አቆጣጠር በዐጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በባሌ፤ በትግራይና በጎጃም ስለተደረጉት የገበሬዎች ዐመጾች[1] ታሪክ ላይ ለዶክትሬት ዲግሪ ያበቃቸውን ጥናት ጽፈው ጨርሰው ያበረከቱ ሰው ናቸው። እኔ ከእኚህ ሰውዬ የጽሁፍ ስራዎች ጋር ለመጀመሪያ የተዋወቅሁት ከዛሬ ሰላሳ አምስት በፊት ይህንን የመመረቂያ ጽሁፉቸውን እዚህ በምኖርበት ሆላንድ ሀገር ውስጥ በሚገኘው የLeiden University የአፍሪካ ጥናት ማእከል መጽሃፍት ቤት ውስጥ አግኝቼ ባነበብኩበት ወቅት ነው። እኚህ ሰው አሜሪካን ሀገር ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በዚያው ሀገር ከሰላሳ ዓመታት ያላነስ በታሪክ መመህርነት አገልግለዋል። ከዚያም ወያኔ ሥልጣን ላይ ከወጣ በሁላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የኢትዮጵያ የጥናት ኢንስትቲዩት ዳይሬክተር ሆኖው ተሹመው አገልግዋል። እኚህ ሰው በሥልጣን ላይ ላለው መንግስት ባለቸው በጎ አመለካከትና በትግሬነታቸው ባገኙት ሰፊ እድል የመከላከያ ሚኒስቴር መረጃዎችን በስፋት ለመመርመር እድል ተሰጥቶአቸው ነበር። በዚህም እድል ተጠቅመው ኢትዮጵያ ከሶማሌያ ጋር ስላደረገቸውና በሰሜን ኢትዮጵያ ስለተደረጉት ጦርነቶች 437 ገጾች ያሉት ዳጎስ ያለ መጽሃፍ[2] ከዛሬ ዘጠኝ ዓመታት በፊት ጽፈው በአሜሪካን ሀገር አሳትመዋል። እኚህ የታሪክ ምሁር በዚያ በጻፉት መጽሃፍ ውስጥ በእኔ እይታ አስገራሚ የምላቸውንና የእሳቸውን የታሪክ አዋቂነት እንደዚሁም እንደ አንድ ታሪክ ጸሃፊ ለእውነት ሊያሳዩና ሊሰጡ የሚገባቸውን ዋጋና ክብር ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ጽሁፎቻቸውን ከዚህ በታች እየጠቀስኩኝ ለአንባቢ አስተዋውቃለሁኝ። መጽሃፉ በእንግሊዘኛ የተጻፈ ስለሆነ እኔው እራሴ የጠቀስኩትን የእንግሊዘኛውን ጽሁፍ ወደ አማርኛ ተርጉሜዋለሁኝ። ጽሁፋቸውን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ ስተረጉም አዛብቼ ተርጉሜውም ከሆነ አንባቢን እንዳላሳስት ብዬ የእንግሊዘኛውንም ጽሁፍ በአባሪነት አካትቼያለሁኝ።

፩ - ፕሮፌሰር ገብሩ በመጽሃፋቸው ውስጥ አሁን በወያኔ ዘመን ባለው ጦር ውስጥ ስላለው የወታደራዊ መኮንኖች የነገድ (ethnic composition of military officer corps) ስብጥር ምን አሉ?

እኚህ ሰው አሁን በኢትዮጵያ በወያኔ መንግስት አገዛዝ ዘመን በሀገራችን ስላለው የብሄራዊ ጦር ዲሞክራሲያዊ ስብጥር “The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa” በሚለውና እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2009 ዓ. ም. ባሳተሙት መጽሃፋቸው ውስጥ የሚከተለውን ጽፈዋል።

የአዲሱ ጦር መሪዎች ስብጥር የህብረተሰቡን ብዝሃነት እንዲያንጸባርቅ ተደርጎ ተዋቅሯል። ምንም እንኳን አዲሱ ጦር ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተዋቀረ ቢሆንም ቅሉ በይበልጥ ወገንተኛና ከፋፋይ ለሆነ የፓለቲካ ታማኝነት የተጋለጠ ነው “The make-up of the officer corps of the new army has been diversified to reflect society. Although the new army is more democratically constituted, it may be more susceptible to sectarian and divisive politics and allegiances[3]”.
ፕሮፌሰሩ የአዲሱ ጦር መሪዎች ስብጥር የህብረተሰቡን ብዝሃነት እንዲያንጸባርቅ ተደርጎ ተዋቅሯል ካሉን በኋላ ዘወር ብለው ደግሞ “በይበልጥ ወገንተኛና ከፋፋይ ለሆነ የፓለቲካ ታማኝነት የተጋለጠ ነው” ይሉናል። ይህ መቼም እርስ በእርሱ የሚቃረን ሃሳብ ነው። ምክንያቱም በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተዋቀረና ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ጦር ለወገንተኛነትም ሆነ ለከፋፋይ ፓለቲካ የሚጋለጥበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም። ፕሮፌሰሩ ምሁራዊ ቅንነት ቢኖራቸው ኖሮ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተዋቅሮአል የሚሉት ጦር ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልክ ለወገንተኛነትም ሆነ ከፋፋይ ለሆነ ፓለቲካ የሚጋለጥበትን ምክንያት ምንድነው ብለው ይጠይቁ ነበር። ነገር ግን ራሳቸውን ይህን ጥያቄ ቢጠይቁ ኖሮ የሚያገኙት መልስ የሚያስደስታቸው አይሆንም። ይህ እሳቸው የህብረሰብን ብዝሃነት በሚያንጸባርቅ መልክ ተዋቀረ የሚሉት ጦር የትግሬዎች የነገድ ፓለቲካ በወለደው የአድሎ ሥርዓት ስለተበተበ አመራሩ በአብዛኛው ከአናሳው የትግሬ ነገድ የወጣ ነው። ስለሆነም የአሁኑ የጦሩ አደረጃጀት የሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶችን ተወላጆች ከከፍተኛ የሥልጣንና የኃላፊነት ቦታዎች የሚያገል ነው። በዚህም ምክንያት ነው ጦሩ ለወገንተኛነት ስሜትና ከፋፋይ ለሆነ የፓለቲካ ታማኝነት የተጋለጠው።

 እንግዲህ ከላይ የጠቀስኩት የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ጽሁፍ አንድ ሰው በአክራሪ ብሄረተኛነት ስሜት አይምሮው ሲበከል እንዴት አድርጎ የሰባት ዓመት ልጅ አይቶ ሊገነዘብ የሚችለውን እውነታ እንደሚክድ ያሳየናል። ፕሮፌሰሩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተዋቀረ በሚሉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጦር ውስጥ በከፍተኛ እርከን ላይ ያሉት ከዘጠና በመቶ በላይ (>90%) አዛዦች ትግራይ ከሚባልና በቁጥር ስድስት በመቶ (6%) ብቻ የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚወክል አናሳ ነገድ የወጣ ነው። በእኔ ትውልድ አድሃሪ ተብሎ በተወገዘው የንጉሰ ነገስታዊ መንግስት ስር ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በወያኔ አገዛዝ ውስጥ ያየነውን ዓይነት ወደ አንድ ነገድ ያጋደለ የወታደራዊ መኮንኖች ስብጥር አልነበረም። በእውቀት-አልባነቱና ስሜታዊነት እንጂ በጥልቀት እውቀትን ፈልፍሎ፤ መረጃን ተንተርሶ መከራከር በማያውቀው “ ትውልድ” በሚባለው የግራ ትውልድ (የእኔ ትውልድካለ እውቀትና በስህተት “ፋሽስት” ተብሎ የተፈረጀው የደርግ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት ዘመን የአንድ ነገድ ተወላጆች የሆኑ መኮንኖች 90% በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ጦር አመራር የያዙበት ሁኔታ አልነበረም። ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ግን ይህን ሁሉ ሀገር የሚያውቀውን፤ ጸሃይ የሞቀውን እውነታ ክደው የወያኔ ትግሬዎችን የዘረኛነት ፓሊሲ በብእራቸው አፋልሰዋል፤ በአደባባይም ዋሽተዋል።

 - ፕሮፌሰር ገብሩ ሀገሮችን ስላፈረሰው በነገድ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት ምን አሉ

የታሪክ ፕሮፌሰሩ በዓለም ውስጥ በሀገር አፍራሽነቱ የታወቀውን በነገድ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ግን የተለየ ውጤት እንደሚኖረውና ሀገር ሊያፈርስ እንደማይችል ሳያፍሩና ህሊናቸውን ሳይሰቀጥጠው በሚከተለው መንገድ ሊያስረዱን ሞክረዋል።
የኢትዮጵያ በነገድ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት አዲስና ማራኪ የሆነ የፓለቲካ ሙከራ ሲሆን በውስጡ አደጋና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችንም የያዘ ነው። ነገር ግን ይህ (በነገድ ላይ የተመሰረተፌዴራሊዝም ችግር ባለመፍጠር በታሪክ የተለየ ሊሆን ይችላል   

“The Ethiopian ethnic-based federalist system is a novel and fascinating political experiment laden with potential problems, but one that may prove to be the historical exception[4]”.

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ከትግራይ በታች ባሉት የኢትዮጵያ ክልሎች የተከሰቱት ደም-አፋሳሽ ግጭቶች፤ የብዙ ሚሊዮን ህዝብ መፈናቀል፤ በራሱ ሀገር ውስጥ ስደተኛ መሆን ወዘተ ለፕሮፌሰር ገብሩ አልታዩአቸውም። ሌላው ቀርቶ ይህ የአንተ ክልል ስላልሆነ ክልሌን ለቀህ ውጣ በሚል አስተሳሰብ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኦሮሞዎችና ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች ከቀድሞው የሀረርጌ ክፍለ ሀገር የተፈናቀሉበትን፤ አንድ ሚሊዮን ያህል የጌዴኦና የጉጂ ኦሮሞዎች ከቀድሞው የሲዳሞ ክፍለ ሀገር የተፈናቀሉበትን፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች በወልቃይት፤ ጸገዴ፤ መተከል፤ ቤኒሻንጉል ወዘተ የተፈጁበትን፤ በጥቂት ቀናት ውስጥ 78,000 የአማራ ተወላጆች ከጉራ ፈርዳና ደቡብ ኢትዮጵያ ቤት ንብረታቸው እየተዘረፈና እየተቃጠለ የተባረሩበት -ሰብዓዊ ድርጊት ለእኚህ የትግራይ ምሁር የጥፋት ሥራ ሆኖ አልታያቸውም ፕሮፌሰር ገብሩ ቋንቋና ባህልን መሰረት አድርጎ ህዝብን እያፋጀ ያለውን፤ ልዩነትና ጥላቻን የሚያራግበውን፤ በኢትዮጵያ ነገዶች መካከል በጥርጣሬ አይን መተያየትን ወዘተ ያስፋፋውንና ከትግራይ በታች ላሉ ለብዙ ሚሊዮን ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን መፈናቀልና ሞት ምክንያት የሆነውን መርዘኛ ሥርዓት በበጎነት መታየት አለበት ብለው በሚከተለው አይነት ተከራክረዋል።

 - የፌዴራል ህገመንግስት ፋይዳ፤ ዲሞክራሲያዊ ማዕቀፍን ስለመፍጠር፤ የራስን ጉዳይ ስለመምራት።

1987 የፌዴራል ህገ መንግስት የኢትዮጵያን አስቸጋሪ ብሄራዊ ክፍፍሎች ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፤ የሚያስችል ዲሞክራሲያዊ ማዕቀፍን ለመፍጠር የተደረገውን ቁርጠኛ ጥረት ይወክላል። ኢህአዴግ በመጨረሻ ላይ የሀገሪቱ የተለያዩ ነገዶች የየራሳቸውን ጉዳዮች በራሳቸው ለመምራት ቋንቋቸውን፤ ባህላቸውን እና ልማዶቻቸውን ለማዳበር የሚያስችላቸውን አዲስ አሰራር (ዘዴበመተግበሩ ሊመሰገን ይገባል ከዚህ ቀደም የተጨቆኑና የተገለሉ ህዝቦች በመቶ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሳቸው እጣ-ፈንታ ወሳኞች/ዳኞች ሆነዋል 

“The federal constitution of 1995 represented the most determined effort to create a democratic framework in which Ethiopia’s intractable national cleavages find a permanent solution. It is to the credit of the EPRDF that if finally implemented an innovative structure that allows the country’s ethnic components sufficient power to manage their own affairs and to develop their languages, cultures and individual customs. Formerly oppressed and marginalized peoples have, for the first time in a hundred years, become arbiters of their own destiny[5]”.

በእርግጥ ነው ፕሮፌሰር ገብሩ ከላይ እንደ ገለጹት የተለያዩ ነገዶች ቋንቋቸውን፤ ባህላቸውንና ልማዶቻቸውን ለማዳበር ችለዋል። የተለያዩ ነገዶች ቋንቋቸውንም ሆነ ባህላቸውን ለማዳበር መቻላቸው በጎ ነገር ነው። ነገር ግን የተለያዩ ነገዶች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ከሌሎች ጋር ድልድይ መስሪያ ሳይሆን የልዩነት መገንቢያም አድረገውታል። የየክልላቸውን ባንዲራ እያውለበለቡ በባዶ ሆዳቸው መጨፈር ችለዋል። ነገር ግን እነዚህ የተለያዩ ነገዶች የሀገራቸው ባለቤት አልሆኑም። እነዚህ ነገዶች በዋናነት የእነዚህን ፓለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ህይታቸውን በሚወስኑት ጉዳዮች ላይ ድምጽ የላቸውም። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንደ ቅኝ ገዢዎች የሞግዚት አስተዳደር ሾሞ ከላይ ሆኖ በህይወታቸው ላይ የሚወስነው ህወሃት እንጂ የእያንዳንዱ ነገድ እውነተኛ ተወካዮች አይደሉም።

እስቲ ይህንን በምሳሌ ላስረዳ። የአማራ ክልል በሚባለው ሰፊ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ብአዴን የሚባል የህወሃት ተወካይ በአማራ ህዝብ ሥም ይህንን ክልል ያስተዳድራል። በብአዴን ውስጥ ከላይ እስከ ታች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየመው ደመቀ መኮንን ጀምሮ እታች ባለው የብአዴን እርከኖች ላይ የተሰገሰጉት የህወሃት ተላላኪዎች ናቸው እንጂ የአማራውን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብሩ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አስመስክረዋል። እነዚህ የህወሃት ተላላኪዎች፤ እንደዚሁም በዚህ የአማራ ድርጅት ውስጥ የተሰገሰጉት አማራ-ጠል የሆኑ የትግራይ፤ የኤርትራ ተወላጆች እንደዚሁም በችሎታቸውና ለአማራ ህዝብ ጥቅም ቀናኢነት ሳይሆን በአድርባይነታቸውና በሆዳምነታቸው የተመረጡት የአማራ ተወላጆች ናቸው። የወልቃይትን፤ የግጨውን፤ የጸለምትን፤ የራያን ወዘተ መሬቶች እየፈረሙ የሰጡት የብአዴን ካድሬዎች የአማራን መብት የሚያስከብሩ፤ የአማራ ህዝብ ጥቅሜን ያስጠብቁልኛል ብሎ የወከላቸው ሰዎች አይደሉም። እነዚህ የብአዴን ተወላጆች የአማራ ክልል ተብሎ ለተሰየመው የኢትዮጵያ ክፍል የተመደበው ዓመታዊ በጀት ሥራ ላይ እንዳይውል እያደረጉ በጀቱ በተደጋጋሚ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል እንዲዛወርና እዚያ ለትግራይ ክልል ልማት እንዲውል አድርገዋል። ሥራ ላይ ሳይውል ቀርቶ ተመላሽ የሚሆነው በጀት የተመደበለትን በጀት ሥራ ላይ አውሎ ለጨረሰ ክልል ተላልፎ እንዲሰጥ በሚያደርገው የህግ ድንጋጌ መሰረት[6] ለትግራይ ክልል ይላክና የትግራይን ህዝብ የሚጠቅሙ ፕሮጄክቶች ይሰሩበታል። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የትግራይ ክልል እድገት[7] በሌሎች ክልሎች ኪሳራ ሲካሄድ ቆይቷል። ይህ ነው እንግዲህ ዶ/ር ገብሩ ታረቀ 


በቅርቡ የአማራ አክቲቪስቶች የሚባሉ ወጣቶች በአማራ ክልል ውስጥ ያለውን እጅግ ኋላቀርነት የሚያሳዩ ምስሎችን (የአማራ ልጆች በፈራረሱና ከከብት ጋጣ በባሰ ደረጃ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩበትን ሁኔታ በፌስ ቡክ ገጾች አሳይተውናል። ህጻናት ዛፍ ጥላ ሥር የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች፤ የፈራረሱና አንዳችም ዓይነት የጤና ተቋማት መሆናቸውን የሚያሳይ ቁመና የሌላቸው የህክምና መስጫ ክሊኒኮች ወዘተ ናቸው በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ራሱን በሚያስተዳድረው የአማራው ክልል ውስጥ የሚታዩት። ይህን መሰል በተዘዋዋሪ መንገድ በወያኔ ትግሬዎች የሚዘወር፤ የአማራውን ህዝብ ሆን ብሎ የሚያደኸይ፤ በተጠና መንገድ ለአማራው ህዝብ የተመደበው በጀት ሥራ ላይ እንዳይውል ሊያደናቅፉ የሚችሉር አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ መዋቅሮችን ፈጥሮ ለአማራው ክልል የተመደበውን በጀት በጊዜ ሥራ ላይ አልዋለም እያለ ተመላሽ በማድረግ የተመደበለትን በጀት በቅልጥፍና ሥራ ላይ ወደሚያውለው የወርቁ የትግራይ ህዝብ ክልል እንዲዛወር የሚያደርግና በህወሃት የሚዘወር የሞግዚት አስተዳደር እንዴት ነገዶች የየራሳቸውን ጉዳዮች በራሳቸው ለመምራት የሚያስችላቸውን አዲስ አሰራር” ተግብረዋል ሊያሰኝ ይችላል።

ህወሃት ከአማራው መሃል የተማረ ሰው የጠፋ ይመስል ገነት ገብረ እግዚአብሄርን የመሰሉ አማራ-ጠል የህወሃት ሰዎችን የአማራ ክልል የከተሞች ልማትና የእንዱስትሪ ልማት ዋና ኃላፊ አድርጎ የአማራው ክልል በልማት የኋሊት እንዲሄድ አድርጓል። ከጣና በለስ ላይ ያለው የመብራት ኃይል በብዙ መቶ ኪሎሜትሮች መስመር ዘርግቶ የትግራይን ከተሞች ሲያበራ፤ ለትግራይ እንዱስትሪዎች የኃይል ምንጭ ሲሆን ጣና በለስ የሚገኝበት የአማራ ክልል ግን ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አንዳችም የኃይል አቅርቦት ሳይደረግለት ኢንቨስተር የተባሉት ሰዎች በአካባቢው የልማት ሥራ ለመስራት ዝር እንዳይሉ ተደርጓል። ይህ በሥልትና በጥናት የተደረገ የወያኔ ትግሬዎች የክፋት ሥራ ነው።

የትግራይ ፋሽስቶች ዋነኛ ጠላታችን ነው የሚሉትን የአማራ ህዝብ ለመጉዳት ምን ያላደረጉት ነገር አለ? ለመሆኑ በረከት ስምዖንን፤ ህላዌ ዮሴፍን፤ ከበደ ጫኔን፤ ገነት ገ/እግዚአብሄርን፤ ካሣ ተክለብርሃንን የመሳሰሉ ትግርኛ ተናጋሪዎች ሁሉም ክልሉን ያስተዳድራል በሚባልበትና ሁሉም በነገድ ማንነት ላይ በተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የራሳቸው ክልል ባልሆነው የአማራ ክልል ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ተደርገው የተሾሙት በምን ቀመር ወይም በምን ሂሳብ ነው? የትኛው አማራ፤ ጉራጌ፤ ኦሮሞ ወይም ኢትዮጵያዊ ሶማሌ ወዘተ ነው በትግራይ ክልል ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ተመድቦ የሚሰራው? የወያኔ ትግሬዎች፤ ኤርትራውያን ወዘተ ህዝባችን ሳይሆን ታሪካዊ ጠላታችን ብለው በሚቆጥሩት ህዝብ ላይ በሚፈነጩባት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት የተለያዩ ነገዶች የየራሳቸውን ጉዳዮች በራሳቸው ለመምራት የሚያስችል አዲስ አሰራር አለ ብለው ፕሮፌሰረ ገብሩ ለመጻፍ በቁ?። ፕሮፌሰሩም ይህንን ሁሉ ከላይ የጠቀስኩትን ሀቅ ያጡታል፤ ወይም አያውቁትም ብዬ አልልም። ነገር ግን ህሊናቸው በአክራሪ የትግራይ ብሄረተኛነት ስሜት ስለታወረ የትግራይ ክልል ተወላጆች በአማራና በሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶች ኪሳራ የሚጠቀሙበትን ይህ የአፓርታይድ ሥርዓት ለእሳቸውና እሳቸው ለወጡበት የትግራይ ክልል ህዝብ ተስማሚ ነው።
ከላይ የአማራ ክልል ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የሚገኝበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አስመልክቼ ፕሮፌሰር ገብሩ ህወሃት-ሰራሽ ስለሆነው የነገድ ፌዴራሊዝም በጎነት የደረሱበትን ድምዳሜ ህፀፅ ነቅሼ ካወጣሁ በኋላ አሁን ደግሞ የጋምቤላን ክልል እንደ ምሳሌ በመውሰድ የእሳቸው ድምዳሜ ቅንነት የጎደለውና ሀሰተኛ መሆኑን አሳያለሁኝ።

 ፕሮፌሰሩ “የተለያዩ ነገዶች የየራሳቸውን ጉዳዮች በራሳቸው ለመምራት የሚያስችላቸውን አዲስ አሰራር (ዘዴ)” ተግብረዋል የሚለውን አመለካከት ግድፈትና ዓይን ያወጣ ውሸት በማሳያነት የማቀርበው የጋምቤላ ክልልን ነው።

በጋምቤላ ክልል የመሬቱ ባለቤት የሆነው ኢትዮያዊው የጋምቤላ ተወላጅ እየተፈናቀለ የመዋዕለ ነዋይ ጌቶች ለሆኑት ኢንቨስተርስ የሚባሉ የውጭ ሀገር ዜጎችና ከለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ጀምሮ የኢትዮጵያ ዋነኛ ባለሃብቶች ለሆኑት የትግራይ ተወላጆች ተከፋፍሏል። ይህ ሲደረግ በልማት ስም ነባሩ የጋምቤላ ህዝብ ከመሬቱ ላይ እየተነቀለና እየተፈናቀለ እሱ ወደማይፈልገው ለምነት የሌለው ሥፍራ ላይ በግዴታ ተወስዶ አንድ ላይ እንዲሰፍር ተደርጓል። የጋምቤላ ህዝብ ይህ ሁሉ ነገር ከመደረጉ በፊት ፍላጎቱ አልተጠየቅም፤ በቅድሚያ ምንድነው ሃሳብህና ምኞትህ ተብሎ እንደ አንድ የሀገር ዜጋ ያማከረው የመንግስት አካል የለም። የጋምቤላ ህዝብ ህይወቱን፤ ህልውናውንና የእራሱንና የልጆቹን ዕጣ-ፈንታ በሚወስን መሬቱ ላይ ከትግራይ ተነስተው የመጡ ባለጊዜዎች የፈለጋቸውን ሲያደርጉ ምንም ማድረግ አልቻለም። ዛሬ በጋምቤላ ክልል በኢንቨስተርነት ከተሰማሩት የሀገር ውስጥ ባለንብረቶች ከሰማንያ በመቶ በላይ የሆኑት ትግራይ ከሚባለው ነገድ የፈለቁ ባለጊዜዎች፤ ባለሃብቶችና ባለጠመንጃዎች ናቸው። ከአንድ ሺህ በላይ ቁጥር ያላቸው የቀድሞ የህወሃት ታጋዮች የሆኑ የትግራይ ተወላጆች የጋምቤላን መሬት ተቀራምተው መያዝ ብቻ ሳይሆን በዚህ በያዙት መሬት ስም በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በብድር መልክ እንዲሰጣቸው ተደርጓል። እነዚህ ባለጊዜዎች በጋምቤላ መሬት እናለማለን ብለው የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ከሆኑ ባንኮች ስምንት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር[8] በላይ ተበድረው ብድሩም የተበላሸ ብድር ሆኖ ሳይከፈል ጠፍቶ ቀርቷል። 

(ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል ለሚገኙ ሰፋፊ እርሻዎች (Commercial Farms) 4.9 ቢሊዮን ብር ብድር እንዳቀረበ ከዓመት በፊት ዘግበን ነበር፡ለዚህ ዘገባ መረጃ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ያስጠኑት የጥናት ውጤት ሲሆን፣ በሰፋፊ እርሻዎች አልሚነት ብድሩን ያገኙት በርካቶቹ ያገኙትን ብድር ሥራ አለማዋላቸውን አረጋግጧል”፡፡ )

ይህንን ብድር ለትግራይ ተወላጆች ሲያመቻችና ሲሰጥ የነበረው ኢሳያስ ባህረ[9] የሚባል የኢትዮጵያ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ነበር። አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ይሏል ይህ ነው። ይህንን የመሰለ የአፓርታይድ ሥርዓት ውጤት የሆነ የአንድን ነገድ ተወላጆች የጥቅም የበላይነት ያረጋገጠ ሥርዓት በትክክለኛ ስሙ የትግሬ የአፓርታይድ ሥርዓት ተብሎ መጠራት ሲገባው ዛሬ “ሙስና፤ ኪራይ-ሰብሳቢነት” እየተባለ በግለሰቦች ባህርይ ጉድለት የመጣ ችግር ተደርጎ ይቀርባል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ዘረፋ የወያኔ ትግሬዎች የፋሽስት/አፓርታይድ ሥርዓት የአንድን ትግራይ የሚባል አናሳ ነገድ ተወላጆች ጥቅም ለማስከበር የተዘረጋ ሥርዓት ውጤት ነው። ይህ ሥርዓትም ሊለወጥ የሚችለው ይህ ፋሽስታዊ የሆነ የአፓርታይድ ሥርዓት ከሥሩ ተነቅሎ ሲፈርስ ብቻ ነው። እንግዲህ የጋምቤላ ህዝብ መሬት በባለ ጊዜ የአንድ ትግሬ የሚባል ነገድ ተወላጆች ብቻ መነጠቅ ሳይሆን በዚህ በወሰዱት መሬት ስም የኢትዮጵያን ህዝብ ሀብት በብድር መልክ ከባንክ ወስደው ገንዘቡ ጠፍቶ መቅረቱ ነው። ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ እንዴት ብሎ የጋምቤላ ህዝብ የራሱን ጉዳይ በራሱ? 


 - 
የወያኔን ህገመንግስት ከአፓርታይዱ የደቡብ አፍሪካ የባንቱስታን ሥርዓት ማወዳደር ስህተት 
ነው

ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ይህን ወያኔ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ጀምሮ የዘረጋውን የአፓርታይድ ሥርዓት ከደቡብ አፍሪካው የባንቱስታን ሥርዓት ጋር ተመሳሳይነት አለው የሚሉትን ወገኖች ቅንነት የጎደላቸውና እውቀት-አጠር የሆኑ ደንቆሮዎች ብለው በጅምላ ወርፈዋል። ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ኢትዮጵያን በቋንቋ ሸንሽኖ የሞግዚት አስተዳደር በመፍጠር በአናሳው የትግራይ ነገድ ተወላጆች የሚሽከረከረውን የአፓርታይድ ሥርዓት ሳያፍሩ በሚከተለው መንገድ አሽሞንሙነው አቅርበውልናል።

እነዚያ እያንዳንዱ ራስገዝ ክልል ለመገንጠል ያለውን የተረጋገጠ መብት አጥብቀው የሚቃወሙት ህገ መንግስቱን ከአፓርታይዱ የባንቱስታን አገዛዝ ጋር አወዳድረውታል (አነጻጽረውታል) እነዚህን መሰል ንፅፅሮች ሀሰተኛ የሆኑና ቅንነት የጎደላቸው፤ ኋላቀርና ድንቁርናን/አላዋቂነትን አመልካች ናቸው።

“Those adamantly opposed to the new dispensation, which allows the autonomies a qualified right to secession, have even compared it to Bantustanism under apartheid. Such analogies are disingenuous at best and benighted at worst[10]. 

የወያኔ መንግስታዊ ሥርዓት የአንድን ትግሬ የሚባል አናሳ ነገድ የጥቅም የበላይነት የሚሰብክና የሚያስከብር፤ ኢትዮጵያን በነገድና በቋንቋ ከፋፍሎ የሚዘርፍ ሥርዓት መሆኑ እንደ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ላሉ ህሊናቸው ለታወሩ ግለሰቦችና የዚህ ሥርዓት ዋነኛ ተጠቃሚ ለሆኑት የትግራይ ተወላጆች ብቻ የተሰወረ ጉዳይ ነው። እስቲ ከዚህ በታች የሰፈረውንና የፌዴራል መንግስት ተብሎ የሚጠራው አካል ከየክልሎቹ ወስዶ ለራሱ ወገኖች ለሆኑ የትግራይ ተወላጆችና እንደዚሁም ለውጭ ሀገር ባለ ሀብቶች የሚያከፋፍለውን መሬት ስፋት እንመልከት። አንባቢ ልብ ሊል የሚገባው የትግራይ ክልል ከሚባለው አንድም ሄክታር ወደ መሬት ባንክ ተላልፎ ለውጭ ኢንቨስተሮች በርካሽ ለሃምሳና ዘጠና ዓመታት እንዲከራይ አልተደረገም። 

ለኢንቨስትመንት ተብሎ ከየክልሉ ለፌዴራል መንግስት የመሬት ባንክ የተላለፈ የእርሽ መሬት ስፋት በሄክታር[11]

አማራ                                         420,000
አፋር                                         409,678
ቤኒሻንጉል BeniShangul               691,984
ጋምቤላ Gambella                       829,199
ኦሮሚያ Oromia                        1,057,866
ደቡብ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች 180,625
የሁሉም ክልሎች ድምር                 3,589,678

ምንጭ፡ የእርሻና የገጠር ልማት ሚኒስቴር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2009 ዓ. ም. ካወጣው ሪፓርት የተወሰደ።

በተጫማሪም እነኚህን የቪዲዮ ማስረጃዎች ይመልከቱ፤
Former Ethiopian University student's testimony on Federal Police
የታራሚዎች አያያዝ-ፕሮግራሙ የተሰራውና ያለፈውን ክስተት ላለመድገም ትምህርት እንድንወስድበት የተዘጋጀ ነው፡፡

 - ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ስለ ወይዘሮ አዜብ መስፍን ታላቅነት፤ አዋቂነት የሚነግሩንም ነገር አለ።

ፕሮፌሰር ገብሩ ስለ ወይዘሮ አዜብ መስፍን ታላቅነት፤ አዋቂነትና እሳቸው ለኢትዮጵያ ሴቶች ስላላቸው ምሳሌነት ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር በማነጻጸር የሚከተለውን በመጽሃፋቸው ውስጥ ጽፈዋል።

በብሄራዊ ደረጃ ሴቶች በጦሩም ሆነ በንግዱ ዓለም ውስጥ ችሎታ ባላቸውና ተፅዕኖ-አሳዳሪ በሆኑ፤ በጣም ታዋቂና እንደ አቶ መለስ ዜናዊ ሁሉ አዋቂ በሆኑት ሚስታቸው (ባለቤታቸው)በወይዘሮ አዜብ መስፍን ይወከላሉ። የዐጼ ምንሊክ ሚስት ከነበሩት ከእቴጌ ጣይቱ በኋላ እንደ ወይዘሮ አዜብ መስፍን በፓለቲካው መስክ (በሀገር ጉዳይግንባር ቀደምና እጅግ ጉልህ የሆነ ተሳትፎ የነበራቸው ሴት አልነበሩም ወይዘሮ አዜብ የቀድሞ የነጻነት ተዋጊ ሲሆኑ እሳቸው ነጻ የወጣችው የኢትዮጵያ ሴት ምሳሌ ናቸው”።

“Success stories abount of women in the army and in the business world. Nationally, they are represented by talented and influential persons, including most notably Azieb Mesfin, Meles Zenawi;s equally savy wife. No politically prominent woman since queen Taitu Bitul, emperor Menelik’s wife, has been so actively and visibly engaged in the pubic arena. A former liberation fighter, she is emblematic of the liberated Ethiopian women[12]”. 

ፕሮፌሰር ገብሩ በስደት የሚገኘውንና በተለይም በምዕራቡ ሀገራት ተበትኖ የሚኖረውን የወያኔን መንግስት የሚቃወም ኢትዮጵያዊ እብሪተኛ፤ ግዴለሽና ኃላፊነት የጎደለው ነው እያሉ በአክራሪ ብሄረተኛ ብዕራቸው ኮንነዋል። ለዝርዝሩ በመጽሃፋቸው ውስጥ ከገጽ 330-331 ላይ የሰፈሩትን ሃሳቦች ያንብቡ። አክራሪ ብሄረተኛነት እንደዚህ ከላይ የታሪክ ምሁሩን የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀን ጽሁፎች በመጥቀስ እንዳሳየሁት አዋቂ ወይም መሃይም ሳይል የታሪክ ፕሮፌሰር የሆነውን ሰው ጭምር ዘረኛ ያደርጋል። ምሁራን ዘረኞች መሆናቸውና የፋሽስት/የናዚ መሪዎችን ተከትለው ማጨብጨባቸው፤ ማጫፈራቸው አዲስ ክስህተት አይደለም።

ለዚህ እንደ ምሳሌ የምጠቅሰው አንድ በሃያኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ታዋቂ የነበረን ማርቲን ሄይደገር[13] የሚባል የጀርመን ፈላስፋ ነው። ይህ በዘመኑ የዓለም ታላቅ ፈላስፋ የሚባል ጀርመናዊ ፕፌሰር የፍራይቡርግ ዩኑቨርሲቲ ቻንስለር (ፕሬዚደንት) የነበረ ታዋቂ ሰው የነበረ ቢሆን የሂትለር ተከታይ የጀርመን አክራሪ ብሄረተኛነት የፈጠረው ስሜት ከፍልስፍና እውቀቱ ላይ ጥላውን ጥሎበትና ህሊናውን አሳውሮት የትንሹና የዘረኛው ሰው የሂትለር ተከታይ ሆኖ እራሱን ለትዝብትና ለውርደት አጋልጧል። አክራሪ ብሄረተኛነት አንድ ሰው የሚኖርበትን ማህበራዊ እውነታንና የዓለም ታሪክን በተጻረረ መልክ በመረዳት በአደባባይ እንዲህ አድርጎ ራሱን ለትዝብት ይዳርጋል። አክራሪ ብሄረተኛነት አንድን የተማረ ፕሮፌሰር ሳይቀር እንዲህ በአደባባይ እንዲዋሽና እንዲቀጥፍ ያደርገዋል። ከላይ የጽሁፍ ስራቸውን የጠቅስኩት ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀን የመሰለ ሰው ዛሬ ቀለም ያልቆጠረ ተራ ሰው የሚያየውን ጥፋት እንዳያይ ህሊናው በአክራሪ ብሄረተኛነት ስሜት ታውሮአል። ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነውን በቋንቋና በማንነት ላይ የተመሰረተ የፌዴራሊዝም ሥርዓትና ይህ ሥርዓት የፈጠረውን የአፓርታይድ አገዛዝ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲን እንዳመጣ ሲነግሩን አንዳችም ዓይነት የህሊና መሸማቀቅ አልተሰማቸውም።

እንግዲህ ከላይ ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት አንድ ሰው በአክራሪ ብሄረተኛነት ስሜት ሲያብድ በዚህ ዓይነት ህሊናው ታውሮ አደባባይ ላይ በመውጣት ካለአንዳች ይሉኝታ ይዋሻል፤ ይቀጥፋል። በአክራሪ ብሄረተኛነት ስሜት ያበደ ማህበረሰብ በአመለካከቱና በአስተሳሰቡ እያነሰና እየቀጨጨ ይሄዳል። ይህም የሚሆነው ይህን በመሰለ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የግለሰብ ማንነታቸውን አጥተው እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ መንጋ ቡድን በጥቂት መሪዎቻቸው ስለሚመሩ ነው። ባለፉት አርባ ሶስት ዓመታት በወያኔ ትግሬዎች አማካይነት ቀስ በቀስ እያደገ በሄደ መልክ ብሄረተኛነት የአብዛኛው ትግራይ ህዝብ ማንነት መገለጫ ሆኗል። ለነገሩ በትግርኛ ተናጋሪዎች ባህል ውስጥ ይሉኝታ ለወትሮውም ቢሆን በስፋት የሚታወቅና የዳበረ ባህላዊ እሴት አይደለም(ይህ በኤርትራ የሚገኙትንም ትግርኛ ተናጋሪዎች የሚጨምር ነው)። ወያኔዎች የትግራይን ነገድ ማንነት የፓለቲካ መሳሪያ አድርገው የትግራይን ህዝብ አመለካከትና እሴቶች ከመለወጣቸውም በፊትም በትግርኛ ተናጋሪዎች ባህል ውስጥ ለራስ ወገን ማድላት የሚያሳፍር ነውረኛ ድርጊት ተደርጎ አይቆጠርም የሚል እምነት አለኝ። ይህም ሁኔታ ወያኔ ትግሬዎች ኋላ ላይ ለፈጠሩት አክራሪ ብሄረተኛነት ጥሩ ርብራብና መደላድል ሆኗል ብዬ እሞግታለሁ።-//-

[1] - Gebru Tareke, “Rural Protest in Ethiopia, 1941-1970: A Study of Three Rebellions” PhD dissertation, Syracuse University, 1977
[2] - Gebru Tareke, The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa, published in 2009 by Yale University Press.
[3] - Gebru Tareke, “The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa”, 2009 (see on Pp. 328)
[4] - ibid, page 327
[5] - ibid, page 329
[6] - አዲስ ዘመን ጋዜጣ የካቲት ቀን .  እትም መለስ ዜናዊ ለፓርላማ ያደረገውን ንግግርና የያዘ ሲሆን መለስ በዚህ ንግግሩ ውስጥ 1988 ጀምሮ የተመደበላቸውን የዓመት በጀት በጊዜው ተጠቅመው የማይጨርሱ ክልሎች ላይ በጀታቸው ተወስዶ ለሌሎች የተመደበላቸውን በጀት በጊዜው ለሚጨርሱ ክልሎች እንደሚሰጥ ተናግሯል። ይህም ፓሊሲ 1988 ጀምሮ በተግባር ላይ ውሏል። በዚህ ዓይነት ነው በተደጋጋሚ አማራ ክልል የሚባለው ክልል በጀቱን በጊዜ መጠቀም አልቻለም እየተባለ በጀቱ እየተወሰደ በቅልጥፍናና በፍጥነት የተመደበለትን በጀት ለሚጨርሰው የትግራይ ክልል እየተላለፈ የተሰጠበት ምክንያት። ይህንን ደግሞ ለማስፈጸም እንዲቻል ነው የአማራውን ክልል ልማትና እድገት ሆን ብለው የሚያደናቅፉ የኤርትራና የትግራይ፤ የሲዳማ እንደዚሁም ለሆዳቸው ያደሩ የአማራ፤ የአገው ካድሬዎች ተመልምለው ይህንን ክልል በማናቸውም የልማት መስፈርት ኋላ-ቀር እንዲሆን ያደረጉት። 
[7] - የትግራይ ክልል እድገት በሁለት መንገዶች እንዲፋጠን ተደርጓል። አንደኛ በፌዴራሉ መንግስት የሚቀረጹ ፓሊሲዎች የዚህን ክልል ህዝብ በበጀት ድልድልም ሆነ በፕሮጄክት ድልድል ከማንም ክልል በተሻለ ተጠቃሚ አድርጓል። በሁለተኛ ደረጃ በመላው ሀገሪቱ ውስጥ ተሰራጭተው የሚገኙት የክልሉ ተወላጆች የሆኑና በያዙት መንግስታዊ ሥልጣን፤ በሚያገኙት መንግስታዊ ድጋፍ (ብድር፤ ካለ ታክስ እቃ ወደ ሀገር የማስገባት፤ ወዘተ ጥቅሞችየሀገሪቱን ሃብት የአንበሳ ድርሻ (በንግድ፤ በእርሻ፤ በእንዱስትሪ፤ በፋይናንስ ወዘተየተቆጣጠሩ ግለሰቦች በርካታ ካፒታል ወደ ትውልድ መንደሮቻቸው እየወሰዱ በትግራይ ክልል ውስጥ ጉልህ እድገትና መሻሻል እንዲመጣ አድርገዋል። 
[8] - ዮሃንስ አንበርብር በሪፓርተር ጋዜጣ ላይ የዘገበው የህዳር 8 ቀን 2009 እትምን ይመልከቱ። 

[9] - Walta Information centre, Ethiopia: Agency quits offering land for large scale agricultural investments, March 22, 2016

[10] - ibid, pp 329
[11] - ምንጭ፡ የእርሻና የገጠር ልማት ሚኒስቴር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 2009 ካወጣው ሪፓርት የተወሰደ
[12] - ibid, pp. 332
[13] - Encyclopaedia Britannica, Martin Heidgger – German Philosopher

No comments: