ቆቤን ለልደቱ አያሌው
ከጌታቸው ረዳ
Ethiopian
Semay
1/15/25
ልደቱ አያሌው <<ለፓልቶክ ወጣት አርበኞች>> የማይችሉት ዱብ ዕዳ ፈተና ይዞላቸው መጥቷል።
ከላይ ፎቶ ልደቱ ሲሆን ከጎን ያለው ፎቶ ደግሞ ከኤርትራ የመጡ ወደ ፖሊስ ሥራ አብይ አሕመድ የቀጠራቸው የኦነግ ተዋጊዎች በዓድዋ ሰሎዳ ተራራ ላይ ጣሊያንን ድል አድርጋ የተውለበለበቺውን ሰንደቃላማችን የአዲስ አባባን ኗሪዎች ለበዓል ሲወጡ የለበሱትን የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ሕብር ያለበትን ልብስና ፎጣ የአብይ አሕመድ ፖሊስ እየነጠቃቸው የሚያሳይ አፓርታይዳዊ ሥርዓት ማሳያ ነው።
ልደቱ ለሕክምና
ወደ አሜሪካ እንደመጣና እዚህ ሕክምና እያለ አፓርታይዱ የአብይ አሕመድ ወረበላው ቡድን ፤ ልደቱን በሽብርተኛነት ከስሶ ለስቅላት
እንደሚፈልገው ሁላችሁም የምታውቁት ዜና ነው። ልደቱ ግን ሕክምናው በከፊል አገባድዶ በ 1 ወር ውስጥ ወደ አገር እንደሚመለስ በለጠፈው
ሰነድ ነግሮናል።
አሁን ልደቱን ያለማድነቅ አይቻልም።
እኔ ልደቱን በሚያስወቅሱት ላይ ስተቸው እንደነበር ተከታታዮቼ ታውቃላችሁ። ቤተመንግሥታችንን አሞኝቶ የተቆጣጠረው አፓርታይዱ “የነጮች ቅጥረኛ” የአብይ አሕመድ የኦሮሙማው ቡድን ካሁን በፊት ልደቱን በሐሰት ወንጅሎ እንዳሰረው ሁሉ ዛሬም ልደቱ ወደ አገር ሲመለስ ያንን የውሸት ውንጀላው በመድገም “እንግልት፤እስራት፤ግርፋት ወይንም ሞት” እየጠበቀው ያለመሆኑን በእርግጠኝነት መናገር በማይቻልበት ሁኔታ ልደቱ ይህንን “አፓርታይድ ሥርዓት” በሰላማዊ ትግል ለመታገል ሕክምናው ጨርሶ በጀግንነት ጨክኖ ወደ አገር ቤት እንደሚመለስ ራሱ ባስታወቀው ዜና ስሰማ የፖለቲካ አካሄዳችን ምንም ቢለያይም የናንተው ስሜት ባላውቅም “ፍርሃትን ደርምሶ” መውጣቱ <<ያጠለቅኩትን ቆቤ በክብር ለልደቱ አንስቻለሁ>>።
እንዲህ ያለ ፍርሐትን የሚጋፈጥ ጀግና ማየት ፈተናው እዚህ ላለው ዲያስፖራ ውስጥ ኑሮው መስርቶ የጀርመን፤ የአሜሪካ፤ የእንግሊዝ የካናዳ ወዘተ…. ሳንድዊች እየገመጠ ኮካኮላ እየተጎነጨ በትንሽዋ የአይፎንና የአንድሮይድ የስልክ መስተዋት እራሱን በማየት 16 ሰዓት ተቀምጦ ሱሪው እያረጠበ (ሴቶቹም ወንዶቹም) መድፍና መትረየስ ሳይተኩሱ በቀረርቶ እየፎከሩ የአገርቤቱን ትግል ካልመራሁት የሚል “ራስን የማቆነጃጀት ውሸት” የሚዋሹ አደገኛ ወጣቶች <<የማለፊያ ፈተናቸው>> ከልደቱ አያሌው ተሰጥቷቸዋል። ፈተናውን ያልፌታል ወይ?
ልደቱ ተከተሉኝ
የሚል መልዕክት በጽሑፉ ባያስተላልፍም ፤ በወሰደው ድፍረት በኔ አተረጓጎም ጥሪው በጣም ግልጽ ነው። እዚህ ፓልቶክ ውስጥ በiPhone መስተዋት ፊታችሁን እያሳያችሁ እንደ ቡና
አጣጪ የሃሜት ባልቴቶች እርስበርስ ስትዘላለፉ ከምትውሉ ፤ በድፍረት ጠላት አለን የምትሉት ጠላት ካላችሁ ጠላታችሁን ለመጋፈጥ
“ተከተሉኝ” የሚል ነው የልደቱ ድፈረት። ይህንን ያለማድነቅ ግብዝነት ነው።
የኔ ምክር
አጭር ነው። ልደቱን ካልተከተልክም ሳንዲውቹንና የስታርባክስ ቡና ሱስህን አቁመህ እንደ ወንዶቹና እንደ ፋኒቶቹ ወደ ጫካ ግባ የሚል ነው”። የልደቱ ድፍረት
በጥሶ ወደ ጅቦች በረት መግባት የሚነግረን መልዕክት ይህ ነው። ፓልቶኮች ሆይ! ይሰማችሗል?!!!
ልደቱ በዚያው
የልብ ቀዶ ጥገናው በሽታው ሳያጋግም ወደ
ጅቦች መንደር ዘሎ መግባትና ጅቦችን መጋፈጥ ያክል ጀግንነት ካላወደስን ምን እናወድስ? ጀግንነት ማለት ላመነበት ራስን መስዋዕት የማድረግ የሚያሳይ ተግባር ነው። የጀግንነት ተግባር እቤት ተቀምጦ በፓልቶክ እንደሚጮክ አይደለም። ጀግንነት ከተጠበቀው በላይ መሄድን በተለይም ፍርሃትን ወይም ችግርን የሚያካትት ድፍረት ነው። ልደቱ ይህንን እጅግ አስገራሚ ውሳኔ
መወሰኑ እዚህ ፈረንጅ አገር ውስጥ በምቾት እየኖሩ ፓልቶክ ላይ ተወዝፈው
ያልሆኑትን ለመሆን የሚለፈልፉ ትግልን እንደ መዝናኛ የሚያይዩት “ወጣት ሴቶችም ወንዶችም” ከፍተኛ <<የማጣሪያ ፈተና>>
ነው። <<የፓልቶክ ክፍለጦር አዛዦች>> ይህንን ጥሪ እና ፈተና ያልፉታል? ነው ዋናው የኔ ጥያቄ።
ለረዢም ሰዓቶች
በፓልቶክና በዩቱብ በየቤታችሁና በየምትሰሩበት በደባሪው የሰክዩሪቲ ጋርድ ሥራ ሰዓት መግደያ እንዲሆናችሁ “በተሌፎን መስተዋት”
እራሳችሁን እያያችሁ ድንቁርናችሁን በማስተዋወቅ እርስበርሳችሁ አየር ባየር በዘለፋና በውሸት “አገር ውስጥ ላለው ሕዝብ ለማትሆኑበት
መስዋዕትነት” ለመጀገነን የምትሞክሩ ወጣቶች ሆይ፤ ከልደቱ በዕድሜ ያነሳችሁ እና የልደቱ ዕድሜ እኩያ የሆናችሁ ሁሉ እንደ ልደቱ ደፍራችሁ ወደ አገር በመግባት የፓልቶክ ንግግራችሁን በተግባር አሳዩን። ይህንን ፈተና መሻገር አለባችሁ!
በተለይ አምሐራ ተወላጅ ወጣቶች የምትከናነቡበት የውሸት ካባ መልበስ ትችሉ እንደሆን እንጂ ስለ አምሐራ ሕዝብ ዲያስፖራ ውስጥ ሳንድዊች እየገመጣችሁ ኮካ ኮላ እየጎነጫችሁ ስለ ፋኖ መሪዎች እገሌ እንደዚህ ይሁን እገሊት እንደዚህ ትሁን ብሎ የማዘዝ መብትም ሆነ ሞራል የላችሁም። እንግዲህ ፈተናው ወዳናንተ መጥቷል።
የሰው ገላ
በነደደበት እናንተ ፓልቶክ ሆናችሁ በሰው የገላ እሳት የመሞቃችሁ አባዜ ይብቃ አቁሙ።"ቆንጆ ውሸት"
በሚስብ ወይም በሚያጽናና መልኩ የሚቀርብ ውሸት እናንተን እንጂ ለተጎጂው ሕዝብ አይጠቅመውም። ወጣቶች ናችሁ ራስን ከሚያቆነጃጅ የውሸት ባሕል ውጡ።
ሁለመናችሁ ሳጠናው <<አሚግዳላችሁ የጠለፋችሁ
ይመስለኛል>> “አሚግዳላ” በሰው አንጎል ውስጥ የምትገኝ ትንሽየ ፍሬ መሳይ ዕጢ ናት። ዕጢዋ የማሰብ ማዕከል የሚጣራባት
ክፍል ነች። ስሜቶችና ቁጣዎች ዋና ማቀነባበሪያ ማዕከል ትቆጣጠራለች። አሚግደላዋ በሆነ ምክንያት ስትበላሽ “የአሚግደላ ጠለፋ”
ወይንም <<amygdala hijack>> ይሉታል ሃኪሞቹ። ይህ ሲሆን ልክ እንደ እናንተው የፓልቶክ ወጣቶች “ሰውየው
ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ድንገተኛ ቁጣና ፍሬ የሌለው የማይጨበጥ የስሜት ንግግር ውስጥ በመግባት ቁጣ ልቅሶ እና “በጨበርበር/ጩኸት”
ተውጦ ጨዋነቱን ይስታል” ማለት ነው።
የናንተው አሚግዳላም የተጠለፈ ይመስለኛል። ከዚህ ሁሉ ዕብደታችሁ
ነጻ ለመውጣት የልደቱን ድፈረት ታጥቃችሁ ስትፈልጉ በጫካ ስትሹ በከተማ ትግል ታግላችሁ አገራችሁን ነፃ አውጡ!
እኔ ግን ከልደቱ ጋር ያለኝ የፖለቲካ ልዩነት እንዳለ ሆኖ
ስለድፍረቱና ቀና አስተሳሰቡ “ቆቤን በክብር አንስቼ አክብሮቴን እገልጻለሁ”
የኮካ ኮላው ትውልድ ፓልቶክ ውስጥ ተጥዶ ራሱን በውሸት ከማቆነጃጀት ባሕል ወጥቶ ወደ አገር ገብቶ ጀግንነቱን እንዲያሳየን ፈተናውን እንዲያልፉት ከልደቱ አያሌው ተሰጥቷቸዋል። መልካም የማለፊያ ፈተና እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ! ካልሆነ ጀግኖቹ እየሞቱ አገር ነፃ ከወጡ በኋላ ለጉብኝትና ለመዝናናት ወደ አገር መሻገር በሰው ደም መዝናናት የነውር ነውር ነው!
ሰላሙን ለናንተ ይሁን
ጌታቸው ረዳ