Thursday, October 17, 2024

አንተ የደርግ ወታደር… ባክህ ይቅር በለኝ?! Ethio think thank Group ስዩም ተሾመ Ethiopian Semay 10/17/24

 

ከአዘጋጁ አስተያየት

ይህ ጽሑፍ የተጻፈው ቆየት ያለ ቢሆንም የዚህ ድረገጽ አዘጋጅ ከቆዩ ጠቃሚ ማሕደሮች ለመለጠፍ ሲመርጥ ይህንን የሥዩም ተሾመ “አንተ የደርግ ወታደር… ባክህ ይቅር በለኝ?!” የሚለው ቀልቤን ስለሳበው ተመርጦ ተለጥፏል። አዘጋጁ በርዕሱ ላይ ስምምነት ስለሌለው ምርጫው የአንባቢው ቢሆንም አንተ የደርግ ወታደር ከማለት አንተ የኢትዮጵያ ወታደር ተብሎ ቢነበብ የተሻለ ነው።

አንተ የደርግ ወታደርባክህ ይቅር በለኝ?!

Ethio think thank Group

ስዩም ተሾመ

Ethiopian Semay

10/17/24

ላመንክበት ዓላማ፥ በቃልህ ፀንተህ ለሀገርህ ለወደቅከው የደርግ ወታደር፣… እባክህ ይቅር በለኝ?! እርግጥ ነው፣ ከቤተ መንግስቱ ደጃፍ የወደቅከው “ለመንግስት ነው” እንዳይባል ደርግ ከወደቀ ሰነባብቷል፣ “ለመንግስቱ ኃይለማሪያም ነው” እንዳይባል ዚምባብዌ መግባቱን ሰምተሃል፣ “ማምለጫ ጠፍቶህ ነው” እንዳይባል ያለኸው አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ነው። ከህዝብና መንግስት የተጣለብህ ኃላፊነት “የሚኒሊክን ቤተ መንግስትን መጠበቅ ነው”። አውቃለሁ… እንዲህ የወደቅከው ለደርግ ሳይሆን ለሀገርህ ነው ፣ ከቁሳዊ ጥቅም ይልቅ ለቃልህ ነው። አንተ በቃልህ ፀንተህ ላመንክበት የወደቅከው የደርግ ወታደር፣ እባክህ ይቅር በለኝ። አንተን ትቼ ገዳይህን ስላመንኩኝ ፀፀቱ ገደለኝ። ከሞት የተረፉት ጓደኞችሁ ልክ እንደ ወራሪ ጦር ሰራዊት ሲበተኑ ዝም አልኩኝ። በድህነት ሲሰቃዩ ግድየለሽ ነበርኩኝ። በርሃብ አለንጋ እና በሰው ዓይን ሲገረፉ ቸልተኛ ነበርኩኝ። ሃጢያቴ ተዘርዝሮ አያልቅም፣… እባክህ ይቀር በለኝ!?

የተዋደቁላት ኤርትራ ከአሰብ ወደብ ጋር እንደ ገጸ-በረከት ለሻዕቢያ ስትሰጥ በቁጭት ሲያለቅሱ ዝም አልኩኝ። ኤርትራ ኢትዮጲያን ስትወር ግን ከወደቁበት ትቢያ ተነስተው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስከበሩ። የኤርትራ ጦር የተሸነፈው በእነሱ አስተዋፅዖ ሳይሆን ከትቢያ ላይ ጥሎ ባነሳቸው “በመለስ ዜናዊ የአመራር ብቃት ነው” ሲሉኝ አመንኩ። ሳይውል-ሳያድር ባድመን ለኤርትራ አሳልፎ መስጠቱን በሰማሁ ግዜ እጅግ ተፀፀትኩኝ። የኤርትራ ስደተኞች በአዲስ አበባ ከተማ እንዲህ በነፃነት የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ ቀናሁኝ። የሀገሬ ልጆች መስቀል አደባባይ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ቢወጡ እንዲህ እንደ ጠላት በጭቃኔ ሲቀጠቀጡ ስመለከት ፀፀቱ ገደለኝ።

ላመንክበት ዓላማ፥ በቃልህ ፀንተህ ለሀገርህ ለወደቅከው የደርግ ወታደር፣… እባክህ ይቅር በለኝ?! አንተን ችላ ብዬ ገዳይህን አመንኩኝ። አንተን የገደለህ እኔም ገደለኝ፣ ሀገር-አልባ አደረገኝ። በኢትዮጲያ ምድር ስደተኛ ሆንኩኝ። በአንተ ላይ የደረሰው በእኔ ላይ ደርሶብኝ ፀፀቱ ገደለኝ። አንተ የደርግ ወታደር፣… ባክህ ይቅር በለኝ?

እጹብ ድንቅ ጽሑፍ እና የጨዋነት ይቅርታ በአክብሮት መቀበል የጨዋ ሕዝብ ግብረመልስ መሆን አለበት! ኢትዮፕያን ሰማይ! Ethiopian Semay